ለአፋር ክልል ከተገዛ የሮለር ፕላስቲክ ፖሊሺት ግዥ ጨረታ ጋር በተገናኘ፣ ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በእስር ላይ የነበሩት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሠራተኞች ዋስትና ተፈቀደላቸው፡፡
የሚኒስቴሩ ሠራተኞች የግዥ ኮሚቴ አባልና ጸሐፊ አቶ የሰውዘር ንጋቱ፣ አባል አቶ ፈቃዱ ራሱና አቶ ዳኛቸው ክንዴ፣ የግዥ ክፍል ባለሙያ አቶ ቴዎድሮስ እማኝና አካውንታንት አቶ ፈለቀ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡
ሠራተኞቹ ለአፋር ክልል የሮለር ፕላስቲክ ፖሊሺት ግዥ ጨረታ በሚፈጽሙበት ወቅት የግዢው ኮሚቴ ግዢውን በመጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ካፀደቀ በኋላ፣ ፕሮፎርማ በነጋታው የሰበሰቡ መሆናቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስረድቷል፡፡
ኮሚቴው ግዥው በ7.36 ሚሊዮን ብር ሚኪ ከሚባል ስቴሽነሪ እንዲገዛ ካፀደቀ በኋላ፣ መጀመርያ እንዲቀርብ የታዘዘው የፕላስቲክ ፖሊሺት ርክክብ ሳይፈጸም 2,273,560 ብር ክፍያ እንዲፈጸም ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ዋጋው እጅግ በጣም የተጋነነ መሆኑን መርማሪው አስረድቷል፡፡ ግዥው ከታወቁ የመንግሥት ድርጅቶች እንዲፈጸም ወይም አቅም ካለው ድርጅት እንዲፈጸም መመርያ የተሰጠ ቢሆንም፣ ከአቅርቦቱ ጋር ምንም የሥራ ግንኙነት ከሌለውና አቅሙ ደረጃ ‹‹ሐ›› ከሆነ አነስተኛ ድርጅት መፈጸማቸውንም መርማሪው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የመረጡት የፖሊሺት ፕላስቲክ ንግድ ፈቃድ የሌለው መሆኑን፣ የተፈለገውን ዕቃ በማቅረብ የማይታወቅና የኮምፒዩተር ችርቻሮ ንግድ ፈቃድ ብቻ ያለው ስቴሽነሪ እንደሆነ፣ በዚህ ዓይነቱ ግዥ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያላግባብ በመጠቀም በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውንና ሕግና መመርያ ተከትለው መሥራታቸውን በማስረዳት የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ዋስትናውን በመቃወም ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ የመርማሪውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ፣ እያንዳንዳቸው የ25,000 ብር ዋስትና አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
መርማሪው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመቃወም ይግባኝ እንደሚል በማመልከቱ፣ ፍርድ ቤቱ ለአምስት ቀናት ውሳኔውን አግዶ የመርማሪውን ይግባኝ ውጤት ሲጠባበቅ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን መርማሪ ፖሊስ የይግባኝ አቤቱታውን መተውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በማሳወቁ፣ ችሎቱ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ ዓርብ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የተጠየቁትን ዋስትና አስይዘው እንዲለቀቁ ድጋሚ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡