Friday, January 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ3.4 ቢሊዮን ብር የ850 አውቶብሶች ግዥ ፈጸመ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ3.4 ቢሊዮን ብር የ850 አውቶብሶች ግዥ ፈጸመ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው የተንሰራፋውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት በ3.4 ቢሊዮን ብር የ850 አውቶብሶች ግዥ ፈጸመ፡፡

ከነዚህ አውቶብሶች መካከል 150 የሚሆኑት አገር ውስጥ ገብተው በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በመገጣጠም ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ከእነዚህ አውቶብሶች ውስጥ 100 የሚሆኑት በሸገር ብዙኃን መገናኛ ድርጅት አማካይነት ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ 50 አውቶብሶች ባለሁለት ደርብ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 25 የሚሆኑት ለሸገር ብዙኃን መገናኛ ድርጅትና 25 ደግሞ ለአንበሳ አውቶብስ ድርጅት ይመደባሉ፡፡

‹‹የእነዚህ አውቶብሶች በብዛት ወደ ሕዝብ መግባት የትራንስፖርት ችግርን ያቃልላል፡፡ ምቾት ያላቸው በመሆኑም በሒደት ሚኒባስ ታክሲዎችን እየተኩ ይሄዳሉ፤›› ሲሉ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡  

በአዲስ አበባ ከተማ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ብቻ ሳይሆን ቀኑን ሙሉ የትራንስፖርት እጥረት እየተስተዋለ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ትራንስፖርት የመጠበቂያ ሠልፍ ሰዓት 15 ደቂቃ ይቆያል ቢልም፣ ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ድረስ ተሠልፈው ትራንስፖርት እንደሚጠብቁ ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ የመኖሪያ መንገዶች ትራንስፖርት እያገኙ አለመሆኑንና ለትራንስፖርት አመቺ የመሠረተ ልማት አለመሟላቱንም ይናገራሉ፡፡

በተለይ መንግሥት ለኮንትራት ታክሲዎችና ለብዙኃን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የሰጠውን ትኩረት፣ ለመለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች (ሚኒባስ)  አለመስጠቱ ለችግሩ መባባስ እንደ ምክንያት እየቀረበ ነው፡፡   

ነገር ግን ኃላፊው እነዚህ አውቶብሶች ሥራ ላይ ሲውሉ ሚኒባስ ታክሲዎች ከሲስተም እየወጡ ይሄዳሉ ይላሉ፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት በኅብረተሰቡ ዘንድ ሚኒባስ ታክሲዎች ተመራጭ የሚሆኑት መቀመጫ ስላላቸው ነው፡፡ እነዚህ አውቶብሶች በመቀመጫ የሚኬድባቸውና ምቾት ያላቸው በመሆኑ ተመራጮች ናቸው፡፡ መንግሥትም ትኩረቱ ብዙኃን ትራንስፖርትን ማበረታታት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ ሊያስገባ ያቀዳቸውን ተጨማሪ አውቶብሶች በነባር መስመሮች ከመመደቡ በተጨማሪ፣ በሌሎች አዳዲስ መስመሮች እንደሚያሰማራ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሀብት መድቦ የአውቶብሶች ግዥ ፈጽሟል፡፡

እነዚህ አውቶብሶች ትራንስፖርት የመጠበቂያ ጊዜ ከማሳጠር በተጨማሪ፣ የከተማውን የትራንስፖርት እጥረት ያቃልላሉ ሲሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...