Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየግብፃውያን ስደት

የግብፃውያን ስደት

ቀን:

ሊቢያ እንደቀደሙት ጊዜያት ለግብፃውያኑ ምሁራን፣ ባለሀብቶችና ሠራተኞች ምቹ አልሆነችም፡፡ በሊቢያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ዘመን የነበሩ መልካም ዕድሎች ዛሬ እየተዘጉ ናቸው፡፡ ሠርቶ መኖርና ወደ ትውልድ ቀዬ ሀብት መላክ ለግብፃውያኑ ፈተና ሆኗል፡፡ ከሙአመር ጋዳፊ መንግሥት መገርሰስ በኋላ በርካታ ግብፃውያን ወደ አገራቸው የተመለሱ ቢሆንም፣ በሊቢያ ሠርተን ያልፍልናል ያሉት እዚያው ከትመዋል፡፡

ላለፉት ሦስት ዓመታት በጦርነት እየተናጠች ባለችው ሊቢያም እየሠሩ ቆይተዋል፡፡ አገሪቷ ለሁለት ተከፍላ በሁለት መንግሥታት ብትገዛም ንግዳቸውንና ሥራቸውን ከማከናወን አልቦዘኑም፡፡ ዛሬ ግን አዲስ እንቅፋት በተለይ ግብፃውያኑ ላይ ተደቅኗል፡፡

በሊቢያዋ ዋና ከተማ ትሪፖሊና በቱብሩክ በተመሠረቱ ሁለት መንግሥታት ሳቢያ ፅንፈኛው የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድን በሊቢያ ተስፋፍቷል፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞውንም በኢስላሚክ ስቴትና በሐማስ ላይ ውግዘቷን ስታወርድ ለከረመችው ግብፅ ፈተና ነው፡፡

በቱብሩክ የሚገኘውንና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘውን የሊቢያ መንግሥት ጦር ታስታጥቃለች የምትባለው ግብፅ፣ በዜጐቿ ላይ ፈተና የተጋረጠው በሊቢያ የሚገኘው አይኤስ ከሳምንት በፊት 21 ግብፃውያንን አንገት መቅላቱን አስመልክቶ የቪዲዮ ምሥል ከለቀቀና ግብፅም አይኤስንና ቁሳቁሶቹን ከሊቢያ ለማውደም የአየር ጥቃት ከጀመረች ወዲህ ነው፡፡

በሊቢያ ያሉ ግብፃውያን በፍርኃት ተውጠዋል፡፡ ትውልድ አገራቸውንም ናፍቀዋል፡፡ የአይኤስ ሰለባ እንዳይሆኑም ሽሽታቸውን ተያይዘውታል፡፡

ግብፃውያን በሊቢያ ያላቸውን ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን ለቀው እንዲወጡ የግብፅ መንግሥት በማስታወቁ ምክንያት 15 ሺሕ የሚጠጉ ግብፃውያን ሊቢያን ለቀው ወጥተዋል፡፡

በሊቢያ በሥራ ላይ የተሰማሩ 21 ግብፃውያን በጽንፈኛው የአይኤስ አሸባሪ ቡድን ከተገደሉ በኋላ፣ የግብፅ መንግሥት ዜጐቹ ከሊቢያ እንዲወጡ ነግሮዋቸዋል፡፡ ግብፃውያኑን በፈጁትና መቀመጫቸውን ሊቢያ ባደረጉት የአይኤስ አማፅያን ላይ የአየር ድብደባ ማካሄዱ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ሳምንት የሊቢያና የግብፅ የጦር አውሮፕላኖች በሊቢያ የአይኤስ መናኸሪያ የሆኑ አካባቢዎችን የደበደቡ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ በግብፃውያኑ ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋን ለመከላከል የግብፅ መንግሥት ዜጐቹ ወደ ቱኒዚያ እንዲገቡ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ከቱኒዚያ ወደ ግብፅ የማመላለሱ ሥራም ተጀምሯል፡፡

የሊቢያን ድንበር አቋርጠው ቱኒዚያ ከገቡት በተጨማሪም በቱኒዚያና በሊቢያ ድንበር ቁጥራቸው ያልታወቀ ግብፃውያን እንደሚገኙ የቱኒዚያ ጉምሩክን ጠቅሶ አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 የሙአመር ጋዳፊን አገዛዝ ለመገርሰስ በሊቢያ አብዮት በተቀሰቀሰበት ወቅት በሊቢያ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ግብፃውያን እንደሚኖሩ ተገልጾ ነበር፡፡ ብዙዎቹም በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎትና የሊቢያ የጀርባ አጥንት በሆነው የነዳጅ ዘይት ዘርፍ ሙያቸውንና ገንዘባቸውን ኢንቨስት በማድረግም ይታወቃሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት አይኤስ 21 ግብፃውያንን መግደሉን አስመልክቶ የቪዲዮ ምሥል በለቀቀ ማግሥት የግብፅ አየር ኃይል የጀመረው የአየር ጥቃት፣ በሊቢያ ለሚኖሩት ግብፃውያንም ሥጋትን አምጥቷል፡፡ ከአይኤስ ሰይፍ ለማምለጥም ግብፃውያኑ ሊቢያን ለቀው ወደ ቱኒዚያ እየተሰደዱ መሆናቸውን፣ በቱኒዚያ ድንበርም ቁጥራቸው የማይታወቁ ግብፃውያን እንዳሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ከኢራቅ ሶሪያ በመመላለስ አሜሪካ ባዋቀረችው የጦር ኃይልም ሆነ በኢራቅና በሶሪያ መንግሥታት ወታደሮች መገታት ያልቻለው አይኤስ፣ ማክሰኞ ዕለት ደግሞ በሶሪያ ከአሶሪያን መንደር ነዋሪዎች 90 ያህሉን መጥለፉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ቡድን እንዳስታወቀው ሶሪያውያኑ የተጠለፉት የአይኤስ ታጣቂዎች ከኩርድ ወታደሮች ባስለቀቁት ሥፍራ ነው፡፡

በአብዛኛው ክርስቲያኖች ይኖሩባታል የምትባለው አሶሪያን ከተማ በኩርዶች የተያዘች ነበረች፡፡ ሆኖም የአይኤስ ታጣቂዎች በሃሳክ ከተማ የሚገኙ ሁለት የአሶሪያን መንደሮችን መቆጣጠር ችለዋል፡፡ የሃሳክ አካባቢም ገሚሱ በኩርዶች ገሚሱ በአይኤስ ተዋጊዎች ቁጥጥር ሥር ይገኛል፡፡    

ለአይኤስ ተዋጊዎች ጠንካራ ይዞታ በሆኑት የኢራቅና ሶሪያ ድንበር አካባቢዎች፣ አይኤስ ከኩርድ ተዋጊዎች የሚገጥመው ምላሽ ቀላል አይደለም፡፡ የኩርዲሽ ፒፕል ፕሮቴክሽን ዩኒት በቀጣናዎቹ ያሉ ሥፍራዎችን በእጁ እያስገባ ነው፡፡ በቅርቡ 24 መንደሮችን ከአይኤስ ያስመለሰ ሲሆን፣ በራቃ ከተማ የሚገኙ 19 መንደሮችንም ተቆጣጥሯል፡፡

የአይኤስ ታጣቂዎች በሶሪያ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናትና የክርስትና መገለጫዎችን እያወደሙ ናቸው፡፡ እነሱ በሚከተሉት የእስልምና ሕግ የሚገዛ ክርስቲያን ከዕምነቱ ተከታዮቹ የተለየ ታክስ እየከፈለ መኖር እንደሚችልም አስታውቋል፡፡ አመለካከቱን የማይከተሉትንና መበቀል የሚፈልጋቸው አገሮች ዜጐችን ደግሞ አንገት እየቀላ በቪዲዮ ይለቃል፡፡

የከፍተኛ የእስልምና አስተምህሮ ‹‹አል አህዛር›› ምሁር የሆኑት አህመድ አል ጣይብ፣ አክራሪነት ቅዱስ ቁራንን ባልተገባ መንገድ ከመተርጐምና የሱኒ እስልምና ምንነትን ካለመረዳት የመነጨ ነው ሲሉ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሳዑዲ ዓረቢያ መካ በተካሄደው ጉባዔ ላይ ተናግረዋል፡፡

የእስልምና ትምህርት አሰጣጥ ላይ ተሃድሶ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ፣ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን መግታት የሚቻለውም የትምህርት አሰጣጡን በማሻሻል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ከታሪክ ታሪክ ሲሸጋገሩ የመጡ ልማዶች መኖራቸውን፣ እነዚህ ልማዶችም የእስልምና ሃይማኖትን ባልተገባ መንገድ ለመረዳት መንገድ እንደከፈቱም ነው የገለጹት፡፡ በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት አሰጣጡን በማሻሻልም ቀድሞ የነበሩ አመለካከቶችን መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የአይኤስ ታጣቂዎች በሶሪያ የያዙትን ዮርዳኖሳዊ የጦር ጄት አብራሪ ከነሕይወቱ በእሳት አቃጥለው መግደላቸውን ተከትሎም፣ ጀሃዲስቶች ሊቀጡ እንደሚገባና እስልምና ጭካኔን አያስተምርም ብለዋል፡፡

ሽብር የአክራሪነት አመለካከት ውጤት እንደሆነና ይህም ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ እንዲሁም ለዓለም ሕዝብ አደጋ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...