በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአፍምቦ ወረዳ በሚገኙ ሰባት አካባቢዎች የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተጀመሩ ሥራዎች ልማዶቹ እየቀነሱ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
የዴንማርክ ልዕልት አልጋወራሽ ሜሪ ኤልሳቤጥ ዶናልድሰን ባለፈው ሳምንት በክልሉ የሚገኘውን አፍምቦና ሚሌ ወረዳ በጐበኙበት ወቅት ገለጻ ያደረጉት የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘሃራ ሁመድ እንደገለጹት፣ የጐጂ ልማዶች ሰለባ የሆኑ ሴቶች በሚሌ ወረዳ በሚገኘው ባርባራ ማያ የእናቶች ሆስፒታል ዕርዳታ የሚያገኙ ሲሆን፣ የማዋለድና የማኅፀን ሕክምና እየተሰጠ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ልዕልቷ በአፋምቦ ወረዳ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን ለመታገል የተቋቋመውን የታዳጊ ልጃገረዶች ክለብ፣ በሚሌ ወረዳ የሚገኘውን ባርባራ ማያ የእናቶች ሆስፒታል፣ የአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማኅበርን ጐብኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የሕግ ማዕቀፎች ዘርግታ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፣ ዴንማርክም ችግሩን በዘላቂነተ ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ እንደምታደርግ ልዕልት ሜሪ ኤልሳቤጥ ተናግረዋል፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት በ2000 ዓ.ም. 52 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ወደ 23 በመቶ ደርሷል፡፡ ያለዕድሜ ጋብቻ ደግሞ ከ32 በመቶ ወደ 8 በመቶ ዝቅ ማለቱን የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡
በሆስፒታል ጉብኝታቸውም ወቅት ቫላሪ ቡሮውኒንግ የአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማኅበርና የሆስፒታሉ ኃላፊ ሆስፒታሉ ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሕይወትን የማዳን፣ የማዋለድ አገልግሎቶችንና የማኅፀን ችግር ያለባቸውን የማከም ሥራ በመካሄድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ዴሞግራፊክ ኤንድ ሔልዝ ሰርቬይ እንዳመለከተው፣ በክልሉ የሴቶች ግርዛት ስርጭት ከፍተኛ ነው፡፡ በተጠቀሰው ዓመት የወጣው የዌልፌር ሞኒተሪንግ ሌላው ሰርቬይ እንደጠቆመው ደግሞ የሴቶች ግርዛት 60 ከመቶ ያህል አድጓል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የዓለም አቀፍ የሥነ ሕዝብና የዩኒሴፍ ድርጅቶች የጋራ ፕሮግራም ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በተዘረጋባቸው ስድስት ወረዳዎች ውስጥ ይህ ዓይነቱ ጐጂ ልማድ ቀንሷል ለማለት ይቻላል፡፡
ልዕልት አልጋወራሽ ሜሪ ከጉብኝታቸው በኋላ ከአቶ አወል አርባ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የክልሉን ልጃገረዶችና ሴቶችን ኑሮ ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በዚህም ሒደት የዴንማርክ ድጋፍና ዕርዳታ እንደማይቋረጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የልዕልቲቱን ጉብኝት በጋራ ያዘጋጁት በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ፣ ዩኤንኤፍፒኤና ዩኒሴፍ ናቸው፡፡