– የሱዳን ውኃና ኤሌክትሪክ ምክትል ሚኒስትር
– ግብፅ ራሷን ካገለለችበት የዓባይ ቀን ክብረ በዓል ተመልሳለች
የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የዓባይ ውኃን በተመለከተ ከመተባበር ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ አሥሩም የተፋሰሱ አገሮች ለዚህ እንዲሠሩ የሱዳን ውኃና ኤሌክትሪክ ምክትል ሚኒስትር ጥሪ አቀረቡ፡፡
ሚኒስትሯ ዶ/ር ታቢታ በትረስ በካርቱም ባለፈው እሑድ የዓባይ እንዲሁም የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የተቋቁመበትን 14ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የውኃ አስፈላጊነት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር በተፋሰሱ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የመኖር ጥያቄ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ተፋሰስ ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦችና ኢኮኖሚያቸው ከግብርና ጋር በተለይም በዓባይ ወንዝ ላይ ከተመሠረተ ግብርና ጋር የተቆራኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከግብርና መሬት ባለፈ ውኃ በተፋሰሱ አገሮች ለሚኖሩ 340 ሚሊዮን ሕዝቦች ወሳኝ መሆኑን፣ ከተጠቀሰው ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ያህሉ የዓባይን ተፋሰስ ተንተርሶ ኑሮውን የመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከግብርና በተጨማሪ የተፋሰሱ ሕዝቦች በአሁኑ ወቅት የኃይል አቅርቦት ፍላጐታቸው በመጨመሩ፣ የዓባይ ወንዝም ለዚህ ዋነኛ መፍትሔ መሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ዘላቂ በሆነ መንገድ ውኃውን ለመጠቀም የተፋሰሱ አገሮች ከመተባበር ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም፤›› ብለዋል፡፡
በናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የ14ኛ ምሥረታ በዓልና የዓባይ ቀን ላይ አሥሩም የተፋሰሱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች የተገኙ ሲሆን፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ራሷን ከኢኒሼቲቩ አግልላ የነበረችው ግብፅ በውኃ ሚኒስትሯ አማካይነት በዓሉን ታድማለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚቀጥለው ሳምንት በካርቱም የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ቴክኒክ ኮሚቴ እንደሚገናኝ ባለፈው እሑድ ዕትማችን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ስብሰባ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ እንዲተገበሩ ከተመረጡ ድርጅቶች መካከል ፕሮፖዛላቸውን መምረጥ ዋነኛ አጀንዳው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከተመረጡት ሰባት የአምስት የአውሮፓና የአውስትራሊያ ኩባንያዎች መካከል፣ አራት ኩባንያዎች ሰነዶቻቸውን ለኮሚቴው ማስገባታቸው ታውቋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል አንድ ወይም ሁለት ኩባንያዎችን የመምረጥ ኃላፊነት በቴክኒክ ከሚቴው ላይ ተጥሎበታል፡፡