Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አለ በጅምላ በአምስት የክልል ከተሞች ቅርንጫፎች ሊከፍት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ገበያን የማረጋጋት ሚና ተሰጥቶት ከዓመት በፊት የተቋቋመው አለ በጅምላ፣ ከአዲስ አበባ ውጪ በአምስት የክልል ከተሞች ቅርንጫፎቹን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡

በንግድ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመውና በአሜሪካው አማካሪ ድርጅት ኤቲ ኬራኒ በኮንትራት እየተዳደረ የሚገኘው አለ በጅምላ፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙት ሦስት የጅምላ መደብሮች በተጨማሪ በሻሸመኔ፣ በሐዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በደሴና በጅማ የጅምላ መጋዘኖችና መደብሮቹን ሊከፍት መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

አለ በጅምላ በያዘው ዕቅድ መሠረት የሻሸመኔና የሐዋሳ መጋዘኖቹን ግንባታ ከሞላ ጐደል በመጠናቀቅ ላይ በመሆናቸው፣ አገልግሎቱ በመጋቢት ወር ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም በባህር ዳር ከተማ ቅርንጫፉን ለመክፈት በያዘው ዕቅድ መሠረት በከተማው የሚገኘውን የጅንአድ መጋዘን በማደስና በአለ በጅምላ የመጋዘን ደረጃ መሠረት በማብቃት፣ በሚያዝያ ወር አገልግሎቱን ለከተማው ነዋሪዎች ለማቅረብ አቅዷል፡፡

በተጨማሪም በዚሁ ዓመት ቅርንጫፎቹን በደሴና በጅማ ከተሞች ለመክፈት በያዘው ዕቅድ መሠረት፣ ከከተሞቹ አስተዳደር አስፈላጊውን የግንባታ መሬት መረከቡን መረጃው ያመለክታል፡፡ የመጋዘን ግንባታውን ለማካሄድ ጨረታ መውጣቱም ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዕቅድ ከተያዙ የክልል ከተሞችና የከተማ አስተዳደሮች መካከል ድሬዳዋና አዳማ ይገኙበታል፡፡

መንግሥት አለ በጅምላን ሲያቋቁም ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት በጅምላ ገበያ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ በገበያው ዋጋ ላይ ከአሥር እስከ 15 በመቶ ልዩነት ማምጣት ነው፡፡ ለዚህም ከኪሳራ በመለስ እስከ ዜሮ በመቶ ትርፍ ድረስ በመሄድ ሽያጭ ሊያከናውን እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ እውን ለማድረግ በ25 ከተሞች 36 መጋዘኖችንና መደብሮችን የመክፈት ዕቅድ ይዟል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከሚገኙት ሦስት የአለ በጅምላ መጋዘኖች እየተረከቡ የሚሠሩ 2,655 ደንበኞች መኖራቸውን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 2,148 ቸርቻሪዎች ሲሆኑ፣ የሸማቾች ማኅበራት ደግሞ 145 ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ 114 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና 248 ሌሎች ደንበኞች መሆናቸውን መረጃው ያስረዳል፡፡

  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች