Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከትርፍ በላይ ለዕድገት እናስብ!

በአክሲዮን ተደራጅተው ከተቋቋሙ ኩባንያዎች ውስጥ በውጤታማነታቸው የፋይናንስ ተቋማትን የሚስተካከላቸው መጥቀስ ይከብዳል፡፡ ሌሎችም አክሲዮን ኩባንያዎች እንደ ባንኮች በሆኑ፣ ባተረፉ፣ ትርፍ ባከፋፈሉ ያስብላል፡፡ እነዚህን  ኩባንያዎችን ለመፍጠር ገንዘባቸውን አዋጥተው እዚህ ደረጃ ላደረሷቸው ባለአክሲዮኖች ምሥጋና ይገባቸውና የፋይናንስ ተቋማት ሀብት በቢሊዮኖች የሚቆጠርበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞችንም አፍርተዋል፡፡

ትልልቅ ግንባታዎችን አከናውነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችን ተሽቀዳድመው እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ አገሪቱ ላስመዘገበችው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም አወንታዊ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በየዓመቱ ከሚያገኙት ትርፍ ውስጥ ለባለአክሲዮኖቻቸው የሚያከፋፍሉት የትርፍ ድርሻም ከፍተኛ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖቹ ኩባንያዎቹን ሲመሠርቱ ካዋጡት ገንዘብ በብዙ እጅ ብልጫ ያለው ጥቅም እንዲያገኙ ማስቻላቸውም እየታየ ነው፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ተደራሽነት በማሳደግ በኩልም አብዛኛውን ድርሻም እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

የፋይናንስ ተቋማቱ ከ50 ሺሕ በላይ ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ቁም ነገሮችን በዝርዝር ማቅረብ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያለው ውጤት የተገኘው ግን በፋይናንስ ተቋማቱ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ ኢንዱስትሪው ተገቢው ቁጥጥር ስለሚደረግበት ጭምር ነው፡፡ ለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተዋፅኦ የሚጠቀስ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር በኪሳራ የተዘጋ የፋይናንስ ተቋም አለመታየቱ የኢንዱስትሪውን ጤናማነት አመላካች ነው፡፡ ይህም ሲባል ግን ችግር አያውቃቸውም ማለት አይደለም፡፡ ተግዳሮቶች የማያውቃቸው፣ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ለውጤት የበቁ ሆነውም  አይደለም፡፡ የደንበኞችን ፍላጎት ያሟሉ፣ ያልተገባ ተግባር የማይፈጽሙ ሆነውም አይደለም፡፡ አገሪቱ በፋይናንስ መስክ መድረስ የሚገባት ደረጃ ላይ አድርሰዋትም አይደለም፡፡ ከሌሎች አንፃር እንመዝናቸው ከተባለም በአቅምም፣ በአቋምም ሚጢጢዎች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የነገው መንገዳቸው ከቀድሞው የበለጠ ፈታኝ እንደሚሆን  ይታመናል፡፡ ለዚያ ካልተዘጋጁ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እንደዘበት የሚከፋፍሉት የትርፍ ድርሻ ነገ ላይገኝ ይችላል፡፡

እነዚህ ተቋማት ሰሞኑን የሥራ ውጤታቸውን የሚገልጹበት ወቅት ላይ ይገኛሉ፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ የ2009 ዓ.ም. ክንውናቸውን ለባለአክሲዮኖቻቸው በማሳወቅ ላይ ናቸው፡፡ ትርፍና ኪሳራቸውን ይፋ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የአብዛኛው ባለአክሲዮን ፍላጎት ምን ያህል አተረፍን፣ ምን ያህል የትርፍ ክፍፍል እናገኛለን የሚለውን ማወቅ ነው፡፡ በአንዳንዶቹ ባንኮች ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ፣ የትርፍ ድርሻ ክፍፍላችን ምነው ቀነሰ፣ አነሰ የሚሉ ቅሬታዎች ተደምጠዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ከቀደመው ጊዜ የበለጠ ትርፍ ቢያስመዘግቡም የትርፍ ድርሻ ክፍፍላቸው ግን መቀነሱ ታይቷል፡፡ ምንም እንኳ የትርፍ ድርሻ መቀነሱ ላይ ጥያቄ እንደሚያነሳ ቢጠበቅም፣ ባለአክሲዮኖች ትርፍ ላይ ብቻ ማተኮራቸው ግን ሳያሳስብ አልቀረም፡፡

ቀደምት የሚባሉት ባንኮች ለባለአክሲዮኖቻቸው የሚያከፋፍሉት የትርፍ ድርሻ ጠቅሞ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከሌሎች አገሮች አኳያ ከፍተኛ መሆኑ ሲነገር የከረመ ነው፡፡ ይሁንና እንደዚህ ይቀጥላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ባንኮች እያተረፉ መዝለቃቸው ባይቀርም የትርፍ ድርሻው እየቀነሰ መሄዱ እንደማይቀር የሚጠቁሙ ምክንያቶች መኖራቸውን መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡

ተቋማቱ ከቀደመው ጊዜ በላይ ማትረፍ ባለመቻላቸው ሳይሆን፣ የባለአክሲዮኖች ቁጥር ብዛት፣ አቅማቸውን ለማጎልበት የሚጠይቃቸው ወጪ እያደገ መምጣትና የመሳሰሉት ምክንያቶች የትርፍ ድርሻቸውን ሊቀንሱት ይችላሉ፡፡ ወደፊት የበለጠ ወጪ የሚጠይቋቸው ኢንቨስትመንቶች  እንደሚኖሩ ሲታሰብ፣ ባለአክሲዮኖች ይህንን ከግንዛቤ ሊወስዱት እንደሚገባ ይታመናል፡፡

እርግጥ ነው ባለአክሲዮኖች የኩባንያዎቻቸውን አካሄድ የመቆጣጠር ከፍተኛ ሥልጣን አላቸው፡፡ ዓመታዊ ትርፍን ብቻ መነሻ ያደረገው ጥያቄያቸው ሲደጋገም ግን ነገሩን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ኢንዱስትሪው የሚገኝበት ሁኔታ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ እንደ የቢዝነስ ተቋም ማትረፍም መክሰርም እንዳለ መገንዘብ ያሻል፡፡ ከሁሉም በላይ እንዲህ ያሉት ተቋማት ከራስ በላይ አገራዊ ፋይዳቸው የጎላ  በመሆኑ ከትርፍ ባሻገር፣ የነገ ጥንካሬያቸውን መገንባት ላይ እያተኮሩ መምጣታቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ተቋማቱ በርካታ ፍትጊያ ይጠብቃቸዋል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ በስትራቴጂው የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ወጪያቸው መጨመሩ አይቀሬ ነው፡፡ ተጨማሪ ጉልበት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንዳንድ መመርያዎችም እንደቀድሞው እንደማያራምዷቸው ይታሰባል፡፡ በመሆኑም የባንኮቹ ዕድገት ቢቀጥልም ለባለአክሲዮኖች የሚደርሰው የትርፍ ድርሻ የሚቀንስበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለዚህም ‹‹ትርፍ አነሰ›› የሚለውን ጥያቄ ምክንያታዊ ማድረግና ተቋማቱ የሚገኙበትን ሁኔታ ማሰብ ያሻል፡፡

ባለአክሲዮን ከትርፍ ባሻገር ለኢንዱስትሪውም ማሰብ ይጠበቅበታል፡፡ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች በሕዝብ ገንዘብ የሚያዙ፣ የሕዝብን ገንዘብ የሚያስተዳድሩ እንደራሴዎች ስለመሆናቸው የሚዘነጋባቸው ጉባዔዎችንም እየታዘብን ነው፡፡ ባለአክሲዮኖቹ ለኩባንያዎቻቸው ካዋጡት ገንዘብ ባሻገር የሕዝብ ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅሱ መታሰብ አለበት፡፡ ባለአክሲዮኖች የኩባንያዎቹ ባለቤቶች መሆናቸው ባይካድም፣ ሁሌም ብዙ ትርፍ እንደማይገኝ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትርፍ ምጣኔው የተጠበቀውን ያህል ያልሆነው የኩባንያዎቹ መሪዎች ድክመት ከሆነ ግን፣ አጣርቶ ዕርምጃ መውሰድ የባለአክሲዮኖች ድርሻ ነው፡፡ አንዳንዴ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ትልቁ ጭንቅ ተቋማቱን ከማጠናከር ባለፈ ለባለአክሲዮኖች ስንት ይከፈል? የሚለው እየሆነ መምጣቱ ከትልቁ ተልዕኳቸው እንዳያዘናጋቸው ማሰቡ አያስገርምም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆኑ በተቋማቱ እጅ ከሚገኘው ገንዘብ ውስጥ በባለአክሲዮኖች የተዋጣው ከ15 በመቶ አይበልጥም፡፡ ቀሪው የሕዝብ ገንዘብ እንደመሆኑ መጠን፣ ትርፍ ብቻ ሳይሆን የነገንም በማሰብ ጠንካራ የፋይናንስ ተቋማት እንዲኖሩን ለማድረግ የባለአክሲዮኖች ድርሻና ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት