Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹ዘጠና ዘጠኝ በመቶ መንግሥት በሚደጉመው ስፖርት በጣልቃ ገብነት ሽፋን ወዳልሆነ አቅጣጫ መሄድ...

‹‹ዘጠና ዘጠኝ በመቶ መንግሥት በሚደጉመው ስፖርት በጣልቃ ገብነት ሽፋን ወዳልሆነ አቅጣጫ መሄድ ጉዳት እንዳለው መዘንጋት የለበትም››

ቀን:

አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችና ውዝግቦች ከወትሮው በተለየ መልኩ ተጠናክረው እንደቀጠሉ ይገኛል፡፡ በዚሁ ምክንያት ጥቅትም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ሊደረግ ታቅዶ የነበረው፣ የፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ለ45 ቀን እንዲራዘም በድምፅ ብልጫ ተወስኗል፡፡ በከፍተኛ ውጥረት ታጅቦ እንዲራዘም የተደረገው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ በቀረበው የ45 ቀን ጊዜ፣ እግር ኳሱ የሚፈልጋቸውን አመራሮች በቦታው ለማስቀመጥ እንደ አንድ አማራጭ ተደርጎ ቢታመንም፣ ነገር ግን በጉባዔተኛው ዘንድ አሁንም ጥርጣሬ ማጫሩ አልቀረም፡፡ በእነዚህና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በታዛቢነት በጉባዔው የታደሙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ተክለ ሰውነት በተለይም በአሁኑ ወቅት ጥያቄ ውስጥ እየገባ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ በዋናነት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳለ ይነገራል፡፡ እዚህ ላይ የሚኒስቴሩ አቋምና እምነት እንዴት ይገለጻል?

- Advertisement -

አቶ ተስፋዬ፡- ሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤቱ እያንዳንዱ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ሕዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ከአቅም ግንባታ ጀምሮ ድጋፍና እገዛ ከማድረግ ያለፈ በአሠራራቸው ጣልቃ አይገባም፡፡ የፌዴሬሽኖች ትልቅ የሥልጣን አካል ተብሎ በሚታመነው ጠቅላላ ጉባዔያቸው በሚያስቀምጥላቸው አቅጣጫ ለደንብና መመርያዎቻቸው ተገዥ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፡፡ እያንዳንዱ አገር አቀፍ ፌዴሬሽን ተጠሪነቱ ለራሱ ለጠቅላላ ጉባዔ ነው፡፡ እርግጥ በመደጋገፍ መርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት አለን፣ እንዲኖርም ይጠበቃል፡፡ በዚህ መሠረት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እንዴት መደራጀት እንዳለባቸው መመርያዎችን ያዘጋጃል፡፡ ፌዴሬሽኖቹም ሆኑ ሚኒስቴሩ ግባቸው ስፖርቱን ማሳደግ ከመሆኑም ባሻገር ተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ በመሆናቸው በርካታ የሚያገናኟቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ እየታየ ያለው ከራሱ ደንብና መመርያ ሳይቀር ባፈነገጠ መልኩ አለመግባባቶችና ውዝግቦች እየተስተዋለ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሲፈጠር የመንግሥት አቋም እንዴት ይገለጻል?

አቶ ተስፋዬ፡- ለዚህም ቢሆን ሙሉ መብት ያለው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ነው፡፡ ጉባዔው ያለውን ነገር መርምሮ ከመመርያና ደንቡ ያፈነገጠ ቢኖርም እንኳ አቅጣጫ የማስቀመጥ ሙሉ ሥልጣን ያለው አካል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እግር ኳሱ አካባቢ ተከስቷል ተብሎ የምንሰማው እሰጣ ገባም በዚሁ መልክ መፍትሔ ያገኛል የሚል እምነት አለን፡፡ ምክንያቱም የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)ም ሆነ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በየጊዜው የሚያሻሽሏቸው ሕጎች በቀጥታ የሚደርሱት ለፌዴሬሽኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥታዊ አካሉ ጣልቃ መግባት የለበትም ብለን የምናምነው፡፡ ሚኒስቴሩ ዋነኛ ኃላፊነት ስፖርቱን የመደገፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ዕውን በዚህ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም እያሉ ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- በፍፁም ጣልቃ መግባት አይፈልግም፣ በመርህ ደረጃም አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ጥፋት ቢያጠፋ አመራሮቹ ራሳቸው በራሳቸው ከስህተታቸው እንዲታረሙ ከማገዝና ቴክኒካዊ ድጋፍ ከማድረግ ውጭ ለምን የሚል ከሆነ የዓለም አቀፍ ተቋም እንደ ጣልቃ ገብነት ነው የሚወስደው፡፡ ከዚህ በመነሳት ሚኒስቴሩ ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው አሠራሮችና ተጠያቂነት እንዲኖሩ ነው አበክሮ የሚጠይቀው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከምርጫ ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ለሚገኙ አለመግባባቶችና ውዝግቦች የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳለበት ይነገራል፡፡ ይቀበሉታል?

አቶ ተስፋዬ፡- በፍፁም፣ ይሁንና ከምርጫ ጋር ተያይዞ የውዝግቦቹ መነሻ ምርጫው መራዘም አለበት፣ የለበትም የሚል እንደሆነ ሚኒስቴሩ ይሰማል፡፡ ያም ቢሆን ግን በምንም መልኩ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ አራዝሙ፣ አታራዝሙ የማለት መብትም ሥልጣንም የለውም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ጉዳዩ የራሱ ባለቤት አለው፡፡ ይልቁንም ሚኒስቴሩ ፊፋ ያለው በጉባዔው አፅንዖት ተሰጥቶት እንዲታይ ነው የሚፈልገው፡፡ ይራዘም ሲባል ምክንያቱ ምንድነው? መራዘም የለበትም ሲባል ለምን ብሎ መጠየቅ እንደሚገባው እናምናለን፡፡ በእርግጥ ሁሉም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከዓለም አቀፍ ግንኙነታቸው ጀምሮ መዋቅራዊ ይዘታቸው የተስተካከለ ነው ብለን ለመናገር አንደፍርም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያት ይኖራችኋል?

አቶ ተስፋዬ፡- ለዚህ እንደ መነሻ ብንወስድ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ ተቋም ያለው ቦታ የ‹‹ቢ›› ደረጃ ሆኖ ዓመታዊ የአባልነት ክፍያም 5,000 ዶላር እንደነበርም እናውቅ ነበር፡፡ ይሁንና በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተነሳሽነት ከ‹‹ቢ›› ደረጃ ወደ ‹‹ሲ›› ደረጃ መውረድ እንዳለበት የቴኒስ ፌዴሬሽን አመራሮች ያምናሉ፡፡  የዓለም አቀፍ ተቋም ደግሞ ፌዴሬሽኑ በ‹‹ቢ›› ደረጃ እያለ የነበረበትን ውዝፍ የአባልነት ክፍያ እንዲከፍል ይጠይቃል፡፡ ሚኒስቴሩ ዓመታዊ ክፍያውን የሚከፍለው ራሱ እንደመሆኑ ፌዴሬሽኑ ወደዚህ ውሳኔ ለመምጣት ያነሳሳውን ምክንያት እንዲያብራራለት ጠይቋል፡፡ ምክንያቱም ከታች ወደ ላይ ማደግ ሲገባው እንዴት ወደ ታች? በሚል ከፌዴሬሽኑ ጋር እየተነጋገረበት ይገኛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ጣልቃ ገብነት ሊባል አይችልም፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚከናወኑ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ሲታሰቡ የፌዴሬሽኖች ድርሻ እንዳለ ሆኖ፣ ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ሊሆን እንደሚገባ ሊወሰድ ይገባል፡፡ መንግሥት እግር ኳሱ ካላስፈላጊ ውጥረት ወጥቶ በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲሄድ ጽኑ እምነት አለው፡፡ አሁን አሁን የሚስተዋለው ከእውነታው የማፈንገጥ ዝንባሌ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ሚኒስቴሩና የሚመለከታቸው አካላት ሚዲያውን ጨምሮ ወደ አንድ ነገር ለማምጣት መድረክ እንደሚያስፈልግ እናምናለን፡፡ እነዚህን የመሰሉ አቅጣጨዎች ማመላከት ጣልቃ ገብነት ሊባል አይገባም፡፡ ምክንያቱም ከስፖርቱ በላይ ያደገ የኅብረተሰብ ስሜት አለ፡፡ የሕዝቡ ጥማት የሚረካበትን ነገር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ እግር ኳሱ ከዓለም አቀፍ መርሁ ውጪ የሃይማኖትና የብሔር ግጭት የሚነሳበት መድረክ ሲሆን እየታየ ነው፡፡ በተጨባጭ እየሆነ ያለውን በጥሞና መመልከት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በእግር ኳሱ በተለይ ምርጫ ሲመጣ የማይገባ ግርግር ይነሳል፡፡ ምክንያት የሚሉት ይኖርዎታል?

አቶ ተስፋዬ፡- በዋናነት የዘርፉን አንኳር ችግር ባለመረዳት የሚፈጠር የአስተሳሰብ ችግር ብለን ነው የምንወስደው፡፡ እንደ አሠራር ተነፃፃሪ ብቃት ያላቸው ዕጩ ሆነው ቀርበው ቢወዳደሩ እንመርጣለን፡፡ የፉክክሩ መድረክም ሕግን መሠረት አድርጎ እንዲሆን የመንግሥት ፍላጎት ነው፡፡ አሁን ለምንመለከተው ሽኩቻ የሚዳርገን የአስተሳሰብ ማነስ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የሚወዳደሩ ሰዎችን ስንመለከት የተለየ ጥቅም ለማግኘት ነው ብለን አንወስድም፡፡ ይሁንና ግን በዚህ ረገድ ገና ብዙ እንደሚቀረን አመላካች ነገሮች አሉ፡፡ ስፖርቱ የሚፈልገውን አመራር ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ የሚመጣው አመራርም ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ጠንካራ የሆነ ቢሆንና ይህንኑ አሟልቶ መምራት የሚችል ቢሆን ይመረጣል፡፡ ሌላው ጊዜ ያለው፣ ፋይናንስ ማድረግ የሚችል ሰው መሆን እንዳለበትም መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽኑ አመራር ለሁለት ተከፍሎ እስከ ድብድብ ደርሷል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰን አመራር መንግሥት እንዴት ያየዋል?

አቶ ተስፋዬ፡- እንደ መንግሥት፣ እግር ኳሱን ጨምሮ ሌሎችም ፌዴሬሽኖች ተቋማዊ አሠራሮችን እንዲከተሉ ይፈለጋል፡፡ ይህን ስል ጣልቃ መግባት አለበት እያልኩ አይደለም፡፡ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ተፈጠረ የተባለውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት ሰምተናል፡፡ እርግጠኛ የሆነ መረጃ ግን የለንም፡፡ ተደርጎም ከሆነ መስተካከል እንዳለበት እናምናለን፡፡ በራሳቸው የውስጥ አሠራር ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ መደባደብ ከሕግ አንፃር ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ አመራርም ይህንኑ ያጣዋል ብለን አናስብም፡፡ እንደሚታወቀው አሁን ያለው አመራር የአገልግሎት ዘመኑ በመጠናቀቁ ምክንያት በእግር ኳሱ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው ስፖርታዊ ጨዋነትን አስመልክቶ መገምገም አልቻልንም፡፡ ሚኒስቴሩ ተገቢው ሪፖርት እንዲደርሰው በተደጋጋሚ ጠይቋል፣ ነገር ግን አልቀረበለትም፡፡ ከዚህ በመነሳት የፌዴሬሽኑ ሕጋዊ አካል በቶሎ እንዲታወቅ እንፈልጋለን፡፡ ሽግግሩ በሰላማዊ መንገድ ሕግና ደንቡን በተከተለ መልኩ እንዲሆን የመንግሥት ፍላጎት ነው፡፡ አስተያየትም ሰጥተናል፡፡ እየታየ ያለው ለፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገሪቱም እግር ኳስ ጤናማነት አዋጪ አይደለም፡፡ ይህን ስንል ግን በጣልቃ ገብነት እንዳልሆነ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከደንብና መመርያ አንፃርስ?

አቶ ተስፋዬ፡- ባለኝ መረጃ በፌዴሬሽኖች ሁለት ዓመት ያገለገለ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደር እንደሌለበት በደንባችን አለ፡፡ መመርያው ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አንድ ሰው በሁለት ፌዴሬሽን ውስጥ ካለ ለሦስተኛ ኃላፊነት ለምርጫ መቅረብ እንደሌለበት ጭምር መመርያው ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት እዚህ ላይ የደንብ ጥሰት ካለ ምን ብለን እንጠይቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የደቡብ ክልል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ተወዳዳሪ ያደረጋቸው አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) የአንድ ፌዴሬሽንና የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

አቶ ተስፋዬ፡- ሚኒስቴሩ ያለው መረጃ ዕጩው ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን መልቀቂያ ማግኝታቸውንና መወዳደር እንደሚችሉ ነው፡፡ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ዕጩ ተወዳዳሪው እንደለቀቁ አሳውቋል፡፡ ስለዚህ እንዳይወዳደሩ መመርያው አያግዳቸውም፡፡ የመመርያው ዓይነትና ይዘት አገሮች የዓለም አቀፍ ማኅበራት ባስቀመጡት ደንብና መመርያ መሠረት፣ እንደየአገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ እንዲተገብሩት በሚፈቅደው መሠረት ማኅበራትን ለማደራጀት የወጣ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደነዚህ የመሰሉ የሚያሠሩ ምክንያቶች አቅም ያላቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለስፖርቱ የሚሰጡትን አገልግሎት ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዕጩ አቀራረብ መንግሥት ጣልቃ ገብቷል ከሚያስብሉ ነጥቦች የክልል ተፎካካሪዎች ውክልና ሲሰጣቸው በክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተረጋግጦ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምን ይላሉ?

አቶ ተስፋዬ፡- በክልሎች አማተሮች ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች ጋር ያላቸው የቅንጅት ሥራ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ መደጋገፍና መተጋገዝ አላቸው፡፡ ለዚህ ነው ለዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች ማረጋገጫ የሚሰጧቸው፡፡ ብዙዎቹ የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢሮዎች በብዙ ነገር ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይህም ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ሊወሰድ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የክልል ዕጩ ተወዳዳሪዎች የተሟላ ማስረጃ እንዲኖራቸው ከማሰብ የተወሰደ ካልሆነ ጣልቃ ገብነት ተብሎ ሊወሰድ አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- ለጥርጣሬ መነሻ ሊሆን አይችልም?

አቶ ተስፋዬ፡- ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአሠራር አኳያ ስንመለከተው ያስኬዳል፡፡ የትርጉም ጉዳይ ካልሆነ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጀምሮ ተቋማዊ ነፃነታቸው እንደተጠበቀ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ሊያደርጉ አይገባም ከተባለ ጉዳዩ ሌላ ጫፍ እንዳይዝ መጠንቀቅም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ላይ መንግሥታት የወሰዱትን ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በፌዴሬሽኑ ተጠያቂነት እንደሌለ የሚናገሩ አሉ፡፡ ምክንያቱም ምርጫ በመጣ ቁጥር የግርግሩና ሁከቱ መነሻ ተጠያቂነት ስለሌለ እንደሆነም ይነገራል?

አቶ ተስፋዬ፡- በዚህ ጉዳይ ከፊፋና ካፍ ጋር የተናጠል ንግግር አድርገናል፡፡ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተደረገው የካፍ ስብሰባ በስፖርት ማኅበራት የመንግሥት ሚና ምን መምሰል አለበት? ተብሎ ውይይት ተደርጓል፡፡ ተቋማቱም ይህንኑ ተስማምተውበታል፡፡ በቅርቡም የጋራ ዕቅድ አዘጋጅተን ዕቅዱን በጋራ ለማስፈጸም የምንሄድት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለማስፈን ሚኒስቴሩ ከኦሊምፒክ ኮሚቴና ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን የሦስትዮሽ ዕቅድ አዘጋጅተናል፡፡ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም አለበት፡፡ በዚሁ መሠረት ከፋይናንስ ሥርዓቱ ጀምሮ እንዴት መመራት እንዳለበት፣ ለውድድሮችና መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ለሌሎችም የሚወጣው ወጪ ከገቢው አንፃር ምን መምሰል እንዳለበት የማጥራትና የመለየት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ በአገራችን ውድድር ተኮር እንቅስቃሴ ስላለ የልማት ሥራው እየተዘነጋ ነው፡፡ ከእግር ኳስ አንፃር ማለቴ ነው፡፡ በአጠቃላይ ማን ምን ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል? የሚለው ዕቅድ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የፊፋን ጨምሮ የሚመጡ የፋይናንስ ድጋፎች ቅድሚያ የሚሰጠው ለየትኛው ዘርፍ መሆን እንዳለበት ጭምር እየታየ ነው፡፡ አገር አቀፉ ፌዴሬሽኖች ያለአግባብ የያዟቸው ኃላፊነቶች ወደ ታች መውረድ ያለባቸው ጉዳዮች በዝርዝር እየታዩ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ዕውን እንዲሆን ደግሞ የሚፈለገው አመራርም መምጣት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኖች ራሳቸው ያወጧቸውን መመርያና ደንቦች የሚጥሱ አሉ፡፡ ለዚህ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተጠቃሸ ነው፡፡ እንዴት ያዩታል?

አቶ ተስፋዬ፡- ለሁሉም ባለቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ነው፡፡ ጉባዔው ፌዴሬሽኑ የሚመራበትን ደንብና መመርያ ማሻሻል መጣልና ማፅደቅ የሚችለው ብቸኛው የሥልጣን አካል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁንም ይኼ ጥያቄ የሚመለከተው ይህንኑ አካል ስለሆነ ሚኒስቴሩን የሚመለከት አይደለም፡፡ እንደኛ በመሰሉ አገሮች በተለይ ስፖርቱ ባላደገበት ሁኔታ የመንግሥት ትልቁ ድርሻ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ከሌሎችም የማኅበራት አደረጃጀቶች እጁን እያወጣ ነው፡፡ ስፖርቱም የዚሁ አንድ አካል ከሆነ ቆይቷል፡፡ ማኅበራት ቢያጠፉም የመንግሥት ፍላጎት ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያርሙ ነው፡፡ ያለው መንግሥታዊ ሥርዓትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ይሁንና 99 በመቶ መንግሥት በሚደጉመው ስፖርት ጣልቃ ገብነትን ምክንያት በማድረግ ወዳልሆነው አቅጣጫ መሄድ ጉዳት እንዳለው መዘንጋት የለበትም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...