Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናወ/ሮ ሰሎሜና ሁለት የሰማያዊ ፓርቲ ሴት ዕጩዎች በዕጣ ከምርጫ ውድድር ውጪ ሆኑ

ወ/ሮ ሰሎሜና ሁለት የሰማያዊ ፓርቲ ሴት ዕጩዎች በዕጣ ከምርጫ ውድድር ውጪ ሆኑ

ቀን:

የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንትም በዕጣ ተሰርዘዋል

ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካሉት 23 የምርጫ ክልሎች መካከል በ18ቱ ከ12 በላይ ዕጩዎች በመመዝገባቸው በዕጣ ተለዩ፡፡ የቀድሞ የመንግሥት ቃል አቀባይ የነበሩት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰና የሰማያዊ ፓርቲ ሁለት የሴት ዕጩዎች በዕጣ ከውድድር ውጪ ሆነዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በዕጣ ከዕጩነት ተሰርዘዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ሴት ዕጩዎች ዕጣ ሊወጣላቸው ባለመቻሉ ከምርጫው የተሰረዙ ሲሆን፣ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ይወዳደሩበት የነበረው የምርጫ ክልል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 መርካቶ አካባቢ እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ አካሄዱን ክፉኛ ተችተውታል፡፡ ‹‹መሠረታዊ የሆነውን ሕገ መንግሥታዊ የዜጎች የመመረጥና የመምረጥ መብት ተጥሷል፤›› በማለት አካሄዱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል በማለት ተቃውመዋል፡፡

በዕጣ የሚባል ነገር በየትኛውም ዓለም የለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ከሆነም ሊደረግ የሚገባው የማጣሪያ ምርጫ ይደረግና በማጣሪያ ምርጫው የተሻለ ውጤት ያገኙት መጨረሻ ላይ ለፍፃሜ ወይም ለዋናው ምርጫ ይቀርባሉ እንጂ፣ አንድ ፓርቲ ዕጣ ስላልወጣለት አይወዳደርም ማለት አስገራሚ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይፋዊ በሆነው የፌስቡክ ገጹ ላይ ግን የኢንጂነር ይልቃልን ትችት ‹‹ክሹፍ አመክንዮ ነው›› በማለት ገልጾታል፡፡ ለዚህም እንደማሳያነት የሚያቀርበው የመጀመሪያ ምክንያት ደግሞ፣ ሕጉ አገልገሎት ላይ የዋለው በ1999 ዓ.ም. መሆኑን ነው፡፡ ሰማያዊንም ሆነ ሌሎች አዳዲስ ፓርቲዎችን ለመጉዳት የተፈጠረ አሠራር አልተዘረጋም ሲልም ተከራክሯል፡፡

ሌላው ቦርዱ የሚያቀርበው መከራሪያ ደግሞ በዚህ ሕጉን ተከትሎ በተካሄደው ፓርቲዎችን በዕጣ የመለየት ሥራ መሠረት፣ ‹‹ሰማያዊ ወደ ዕጣ ከገባባቸው 18 የምርጫ ክልሎች በሦስቱ ዕድል ሳይቀናቸው ሲቀር በ15ቱ ዕጩዎች አልፈውለታል፤›› የሚል ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ለሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አዋጁ በ1999 ከመውጣቱ አንፃር ፓርቲው ከዚህ ቀደም በዚህ አዋጅ ላይ ያሰማው የተቃውሞ ድምፅ ነበር ወይ በማለት ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱም፣ ‹‹እነዚህን ሕጐች በመቃወም በተደጋጋሚ ሠልፍ ወጥተናል፡፡ አፋኝና ፀረ ሕገ መንግሥት የሆኑ አዋጆችን ለምሳሌ የፀረ ሽብር፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የመረጃ ነፃነትና የምርጫ አዋጆች ላይ ተቃውሞአችንን አሰምተናል፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ይህን አንቀጽ በተናጠል ባይሆንም አዋጆቹን በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ እሳቤዎች እናድናቸው በሚል ብዙ ጊዜ ስንጮህ ነበር፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ‹‹የእኔ ከዚያ ቦታ መውጣት በፓርቲው አጠቃላይ ሥራ ላይ የሕግን ኢፍትሐዊነት ከማሳየት ባለፈና በአጠቃላይ የምርጫው ሒደት ብዙ ችግር ያለበት መሆኑን ከማሳየት በዘለለ፣ በእኔ ሥራም ሆነ በሰማያዊ አቋም ላይ በተለየ ሁኔታ የሚያሳድረው ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ወ/ሮ ሰሎሜ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ማብራያ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹በሕጉ መሠረት ነው የተወሰነው፡፡ በእኔ ላይ ለብቻዬ የደረሰ ነገር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ነገር ግን ውሳኔው በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍና የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት የሚፈልጉ ግዴታቸውን በመወጣት በአገራቸው ፖለቲካ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች ዜጐችን እንዴት ነው የሚያየው በማለት ከመጠየቅ ባለፈ፣ የዜጐችን ተሳትፎ ይገታል ብዬ አስባለሁ፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡  

ወ/ሮ ሰሎሜ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን ያህል እንኳን ለግል ዕጩዎች መብት ትኩረት አለመስጠቱን ተችተዋል፡፡ ‹‹ዕጣ እንኳን አናወጣም፡፡ በቀጥታ ነው ከውድድር ውጪ የምንሆነው፡፡ ነገር ግን የግል ዕጩ የሚያልፍበት ሒደት ግን ከባድ ነው፡፡ ፊርማ ማሰባሰብ አለ፣ ምንም ዓይነት የመንግሥት ድጋፍ አይሰጥም፣ የአየር ሰዓት አይሰጥህም፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ይህን ያህል ጥረት ካደረገ ሌላው ቢቀር ዕጣ የማውጣት ዕድል እንኳን ቢሰጥ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፤›› በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለብዙ ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ ሒደት እንደሆነ ወ/ሮ ሰሎሜ የገለጹ ሲሆን፣ በአገሩ ፖለቲካ መሳተፍ የሚፈልግን ነገር ግን አሁን ባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨዋታ ደስ የማይለውን አካል ለማቀፍ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...