Sunday, September 24, 2023

ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት የአገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች ይፈታል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በ2008 ዓ.ም. ከተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣና አለመረጋጋት በኋላ በተከፈተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ንግግር ለማድረግ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት እስከ ማሻሻል የሚደርስ ተሃድሶ መንግሥት እንደሚያከናውን ቃል ገብተው ነበር፡፡

ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በምክር ቤቱ ተገኝተው የመንግሥታቸውን የ2009 ዓ.ም. ዕቅድ ለምክር ቤቱ አባላት ባብራሩበት ወቅት፣ መንግሥት ከሚያከውናቸው ዓበይት ተግባራት መካከል የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት ማሻሻል አንዱና ዋነኛው እንደሚሆን ቃል ገብተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በአገሪቱ ተመዝግበው የሚገኙ 15 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር በተለያዩ የአገሪቱ የምርጫ ሕግ ማዕቀፎችና የምርጫ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት ማካሄድ ጀምረዋል፡፡

ምንም እንኳን ፓርቲዎቹ የሚወያዩባቸውን ዓበይት አጀንደዎች ለመቅረፅና የድርድሩ አካሄድ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ለመስማማት የቅድመ ድርድር ማራቶን አካሂደው ነበር፡፡

በዚህ አጀንዳ የመቅረፅና ገለልተኛ የሆኑ አደራዳሪዎች ድርድሩን ሊመሩት ይገባል በማለት ሲከራከሩ የቆዩት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) ያቀረቡት ሐሳብ፣ በተለይ ከገዥው ፓርቲ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ድርድሩ በቅድመ ድርድር ደረጃ እያለ አቋርጠው ወጥተዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ቅድመ ድርድሩን አቋርጠው ከወጡ በኋላ በተከናወኑ የአጀንዳ መቅረፅና የአደራዳሪዎች ሚናና ማንነት ላይ የተስማሙት 15 ፓርቲዎች ድርድራቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፓርቲዎቹ በመጀመርያ ለውይይት የመረጡት አጀንዳ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2003ን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ነበር፡፡ ፓርቲዎቹ በወቅቱ ባደረጉት ድርድርም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅን ለማሻሻል ከስምምነት ስለደረሱ፣ ወደ ሁለተኛው የድርድር አጀንዳ ተላልፈው በሁለተኛው አጀንዳ ላይ እየተደራደሩ ነው፡፡

በመጀመርያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅን በተመለከተ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ ከስምምነት በደረሱባቸው ነጥቦች ላይ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርድሩን አቋርጠው የወጡ የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች ተቋውሟቸውን አሰምተው ነበር፡፡

ለግለሰቦቹና ለፓርቲ አመራሮቹ የተቃውሞ መነሻ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ፣ ከድርድሩ የተገኘው ውጤት ነው፡፡ በድርድሩ ውጤት መሠረት አንድ ፓርቲ በአገር አቀፍ ፓርቲነት ለመመዝገብ የሚያስፈልግ የነበረውን 1,500 አባላት ሲኖሩት ነው የሚለውን የአዋጁን አካል፣ ወደ 3,000 በማሳደጋቸውና የክልል ፓርቲዎች የመሥራች አባላት ቁጥርን ከነረበት 750 ወደ 1,500 ከፍ እንዲል ማድረጋቸው ነው፡፡

በዚህም መሠረት ከድርድሩ የወጡት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ይህ የድርድሩ ውጤት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ፣ አዳዲስ ፓርቲዎች ወደ መጫወቻ ሜዳው እንዳይገቡ ይከለክላል በማለት ነበር ተቃውሟቸውን ያሰሙት፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ድርድሩን የሚቃወሙት አካላት የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት እንደሚመዘገቡ አለመቻል ሳይሆን፣ የተመዘገቡት እንኳን ባለው የመጫወቻ ሜዳ ላይ እኩል ዕድል አለማግኘታቸው ነው በማለት ድርድሩንና ውጤቱን አጣጥለውታል፡፡

ምንም እንኳ እነዚህ ወገኖች የድርድሩን አጠቃላይ ውጤትና ድርድሩን ራሱን ቢቃወሙም፣ በድርድሩ እየተሳተፉ የሚገኙት ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ እንዲህ ያለውን ወቀሳ አይቀበሉትም፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እየተካሄደው ያለውን ድርድር ዞሮ ዞሮ የሚጠቅመው ሁሉንም የአገሪቱን ፓርቲዎች ነው በማለት ወቀሳውን የሚያጣጥሉት ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲ ደግሞ ድርድሩና ከድርድሩ የሚገኘው ውጤት የአገሪቱ ሕግ አካል ስለሚሆን፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረውና በውጤቱም ሁሉም ፓርቲዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመሞገት ወቀሳውን ያጣጥለዋል፡፡

ምንም እንኳ እየተካሄደ ያለው ድርድር ገና ከመጀመርያው ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ ግን የያዙትን ድርድር ቀጥለውበታል፡፡

በዚህም መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅን በማሻሻል የተጀመረው ድርድር ወደ ሁለተኛው አጀንዳ፣ ማለትም የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ 532/99ን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ድርድራቸውን ቀጥለዋል፡፡

በዚህ አዋጅ ላይ እየተካሄደ የነበረው በተለይ ከአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ጋር የተያያዘውን አሠራር ለማሻሻል በተደረገ ድርድር መሠረት፣ ፓርቲዎቹ የአገሪቷ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን ተስማምተዋል፡፡

ምንም እንኳ ፓርቲዎቹ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን ቢስማሙም፣ የቅይጡ የመቶኛ ድርሻ ላይ መስማማት ተስኗቸው ለሁለት ወራት ያህል ድርድር ሲያደርጉ ነበር፡፡

በድርድሩ ወቅት ጎልተው የወጡት ልዩነቶች ደግሞ ገዥው ፓርቲና ለዚህ ድርድር ዓላማ ሲባል ኅብረት በፈጠሩት 11 የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት የመቶኛ ድርሻ መጠን መለያየት ምክንያት ነው፡፡

አሥራ አንዱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቅይጡ የመቶኛ ድርሻ እኩል 50 በ50 እንዲሆን የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በተናጠል እንዲሁ የተለያዩ የመቶኛ ድርሻዎችን በአማራጭነት አቅርበዋል፡፡ ለምሳሌ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) 75 በመቶ የተመጣጣኝ ውክልናና የ25 በመቶ የአብላጫ ውክልና ሥርዓት እንዲኖር ያቀረበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የተመጣጣኝ ውክልና እንዲሆን ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ እነዚህን የመቶኛ ድርሻዎች ሲያቀርቡ ገዥው ፓርቲ በበኩሉ መጀመርያ ላይ የ90 በ10 የመቶኛ ድርሻ፣ ከዚያም 85 በ15፣ እንዲሁም በመጨረሻ የ80 በ20 የመቶኛ ድርሻ በማቅረብ የመጨረሻው እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳ አሥራ አንዱ ፓርቲዎች የመቶኛ ድርሻቸውን ወደ 40 በ60 የቀየሩት ቢሆንምና ኢራፓም በአቋሙ ቢፀናም፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንዲሁ በአቋሙ በመፅናት ያቀረበው የ80 በ20 የመቶኛ ድርሻ በፓርቲዎቹ ተቀባይነት አግኝቶ፣ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትትዩ እንዲሆን ተስማምተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በዚህ ቢስማሙም ቅሉ በአጠቃላይ ሒደቱ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው አካላት አሁንም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡

ከዚህኛው የድርድር ውጤት በኋላ እያሰሙት ያለው ተቃውሞ ደግሞ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ የተገደደው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት አለመረጋጋቶች ሥጋት ስለፈጠሩበት እንደሆነ በመግለጽ ሲሆን፣ በድርድሩ እየተገኘ ያለው ውጤት ደግሞ ድርድሩ ከተነሳበት ዓላማ አንፃር መንገዱን የሳተና የሕዝቡን ጥያቄ የማይመልስ ነው በማለት በመሞገት ነው፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበርና በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም የፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን ያገለሉት አቶ ሙሼ ሰሙ ውጤቱን ክፉኛ ይተቻሉ፡፡

በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር አገሪቷ ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተሟላ ሁኔታ ይወክላል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል፡፡

አገሪቷ ውስጥ የምርጫ ሥርዓቱን አስመልክቶ ያለው ትልቁ ፈተና ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ የማካሄድ እንጂ የመወከል ጉዳይ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ አሁን ተደረሰበት የተባለው ስምምነት ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ዓይነት ነገር ነው ይላሉ፡፡

‹‹አሁን እየተካሄደ ያለው ዓይነት ድርድር የሚመጣው መጀመርያ የምናካሂደው ምርጫ ፍትሐዊ ሆኖ፣ በዚያ ፍትሐዊ ምርጫ ተገቢውን ወንበር ማግኘት እንደማንችል ሲረጋገጥ ነው፡፡ ያ ገና አልተረጋገጠም፡፡ ምክንያቱም ይህን ከሚያካሂደው ተቋም ጋር ፀብ ላይ ነው ያለነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በተጨማሪም ከገዥው ፓርቲ ጋር በተያዙት አጀንዳዎች ላይ እየተደራደሩ የሚገኙት ፓርቲዎች እየተስማሙ በመጡባቸው አጀንዳዎች መሠረት አገሪቷ ውስጥ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ እንደተካሄደ ነው በሚለው ተስማምተዋል እንደ ማለት ነው በማለት ይተቻሉ፡፡

ይህን ሐሳብ የሚጋሩት የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታነህ ባልቻ፣ ‹‹ከድርድሩ ፓርቲያችን ራሱን ያገለለው መሠረታዊ የሆኑ የአገሪቷን ፖለቲካዊ ችግሮች አይፈታም የሚል አቋም ስላለ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

‹‹ከመጀመርያው አንስቶ አጠቃላይ የድርድሩ ማዕቀፍና አደራዳሪዎችን በተመለከተ ገለልተኛ የሆነ አደራዳሪ ይሰየም እያለን ስንከራከር የነበረው፣ ድርድሩ አቅጣጫውን እንዳይስትና ከመስመሩ እንዳይወጣ ስለፈለግን ነው፤›› በማለት አሁን በድርድሩ እየተገኘ ያለው ውጤት በአገሪቱ ከተከሰተው አጠቃላይ አለመረጋጋት አንፃር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የለም በማለት ይሞግታሉ፡፡

ፓርቲዎቹ ከስምምነት የደረሱበትን ነጥብ ተከትሎ ግን የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ከዚህ ቀደም ከነበረበት የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት፣ ወደ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት ይሸጋገራል፡፡

የተለያዩ የዘርፉ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ፣ ይህ ቅይጥ ትይዩ የሚገባለው የምርጫ ሥርዓት ሁለቱን የምርጫ ሥርዓቶች በአንድ ላይ የሚይዝ ነው፡፡

ስለዚህ በቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት መሠረት አገሪቱ 80 በመቶ የአብላጫ፣ 20 በመቶ ደግሞ የተመጣጣኝ ውክልናን የሚያቅፍ የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች፡፡

የቅይጥ የምርጫ ሥርዓትን መከተል በአብዛኛው የመወከልን ጥያቄ ምላሽ የሚያስገኝ ሲሆን፣ በተጨማሪም የመራጮች ድምፅ እንዳይባክን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ይባላል፡፡

የአገሪቷን የምርጫ ሥርዓት ከማሻሻል ጋር ተያይዞ ከተለያዩ ወገኖችና ግለሰቦች የሚነሳው ጥያቄ ግን፣ ይህ የምርጫ ሥርዓት መንግሥት እንደሚለው ምን ያህል የፖለቲካ ምኅዳሩን ያሰፋዋል የሚል ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት ቅይጥ ትይዩ የሚባለው የምርጫ ሥርዓት የድምፅ መባከንን ከማስቀረትና ከውክልና አንፃር ጠቀሜታ እንዳለው በመግለጽ፣ ተግባራዊ ቢሆን የታሰበው የመቶኛ የድርሻ ክፍፍል ግን የአገሪቷን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት በሚኖረው ድርሻ ውጤት እንደማያመጣ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይህ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት የፖለቲካ ምኅደሩን ከማስፋት አንፃር ኢሕአዴግ እንደሚለው ውጤት የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የሚጨመሩት 110 ወንበሮች እንዳለ ለተቃዋሚዎች ብትሰጣቸው እንኳን እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሊያመጡ አይችሉም፤›› በማለት፣ ውጤቱ የአገሪቷን የፖለቲካ ምኅዳር ከማስፋት አንፃር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አናሳ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም የተቀመጠው የአንድ መቶኛ ዝቅተኛ የመነሻ ወለል (ትሬሽሆልድ) በራሱ ለአገሪቱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፅ ለማግኘት አስቸጋሪ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ለምሳሌ በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን መራጮች ቢኖሩ ከአንድ በመቶ በታች ያገኘው ፓርቲ ከክፍፍሉ ውጪ ይሆናል፡፡ ስለዚህ 30 ሚሊዮን ድምፅ ተሰጠ ቢባል አንድ ሰው ፓርላማ ለመግባት ከ300 ሺሕ ድምፅ በላይ ማግኘት ይጠበቅበታል በማለት አብራርተው፣ ‹‹በዚህ ሥሌት መሠረት ደግሞ የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ መቀመጫ ሊያገኙ አይችሉም፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

እየተካሄደ ባለው ድርድር እየቀረቡ ያሉ ሐሳቦችን ከሚተቹት አንዱ አቶ ሙሼ፣ መጀመርያ ላይ ድርድሩ እንዲጀመር የነበሩት ገፊ ምክንያቶች በድርድሩ መቅረብ እንደነበረባቸው ይገልጻሉ፡፡

‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸው አጀንዳ አላቸው፡፡ ለምሳሌ መድረክ ማጣት፣ አፈናው፣ እንግልቱ፣ እስሩና መሰደዱ የፈጠሩባቸውን ተፅዕኖ ለማስለወጥ የሚያደርጓቸው ትግሎች አሉ፡፡ ይህ በአብዛኛው የፓርቲዎች ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝባዊ ጥያቄዎችም ነበሩ፡፡ የአስተዳደር፣ የአገልግሎት፣ የፍትሕ ዕጦት፣ የሥራ አጥነት ችግር፣ ወዘተ.፡፡ ስለሆነም እነዚህ ጥያቄዎች በዚህ ድርድር ላይ በትይዩ መቅረብ ነበረባቸው፤›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -