የያዩ ቁጥር አንድ ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተትና የግንባታ ጉድለቶች ምክንያት፣ የኮንትራክተሩ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የአቅም ችግር መሆኑን የፕሮጀክቱ ባለቤት የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ገለጹ።
የቦርድ ሰብሳቢውና የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጀቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቡዕ ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት፣ ከኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኮንትራክተሩ አቅም ውስን በመሆኑ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ማጠናቀቅ አለመቻሉን፣ የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታው ከመጓተቱ በዘለለ፣ በፋብሪካው ግንባታ ላይ ችግሮች መከሰታቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት በአካል ተገኝተው መታዘባቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ በማስረጃነትም የፋብሪካው የድጋፍ ግንብ ስድስት መቶ ሜትር ያህል መሰንጠቁን፣ የኩሊንግ ታወሩ እየሰመጠ መሆኑን፣ ግንባታው በተመረጠበት አካባቢ ረዥም የመሬት መሰንጠቅ መኖሩን በማውሳት መንስዔውንና ዘላቂ መፍትሔውን ጠይቋል፡፡ በኮንትራክተሩ ሜቴክ፣ በፕሮጀክቱ ባለቤትና በአማካሪው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መካከል መግባባት አለመኖሩንም ጠቁሟል። በአማካሪ ተቋሙ የሚሰጡ የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦች በኮንትራክተሩ ተግባራዊ እንደማይደረጉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በመግለጽ ማብራርያ ጠይቀዋል።
የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ሚኒስትር ሞቱማ መቃሳ ሜቴክ ባለው አቅም ሥራውን ለመሥራት የገባበት ቢሆንም፣ የአቅም ውስንነት ያለበት በመሆኑ ፕሮጀክቱን በወቅቱ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ ገልጸዋል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመደጋገፍ ያሉትን ችግሮች በጥናት መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሞቱማ፣ በዚህ ፕሮጀክት የተነሳ “መንግሥት ከሕዝቡ ከፍተኛ ጥያቄ እየተነሳበት” ነው ብለዋል።
በፋብሪካው የአቃፊ ግንብ 11 እና 12 (Retaining wall) መሰንጠቅና መስመጥ፣ እንዲሁም በኩሊንግ ታወር በተከሰተው የመስመጥና የመሰንጠቅ ችግር የተከሰተው በ2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ መፍትሔ እንዳላገኘ በወቅቱ የፕሮጀክቱ ባለቤት አመራሮችና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በየነ ገብረ መስቀል ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የአማካሪው ድርጅትና የሥራ ተቋራጩ ጂኦቴክኒካል ኢንጂነሮች በጋራ ባስቀመጡት የመፍትሔ አቅጣጫ ወደ ሥራ እንዲገባ ከማድረግና ከመደገፍ አኳያ እንደሚከታተሉ ገልጸዋል።
ሜቴክ ለማዳበሪያ ፋብሪካው 60 በመቶ ክፍያ ተከፍሎት የፈጸመው ከ50 በመቶ በታች ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ሦስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ክፍያ መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል። ፕሮጀክቱን በአነስተኛ ወጪና የጊዜ ገደብ ውስጥ ሠርቶ እንደሚያስረክብ በመግለጹ ምክንያት፣ በ600 ሚሊዮን ዶላር ገንብቶ ለማስረከብ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ፈጽሞ ከነበረ አንድ የቻይና ኩባንያ ተነጥቆ ለሜቴክ መሰጠቱን መዘገባችን ይታወሳል። ከዓመት በፊት ለፕሮጀክቱ በነበረው ትንበያ ፋብሪካውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው 19 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተገምቶ ነበር።