Monday, September 25, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ምርጫው የፖሊሲ አማራጮች መወዳደሪያ ይሁን!

የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ቁምነገሮች መካከል አንዱ፣ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ያሉዋቸውን የፖሊሲ አማራጮቻቸውን በነፃነት ለሕዝቡ ማድረሳቸው ነው፡፡ ዘመናዊው ዓለም የሚግባባበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሕዝብ ፈቃድ በነፃነት የሚካሄድ እንጂ፣ በዘፈቀደ የሚከናወን ማስመሰል አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ምርጫው የፖሊሲ አማራጮች መወዳደሪያ ይሁን የሚባለው፡፡

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ሁሉም አማራጭ የሚባሉ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ምርጫው ያለ እንከን እንደሚከናወን ቃል ሲገባ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በተቻላቸው መጠን ለሒደቱ ስኬት መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ የምርጫው ወሳኝ ኃይል የሆነውና በድምፁ የሚወስነው ሕዝብ የተሻሉ አማራጮችን ያገኝ ዘንድ ባለድርሻ አካላትም አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ ይጠናቀቃል ሲል ሒደቱ በተባለው መንገድ እንዲከናወን ኃላፊነት አለበት፡፡ ምንም እንኳ ኢሕአዴግ አንደኛው ተወዳዳሪ ፓርቲ በመሆኑ የራሱን የፖሊሲ አማራጮችና ያከናወናቸውን ተግባራት የማስተዋወቅ መብት ቢኖረውም፣ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የዕደሉ ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ምንም ዓይነት መሰናክል መጋረጥ የለበትም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ወደ ምርጫ ሲገቡ ከምርጫው ምን ማትረፍ እንደሚኖርባቸው በመገንዘብ፣ ለሒደቱ ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ራሳቸውን ማስገዛት አለባቸው፡፡ ሁሉም ወገኖች ራሳቸውን የሚያቀርቡት ለሕዝብ ውሳኔ ነውና ሕዝቡን ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡

ምርጫ ለአንድ አገር ሕዝብ ህልውና በመሆኑ፣ ለታይታ ወይም ለማስመሰል የሚደረግ ከንቱ ተግባር አይደለም፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት በገነቡ አገሮች ምርጫ የፖሊሲ አማራጮች የሚወዳደሩበት፣ ሕዝብ በምልዓት የሚሳተፍበት፣ በአገር ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ኹነቶች የሚስተናገዱበትና ዘለቄታዊ ለሆነ ዕድገትና ብልፅግና መሠረት የሚጣልበት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዜጐች ነፃነታቸውን በማረጋገጥ የሚበጃቸውን መንግሥት የሚመሠርቱበት ስለሆነ፣ የተለያዩ አማራጮች በነፃነት ይስተናገዱበታል፡፡ ለአገር ጠቃሚ የሆነ አጀንዳ የያዘ የፖለቲካ ፓርቲ ከሌሎች የተሻለ ድምፅ ያገኝበታል፡፡

በዘንድሮ ምርጫ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሕዝቡ ሲቀርቡ ምን ይዘው እንደመጡ በግልጽ ማስረዳት አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ምን እንደሠራና ወደፊት ምን እንዳሰበ ለሕዝብ ብይን ራሱን ሲያቀርብ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የራሳቸውን የተሻለ አማራጭ ሲያቀርቡ ዴሞክራቲክ ባህሪ መላበስ አለባቸው፡፡ አንዱ ሌላው ላይ ጭቃ እየለጠፈ አላስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ካተኮሩ፣ ምርጫው ሰላማዊነቱና ዴሞክራሲያዊነቱ ይቃወሳል፡፡ ይልቁንም ሁሉም ወገኖች የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ምርጫውን የሚገዙ ሕጐች እንዲከበሩ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር፣ በሐሰት ስም ማጥፋትና አሉባልታ እንዳይከሰት፣ በጉልበት የታጀበ ትንቅንቅ እንዳይፈጠር፣ ወዘተ ተግተው መሥራት አለባቸው፡፡

በምርጫ ወቅት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በሚደረጉ ክርክሮችም ሆነ ቅስቀሳዎች አንዱ ከሌላው የተሻለ መሆኑን ማሳየት ያለበት ጥርት ባሉና ግልጽ በሆኑ የፖሊሲ አማራጮች ብቻ ነው፡፡ ስድብ፣ ዘለፋ፣ አሽሙርና አሉባልታ ሲበዛ መራጩ ሕዝብ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ አመኔታ ያጣል፡፡ ዴሞክራቶች ቅድሚያ የሚሰጡት ለሐሳብ ልዩነት በመሆኑ ሐሳብን በሐሳብ መመከት ያቃታው ወገን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከነጐደ የዴሞክራሲውን ሒደት ያበላሸዋል፡፡ ራሱንም ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እየተነገረ ኢዴሞክራሲያዊ ተግባራት ሲጀመሩ የሐሳብ መምከንን ያሳያል፡፡ ከዚህ ይልቅ ለሕዝብ ፈቃድ እገዛለሁ የሚል ፓርቲ ወደ ሕዝብ የሚቀርበው የተሻሉ አማራጮችን ይዞ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እዚህ ላይ ያተኩሩ፡፡

ከዚህ ቀደም በተከናወኑ ምርጫዎች ሕዝብን የሚያሳዝኑ ተግባራት ይፈጸሙ የነበሩት ከዴሞክራሲያዊው መንገድ ይልቅ ተቃራኒው በመመረጡ ነው፡፡ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎች ሲካሄዱ ውጤቱ እልቂት ነው፡፡ ውድመት ነው፡፡ ምርጫ የሕዝብ ነፃነት መገለጫ መሆን ሲገባው በብጥብጥና በሁከት ሲታመስ አገር ትጐዳለች፡፡ ነገር ግን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ሒደት ውስጥ ሲከናወን፣ ስህተቶችን ለማረምና አላስፈላጊ ተግባራትን ለመግታት ያግዛል፡፡ ችግር ሲፈጠር ሕጉን ተገን በማድረግ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ፣ በስሜታዊነት ነውጠኛ መሆን ጉዳት ያስከትላል፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ችግሮችን በማሰብ ለአገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ መትጋት የግድ ይላል፡፡

ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመላ አገሪቱ የሚያደርጉትን ሕጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ መደገፍ አለበት፡፡ ከላይ እስከ ታች ያሉ መንግሥታዊ መዋቅሮችም ሆኑ የፓርቲው አካላት ኢዴሞክራሲያዊ ጫና እንዳያደርጉባቸው የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር በጠበበ ቁጥር ፓርቲዎቹ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ይዘው ወደ ሕዝቡ መቅረብ ስለሚቸግራቸው፣ ይህ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ተብሎ ቃል ሲገባ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት አማራጮቻቸውን ይዘው ለውድድር መሠለፍ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ለሕዝብ የማይጠቅሙ ናቸው እየተባለ ጫና መደረግ የለበትም፡፡ መጥቀማቸውና አለመጥቀማቸው መወሰን ያለበት በሕዝብ ድምፅ ብቻ ነው፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የገዥው ፓርቲ ድክመቶች ላይ ብቻ እየደሰኮሩ፣ አማራጮቻቸውን በግልጽ ይዘው መቅረብ ካልቻሉ የራሳቸው ድክመት ነው፡፡ የፖሊሲ አማራጮቻቸው ይዋል ይደር ተብለው የሚቀመጡ ሳይሆኑ፣ ለሕዝብ ቀርበው በይፋ መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ የራሳቸውን የቤት ሥራ ሳያከናውኑ የሌላውን ድክመት ለማጋለጥ መሯሯጡ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የድክመት መደበቂያ ሆኖም አያገለግልም፡፡ በምርጫው ሲሳተፉ በሙሉ ልብና ጥንካሬ መቅረብ አቅቷቸው አማራጮቻቸውን ማሳየት ካቃታቸው በራሳቸው ነው ማዘን ያለባቸው፡፡

በአጠቃላይ የግንቦቱ ምርጫ የፖሊሲ አማራጮች መወዳደሪያ ይሆን ዘንድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከልባቸው ይሥሩ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች በነፃነት ውድድር የሚደረግባቸው በመሆናቸው የሕዝብ ተሳትፎ ጐልቶ ይታይባቸዋል፡፡ ለሕዝብ ተሳትፎ ቅድሚያ የሚሰጥ የፖለቲካ ፓርቲ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦችን ይዞ ሲቀርብ፣ ከዚህ በተቃራኒ የሚቆም ግን ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በዚህ ምርጫ ወቅት ዋናውና ተፈላጊው ጉዳይ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጮቻቸውን ይዘው ለሕዝብ ዳኝነት መቅረብ ብቻ ነው፡፡ ምርጫውም የፖሊሲ አማራጮች መወዳደሪያ ነው መሆን ያለበት!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...