Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለስንቱ ደረት ይደቃ?

እነሆ ከቤላ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ጎህ ቀዷል ፍጥረት አልገፈፍ ካለው የጨለማ ኑሮ ሊሸሽ መንገዱን ተያይዞታል። ልብ ባይከተለው፣ ቀልብ ስንቅ ባይሆነው፣ እግር ልማዱ ነውና እየተራመደ ያስኬደናል። እንራመዳለን! እንደ ሰነፍ ገበሬ ማሳ በቆምንባት መሬት የዘራነውን ዘር አረም ይጫወትበታል። ቀና ሲሉ አንገት መድፋት፣ አደግን እያሉ መቀጨት ከጥንትም የዓለም ጠባይ ሆኖ ደግሞ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ያደረሰን መንገድ ነገን ሊያሳየን በተስፋ ደግፎ ወዲያ ወዲህ ያንቀዠቅዠናል። አለሁ ሲሉ እንደ ዋዛ መቅረት፣ በረታሁ ሲሉ በአልጋ መያዝ፣ ሆነልኝ ሲሉ አመድ ማፈሱን ተላምደነዋል። ከመላመዳችን ብዛት ሞትና ሕይወትን በምትለይ ቀጭን የመሆንና ያለመሆን መስመር መጓዛችንም አያስደነግጠንም። ይህ መዛል ይባላል። እያደር በአቅጣጫው ልብን የኋሊት እየጎተተ የሚጥለው ፋይዳ ቢስ ጉዳይ መጨመር አያስበረግገንም። ‘እህ?’ ስንባል ‘ይህቺን ታህል አለሁ! ይህቺን ታህል እተነፍሳለሁ!’ ነች መልሳችን።

ሞሳነትን ሳንወድ በግድ ተግተናት ከነፍስና ሥጋችን ጋር ያዋሃድናት የራዕያችን ሁሉ መነሻ መሆኗ ጥቂቶችን ፀጉር ያስነጫል። በቀረው መንገዱን አማን አገሩን ሰላም ያድርጋው የሰርክ መፈክር ነው። ከዚያ አልፎ ጉጉት፣ ከዚያል አልፎ ውጥን እንኳን ‘በዘንድሮ በአምናውም አልተዳርኩ’ እያሰኘ እጃችንን አጣጥፎ አስቀምጦናል። በዳና ጉሰማ ተመላልሰን ካጎደጎድነውና ካረስነው መሬት ይልቅ፣ እንዲህ በየጥጋጥጉ ነገር ዓለሙን ለባለፀበሎች በፈቃዳችን ትተን የተቀመጥንበት ሥፍራ ጥልቀት አለው። የማጣታችን መለኪያም ክፍለ ዘመን ነው። ዳገቱን የወጣንበትን፣ ቁልቁለቱን የተንደረደርንበት ዕድሜ ቀርጥፎ ይበላዋል። መንገድ እያመጣን መንገድ እየወሰደን አንዴ ሲያጣላን አንዴ ሲያዋድደን በቅብብሎሽ እዚህኛው ፌርማታ ላይ በዚህ ስሜት ተገናኝተናል። ‘ዋ’ አለ አሞራ!

“አንተዬ እስኪ ቶሎ ቶሎ በል! ምን ያለው ቀርፋፋ ነው እናንተ?” የአነጋገሯ ዘዬ ከተሜ ባያስብላትም ሞንሟና በመሆኗ ወያላውን ይዛዋለች። “አይዞሽ! አሁን ይሞላል። ያውም በእኛው ተነሳሽነትና በእኛው ድምፅ ነው የምንሞላው። እንኳን እዚህ ላይ ዓባይ ላይ ቆርጠናል፤” ወያላው ንጭንጯን አብርዶ እሷው ውስጥ ትውስታ ለመቆስቆስ ያሰበ ይመስላል። ጓደኞቹና ተራ አስከባሪ ወጠምሻዎች ላይ እንደ አንበሳ እየተንጎማለለ እዚህች ልጅ ጋ ሲደርስ ወገቡን እንደተመታ እባብ ይርመጠመጣል። “ስለሌላ ነገር ማን ጠየቀህ? ወሬውን ትተህ ጥራማ!” ትላለች። ሐሳቧን ማርጋት ቀልቧን መሰብሰብ እንደከበዳት ያስተዋለ በጠዋት አክለፍልፎ ያስወጣትን የማጀቷን አኳኋን እንዲሰልል ይገፋፋል። ወያላው፣ “ይሞላል ስልሽ! ዋናው ማመን ነው!” አላት። ይኼን ሲላት እርጎ የመሰለ ነጠላቸውን በወጉ ያጣፉ ሴት ወይዘሮ እጁን ተደግፈው ይገባሉ። ሥፍራቸውን እንደያዙ በረጁሙ ተንፍሰው፣ “ዋናው ማመን ነው አልክ?” አሉት። “አዎ! ምንም ሳንይዝ አለማመን ተጨምሮማ እንዴት ሆኖ?” አላቸው። ሳቅ ብለው፣ “ኧረ ልክ ነህ ይኼው አለን እንዳመንን። ቋጠሯችን ሳይፈታ፣ ጥያቄያችን ሳይመለስ፣ ስንጮህ ዝም እያለ ይኼው አለን እንዳመንን፤” አሉ እንደማቃሰት ብለው። መቼ ይሆን በመንግሥታት የምናኮርፈው አንሶን ወደ ፈጣሪ የዞርነው?

“ምነው እትዬ?” እንዲያሳለፍት አልያም እንዲጠጉለት ፈልጎ ዓይን ዓይናቸውን የሚያይ ወጣት ፊታቸው ቆሟል። ወይዘሮዋ ወጣቱን ቀና ብለው ዓይተው አንገቱን አንቀው ይስሙታል። “አንተ! ና እስኪ ጎኔ ቁጭ በል። ሥራ ይዘህ ከራስህ የሚተርፍ ገንዘብ ኖሮህ ምርኩዝ ባትሆነኝም፣ እንዲህ ትልቅ ሰው ሆነህ ሳይህ እኮ እንዴት እንደምደሰት አታውቅም?” ይሉታል። ለመሆኑ ሥራ እየፈለግክ ነው? ታመለክታለህ በየመሥሪያ ቤቱ?” ይጠይቁታል። “አይ እማማ እንኳን ለሥራ ‘ፌስቡክ’ ላይም ‘ሪኩዌስት’ የሚመልስ ሰው እየመነመነ ነው፤” ሲላቸው ፈቀቅ ብለውለት ተቀመጠ። ታክሲያቺን ስለሞላ መንቀሳቀስ ጀምረናል። ከአንድ አካባቢ የተሰበሰቡ ተሳፋሪዎች በአብዛኛው ስለሚተዋወቁ ለዓውዳ ዓመት የተሰባሰቡ ቤተ ዘመድ መስለዋል። ጋቢና የተቀመጠው መጨረሻ ወንበር ወዳለው ዞሮ፣ “ሒሳብ እኔ ነኝ እሺ? ትናንት የተሸነፋችሁት ይበቃል፤” ይላል። የዕቁብና የዕድር ስብስቦች በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ታዳሚዎች ማኅበራት መቀየራቸውን በፎርም የሚነግረን ይመስላል። “ብቻ ዲግሪህን ደህና ቦታ አስቀምጠው። ጋዋን ለብሰህ የተነሳኸውን ፎቶም አሳጥበህ በትልቁ ግድግዳ ላይ አኑረው። የት አባቱ! ማንን ደስ ይበለው ብለህ? እውነት በሥራ የሚያልፍ ቢሆን ኖሮ አህያ ላይ የሚደርስበት አለ?” ወይዘሮዋ ሳይታሰብ ጮሁ። ሆድ ለባሰው የሚሆን ማንፀሪያ የማይገጥም ፍጥረት ጠቀሱ። “ሥራ ፍለጋ ከምንባክነው በላይ አፅናኝ ፍለጋ ዓለምን ባንዞር ከምላሴ ፀጉር!” ይላል አንዱ ወደ መጨረሻ ወንበር። ድሮስ ሰው ወደ ኋላ ቀረት ቀረት የሚለው ለነገር አይደል? 

ጋቢና ደግሞ በሞቀ በደመቀ መንፈስ የአውሮፓ ኳስ ፍልሚያ ይዘከራል። በሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኞች ከየኢንተርኔት ድረ ገጹ የቃረሙትን ሳይሳሱ ያንበለብሉታል። ከሾፌሩ ጀርባ ደርሳ፣ “እንዲያው ካልጠፋ ጊዜ በሁዳዴ?” እያለች ብቻዋን የምታወራ ያቺ ወያላውን ስትነዘንዝ የነበረች ሸጋ ልጅና የቆዘመ ወጣት ተቀምጠዋል።  ከጀርባ ‘እንደ እናት አሳድጌሃለሁ’ የሚሉት ወይዘሮና ሥራ አጡ ባለዲግሪ ወጣት አሉ። ከእነሱ ጀርባ አሥር ጊዜ “ሰሙ ወይ እርስዎ ቤት የዕድር ወንበር አለ እንዴ? ስንቆጥረው ጎደለ እኮ!” እያለ ወይዘሮዋን የሚነዘንዛቸው ጎልማሳና እኔ አለን። መጨረሻ ወንበር ሦስት ወንዶች መሀል አቀርቅራ ደብተሯን የምታነብ የሃይስኩል ተማሪ።

ወይዘሮዋ የጎልማሳው ንዝንዝ ሲበረታባቸው ሾፌሩን፣ “እስኪ ሬዲዩኑን ቀንሰው አንተ! እናንተ አትበቁም ደግሞ ለኳስ? እንኳን ኳስ ኑክሌር ሳይንስ የት አደረሰን? ይኼው መንገድ ለመንገድ የሰው ልጅ ደም ደመ ከልብ ሆኖ እየቀረ፤” ብለው ደግሞ ወደ ጎልማሳው ዞሩ፡፡ “ሁለት ተመሳሳይ ጣቢያ ተከፍቶ እኮ መደማመጥ አልቻልንም። ምን አሉኝ?” ጠየቁ። ጎልማሳው ስለዕድሩ ወንበር መጉደል አብራራ። ወይዘሮዋ እንደመቆጣት አሉ። “ምነው ስመኝሽ! የሕዝብ ድምፅ ይጭበርበር፣ ዲሞክራሲ ይጭበርበር፣ ግድ የለም! ድሮስ ሴረኞች ምን ሠርተው ይብሉ? ግን እንዲያው ቢጭበረበር ቢጭበረበር የዕድር ወንበር ይጭበረበራለል? ምን ልትለኝ ነው ዛሬ ቀን ገና ደጁን ሳልሳለም?” አሉና አኮረፉ። ጎልማሳው፣ “እትዬድምፅና ዲሞክራሲስ ከሕዝብ የሚጭበረበረው ለወንበሩ ሲባል አይደል?” አላቸው። “አንተ ሰው ዛሬ ነገር አታምጣ። ደጁን ልሳለምና ኋላ መጥተህ አናግረኝ። ታዛቢ የለም ብለህ ነው ቆጥረህ የወሰድከውን ወንበር እርስዎ ጋር ቀርቷል የምትለኝ?” ደህና የተጣፋውን ነጠላ እየነጠሉ መልሰው ያጣፋሉ። “አይቆጡ እንጂ! እኔ እኮ ከአለ አለ ከሌለ የለም እንዲሉኝ ነው የጠየቅኩዎ። ደግሞም ስለድምፅና ዲሞክራሲ ሲያነሱ ስለወንበር ቀለድኩ እንጂ እኔ እርስዎንም የፖለቲካ ፓርቲዎችንም ልኮንን አይደለም፤” ብሎ ጎልማሳው ወደ እኔ አይቶ ሲያበቃ፣ “ምነው ዘንድሮ ግን እውነትን እውነት ሐሰቱን ሐሰት ብሎ መገላገል እያለ ዙሪያ ጥምጥም የሚሄደው በዛ?” አለ። ወይ እውነትና ሐሰት እቴ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው ሒሳብ ሲቀበል ያቺ ልጅ የምታልጎመጉመውን ሲያዳምጥ ቆይቷል።  “ሁዳዴ ምን አደረገ ደግሞ? ይኼው ያለአዋጅ እንፆም የነበርን ሰዎች በይፋ በአዋጅ እንፆማለን። ምን ሆነሻል?” አላት። “በጠዋት የሰማሁት መርዶ ሳያንሰኝ ደግሞ የአንተ ማድረቅ በዛ፡፡ ተወኝ አደራህን! ኧረ!” አለችው። ከወይዘሮዋ አጠገብ የተሰየመው ወጣት፣ “ሰው ሞቶብሽ ነው?” ብሎ ወደ እሷ አሰገገ። ይኼን ጊዜ እንባዋ ዱበ ዱብ። “አንድ ያለችኝ አህቴ . . .” ማውራት አቃታት። እዬዬዋን ስታስነካው ሁሉም ጨዋታውን አቁሞ ወደ እሷ ይመለከታል። ሾፌሩ፣ “ሃሎዝም አስብላት፡፡ ምን እኔን ታየኛለህ?” እያለ ወያላው ላይ ይጮሃል። “እህ! እንዴት ያለ ነገር ነው? ለጥይት የከፈልንበት ዘመን አለፈ ስንል ደግሞ ለእንባ ክፈሉ ልንባል ነው? ተዋት ገና እርሟን መቼ አወጣች!” ጎልማሳው ሾፌሩን ይገስጻል። “ታማ ነበር?” አጠገቧ የተቀመጠው ወጣት አፉን ይፈታል። “ደክማለች መጥተሽ እያት ነው ያሉኝ። አንዴ አትያዝ እንጂ ከተያዝክ ዘንድሮ ማን ያተርፍሃል? ያውስ ገንዘብ ሳይኖርህ? ያላቸውም አልሆነላቸው፤” ብላው አረፈች። ተሳፋሪዎች እርስ በእርስ እየተያዩ፣ “አንቺ? ምን ዓይነቷ ነች እባካችሁ! ገና በእግዜር እጅ ሳለች ለሞት አሳልፈሽ ሰጥተሽ ነው በሟርት እህትሽን ገለሽ የምታለቅሺው? በይ ዝም በይ አሁን በፈጣሪ ሥራ አትግቢ፤” ብለው ወይዘሮዋ የምራቸውን ተቆጡ። እሳቸው እንዳሉት ገና ደጁን ሳይሳለሙ የሚለክፋቸው በዝቷል። “ጉድ! ይኼማ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መንፈስ ነው። ገና ያልተበላውን በድምፅ የሚወሰን ሎተሪ አስቀድመው በአፋቸው እንደሚያስበሉት ይህቺም እንደዚያው ተጋብቶባት ነው፤” ሲል አንዱ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ፣ ‘ምንና ምን’ በሚል አስተያየት ሁሉም ዞር ዞር እያለ ገላመጠው። አይጣል እኮ ነው እናንተ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ገሚሱ የደከመች እህቷን ገና ሳታያት ለሞት አሳልፋ የሰጠቻትን ልጅ ይገስጻል። ገሚሱ ከወያላው ጋር መልሴን አምጣ እያለ ዓደዋ ካልተደገመ ይላል። ወያላው፣ “እኔ የሰው ገንዘብ አልወድም ጊዜ ስጡኝ፤” እያለ በአጭበርባሪነት መፈረጁን ይቃወማል። ወይዘሮዋና አጠገባቸው የተቀመጠው ወጣት ‘እኔ ልክፈል የለም እኔ’ ትግል ገጥመው እንዳይሆን ይሆናሉ። ጋቢና የተቀመጡት ተሳፋሪዎች ከመቼው አዲስ አበባ ስታዲየም ገብተው የአገራችንን ፕሪሚየር ሊግ መውቀጥ እንደጀመሩ አላወቅንም። ጭራሽ አንዱማ፣ “ለምን ኳሱን እርግፍ አድርገው አይተውትም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ‘ለመሸነፍ አንድ ስታዲየም ይበቃል’ ያሉት እኮ ወደው አይደለም!” ይላል ከእነ አካቴው። ከጀርባዬ የተቀመጡት ወጣቶች ደግሞ፣ “ይኼ ታክሲ ይኼን ጊዜ ወይ ጋዜጣ አልያም የፌስቡክ ድረ ገጽ ቢሆን ኖሮ እያንዳንድሽ ሸቤ ተወርውረሽ ነበር። አሸባሪ ሁላ!” እያሉ የምፀት ሳቃቸውን ከጣራ በላይ ይለጉታል። “ወይ ሽብርና ሽብርተኝነት!” ሲል አንደኛው “አሁንማ አውሮፓ ሳይቀር የእኛን የፀረ ሽብር ሕግ ቃል በቃል ‘ኮፒ’ ወደማድረጉ ተቃርቧል እየተባልን ነው እንጃልን?” ይላል ሌላኛው። ሦስተኛው ደግሞ ደህና ድምጿን አጥፍታ የተመጠችዋን ተማሪ፣ “ኧረ በፈጠረሽ ስለ አሸባሪነት እያወራን አንቺ ታጠኛለሽ? አትሳተፊም?” ቢላት ደንግጣ ቀና ብላ አይታው፣ “እፎይ! ‘እኔ እኮ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር’ ዓይነት መፈክር ስትፎክርብኝ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በየት በኩል ተመልሰው መጡ ብዬ እንዴት ደነገጥኩ?” ብላ ወደ ደብተሯ አዘቀዘቀች። ታዳጊዋ ያለፈውን ወዲያ አሽቀጥራ ለነገ ማንነቷ ዛሬ መትጋቷ ዋጋ እንደሚሰጣት ፍፁም እንዳረጋገጠች ያስታውቅባታል። አንዳንዱን እንዲህ የመኖር ጥበብ በልጅነቱ ሲገባው ሌላውን በሽምግልናው አልጠጋው እያለ በሟርት ያልሞተውን ሲገል፣ ያላደገውን ሲቀጭ፣ የተሠራውን እንዳልተሠራ ሲያሳንስ ያኖረዋል። ወያላው “መጨረሻ” ሲል ዓይኔ ዙሪያዋን የከበባትን ሟርታዊ አስተሳሰቦች ቸል ብሎ የነገ ተስፋዋ ላይ ያነጣጠረችው ታዲጊ ላይ ይንከራተት ነበር። ሁሉን አጠልሽቶ እንዴት ይዘለቃል? “ቁልቁል መንደርደር የሚያልም መልሱ ዳገት ይሆንበታል፤” ያለው ማን ነበር? ቁልቁለትና ዳገት መሳደዱ በዛ እኮ? ታዳጊዋን እያሰብኩ ተቸክሎ የቀረው አሳዘነኝ፡፡ ለስንቱ ደረት ይደቃ? መልካም ጉዞ!      

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት