Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርስለ እግር ኳሳችን የሚሰማኝን ልናገር

ስለ እግር ኳሳችን የሚሰማኝን ልናገር

ቀን:

እግር ኳሱን ከ60ዎቹ አጋማሽ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ ለመከታተል ከቻሉ አንዱ ዕድለኛ ነኝ፡፡ አሁንም መሄጃ ካጣሁና እግር ከጣለኝ ብቅ ማለቴ አለቀረም፡፡ በዚያን ወቅት የነበሩ አመራሮች ከስፖርቱ ጋር የነበራቸው ቁርኝት የላቀ በመሆኑ፣ በተጨዋቾቹ ዘንድ ከበሬታ እንዲያገኙ አስችሏቸው ነበር፡፡

እንዳሁኑ ኳስ የሚጠልዙ፣ ጎል ሲቆጠርባቸው አጸፋውን ለመመለስ እልህ የማይታይባቸው ሀሞተቢስ ተጨዋቾችን መመልከት አልተለመደም፡፡ ተመልካቹ 90 ደቂቃ እንደፈነጠዘ ጨዋታው ያልቃል፡፡ ምሬት፣ ብስጭትና ንዴት ብሎ ነገር የለም፡፡ በክለባቸው መለያና በአገራቸው ባንዲራ ቀልድ በማያውቁና መሸነፍ በሚጎመዝዛቸው ተጨዋቾች እየተደሰተ ሁሉም እንዳመጣጡ ከስፖርት ሜዳ ውሎ ይመለሳል፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ደመወዝ፣ ዘመናዊ መኪና ማሽከርከርና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ መዝናናት ለእነሱ እንደ ሰማይ የራቀ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ቅንጦት ሰምተውም፣ አይተውም አያውቁም፡፡

እስቲ ከብዙዎቹ የኳሱ ጠበብት ጥቂቶቹን ላስታውስና ወደ አሁኖቹ ልመለስ፡፡

  1. ኢታሎ ቫሳሎ                            9. ተስፋዬ ተወልደ (ቸንቶ)
  2. ኑሪ (ጉምሩክ)                           10. ገብሩ ወልደ አማኑኤል
  3. ጌታቸው አበበ (ዱላ)                      11. ሸዋንግዛው ተረፈ
  4. መንግሥቱ ወርቁ (ፊት አውራሪ)            12. አፈወርቅ ጠናጋሻው   
  5. ክብሮም ተክለ መድህን                     13. ተስፋሚካኤል ዳኜው   
  6. መሐመድ ሸዳድ                           14. ገብረመድህን ኃይሌ
  7. ሙሉዓለም እጅጉ                          15 ሰሎሞን ማንቲሳ
  8. መሠረት አሳና (አ.አ.ድ)                     16. ኤልያስ ጁሀር

እነዚህ ሲወደሱ የሚኖሩ የምንጊዜም የአገራችን ውድ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የአሁኑ እግር ኳስ በአንፃሩ ከባህላዊው የገና ጨዋታ የሚለየው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ኳስ ከመረብ የሚያገናኝ አጥቂ በሌለበት፣ አጥቂዎችን የሚያስቆም ተከላካይ በማይታይበት በዚህ ወቅት፣ ለአንድ ተጨዋች እስከ 168,000 ብር የወር ደመወዝ መክፈል በእኔ አስተያየት ማላገጥ ይመስለኛል፡፡ ይኼ ገንዘብ ተጨዋቹ ፊርማውን ለማኖር የሚከፈለውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዝብ፣ ለትጥቅ፣ ለምግብና ለሆቴል የሚወጣውን ወጪ አያካትትም፡፡ በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስፖርት ሚኒስትሩን ጨምሮ የሌሎች አምስት ሚኒስትሮችን ደመወዝ ይሸፍናል እንደማለት ነው፡፡

በአገሪቱ በተከሰተው የኑሮ ውድነት ሕዝቡ በሚሰቃይት ወቅት፣ ከ8.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለከፋ ድርቅ ቢጋለጥም ከለጋሽ አገሮች በቂ ምላሽ አልተገኘም እየተባለና ፍትሐዊና ወቅቱን ያላገናዘበ የገንዘብ ብክነት በስፖርት ሰበብ እየታየ መሆኑ በርካታ ዜጎችን እንደሚያስቆጭ እገምታለሁ፡፡ ‹‹ሰው ያደረገው አይቅርብኝ፤›› በሚል ግብዝ አመለካከት የተቃኙ አንዳንድ የስፖርት አመራሮች፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ለሚጀመር ጨዋታ ከሌሊቱ በ9 ሰዓት እየተሰለፈ ቦታ ለማግኘት የሚሽቀዳደመው ተመልካች ዘወትር ሽንፈት በመቅመስ የሚደርስበትን ብስጭጥ በጩኸት መግለጹን ሲቃወሙ መስማት ግር ያሰኛል፡፡ ለእንዲህ ያለው ጉዳይ ለመቅረፍ የሚሰማ ጆሮ የላቸውም፡፡ ምናልባትም የሜሲን፣ የኔማርን፣ የሮናልዶንና የሉዊዝ ስዋሬዝን ሳምንታዊ ክፍያ ከእኛ አገር ኳስ ጠላዦች ክፍያ  ጋር በማነጻጸር ሳያሾፉብን አይቀሩም፡፡

ስለዚህ ለወደፊቱ ምን ይደረግ? የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መዋቅርና አመራር ልምድ በተካኑ ልሂቃን በጥልቀት ከተጠና በኋላ በአገር ውስጥና በውጭው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥሪ በማቅረብ ግልጽነትና ተጠያቂነት በተላበሰ መልኩ ችሎታን መስፈርት ያደረገ ምደባ መፈጸም፡፡

ከ35 ዓመት በላይ ውጤት ላልተገኘበት እግር ኳስ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ከማባከን ይልቅ ለአሥር ዓመታት ያህል በመዝጋትና በመላ አገሪቱ በተዋቀሩ ወረዳዎች ዕድሜያቸው ከስምንት ዓመት ያልበለጠ ሕፃናትን መልምሎ በማደራጀት ለወደፊቱ የሚያስተማምን ሥልጠና መስጠት፡፡

ካለፈው ልምድ እንደቀሰምነው ከዩኒቨርሲቲዎች በቀጥታ ለብሔራዊ ቡድን የተሠለፉትን ያህል አሁንም ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መዋቅር በመዘርጋት ብቃታቸው የተመሰከረላቸውን የስፖርት መምህራን በመቅጠር ከአሥር ዓመት በኋላ ጋናን፣ ካሜሮንን፣ ኮትዲቯርንና ግብፅን በብቃት ማሸነፍ የምንችልበትን አቅም መፍጠር ይገባል፡፡

ከላይ ለዘረዘርኳቸው መሠረታዊ የለውጥ ሐሳቦች ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች በየፊናቸውም ሆነ በጋራ በመቀናጀት በቂ የእግር ኳስ ማዘውተሪያ ሜዳዎች መገንባት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በዘፈቀደና ባልተጠና አሠራር የሚደረገው የገንዘብ ወጪ በማጠፍ እንዳስፈላጊነቱም ተጨማሪ በጀት በማፈላለግ እየሞተ ያለውን እግር ኳስ መታደግ ይቻላል፡፡

 የአንዳንድ አፍሪካ አገሮች ተሞክሮም ይኼንኑ ያሳያል፡፡ የስፖርት ጋዜጠኞቻችንም በየልምምድ ቦታው በመገኘት ስለሥልጠናው ጠንካራና ደካማ ጎን ተጨዋቾች ስላላቸው ቅሬታና በዚሁ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት ስለሚሰጡት አስተያየት መድረኮች የሚዘጋጁበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሙያዊ ግዴታቻው መሆኑን ማሳሳብ እወዳለሁ፡፡

(ውብሸት ተክሌ፣ ከገርጂ)

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...