Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያ ቱሪዝም በመንታ መንገድ ላይ

የኢትዮጵያ ቱሪዝም በመንታ መንገድ ላይ

ቀን:

ከኢትዮጵያ ተፈጥራዊ ሀብቶች አንዱ የኤርታሌ እሳተ ገሞራ የጎብኚዎችን ትኩረት በመሳብ ይታወቃል፡፡ በርካቶችን የሚያስደንቀውን ህያው እሳተ ገሞራ ለማየት ባህር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች አያሌ ናቸው፡፡ መሬት ላይ የተንጣለለ ቀስተ ደመና የሚመስለውና በህብረ ቀለማት ያሸበረቀውን ዳሎልም ከኤርታሌ በማስከተል ይጎበኛል፡፡ በሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ጉልህ ድርሻ ያለው የድንቅነሽ (ሉሲ) ቅሪተ አካል የተገኘበት ሀዳርም የቱሪስቶች መዳረሻ ነው፡፡ የአካባቢው ማኅበራዊ መስተጋብር መገለጫ የሆነውን ዳጉ የመረጃ መለዋወጫ ስልት እንዲሁም ባህል የሚንፀባረቅበት አለባበስ፣ አመጋገብና የተለያዩ በዓላት አከባበርም ቱሪስቶችን ይስባሉ፡፡

ኤርታሌ ቀድሞ ከነበረበት ቦታ እሳቱ ከስሞ በቅርብ ርቀት ሌላ እሳተ ገሞራ መፈንዳቱ ዓምና ከታዩ አስደናቂ ተፈጥሯዊ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ የተለያዩ አገሮች ቱሪስቶችና ተመራማሪዎችም በቦታው ተገኝተው ሁነቱን ተመልክተዋል፡፡ እኛም ሁኔታውን ለመዘገብ ወደ አካባቢው ባመራንበት ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊ አስጎብኚ ቱሪስቶችን ሲያስጎበኝ ገጠመን፡፡ ቱሪስቶቹ በአካባቢው ተፈጥሯዊ ሀብት በእጅጉ ቢማረኩም፣ ከመሠረተ ልማት ዝርጋታና የቱሪስት ማረፊያ ቦታዎች አቅርቦት አንፃር ብዙ እንደሚቀር ገለጹልን፡፡

አስጎብኚውም፣ ኢትዮጵያ በብዙኃን ዘንድ ከሚታወቁ የቱሪስት መስህቦች በዘለለ ያላትን እምቅ ሀብት ባጠቃላይ ለቱሪዝም አለማዋሏ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ አናሳ እንዳደረገው ተናገረ፡፡ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያለው ማኅበረሰብ ከቱሪዝሙ እምብዛም አለመጠቀሙ፣ በቱሪዝምና በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዳሻከረው ማስተዋሉንም ገለጸልን፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም በመንታ መንገድ ላይ

 

የቱሪዝም ባለሙያዎች እንደ ዋነኛ ክፍተት ከሚያነሷቸው አንዱ በቱሪዝሙ የማኅበረሰቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ውስን መሆኑ ነው፡፡ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ወደ ስፍራው ከሚሄዱ ቱሪስቶች ከሚገኘው ገቢ ምን ያህል ተጠቃሚ ናቸው? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ከአጠቃላይ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ማለትም በማስጎብኘት፣ ለቱሪስቶች የተለያዩ ቁሳቁሶችን፣ ምግብ ወይም ማረፊያ በማቅረብ መጠቀም ቢችሉም እውነታው ከዚህ የራቀ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ  አለመሆኑ ቅርሶችን በመጠበቅና ቱሪዝምን በአዎንታዊ ጎኑ በመመልከት ረገድ ክፍተት ፈጥሯል፡፡

የማኅበረሰቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መሆን ከዘርፉ እንቅፋቶች አንዱ ሲሆን፣ በመዳረሻ ልማት፣ የቱሪስት ሀብቶችን በማስተዋወቅና በማስጎብኘት ረገድም መሰናክሎች እንዳሉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ የዘርፈ ብዙ ሀብቶች ባለቤት መሆኗን ከባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሌሎችም መዳረሻዎች ማራኪነት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ከተዘረዘሩት የቱሪስት መስህብ ዓይነቶች አንዱ ብቻ ጎልቶ የሚታይባቸው አገሮች ከኢትዮጵያ በበለጠ በቱሪዝም ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡

ዘ ቴሌግራፍ ጋዜጣ የዓለም የቱሪዝም ድርጅትን ጠቅሶ ዓምና ባስነበበው ዘገባ መሠረት ሲሸልስ፣ በሀማስ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ፊጂ፣ ካምቦዲያ፣ ሞሪሽየስና ሌሎችም በርካታ አገሮች ዋነኛ ገቢያቸውን የሚያገኙት ከቱሪዝም ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ሀብት ያላት አገር የነዚህን አገሮች ግማሽ እንኳን ከቱሪዝም አለመጠቀሟ አስገራሚ ተቃርኖ ነው፡፡

ለአብነት ቻይናን ብንወስድ፣ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ በተለያየ መንገድ እንዲሳተፍ ይደረጋል፡፡ ከሚዳሰሱ ቅርሶቻቸው በተጨማሪ የማይዳሰሱ ሀብቶችንም ለዓለም ሕዝብ ስለሚያስተዋውቁ በየዓመቱ በርካታ ጎብኚዎች ይጎርፋሉ፡፡ ቻይና አሁን ያለችበት ደረጃ ከመድረሷ በፊት የነበረውን ጥንታዊ ታሪክ በትርኢት የሚያቀርቡባቸው ቦታዎች በብዛት ይጎበኛሉ፡፡ ሥነ ጥበብ፣ ተፈጥሯዊ ሀብቶች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶችም ለቱሪዝም ግብዓት ናቸው፡፡ በአገራቸው ቱሪስቶች ምግብ፣ መጠጥና ቁሳቁሶች የሚሠሩበትን ባህላዊ ሒደት የሚከታተሉባቸው ቦታዎችም ትኩረት ሳቢ ናቸው፡፡ ይህ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘሙ ባሻገር፣ ቻይና በዓለም የቱሪስት ድርጅት በዓለም በግንባር ቀደምነት በሚጎበኙ አገሮች ዝርዝር እንድትመዘገብ አስችሏል፡፡

ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢጨምርም አሁንም የሚፈለገውን ደረጃ አለመደረሱን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ጎረቤት አገር ኬንያን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር ቱሪዝሙ ገና ብዙ እንደሚቀረውም ይገልጻሉ፡፡ ይኼንን በማስመልከት ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የተዘጋጀ ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም በመንታ መንገድ ላይ›› በሚል ለውይይት መነሻ ጥናት የቀረበው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ  መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ ፍሥሐ (ዶ/ር) ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የቱሪስት መስህቦች ያሏት አገር ከመሆኗ በተጨማሪ ለዘመናት ሀብቶቹ ተጠብቀው ቢቆዩም፣ ማኅበረሰቡ በቱሪዝም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ማኅበረሰቡ ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ ካልሆነ የአገር ሀብት ለሆነው ባህል፣ ቅርስና የተፈጥሮ ሀብት ተቆርቋሪ አይሆንም፡፡ በአንድ አካባቢ የቱሪዝም ሀብት እያለ፣ ቱሪስቶች ቦታውን እየጎበኙና ገንዘብ  እየተገኘ ማኅበረሰቡ ካልተጠቀመ ቱሪዝሙን ወደ መጥላትም ይሄዳሉ፤›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ቀጣይነት ያለው ቱሪዝም ለመፍጠር የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ቢኖርም በርካታ ወጣት ሥራ አጥ ነው፡፡ ሥራ አጥነት በከተማ 16.5 በመቶና በገጠር 4.5 በመቶ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ቱሪዝም ከሥራ ፈጠራ አማራጮች አንዱ እንደመሆኑ ዘርፉን በማጎልበት ለብዙዎች የሥራ ዕድል መክፈት ይቻላል፡፡ አጥኚው እንደሚሉት፣ ቱሪዝም እንደ አንድ የኑሮ ዘይቤ አልተወሰደም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ የሚወስደውን ግብርና ከቱሪዝሙ ጋር ማስተሳሰር ይቻላል፡፡ የግብርና ሒደትን ቱሪስቶች እንዲጎበኙ ማድረግና የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ የሚያመርተውን ለቱሪስቶች ወይም ቱሪስቶች ለሚስተናገዱባቸው ማረፊያ ቦታዎች እንዲያቀርብ ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በዓለም ላይ የተተገበሩ የቱሪዝም ዓይነቶች ለተፈጥሮ አደገኛ ሆነው ስለተገኙ፣ በአሁኑ ወቅት የሚበረታታው ከአካባቢ ጋር የማይፃረር ማኅበረሰብን የሚያሳትፍ ቱሪዝም (ኮምዩኒቲ ቤዝድ ኢኮቱሪዝም) ነው፡፡ ‹‹አካባቢያችን እየተንከባከብን ጎን ለጎን ቱሪዝሙን ማሳደግ አለብን፤›› የሚሉት ዶ/ር ሙሉጌታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጥሮ ሀብቱም የሰው ኃይሉም እንዳለ ያትታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም በመንታ መንገድ ላይ

 

የቱሪዝምን ጽንሰ ሐሳብ ለማኅበረሰቡ ለማስገንዘብ ቀላል ከመሆኑ ባሻገር፣ እስካሁን በቱሪዝሙ ያልተሰማራ ሰፊ የሰው ኃይል አለ፡፡ ‹‹ቱሪዝም ማኅበረሰብ ከሌለበት አያድግም፤›› በማለትም በቀጣይ ዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስረግጣሉ፡፡  በመዳረሻ ቦታው ያሉት የቱሪዝም ሀብቶችን እንዴት ወደ ገቢ ምንጭነት እንቀይር? ምን ዓይነት የቱሪዝም ዘርፎችን መከተል ያዋጣል? የሚሉት ጥያቄዎችም መመለስ አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሌላው ክፍተት የቱሪዝም ካርታ አለመኖሩ ነው፡፡ የአገሪቱ ተፈጥሮ፣ ሕልው ባህልና ታሪክ የት እንደሚገኝ፣ ምን ዓይነት ታሪካዊ ዳራ እንዳለውና ለምን ቱሪስቶችን እንደሚስብ የሚያስረዳ የቱሪዝም ካርታ የለም፡፡ ‹‹የተሟላ ዝርዝር መረጃ የሚያቀርብ የቱሪዝም ካርታ ባለመኖሩ ቱር ኦፕሬተሮች በዘልማድ ለማስጎብኘት ተገደዋል፤›› ይላሉ፡፡

እንደ ማሳያ ሀዳርን ብንወስድ፣ ዛሬም የአካባቢው ተወላጆች በባህላዊ መንገድ ቱሪስቶችን መንገድ ይመራሉ፡፡ በአንፃሩ የጎረቤት አገር ኬንያ የእንስሳት ማቆያ ሳፋሪዎችን የሚያስጎበኙ ነዋሪዎች ሙያዊ ሥርዓቱን የተከተሉ ናቸው፡፡ አጥኚው፣ በአገሪቱ በዕውቀት፣ በጥናትና በሥነ ምግባር የተደገፈ የማስጎብኘት ሥራ እንደሌለ ይጠቁማሉ፡፡ ለቱሪስት መዳረሻዎች ካርታ፣ ማንዋልና ቢልቦርድ ከማዘጋጀት ጋር በተያያዘ የመዳረሻ ልማት መጠናከርም ይገባዋል፡፡

‹‹በመዳረሻ ልማት፣ በአንድ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተመርኩዞ ክፍተቶችን በመለየት በቱሪዝሙ መልካም አስተዳደር መስፈን አለበት፤›› ይላሉ፡፡ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ባህላዊ ምግብ፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶችና ባህላዊ መጓጓዣ በማቅረብ በቱሪዝሙ መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ባህላዊ ቤት በመሥራትም መዳረሻውን ምቹ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ‹‹ማኅበረሰቡን የማብቃት፣ መዳረሻ የማልማትና የቱሪዝም ካርታ የማዘጋጀት የቤት ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ የማስተዋወቅ ሥራው ይመጣል፤›› ሲሉ ስለ ቀጣዩ ደረጃ ያስረዳሉ፡፡

የየትኛው አገር ጎብኚዎች በምን ዓይነት የቱሪስት መዳረሻ ሊማረኩ እንደሚችሉ በማጥናት ስልታዊ ማስተዋወቅ መካሄድ አለበት፡፡ ከአንድ አገር ዜጎች ባህል፣ ልማድና ፍላጎት አንፃር የቱሪስት መዳረሻዎች በኤምባሲዎች፣ በአትሌቶች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ሊተዋወቁ ይችላሉ፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ እንደ ምሳሌ ጀርመናውያን አዕዋፋትን በመጎብኘት፣ ፈረንሳውያን በቅርስ ጉብኝት እንደሚታወቁ ይጠቅሳሉ፡፡

ታሪክ፣ ቅርስና ተፈጥሮን ካማከለ ቱሪዝም በተጨማሪ፣ የስፖርት ቱሪዝም፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝምና ሌሎችም አማራጮችን መጠቀምም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ እውቅ አትሌቶች አገር ከመሆኗ አንፃር በዘርፉ በርካታ ቱሪስቶችን መሳብ ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ  የአፍሪካ መዲና ናትና በርካታ ስብሰባዎች ስለምታስተናግድ ወደ ቱሪዝም መወለጥ ይቻላል፡፡ እንደ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ አዳማ ያሉ ከተሞችም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ መሆን ይችላሉ፡፡ ወደ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሕይወት ግብርና ተኮር ከመሆኑ አንፃር፣ ግብርናንም ለቱሪዝሙ ተጨማሪ ግብዓት ማድረግ ይቻላል፡፡ ሌላው አገሪቱ ለቱሪስቶች ስትተዋወቅ ጥናትና ምርምርን በተመረኮዘ መንገድ መሆን አለበት፡፡

የቱሪዝም ሥልጠና የሚሰጡ ተቋሞች መብዛታቸው፣ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝሙ ያለው ተሳትፎና የአስጎብኚ ድርጅቶች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ እንደ መልካም አጋጣሚ ይወሰዳሉ፡፡ ሆኖም የግሉ ዘርፍና መንግሥት ከሚያገኘው ጥቅም ጎን ለጎን የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ፣ ኅብረተሰቡ ቱሪዝሙን ወደ መጥላትና ወደ መቃወም ሊያመራም ይችላል፡፡

አጥኚው እንደሚሉት፣ አስጎብኚዎችና ሌሎችም የቱሪዝሙ ዘርፍ ሙያተኞች ተገቢውን ሥልጠና ማግኘት አለባቸው፡፡ ስለሚያስጎበኙት ቦታ ከማወቅ በተጨማሪ በሥነ ምግባርም የታነፁ መሆን ይገባቸዋል፡፡

አያይዘው የሚያነሱት፣ በአንድ የቱሪስት መዳረሻ ያለውን ባህል የሚያሳይና የተፈጥሮ ሀብቱን የማይጎዳ የቱሪስቶች ማረፊያ በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ መሳተፍ እንዳለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም ሙዚቃ፣ ጭፈራና ፌስቲቫል ያማከለ ቱሪዝም መበልጸግ አለበት፡፡

የሚመጡትን ቱሪስቶች ቁጥር ከመጨመር ባሻገር፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብት በመጠበቅ ረገድ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ቱሪስቶች ወደ አንድ አካባቢ ሲሄዱ የማኅበረሰቡን ወግና ሥርዓት መገንዘብ አለባቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ባህሉን በተገቢው ሁኔታ ማስተዋወቅና ከሌላ ባህል ከመጡ ቱሪስቶች ጋር እንዴት መግባባት እንደሚችልም መገንዘብ አለበት፡፡ በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን ቴክኖሎጂ ነክ ቁሳቁሶች በስፋት በቱሪስቶች ጥቅም ላይ ስለሚውሉ፣ በተፈጥሯዊ ሀብት ጉዳት እንዳይደርስ ጥበቃም ያስፈልጋል፡፡

‹‹ማኅበረሰቡ ቱሪዝምን እንደ አማራጭ የገቢ ምንጭ መውሰድ አለበት እንጂ ብቸኛ መንገድ መሆን የለበትም፤›› የሚሉት ዶ/ር ሙሉጌታ ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የቱሪዝም መሪ እቅድ መተግበር እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ ከፌዴራል ጀምሮ፣ በክልል፣ በወረዳና በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የተዋቀረ አሠራር መተግበር እንደሚያሻም ያክላሉ፡፡ በአሁን ወቅት ቱሪዝም ከለኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የ4.5 በመቶ ድርሻውን ይወስዳል፡፡ በዘርፉ ያሉ ችግሮች ከተቀረፉ በቀጣይ ዓመታት የገቢ መጠኑን ማሳደግ እንደሚቻል በአጥኚው ተመልክቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...