የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው ሰባት ሠራተኞችና ሁለት አማካሪዎች (በሌሉበት)፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ በድምሩ ከ81.2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው፣ ሐሙስ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዘጠኙ ተከሳሾች ላይ ሰባት ክሶችን አደራጅቶ ያቀረበ ሲሆን፣ ክሶቹን እንደ ተከሳሾቹ የድርጊት ድርሻ ከፋፍሎ አቅርቧቸዋል፡፡ በመሆኑም በድርጅቱ የጭነት ማስተላለፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ መስፍን ተፈራና የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ ሲሳይ አባፈርዳ ክሱ የቀረበባቸው፣ በጋራ ፈጽመውታል በተባለው ድርጊት ነው፡፡
ሁለቱ ተከሳሾች ክስ የተመሠረተባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅት ለሆኑት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ለኮሜት ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር፣ ለበከልቻ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርና ለዕለት ደራሽ አክሲዮን ማኅበር 280 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ግዥ ጋር በተገናኘ መሆኑን፣ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡
ተሽከርካሪዎቹን ለመግዛት በኢትዮጵያን ሔራልድ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ፣ አሸናፊው ድርጅት ያቀረባቸው ተሽከርካሪዎች በውሉ ላይ በተቀመጠው ስፔስፊኬሽን መሠረት አለመሆኑንና ድርጅቱ ያስያዘው የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና (Performance Bond) ጊዜው ያለፈበት መሆኑን እያወቁ፣ ተከሳሾቹ ርክክብ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከስፔስፊኬሽን፣ ከውሉና ከሌሎች ‹ቴክኒካል ኮምፕሊያንስ› ሰነድ አንፃር ሲመረመሩ 11 ጉድለቶች የተገኘባቸው መሆኑን የቴክኒክ ኮሚቴው ሪፖርት ሲያደርግ፣ አቅራቢው ድርጅት እንዲያሟላ ማድረግ ሲገባቸው፣ ጊዜያዊ ርክክብ ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡ ጊዜያዊ ርክክቡ ከተደረገ በኋላ አቅራቢው ድርጅት ስለጉድለቶቹ ማብራሪያ እንዲሰጥ በማድረግና ጉድለቶቹን ወደ ሁለት ዝቅ እንዲሉ በማድረግ፣ ባልተሟሉት ጉድለቶች ምክንያት በሕዝብና መንግሥት ላይ የ7,546,500 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
ከድርጅቱ ዘጠኝ አዳዲስ መርከቦችን ከማስገንባትና 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል አከባበር ጋር በተገናኘ 1,458,217 ብር በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብሎ፣ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው የድርጅቱ የጂቡቲ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት አቶ ሲራጅ አብዱላሂ ላይ ነው፡፡ አቶ ሲራጅ ከሚገነቡት አዳዲስ ዘጠኝ መርከቦች ጋር በተገናኘ ምን እንዳደረጉ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም፣ ከድርጅቱ 50ኛ ዓመት በዓል አከባበር ጋር ፈጽመውታል ያለውን ድርጊት አብራርቷል፡፡ በዓሉን ለማክበር የሚያስፈልጉ ግዥዎችን በቀጥታ ለመፈጸም፣ በድርጀቱ በተሻሻለው የግዥ መመርያ ቁጥር 02/2006 መሠረት መከናወን እንደነበረበት ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ከአንድ አቅራቢ ብቻ ግዥ የሚፈጸመው አገልግሎቱ የሚገኘው ከአንድ ተወዳዳሪ ብቻ መሆኑና ሌላ ተወዳዳሪ አለመኖሩ ሲረጋገጥና አስቸኳይ ሲሆን፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚው ተረጋግጦና በሥራ አመራር ቦርድ ተፈቅዶ መሆኑ እየታወቀ፣ ተከሳሹ ግን ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ከተለያዩ ድርጅቶች የተለያዩ የበዓል ማክበሪያ ቁሳቁሶች እንዲገዙ በማዘዝ፣ የተጠቀሰውን ያህል ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
በድርጅቱ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወትና የየብስ ወደቦች ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መምርያ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተናገር ይስማው የተከሰሱት፣ ለሰመራ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የክሬን ኪራይ ውል ከመፈጸም ጋር በተገናኘ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ የድርጅቱ ክሬን መበላሸቱንና ለማስጠገንም ከአቅም በላይ መሆኑን ለኃላፊዎቹ ሲነገራቸው፣ ክሬን አስመጪ በሆነው ሐግቤስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በኩል በአስቸኳይ ከማስጠገን ይልቅ፣ ኃላፊዎቹ የመረጡት መከራየትን መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ሔኖክ አሰፋ የኮንስትራክሽን መሣሪዎች አከራይ ድርጅት ጋር ውል በመፈጸም፣ ለሦስትና ለአራት ሰዓታት 6,000 ብር በመክፈል በ14 ወራት ውስጥ 2,225,600 ብር እንዲከፈል በማድረግ፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከፍተኛ የሆነ ወጪ እንዲያወጣ በማድረግ፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ የ65,594,160 ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የሚል ክስ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው፣ በድርጅቱ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በነበሩት ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ላይ ነው፡፡ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከነበሩት አቶ አህመድ ቱሳ ጋር በመሆን የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ ለኮንቴይነር ኪራይ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ በሚል ድርጅቱ ኮንቴይነር እንዲገዛ የአዋጭነት ጥናት አስጠንተው በድርጅቱ ቦርድ ማፀደቃቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ቦርዱ ካፀደቀ በኋላ 2,580 ኮንቴይነሮችን በ199,237,000 ብር ለመግዛት የወጣውን ጨረታ፣ ጄኔራል ኤክስፖርት ማሸነፉንም አክሏል፡፡ ነገር ግን በበጀት ዓመቱ ግዥው እንዳልተፈጸመ ዓቃቤ ሕግ ጠቁሞ አሸናፊ ድርጅት በድጋሚ በድርጅቱ የግዥ መመርያ አንቀጽ ዘጠኝ መሠረት ግዥው እንዲፈጸም ማድረግ ሲገባ፣ ተከሳሹ ባለማድረጋቸው አቶ አህመድ ቱሳ ግዥው እንዲሰረዝ መወሰናቸውን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሟል፡፡ ግዥው ከተሰረዘ ከግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለ2,580 ኮንቴይነሮች ኪራይ 65,594,160 ብር ወጪ መደረጉንና በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወትና የድርጅቱ የፋይናንስ አካውንት መምርያ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሳሙኤል መላኩ ላይ ዓቃቤ ሕግ በጋራ ክስ ያቀረበባቸው፣ ከሞጆ ደረቅ ወደብ መጋዘን ቁጥር አንድ ግንባታ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ ደረቅ ወደቡን ለማስገንባት ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በ67,989,786 ብር ለማስገንባት ከተቋራጩ ጋር ውል መፈጸሙን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስታውሶ፣ ተቋራጩ ቅድመ ክፍያ ጠይቆ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዋጋ 30 በመቶ 20,391,935 ብር በሦስት ጊዜ ክፍያ መክፈሉንም አክሏል፡፡ ለተቋራጩ ቀሪው ክፍያ የሚፈጸምለት ሥራው በአማካሪው ድርጅት ተገምቶና ፀድቆ ሲቀርብ መሆኑ እየታወቀ፣ ተቋራጩ በድጋሚ 14,100,000 ብር እንዲከፍለው ሲጠይቅ፣ ተከሳሾቹ እንዲከፈለው በማድረጋቸው ከመመርያ ውጪ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረጋቸው የ4,410,000 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሌሉበት ክስ የመሠረተባቸው የኮንስትራክሽን ዲዛይን አክሲዮን ማኅበር መሐንዲሶች የነበሩት አቶ ሰሎሞን ለገሰና አቶ ተስፋዬ አማረ ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ ድርጅቱ ለሚያስገነባው ሞጆ ደረቅ ወደብ መጋዘን ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 አማካሪ ሆነው ሲሠሩ፣ ተቋራጩ ያልሠራውን ሠርቻለሁ በማለት ክፍያ ሲጠይቅ፣ በማፅደቅና የመጋዘኑ ጣሪያ የተሠራበት ማቴሪያል ከታዘዘው ውጪ መሆኑን እያወቁ ክፍያ እንዲፈጸም ሊያደርጉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ጠቁሞ፣ ክፍያው ግን እንዳልተፈጸመ ገልጿል፡፡ ክፍያው ተፈጽሞ ቢሆን ግን በድምሩ 2,532,788 ብር ጉዳት ይደርስ እንደነበር አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና 3)፣ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 (1ሐ እና 3)፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 (1ሀ እና 3)፣ አንቀጽ 411(1ሐ እና 3) አንቀጽ 27(2)፣ አንቀጽ 411(1ሐ እና 2) ሥር የተደነገገው ተላልፈዋል ብሎ፣ ዓቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለእያንዳንዱ ተከሳሽ ክሱ እንዲደርስ አድርጎ ክሱን በችሎት አንብቧል፡፡ ክሱ ግልጽ መሆን አለመሆኑን ጠይቆ ካረጋገጠ በኋላ፣ በክሱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ጠይቋል፡፡ የአቶ መስፍንና የአቶ ሲሳይ ጠበቆች በሰጡት አስተያየት፣ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽና የተዘረዘረው ፍሬ ነገር የማይገናኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ዋስትና ስለማይከለክል፣ ደንበኞቻቸው በዋስ ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ ሌሎቹም ተከሳሾች የደም ግፊት፣ የኩላሊት፣ የልብና የጨጓራ ሕመም እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ በልዩ ሁኔታ በቂ ዋስ ጠርተው በውጭ ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ዋስትናን በሚመለከት በሰጠው አስተያየት፣ በተከሳሾቹ ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ከአሥር ዓመታት በላይ ሊያስቀጣ እንደሚችል አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ሕጉ ራሱ ክልከላ ስለጣለበት ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይቻል አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ አቶ መስፍንና አቶ ሲሳይ ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት በቅድመ ክስ መቃወሚያ ላይ የሚያነሱትን ክርክር ዓይቶ ብይን እንደሚሰጥበት አስታውቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸው በክሱ ላይ የተጠቀሱት አንቀጾች ዋስትና እንደሚከለክሉና ከፍርድ ቤቱ ሥልጣን በላይ መሆኑን አስረድቶ፣ የክስ መቃወሚያው ካላቸው ለመጠባበቅ ለኅዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡