ኢትዮጵያውያን በመረጡበት ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራት፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብታቸው በሕግ የተረጋገጠ ቢሆንም ተግባራዊ ባለመሆኑ ብቻ፣ በበርካታ ዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ በደል ተፈጽሟል፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ‹‹መጤ›› እየተባሉ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ሲፈናቀሉና ሲገደሉ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታይቷል፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሕገ መንግሥት አማካይነት ቃል ኪዳን በተገባበት አገር ውስጥ፣ ዜጎች በታጠቁ ኃይሎች ሳይቀር የግፍ ፅዋ ቀምሰዋል፡፡ በተደራጁ ኃይሎች አማካይነት ተቀስቅሰው በተነሱ አፍለኞች ሳይቀር ለዘመናት አብሮ በሰላም ከኖረ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ በርካቶች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተሰደዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን ሥጋት ላይ የጣሉ ግጭቶች ፍንትው አድርገው የሚያሳዩት፣ አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን ነው፡፡ ከክልል መንግሥታት እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ምን እየሠሩ ነው የሚል ሥጋት አዘል ጥያቄ የሚነሳው፣ የዜጎች በሰላም የመኖር መብት ከአደጋ ጋር በመጋፈጡ ነው፡፡ የፖለቲካ ሽኩቻ ውጤት የሆነው ይህ አደጋ አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንጀራ ፍለጋ የተሰማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ይኖራሉ፡፡ የእነዚህን ወገኖች ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ደግሞ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲያቅታቸው ሕግ አይከበርም፡፡ ሕግ ካልተከበረ ደግሞ ዜጎች ያፈሩትን ሀብት የሚፈልግ ወይም በጠባብ ብሔርተኝነት የተለከፈ ኃይል ሕገወጥ ድርጊት ይፈጽማል፡፡ ብሔርን መነሻ ያደረጉ ጥቃቶች የሚፈጸሙት ከኋላ የሚቆሰቁሱ ኃይሉች ስላሉ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች አንድም ሥርዓቱን በዚህ መንገድ ለመጣል የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሆነው ለፖለቲካዊና ለኢኮኖሚያዊ የበላይነት ትንቅንቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ የሕግ የበላይነት እንዲጠፋ ተደርጎ ገለልተኛ ሆነው ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው የፀጥታ ኃይሎች ጭምር የግጭቱ አሟሟቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተነሳው ግጭት ከዚህ ምልከታ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጥቃት የተፈጸመባቸው የሌሎች ብሔሮች ተወላጆችም የእዚህ ዓይነቱ ሴራ ሰለባ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ መቀጠል ይቻላል?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰጡት ምላሽ የሚጠቁመው ነገር አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው ችግር በገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል ሳይሆን፣ በአመራሩ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው በፓርቲ አመራሮች ዘንድ ሁሉንም ሕዝብ እንደ ራስ ሕዝብ ያለማሰብ አቋም መኖሩን፣ ይህም ችግር የሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና የአጋር ድርጅቶች መሆኑን በግልጽ አስረድተዋል፡፡ የፀጥታ አካላትም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት ማስከበር ሲገባቸው፣ በደምና በጎሳ በመለየት ሕዝብን የማየት አዝማሚያ እንደስተዋለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በግጭት ውስጥ የተሳተፉ መኖራቸውን ጭምር ነው ያወሱት፡፡ ይህ በመሠረቱ የሕግ የበላይነትን የሚፃረርና አብሮ መኖርን ችግር ውስጥ የሚከት የአገር ሕመም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብን ፍላጎት የሚቃረንና የዘመናት መስተጋብሩን የሚደረምስ ሕገወጥ ድርጊት ነው፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር ሲፈጸም ዝም ብሎ ማየት ካላስጠየቀ ምን ሊያስጠይቅ ነው? ሕገ መንግሥቱ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው በግልጽ የደነገገላቸው የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግሥታት ምን እየሠሩ ነው? አመራር የሚባሉትስ ይህንን በሕግ የተገደበ ሥልጣናቸውን ለሌላ ዓላማ ሲያውሉት ዝም ማለት ምን ማለት ይሆን? ይህ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በግልጽ ሊነገረው ይገባል፡፡
ሌላው ዘወትር የሚነሳው የመንግሥት ዝግ ፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ መንግሥትን የሚመራው ኢሕአዴግ ባህሌ ነው ብሎ የሚመፃደቅበት ዝግ ፖሊሲ፣ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህ የዝግ ፖሊሲ ባህል በዚህ ኢንፎርሜሽን ያለ ገደብ በሚፈስበት ዓለም ውስጥ ሥፍራ የለውም፡፡ ለዘመኑም አይመጥንም፡፡ ኢሕአዴግ የውስጥ የፖለቲካና የሐሳብ ትግሉን ይፋ የማድረግ ግዴታ ባይኖርበትም፣ ከመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን መሸፋፈን ግን አይችልም፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መንግሥት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትም አለበት፡፡ አገር በግጭቶች እየታመሰች፣ ክቡር የሆነ የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች እየተፈናቀሉና የአገር አንጡራ ሀብት እየወደመ ሕዝብ ስለአገሩ መረጃ የለውም፡፡ ያልተሟሉና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መረጃዎች በመንግሥት አካላት እየተለቀቁ ግራ ሲጋባ ነበር፡፡ መንግሥት ኃላፊነት የሌለበት ይመስል መረጃ ነፍጎ ሕዝብ ለአሉባልታና ለሐሰተኛ ወሬ ጭምር እየተዳረገ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መረጃ ከመስጠት አንፃር በመንግሥት በኩል ችግር ስለነበር፣ ሕዝብ በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚናፈሱ አሉባልታዎችና ፕሮፓጋንዳዎች መጋለጡን አምነዋል፡፡ መንግሥት በሕጉ መሠረት ሥራውን ማከናወን ሲያቅተው ውዥንብር ይነግሣል፡፡ ውዥንብር በተራው ለግጭት በር ይከፍታል፡፡ ይህ የዝግ ፖሊሲ ባህል የፈጠረው ጣጣ መፍትሔ ካልተበጀለት ችግሩ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከዚህ ዘመን ጋር አብሮ ስለማይሄድ አስቸኳይ ማስተካከያ ያስፈልገዋል፡፡
የዜጎች ደኅንነት ማንንም ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው የባይተዋርነት ስሜት የሚሰማቸው ብሔርተኝነት እየተለጠጠ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ሲፈታተነው ነው፡፡ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው፣ በራሳቸው መዳኘታቸው፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማሳደጋቸው፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበታቸውና በማንነታቸው መኩራታቸው መከበር አለበት፡፡ ነገር ግን በተለይ ወጣቶች ራሳቸው ላይ አጥር ሠርተው ሌሎች ወገኖቻቸውን አትድረስብኝ አልደርስብህም የሚል ችግር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉት፣ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች መሆኑንም ማመን ተገቢ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ለዘመናት አብሮ የኖረው ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠባብነትና የጋራ እሴቱን የሚንዱ ድርጊቶችን እንደማይቀበል በታሪኩ በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ የሚፈልገው በክፉና በደግ ጊዜያት አብሮ ተደጋግፎ እንደኖረው በዚሁ መሠረት መቀጠል ነው፡፡ ይህንን አስደሳችና የሚያኮራ የጋራ እሴት ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ መሠረት ማድረግ ሲገባ፣ ለግለሰቦችና ለቡድኖች ጥቅም ብቻ ሲባል ግጭት እየፈጠሩ አገር ማመሰቃቀል ሊቆም ይገባል፡፡ ተወደደም ተጠላም በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ሳይቀሩ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ማንም የለም፡፡
አሁን አገርን ማረጋጋትና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ትልቁ ኃላፊነት በመንግሥት ላይ ነው፡፡ ሙስናም ይባል ኪራይ ሰብሳቢነት ሰበብ እየተደረገ በዜጎች ሕይወት ላይ መቀለድ መብቃት አለበት፡፡ የክልሎችም ሆነ የፌዴራል መንግሥት መዳከም የሚበጀው ለአገር ጠላቶች ብቻ ነው፡፡ ሲጠናከሩ ደግሞ የሚጠቀመው መላው ሕዝብ ነው፡፡ ይህ መጠናከር የሕግ የበላይነትን ካላሰፈነ ደግሞ ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መስፈን የሚጠቅመው ለሕዝብ ደኅንነት መጠበቅ ነው፡፡ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ መግባት ብቻ ሳይሆን፣ ዘለቄታዊ ሰላሙ የሚረጋገጠው በሕግ የበላይነት ብቻ ነው፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው በእኩልነትና በመተሳሰብ መኖር የሚቻለው ሕግ የበላይ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ከአቅማቸው በላይ እየሆነ በሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት እየደረሰ ያለው የሕግ የበላይነትን የሚጋፉ በመብዛታቸው ነው፡፡ ብሔር እየመረጡ ማጥቃት፣ መግደልና ማፈናቀል የሕገወጥነት ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን እርኩሰት መቆጣጠር አለመቻል ደግሞ ሌላው የሕገወጥነት መገለጫ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ዕብደት ውስጥ በመውጣት አገርን መታደግና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር አለመፍጠር አገርን ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ ሕዝብን ለመከራ ይዳርጋል፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡ መብቶቹ ያለመሸራረፍ ይከበሩ፡፡ ሕገወጦች አደብ ይግዙ፡፡ ለዚህ ደግሞ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት የሕዝብን ደኅንነት የማስጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለባቸው!