Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የመጠበቅ ጉዳይ የማይገረሰስ የኢሕአዴግ መርህ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ...

‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የመጠበቅ ጉዳይ የማይገረሰስ የኢሕአዴግ መርህ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ቀን:

  • አፈ ጉባዔ አባዱላ የድርጅቱን ውሳኔ የመቀበል ግዴታ አለባቸው ብለዋል

በአገሪቱ ከሚታዩ የፖለቲካ ክስተቶች በተቃራኒ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አሁንም ጥብቅ የሆነውን ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ እንደሚገኝ፣ ይህንንም ማዕከላዊነት ጠብቆ የማቆየት ጉዳይ የማይገረሰስ የገዥው ፓርቲ ምሰሶ እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከረዥም ጊዜ ቆይታ በኋላ ሐሙስ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤታቸው ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ  ሲሰጡ፣ ገዥው ፓርቲ የሚታወቅበትን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በአንድ ፓርቲ የበላይ ከፍተኛ አመራር ውሳኔዎች የሚተላለፍበትና ይህ ውሳኔ እስከ ታችኛው መዋቅር ተግባራዊ የሚሆንበት አሠራር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ጽንሰ ሐሳብና አሠራር የሶሻሊዝም ሥርዓት በዓለም ጉልህ ሆኖ በቆየባቸው ጊዜያት የተወለደ ቢሆንም፣ እስካሁን በተለያዩ የዓለም አገሮች በተለይም በሩቅ ምሥራቅ አካባቢ የሚታወቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ጽንሰ ሐሳብና አሠራር በተለይ በኢሕአዴግ ያለፉት 26 ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ የሆነና የፓርቲውም የሚታወቅ ባህል ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን የፓርቲውን አሠራር የሚፈትኑ የማፈንገጥ አዝማሚያ ያላቸው እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ የፖሊሲ ማዕቀፍ ውጪ ‘ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ’ (Public Private Partnership) ሥልቶችን በመከተል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በተናጠል መከተል መጀመራቸው፣ ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ቀደም ሲል ተቃውመውት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ሪፖርተር ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን አስመልክቶ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ የሚታወቅበት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መሸርሸሩን የሚያመለክቱ ክስተቶች መኖራቸውን፣ ከእነዚህ መገለጫዎች ውስጥ አንዱ የፓርላማው አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ከሥልጣን ለመልቀቅ መፈለጋቸውን በይፋ ከገለጹ በኋላ፣ የሕዝባቸውንና የድርጅታቸውን ክብር ለማስመለስ እንደሚታገሉ መግለጻቸውን በአብነት አንስቷል፡፡

ይህ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በመሸርሸር ኢሕአዴግን ሊበትነው ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የመጠበቅ ጉዳይ የማይገረሰስ የኢሕአዴግ መርህ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አንድ ሰው ከድርጅቱ በመውጣቱ ምክንያት ኢሕአዴግን የሚያህል ግዙፍ ድርጅት ይበተናል ብሎ ማሰብ ስህተት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ አፈ ጉባዔ አባዱላ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ስላቀረቡት ጥያቄ ሪፖርተር ጋዜጣ መረጃ ደርሶት ከዘገበ በኋላ፣ ሐሳቸውን በግልጽ ለማስረዳት አቶ አባዱላ ወደ ሚዲያ መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ድርጊታቸው ስህተት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹አቶ አባዱላ አሁንም ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ጥሰዋል ማለት አይደለም፡፡ መልቀቂያቸውን አስመልክቶ ድርድር ላይ ነን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ድርጅቱ በወሰነው መሠረት የመሄድ ግዴታ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማፈናቀልና በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን መነሻ ምክንያት አስመልክቶ ሲያብራሩም፣ ‹‹የከፍተኛ አመራሩ የተሳሳተ አመለካከት››ን ጠቅሰዋል፡፡

ከኢሕአዴግ መሠረታዊ መርሆዎች መካከል አንዱ የትኛውም አካባቢ ያሉ ሕዝቦችን በእኩል ዓይን ማየት መሆኑን ጠቁመው፣ የሚታዩ ችግሮች አመራሩ በአንድ አካባቢ ያለን ሕዝብ ‹‹የእኔ ሕዝብ›› በሌላ አካባቢ ያለን ሕዝብ ‹‹የሌላ ሕዝብ›› ብሎ ማየት የወለደው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመላው የኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች የተሳሳተ አስተሳሰብ በሚይዙበት ወቅት፣ የሚያራምዱት ብሔር ተኮር አጥፊ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በዚህ አመለካከት ላይ በኢሕአዴግ አመራሮች መካከል ሰፊ ትግል ተካሂዶ የተያዘው አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን፣ በሁሉም የኢሕአዴግ መሥራች ድርጅቶችና አመራሮች መካከል መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡

ችግሩ መሠረታዊ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አገሪቱ እንዳትበታተን ከተፈለገ በየትኛውም አካባቢ ያሉ ሕዝቦችን አመራሩ በአንድ ዓይን ሊያይ ይገባል ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ችግር የፀጥታ ኃይሎችም ደም ለይተውና ዘር ቆጥረው መሰለፋቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ፍጭት ተካሂዶ ስምምነት የተደረሰበት በመሆኑ፣ ይህንን ተግባራዊ የማድረግና የማስፈጸም ኃላፊነት በሁሉም አመራሮች ላይ እንደሚወድቅና ይህም የድርጅቱን ማዕከላዊነት የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ዕቅድ አውጥቶ በግጭቶች የተሳተፉትን በሙሉ በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች በተሳተፉ አመራሮች ላይ የእያንዳንዱ ድርጅት ፖለቲካዊ አመራሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎች መያዛቸውንና ቀሪዎቹ በቀጣይ ጊዜያት የሚያዙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎችን ግጭት መርምሮ ሪፖርት እንዲያቀርብ መታዘዙንና ይህንን ተከትሎም ዕርምጃ መውሰድ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...