Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ‹‹የመጨረሻዋን ተስፋ›› እንዲጠቀሙበት ጥሪ ቀረበ

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ‹‹የመጨረሻዋን ተስፋ›› እንዲጠቀሙበት ጥሪ ቀረበ

ቀን:

ከዓመት በላይ የዘለቀውን የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ለማቆምና ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ተፋላሚ ኃይሎቹ ‹‹የመጨረሻውን መልካም አጋጣሚ›› ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉ፣ ዋና አደራዳሪው አምባሳደር ሥዩም መስፍን አሳሰቡ፡፡

በተመሳሳይም የአውሮፓ ኅብረት፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካና ኖርዌይ የሚገኙበት የትሮይካ ቡድንና የቻይና መንግሥትም የሳልቫ ኪርን መንግሥትና በሪክ ማቻር የሚመራውን የአማፂያን ቡድን ‹‹መጨረሻ›› ለተባለው የሰላም ድርድር ራሳቸውን በማዘጋጀት፣ በሕዝባቸው ላይ የተከሰተውን ስቃይ እንዲያቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ በመፍታት በሕግ የሚተዳደር ሕዝብና መንግሥት ለመመሥረት ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች በማስታረቅ ላይ የሚያተኩረው ሦስተኛው ዙር የመጨረሻው ውይይት፣ የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.  ተጀምሯል፡፡

- Advertisement -

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ዋና አደራዳሪው አምባሳደር ሥዩም፣ ‹‹በዛሬው ዕለት በሦስተኛው ምዕራፍ የመጨረሻውን ድርድር ጀምረናል፡፡ ይህ ደግሞ በሰላም ድርድሩ ፍሬያማነት የመጨረሻው መልካም አጋጣሚ ሲሆን፣ በደቡብ ሱዳን አዲስ የሰላም ጮራ ይፈነጥቃል፡፡ ስለዚህ ይኼንን አጋጣሚ አሳልፈን መስጠት የለብንም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እ.ኤ.አ. እስከ መጋቢት 5 ቀን 2015 ለስምምነታቸው ማነቆ ለሆኑት ለሥልጣን ክፍፍልና ለሚፈጠረው የሽግግር መንግሥት መዋቅር ላይ ስምምነት እንደሚደርሱም ነው የገለጹት።

ዋና አደራዳሪው ተፋላሚ ወገኖች በኢጋድ 29ኛው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ይህ ድርድር የመጨረሻ እንዲሆን በተስማሙት መሠረት፣ በድርድሩ ላይ በሚለያዩዋቸው ሁለት ዋና ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዚሁ የሰላም ውይይት ላይ በተለይም እ.ኤ.አ. መጋቢት 5 ይጀምራል የተባለው የሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ውይይት ላይ ሁለቱም መሪዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ከወደ ጁባ የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሰላም ውይይቱ ውጤት የሚያመጣ ከሆነ ለፊርማ ብቻ እንደሚገኙና በውይይቱ ላይ ግን የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው እየተዘገበ ነው፡፡ ነገር ግን አምባሳደር ሥዩም የኪርን አቋም ያልተቀበሉት ሲሆን፣ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ባለፈው ወር በፈረሙት ስምምነት መሠረት እንዲገኙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ተፋላሚ ወገኖቹ በርከት ላሉ ጊዜያት በኢጋድ አደራዳሪነት የተኩስ ማቆም ስምምነት ቢያደርጉም፣ በተደጋጋሚ ስምምነቱን በመጣስ ውጊያቸውን ሲቀጥሉ ተስተውሏል፡፡

አሁንም ቢሆን ለመጨረሻ ጊዜ የተፈረመው የተኩስ ማቆም ስምምነት ተስፋ የተጣለበትና የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ያግዛል የተባለው፣ የየካቲት አንዱ ስምምነት እየተጣሰ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ እንዳለም አምባሳደር ሥዩም አልሸሸጉም፡፡

አሁን በአዲስ አበባ በቀጠለው ድርድር ሁለቱ መሪዎች በፈረሙት ስምምነት መሠረት በሚለያያቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 5 ቀን እስከ መጋቢት 30 ስምምነቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ማዕቀፎች ከተሠሩ በኋላ፣ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ የቅድመ ሽግግር ጊዜ ይሆናል።

በኢጋድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ከመጋቢት 5 እስከ ሚያዝያ 1 ቀን ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የመተግበሪያ መንገዶች ይዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ መጠናቀቅ በኋላም እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ያሉት የሦስት ወራት ጊዜ የቅድመ ሽግግር ዝግጅት ተብሎ የታቀደ ሲሆን፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የኪር መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ሐምሌ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጠናቀቃል፡፡ ከዚያም የሽግግር መንግሥቱ ይመሠረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሥዩም ከስብሰባው በኋላ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ በሰኔ ወር መጨረሻ የሽግግር መንግሥት እንደሚቋቋምና ለዚህም አደራዳሪዎቹን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

ነገር ግን የሥልጣን ክፍፍሉ አሁንም ቢሆን ዋናው ፈተና መሆኑን አቶ ሥዩም ጠቁመዋል፡፡ ቀጣዩ ድርድር በተፈለገው መንገድ ከተጓዘና የሽግግር መንግሥቱ መመሥረት የሚቻል ከሆነ፣ የሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥቱ ለ30 ወራት እንደሚቆይና በመጨረሻም አዲስ ሕገ መንግሥት ለደቡብ ሱዳናውያን እንደሚያረቅ ይጠበቃል፡፡

 በድርድሩ ላይ የተገኙት የሃይማኖት መሪዎች በበኩላቸው፣ ተደራዳሪ ወገኖች የደቡብ ሱዳን ሕዝብን ስቃይ ለማስቆም ፈጣሪ የሰጣቸውን ጥበብ ተጠቅመው ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሴቶችና ሕፃናትን ጥቃት አስቁሞ በአገሪቷ ሥርዓት ለማስፈን እስካሁን የተስማሙባቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ሲሉ የገለጹት ደግሞ የሴቶች ተወካዮች ናቸው። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ ጦርነቱ ካገረሸበት ካለፉት 14 ወራት ጀምሮ ሁለቱም ወገኖች ከ12 ሺሕ በላይ ሕፃናትን መልምለው ለጦርነቱ ማግደዋል በማለት ውግዘት እየደረሰባቸው ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...