‹‹አንድም ሴት ሕይወት ስትሰጥ መሞት የለባትም›› በሚል መሪ ቃል በቅርቡ የተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት የአሬንሲያ ላቲና፣ የሰርቤ ኮንትራ ቤዝና የሌሎችም ጀርመናዊ ሙዚቀኞች ሥራ ቀርቦበታል፡፡ ከኢትዮጵያ ሙኒትና ዮርግ፣ ዳዊት ጽጌ፣ ዮሐና አሸናፊና ኃይለኢየሱስ ግርማ ዘፍነዋል፡፡ ኮንሰርቱ እናቶችና ሕፃናትን ከሞት ለመታደግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለማስተዋወቅና ገቢ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሙዚቃዎቹ ከመዝናናት ጎን ለጎን ስለ እናቶችና ሕፃናት ታዳሚው እንዲገነዘብ በራሪ ወረቀቶች ታድለዋል፡፡
ወ/ሮ ሳራ ሐሰን የውሜን ፎር ላይፍ መሥራችና ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ከኮንሰርቱ የውሜን ፎር ላይፍ ሥራዎችን የሚያስፋፋ ገቢ በማሰባሰብ ከጋንዲ ሆስፒታል በተጨማሪ በገጠሩ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አንዳንድ የሕክምና መስጪያ ማዕከሎች በወሊድ ወቅት እናቶች ስለሚያስፈልጋቸው እንክብካቤ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ማቀዳቸውን ይናገራሉ፡፡
እናቶች ወደ ሆስፒታል ሄደው በቂ አልጋ አለመገኘቱ አንዱ ችግር ሲሆን፣ ይህን ለመቅረፍ የድርጅቱ ተቀዳሚ ግብ እ.ኤ.አ. በ2020 ጋንዲ ሆስፒታል 1,000 አልጋዎች እንዲኖሩት ማስቻል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በሆስፒታሉ ለተገነባው አዲስ ሕንፃ ለእናቶችና ሕፃናት የሚሆን የሕክምና መርጃ ቁሳቁስ በማሟላት ላይም ናቸው፡፡ የተነሱለትን ዓላማ ለማሳካት የተዘጋጀው ኮንሠርት የመጀመሪያቸው ሲሆን፣ ስለ ችግሩ አሳሳቢነት በማሳወቅ አጋዥ ተቋሞች እንደሚያፈሩ ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ በወሊድ ወቅት፣ ከወሊድ በፊትና ከወሊድ በኋላም ሴቶች ወደ ሕክምና ጣቢያ እንዲመጡ ከማድረግ አንስቶ በቂ የሕክምና መሣሪያ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚሠሩ ይገልጻሉ፡፡
የድርጅቱ መሥራችና አባል ወ/ሮ ዘሚ የኑስ እንደሚሉት፣ የእናቶችንና ሕፃናትን ሕይወት መታደግ የጥቂት ተቋሞች ኃላፊነት ብቻ መደረግ የለበትም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ባለው አቅም ይመለከተኛል በሚል የየድርሻውን እንዲወጣና የድርጅቱን አርአያ በመከተል ብዙዎች እንዲሳተፉ ለማድረግም ኮንሰርቱ መዘጋጀቱን ያስረዳሉ፡፡ በግንዛቤና የመሣሪያ እጥረት ሳቢያ እየተከሰተ ያለውን ሕልፈት ቀስ በቀስ ለመቅረፍ እንደሚሠሩ የሚያስረዱት ወ/ሮ ዘሚ፣ ጋንዲ ብዙ ሴቶች የሚወልዱበት በመሆኑ በመነሻነት ቢመረጥም፣ ችግሩ በይበልጥ የተንሰራፋባቸው አካባቢዎች ቀጣይ ይሆናሉ ይላሉ፡፡
ውሜን ፎር ላይፍ (ሴቶች ለሕይወት) ሴቶች በወሊድ ወቅት ሕይወታቸውን እንዳያጡ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ ፈቃድ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ መሥራቾቹ ሰባት በጎ ፈቃደኛ ሴቶች ናቸው፡፡ ድርጅቱ ሥራ ከጀመረ ሦስት ዓመቱ ሲሆን፣ ወደ 5 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ እናቶች የሚወልዱበት አልጋ፣ የሕፃናት ማሞቂያ ኢንኩቤተር፣ ዊልቸርና የኦፕሬሽን ጠረጴዛ ለጋንዲ ሆስፒታል በዕርዳታ አበርክቷል፡፡ ድርጅቱ በዋነኛነት የሚሠራው ኢትዮ ዊትንና ሂዩማን ብሪጅ ከተባሉ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ነው፡፡