Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየምርጫ 2007 ጉዳዮችና የሕዝብ ተሳትፎ

የምርጫ 2007 ጉዳዮችና የሕዝብ ተሳትፎ

ቀን:

በአይተን ጂ. Anchor

በማንኛውም የዴሞክራሲ ሥርዓት የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝቡም ይህንን ሥልጣኑን ይመሩኛል ለሚላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰብ ተወዳዳሪዎች የሚያስተላልፍበት ሒደት በየጊዜው የሚያካሄደው ምርጫ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ምርጫ የዜጎች ሰብዓዊ የፖለቲካ መብት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዜጎች መንግሥታቸውን የሚቆጣጠሩበትና የሚቀይሩበት የሥርዓቱ ዋስትና ነው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንዶች ከሁሉም የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫዎች የመጀመሪያው (Threshold Indicator) ምርጫ ነው የሚሉት፡፡ እርግጥ ነው እነዚህን ግቦች የሚያሳካ ምርጫ ለይስሙላ የሚካሄድ ሳይሆን ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በአገራችን በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው 5ኛው አገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ላለፈው አንድ ወር ያህል ተካሂዷል፡፡ የመራጮች ምዝገባ ሒደቱን በሚመለከትም የተለያዩ አካላትና ኅብረተሰቡ አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ እኔም በእነዚህ በተነሱ ነጥቦችና በምርጫ ሒደት ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎን በሚመለከት አንዳንድ ነጥቦችን ለማለት ወደድኩ፡፡

ለምርጫ መመዝገብ ወይም መምረጥ መብት ወይስ ግዴታ?

ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ የሕግ ባለሙያ መሆኔን የሚያውቅ የሠፈሬ ልጅ፣ በሠፈራችን ቅያስ ውስጥ የተቋቋመው የምርጫ ጣቢያ ውስጥ የሚሠሩት ምርጫ አስፈጻሚዎች ባለፈ ባገደመ ቁጥር ምርጫ ተመዝገብ እያሉት መሆኑን ገልጾልኝ፣ ለምርጫ መመዝገብና መምረጥ በሕግ የተጣለበት ግዴታ መሆን አለመሆኑን እንድነግረው ጠየቀኝ፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ማንኛውም ዕድሜው 18 ዓመት የደረሰ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አድልዎ ሳይደረግበት የመምረጥ መብት አለው፡፡ ሌሎች የአገሪቱ የምርጫ ሕጎችም በአዕምሮ ሕመምና በፍርድ የመምረጥ መብታቸው ከተገደበ ሰዎች ውጪ፣ ይህንን መብት ለዜጎች ያረጋግጣሉ፡፡ የአገሪቱ ሕጎችም ሆኑ አገራችን የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በዚህ መብት ላይ የሚያስቀምጡት ጥበቃ፣  ለመምረጥ ብቁ የሆኑ ዜጎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለምርጫ ተመዝግው እንዳይመርጡ የሚደረጉ ክልከላዎችን ማስቆም ላይ ያጠነጥናሉ እንጂ፣ በተቃራኒው ዜጎችን በመራጭነት ተመዝግበው እንዲመርጡ የሚያስገድዱ አይደሉም፡፡

ይሁንና መምረጥን ግዴታ የሚያደርጉ አገሮች በጭራሽ የሉም ማለት አይደለም፡፡ እንደ አውስትራሊያ ያሉ አገሮች ለመምረጥ ብቁ የሆኑ ዜጎችን በምርጫ እንዲሳተፉ የሚያስገድዱበት ሕጎች አሏቸው፡፡ በእነዚህ አገሮች ለመምረጥ ብቁ ሆኖ የማይሳተፍ ዜጋን ለመቅጣት አነስተኛ የገንዘብ መቀጮን ጨምሮ የተለያዩ አነስተኛ ቅጣቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ የእነዚህ አስገዳጅ ሕጎች መነሻ ምርጫን እንደ ዜግነት ግዴታ መመልከትና የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ በማረጋገጥ ለሚመሠረተው መንግሥት ትክክለኛ ቅቡልነት (Legitimacy) ለመፍጠር በማሰብ ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ምርጫን ግዴታ የሚያደርጉ ሕጎች የሰዎች ነፃነትን ከመጋፋት አንፃር ከሚቀርብባቸው ትችት በተጨማሪ በተግባርም ብዙ አዋጭ ሲሆኑ አይታዩም፡፡ አስገዳጅ ሕጎቹ ዜጎችን ወደ መመዝገብና ወደ ምርጫ ጣቢያ ከማምጣታቸው ባለፈ በአግባቡ መምረጣቸው የሚረጋገጥበትን መንገድ ማስቀመጥ አይቻላቸውም፡፡ በሚስጥር በሚሰጠው ድምፅ መስጫ ውስጥ ባዶ ወይም ዋጋ የሌለው የምርጫ ካርድ በማስገባት ሕጉ ግቡን እንዳይመታ የማድረግ አጋጣሚው የሰፋ ነው፡፡

እንደኛ ባሉ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል በሌለባቸው ታዳጊ ዴሞክራሲዎች ደግሞ የአስገዳጅ መራጭነት ሕጎችን ማውጣት የባሰ አደጋ ሊያመጣ ይችላል፡፡ በተለይም በሥልጣን ላይ ያሉ መንግሥታት ይኼንን ሥልጣን ያላግባብ በመጠቀም ለራሳቸው ጥቅም እንዲያውሉት በር ይከፍታል፡፡ ለዚህም ነው በአገራችን ለምርጫ መመዝገብና መሳተፍ ከዜግነት የሞራል ግዴታ የሚመነጭ መብት እንጂ ግዴታ ያልሆነው፡፡

የሕዝብ ተሳትፎ አንድምታዎች

የአንድ የምርጫ ሒደት ለመምረጥ ከሚችሉ ዜጎች መካከል የተመዘገቡት፣ ከተመዘገቡትም ውስጥ በምርጫው ቀን ድምፃቸውን የሰጡ ዜጎች ቁጥር ብዛት አንደኛው የነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መለኪያ ነው፡፡ በተጨማሪም ለመራጭነት ብቁ ከሆኑ ዜጎች ውስጥ በብዛት መሳተፋቸው የሚመሠረተውን መንግሥትን ቅቡልነት (Legitimacy) ከማረጋገጥ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በተቃራኒው የመራጭ ተመዝጋቢው ዜጋ ቁጥር ለመምረጥ ብቁ ከሆነው ዜጋ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በጣም ያነሰ ከሆነ፣ በዚህ ሒደት የሚያሸንፈው ፓርቲ ተቀባይነት ያለው ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ የለየላቸው አምባገነኖች እንኳን ምርጫ ሲያካሂዱ የሕዝብ ተሳትፎን ለማብዛት ብዙ ርቀት የሚጓዙት፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ በ2002 በሳዳም ሁሴን መንግሥት የተደረገውን ፕሬዚዳንታዊ ሪፈረንደም ወይም ምርጫ 100 በመቶ የሕዝብ ተሳትፎ እንደነበረው መገለጹን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይሁንና በሃይማኖታቸው ምክንያት በምርጫ ላለመሳተፍ ከሚወስኑ ዜጎች በተጨማሪ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ዜጎች በምርጫ ላለመመዝገብና ላለመሳተፍ ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች ስለምርጫና መራጭነት መብታቸው በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ለምርጫ ላይመዘገቡ ይችላሉ፡፡ በተለይም የተማረና የዜግነት መብቱን የሚረዳ ዜጋ ብዛት ጥቂት በሆነባቸውና ለዘመናት በአምባገነን ሥርዓቶች ውስጥ ያለፉ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሚገኙ መራጮች፣ በግንዛቤ ማጣት ምክንያት በራሳቸው ተነሳሽነት በምርጫ ላይሳተፉ ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል ስለፖለቲካ ግድ የማይሰጣቸው፣ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ የማይጥማቸው ዜጎች ለምርጫ ላይመዘገቡ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከተሞች ባሉ ወጣቶች ዘንድ ይህ ፍላጎት ማጣት ጎልቶ የሚታይ ይመስለኛል፡፡ በመሠረቱ ሁሉም ዜጋ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እኩል ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና ዕውቀት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ተገቢ አይመስለኝም፡፡

አንዳንዶች ደግሞ በምርጫ ሒደቱ ላይ እምነት ስለሌላቸው በምርጫው ላለመሳተፍ ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ምርጫውን በሚያስተዳድረው ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትና ገዥው ፓርቲ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ያካሂዳል የሚል እምነት ከማጣት፣ በሒደቱ ተስፋ በመቁረጥ ላለመሳተፍ ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ የተቃውሞ አቋም ኖሯቸው ብቁና ለመመረጥ የሚበቃ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም በሚል እምነት በምርጫው ላለመሳተፍ የሚወስኑም ይጠፋሉ ብዬ አላስብም፡፡

የሰሞኑ ምርጫ ምዝገባ ጉትጎታና ቅስቀሳ ወይስ የመብት ጥሰት?

ባለፈው ሳምንት ኢትዮ ምህዳር በተባለው ጋዜጣ ላይ የምርጫ ካርድ መውሰድ ወይም አለመውሰድ በሚል ርዕስ አቶ በለጠ ጎሹ በተባሉ ጸሐፊ በቀረበ ጽሑፍ ላይ፣ የሰሞኑ የምርጫ ተመዝገቡ ቅስቀሳ ሕዝቡን በመደለል፣ በማስፈራራት ወይም በማስገደድ እየተከናወነ እንደሆነ በመጥቀስ በአንዳንድ ቀበሌዎች ለተመዝጋቢዎች አስቤዛ የሚሸምቱበት ካርድ በማደል፣ ያልተመዘገቡ ሰዎች ኮንዶሚኒየም እንደማይደርሳቸውና ሥራ የማግኘት ዕድላቸው የተመናመነ እንደሆነ በማስወራትና ሌሎችም መደለያዎችን በመጠቀም እየተከናወነ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በእኛ ሠፈር ያሉ ምርጫ መዝጋቢዎች ኮታ አልሞላልኝም እኔ ዘንድ ተመዝገቡ ከሚል ልምምጥ ጀምሮ፣ በሥራ መውጫ ሰዓት ያልተመዘገቡ ሰዎችን በመጠበቅ ከፍተኛ ጉትጎታ ሲያደርጉ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡

እነዚህ ተግባራት በትክክል ተፈጽመዋል ወይስ የፈጠራ ናቸው የሚለውን የማስረጃ ጥያቄ ወደጎን ትተን፣ የምርጫ ተመዝገቡ ቅስቀሳውን አንድምታ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የምርጫ ቦርድ መራጩ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በወቅቱ በመመዝገብ የመምረጥ መብቱን ሊጠቀምበት ይገባል በሚል ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በመሠረቱ የመምረጥ መብትን ለዜጎች ከማረጋገጥ አንፃር በሕገ መንግሥቱና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት መንግሥት ተገቢ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡ የምርጫ ግብዓቶችን ከማሟላትና የምርጫ ሒደቱን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለሕዝቡ ስለመምረጥ መብቱ በማስተማርና በማነሳሳት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ማስቻል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ የምርጫ ቦርድ የተመዝገቡ ቅስቀሳው በተለይም በዕውቀት ማነስና በግዴለሽነት ያልተመዘገቡ ዜጎችን ስለመብታቸው አውቀው እንዲጠቀሙ ለማድረግ ከሆነ አስፈላጊ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ነገር ግን የተመዝገቡ ቅስቀሳውን ገደብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በአገራችን በመራጭነት መሳተፍን የሚያስገድድ ሕግ አለመኖሩ የመምረጥ መብትን የግለሰብ ዜጎች የግል ምርጫ ያደርገዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ፣ መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት የዜጎችን የመምረጥ መብት ማክበርና ማስከበር እንደሚጠበቅባቸው ሁሉ፣ የዜጎችን ያለመምረጥና ያለመመዝገብ ውሳኔ ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይኼንን ውሳኔ የተለያየ ጫና በመፍጠር ለማስቀየር የተሞከረ እንደሆነ ጉዳዩ የመብት ጥሰት ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የ2002ቱን አገራዊ ምርጫ ታዝቦ ያወጣው ሪፖርት በምርጫው ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ጥሰቶች እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡ በሪፖርቱ እንደተቀመጠው በአንዳንድ ቦታዎች በቀበሌ አስተዳዳሪዎች አማካይነት የምርጫ ካርድ መውሰድን እንደ ግዴታ በመቁጠር፣ በኅብረተሰቡ ላይ ጫና የመፍጠር ሁኔታ መታየቱን በግልጽ አስቀምጧል፡፡

በአሁኑ የምርጫ ምዝገባም ወቅትም ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ተመሳሳይ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ይሁንና ይኼንን ለመከላከል ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ የሚጠበቅበት የምርጫ ቦርድ፣ ችግሩ ከዚህ ቀደም ያልተከሰተና አሁንም እየተነሳ እንዳልሆነ መቁጠርን መርጧል፡፡ እንደውም ባሁኑ ጊዜ ብዙ ቅሬታ እየቀረበ ያለው የምርጫ ቦርድ መዝጋቢ ብሎ ባስቀመጣቸው ሠራተኞች መሆኑ ቦርዱን ተገቢ የቁጥጥር ተግባር እንዲያከናውን ሊያደርገው ይገባ ነበር ፡፡

ከመመዝገብ ወይም ካለመመዝገብ ማን ይጠቀማል?

የምርጫ ቦርድ በአገራዊ ምርጫዎች ላይ የሕዝብ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ይገልጻል፡፡ ከሰሞኑም የምዝገባ ጊዜው ሳይጠናቀቅ ወደ 35 ሚሊዮን ገደማ መራጮችን መመዝገቡን ገልጾልናል፡፡ አቶ በለጠ በኢትዮ ምህዳር ላይ የምረጡኝ ዘመቻውን ጉትጎታ በመጥቀስ የተመዝጋቢው ሕዝብ ቁጥር ሲበዛ ኢሕአዴግ እንደሚጠቀምና ዞሮ ዞሮ ምርጫው ነፃና ገለልተኛ እስካልሆነ ድረስ፣ ኢሕአዴግም በምርጫው ከሥልጣን ይወገዳል ብለው ስለማያስቡ ለምርጫ እንደማይመዘገቡ ይገልጻሉ፡፡

እንደ ግለሰብ ይህ መብታቸው መከበር አለበት፡፡ ይሁንና ይነስም ይብዛም ተመዝግበው የሕዝብን ድምፅ የሚጠብቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉበት ሁኔታ ለምርጫ መመዝገብ ኢሕአዴግን ብቻ እንደሚጠቅም ማተት ፓርቲዎቹን በሙሉ እንደ አጃቢ የመቁጠር አዝማሚያ ይመስላል፡፡ ስለ 35 ሚሊዮን ተመዝጋቢ ዜጋ በፍረጃ መናገርና በምርጫ እንዳይመዘገቡ መቀስቀስ ግን የተመዘገቡ አባላትና ደጋፊዎች ያሉትን ገዢ ፓርቲ ከመጥቀም ውጪ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡

ጸሐፊው በአሁኑ ወቅት ለምርጫው እየተመዘገቡ ያሉት ከኢሕአዴግ ጋር የጎሳ ወይ የጥቅም ትስስር ያላቸው ወይም በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ የሚገኙና የዋጋ ንረቱ የደቆሳቸው፣ ወይም በአንድ ለአምስት ወጥመድ ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸውም ይሉናል፡፡ ይህም አመለካከት ሕዝብ በብዛት ከተመዘገበ እኛን ነው የሚመርጠው በማለት አስገዳጅ ጫና ከሚያደርጉት የገዢው ፓርቲ አባላት የታበየ አመለካከት እኩል ሕዝብን አጠቃሎ የሚፈርጅ አደገኛ አዝማሚያ ነው፡፡

የሕዝቡ የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም ማስገደድ ሞኝነት ነው፡፡ ዜጎች ያልተመዘገቡት መብታቸውን ስለማያውቁ ነው በሚል አሰልቺ ጉትጎታ ማድረግ ሕዝቡን መናቅና ተጠራጣሪ ማድረግ ነው፡፡ ብዙ ሰው ከተመዘገበ እኔን ይመርጠኛል ማለትም ግልጽ ማናለብኝት ነው፡፡ ለምርጫው የተመዘገበን አድርባይና የተገዛ ነው ማለትም ሕዝብንና ራስን መስደብ ይመስለኛል፡፡

የዜጎች ለምርጫ መመዝገብ በራሱ ውጤት ነው፡፡ የምርጫው ሥርዓትና ሜዳው እጅግ የጠበበ ስለሆነ የመንግሥት ለውጥ አይመጣበትም ብንል እንኳን፣ ለሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን ስሜት ለመፍጠርና ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረጉ አይቀርም፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተወደደም ተጠላም ሒደት ነው፡፡ ይህንን ሒደት ለማፍጠን ሁሉን ነገር ካልተቆጣጠርኩ የሚለው መንግሥት ዋነኛ ኃላፊነቱን መውሰድ ቢገባውም ሕዝቡም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም፣ የዴሞክራሲ ተቋማትም ለሥርዓቱ መገንባት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ሲባል ሌላ የእርስ በርስ ጦርነትና ብጥብት ውስጥ መግባት የለብንም በሚለው ሐሳብ ዙርያ ከስምምነት ከተደረሰ ደግሞ ቁልፉ የሕዝቡ ተሳትፎ ነው፡፡ እናሸንፋለን ብለን ስናስብ ብቻ የምናበረታታው፣ እንሸነፋለን ብለን ስናስብ የምናዳክመው ከሆነ ሕዝቡን የሥልጣን ባለቤት የማድረግ ጉዳይ ሳይሆን የራሳችን ጉዳይ እናደርገዋለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...