Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶች የክልሎች አመራሮች ኃላፊነት ይወስዳሉ ተባለ

  በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶች የክልሎች አመራሮች ኃላፊነት ይወስዳሉ ተባለ

  ቀን:

  በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ላሉ ሕገወጥ ሠልፎችና ግጭቶች የክልሎች አመራሮች ኃላፊነት እንደሚወስዱ፣ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

  የጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዓርብ ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ የተካሄደው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤትና የክልል ደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባ ሲጠናቀቅ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የክልሎች አመራሮች እየተካሄዱ ያሉ ሕገወጥ ሠልፎችንና ግጭቶችን ማስቆም አለባቸው፡፡

  የአሸባሪዎችን ባንዲራ ይዘው ሕገወጥ ሠልፍ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይህንን አደገኛ እንቅስቃሴ የክልል አመራሮች የማስቆም ግዴታ ምክር ቤቱ እንደጣለባቸው ገልጸዋል፡፡

  እንደነዚህ ዓይነት አዝማሚያዎች ሲኖሩ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው፣ ይህ ተፈጻሚ ካልሆነ ግን ራሳቸው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ምክር ቤቱ መወሰኑን አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡

  ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት ተሳታፊ የነበሩ የፀጥታ አካላትና ከፍተኛ አመራሮች እንደነበሩ ጠቁመው፣ እነዚህ ሰዎች በብሔራዊ ደኅንነት መለየታቸውንና በቅርቡም ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጸዋል፡፡

  አቶ ሲራጅ እንደተናገሩት፣ የስብሰባው ዋና ዓላማ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለችበትን የፀጥታና የሰላም ሁኔታ ገምግሞ አዳዲስ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው፡፡ በግምገማው ወቅትም በ2010 ዓ.ም. አገሪቱ ካለችበት የፀጥታ ችግር እንድትወጣ አዳዲስ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አነሰም በዛ በሁሉም ክልሎች የፀጥታ ችግር እንዳለ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይህንን ችግር ለመፍታት የብሔራዊ ደኅንነትና የክልል የፀጥታ አካላት ተባብረው እንዲሠሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ ‹‹ሁሉም ክልሎች የራሳቸውን አቅደው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ከስምምነት ላይ ደርሰናል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ዕቅድም ለአንድ ዓመት የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው በሚመለሱበት ላይ ምክር ቤቱ ውይይት ማድረጉንና ስምምነት ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

  ተፈናቃዮችን በአስቸኳይ ለማቋቋምም በአሁኑ ወቅት በፌዴራል መንግሥት በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

  በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ የፀጥታ አካላት መለየታቸውንና በእነሱ ላይም ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ መንግሥት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

  በግጭቱ ወቅት ለብሔራቸው ወግነው ግጭቱ እንዲባባስ ያደርጉ የነበሩ የፀጥታ አካላት እንደነበሩና እነሱን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

  በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የፀጥታ መደፍረስ ዕልባት ለመስጠትም፣ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ በመስጠት እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡  

  በብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓብዩ አሠፋ፣ የአየር ኃይልና የምድር ጦር አመራሮች፣ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ፣ የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባዎችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው ነበር፡፡  

  ስብሰባው ግማሽ ቀን ብቻ እንደሚፈጅ ዕቅድ ቢወጣለትም፣ በሰዓቱ መጠናቀቅ ባለመቻሉ እስከ ቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ቆይቷል፡፡

  በስብሰባው ላይም አገሪቱ ያለችበት የፀጥታ ጉዳይ ተነስቶ ብዙ ክርክርና ውይይት እንደተደረገበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ አንዳንድ ተሳታፊዎች መንግሥት ችግሩን ለማስቆም የወሰደው ዕርምጃ አነስተኛ እንደሆነ ከማንሳትም በላይ፣ በ2010 ዓ.ም. የአገሪቱን ፀጥታ ለማስከበር የቀረበው ዕቅድ ከፍ ባለ ደረጃ ሊቀርብ ይገባ እንደነበር መግለጻቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...