ጥበብ ዶሮዪቱ ሰው ጫጩቷን በሀብት ክንፎቿ ታቅፋለች፡፡
ዕውቀት ፏፏቴ ባስተዋይ ልብ ወንዝ ትንሿሿለች፡፡
ጨው ድንቁርና በክረምት ትምርት ይሟሟል፡፡
አዟሪት ባሕር ምቀኝነት የሚዋኟትን ታሰጥማለች፡፡
እነሱ ዘወርዋራ መኾኗን አያውቁምና
እናት ግእዝ አለመታወቅ ምጧን ረሳችው፤
ዐማርኛ ልጇ ተወልዷልና፡፡
ትጋት ተራራ በምንጯ ሀብት ኹሉን ታረካለች፡፡
የድንቁርና ጌታዋና አዛዧ ስንፍና ነው፡፡
ቤት ዐማርኛን ለማስፋት ልቤ ይጓጓል፡፡
አለመማር ዕፅ ከንቱ በሠርክ ችግር ኳ፣ ኰርኳ ብሎ ይወድቃል፡፡
ይህ የግጥም አንድ አንጓ የተገኘው ባለፈው ሳምንት የሕትመት ብርሃንን ዳግመኛ ከ45 ዓመት በኋላ ካገኘው የአለቃ ደስታ ተክለወልድ (ደተወ) ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› ነው፡፡
የቃላት ጉልላቱ አለቃ ደስታ ‹‹ያማርኛ ሠምና ወርቅ›› ባሉት ቅኔያቸው ያማርኛን ቤት ለማስፋት ልባቸው የጓጓውን ያህል በመሥራት ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን መዝገበ ቃላታቸውን ትተውልን አልፈዋል፡፡
ከሁለት አሠርት ባልተሻገረ መልኩ በመካነ ትምህርት ውስጥም ሆነ በግለሰቦች ዘንድ በ27 ብር ተደራሽ የነበረው መዝገበ ቃላቱ በተለይ ለሩብ ምእት ዓመት ያህል በመጥፋቱ አሮጌ ተራ መደብሮች ዘንድ እስከ 1,500 ብር ድረስ ይሸጥ ነበር፡፡
ሙሉ መጠርያው ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት በካህናትና በሀገረ ሰብ ቋንቋ›› የሆነውና የፊደሉ ተራ አቡጊዳን የሚከተለው መጽሐፉን ሊቁ ያዘጋጀቱት ከ1921 እስከ 1950 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ነው፡፡
1248 ገጽ እና 523 ሥዕሎች ያሉበት መዝገበ ቃላቱ ከቃላት ፍችው በፊት አምስት ክፍል አሉት፡፡ በመጀመሪያው ክፍል የቋንቋው ታሪክ ፊደልና የፊደል ነገር የንግግር ክፍሎች ልዩ ልዩ ርባታዎችና የግእዝ ነገር አሉበት፡፡
ሁለተኛው ክፍል አገባብ (ሰዋሰው)፣ ሦስተኛው ያማርኛ ሠምና ወርቅ፣ አራተኛው ምክር በሁለት ዐይነት ግጥም ከመጨረሻው አምስተኛው ክፍል ግስን ይዟል፡፡ የአለቃ ደስታ እጅግ ከፍያለ ጥረት የታየበትና የሕይወት ዘመን ሥራ የሆነው መዝገበ ቃላቱ በዓመቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡ አራተኛው ምክር በሁለት ዓይነት ግጥም በመጨረሻ አምስተኛው ክፍል ግስን ይዟል፡፡
የአለቃ ደስታ እጅግ ከፍያለ ጥረት የታየበት የሕይወት ዘመን ሥራ የሆነው መዝገበ ቃላት በዓመቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡
ሐምሌ 19 ቀን 1893 ዓ.ም. በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ላይ ወግዳ ጎሽ ውኃ ቀበሌ የተወለዱት አለቃ ደስታ፣ ያረፉት ጳጉሜን 2 ቀን 1977 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ከአጥቢያቸው ጀምሮ እስከ ደብረ ሊባኖስ የቅኔና የዜማ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ቀለምን ፈጥኖ በመቀበልና በማስተዋል ችሎታቸው የተመሰከረላቸው አለቃ ደስታ የመጻሕፍት አንድምታ ትርጓሜን አደላድለዋል፡፡ በብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማተሚያ ቤት ቅዱሳት መጻሕፍትን በማረምና በማስተካከል ከ1916 እስከ 1920 ዓ.ም. ድረስ የሠሩ ሲሆን፣ በእርሳቸው አረጋጋጭነት በርካታ መጸሕፍት ለሕትመት በቅተዋል፡፡
በሀገረ ጀርመን በታተመው ኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ እንደተዘገበው፣ ወደ ድሬዳዋ በመሄድ በአልዓዛር ማተሚያ ቤት ሥራቸውን የቀጠሉበት አጋጣሚ የተፈጠረው ከሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መተዋወቃቸው ነበር፡፡ ከ30 ዓመት በፊት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምን እየሠሩ ዐምድ አጋጣሚውን እንዲህ ያስታውሰዋል፡፡
‹‹አለቃ ኪዳነ ወልድ ብርሃንና ሰላምን ሲጎበኙ ደስታ ተክለ ወልድ የግእዙን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ ሲያነብቡና ሲያናብቡ ሰምተው ‘ከኔ ጋር ሥራ’ ብለው ጠይቀዋቸው ነው ይባላል፡፡ ከዚህም የተነሣ በድሬዳዋ አልአዛር ማተሚያ ቤት 16 ዓመት ያህል ሠርተዋል፡፡ እንደገና ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በብርሃንና ሰላምና በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤቶች አገልግለዋል፡፡
‹‹አስተማሪዬ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የጀመሩትን ግእዝ አማርኛ ግስ እንድጨርስ አዘውኝ ነበር፡፡ እነሆ እስከ ዛሬ ደክሜበታለሁ፤ አልተጠናቀቀልኝምና አንተ ተረክበኸኝ ሥራውን ቀጥል፡፡ ዘርሁን፤ ዘር ይውጣልህ›› ብለው አለቃ ኪዳነ ወልድ ለአለቃ ደስታ አደራ ሰጥተው ነበር፡፡ አለቃም አደራውን ጠብቀው በ1948 ዓ.ም. ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ ሌት ከቀን በመሥራት ‹‹መጽሐፍ ሰዋሰው ወግስ፤ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተባለውን የመጀመሪያ ታላቅ መዝገበ ቃላት አሳትመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት የታሪክ ምሁሩ ነፍስ ኄር ዶ/ር ብርሃኑ አበበ ስለ አለቃ ክፍሌና ስለ አለቃ ኪዳነ ወልድ ለ‹‹ምን እየሠሩ ነው?›› አዘጋጅ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹አለቃ ክፍሌ በወቅቱ የአገሪቱ የቀለም ሰዎች ከተባሉት አንዱ ነበሩ፡፡ ዘመኑም የአፄ ዮሐንስ ነበር፡፡ የሃይማኖት ክርክሩ ቦሩ ሜዳ ላይ ተነሥቶ አለቃ ክፍሌ በኋላቀር ካህናት ከሃዲ መስለው በመታየታቸውና በአፄ ዮሐንስ ዘንድ እጅግ ፊት በማጣታቸው የሸዋ ንጉሥ የነበሩት ምኒልክ አገር ጥለው እንዲሰደዱ ይመክሩዋቸዋል፡፡ ከዚያም በምድረ ሱዳን አድርገው ግብፅ ቀጥለውም ወደ ኢጣልያ ይሻገራሉ፡፡ እነ አግናጥዮስ ጒይዲንና ሌሎችንም ግእዝ ካማርኛ ያስተምራሉ፡፡ ቀጥሎም እርጅና ሲመጣባቸው ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም አለቃ ኪዳነ ወልድን ያገኛሉ፡፡ ያላቸውን ዕውቀት ከውድ መጻሕፍታቸው ጋር ለኪዳነ ወልድ ያስረክባሉ፡፡ በተለይም የግእዝና የአማርኛ መዝገበ ቃላት በውል ተሰናድቶ እንዲታተም ለኪዳነ ወልድ አደራ ይሰጣሉ፡፡ በአገሪቱ ዘመናዊ ማተሚያ ሲቋቋም አለቃ ኪዳነ ወልድ ለመጻሕፍት ትርጓሜ ሥራ ወደ አገራቸው ይጠራሉ፡፡ እሳቸው ከአለቃ ክፍሌ የተቀበሉትን አደራ ለአለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ያስረክባሉ፡፡ የዚህ ዐቢይ መዝገበ ቃላት ሥራ መነሻው ይህ ነው፤›› በማለት ስለሦስቱም ሊቃውንት ያላቸው ግምት ከፍተኛ መሆኑን አንፀባርቀዋል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ የሦስቱንም የቀለም ሰዎች ታሪክ በፈረንሣይኛ ቋንቋ አዘጋጅተው ‹‹ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወዘደኃርት›› ከተባለው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፍ ጋር አዳብለው በ1978 ዓ.ም. በጀርመን ማሳተማቸው ይታወቃል፡፡
አለቃ ደስታ ለኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ካበረከቷቸው ሥነ ጽሑፋዊ ትሩፋቶች መካከል የግእዝ መማርያ ‹‹ርባሐ ስም ወአንቀጽ›› (1946 ዓ.ም.) እና ‹‹ገበታ ሐዋርያት›› (1928 ዓ.ም.) ይገኙበታል፡፡
‹‹አንባቢ ሆይ ያማርኛ ቋንቋ ይህ ብቻ እንዳይመስልህ ከዚህ የቀረውን የእንስሳትንና የአራዊትን የአዕዋፍን፣ የዓሣትን፣ የዕፅዋትን፣ ያገርንና የሰውን ስም አምልተን፣ አስፍተን፣ ከነትርጓሜው ለማሳየት ሐሳብ አለን፤ ለዚሁም ያምላካችን ፈቃዱ ይሁን፤›› ብለው በመዝገበ ቃላቱ ላይ ጽፈው ነበር፡፡ ያልታተሙትን ሥራዎቻቸውን ሁለተኛውን እትም ያሳተሙት ልጆቻቸውና ወራሾቻቸው ለንባብ እንደሚያበቁት ይጠበቃል፡፡
ዳግመኛ የታተመው ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት በካህናትና በሀገረሰብ ቋንቋ ተጻፈ ከደስታ ተክለ ወልድ ዘሀገረ ወግዳ የፊደሉ ተራ አቡጊዳ›› የመሸጫ ዋጋ 800 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡