Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ዘለል ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ሊጀምሩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሁለቱ አገሮች ውስጥ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ድንበር አቋርጠው ከአንዱ አገር ወደ ሌላው እንዲጓጓዙ ያስችላል የተባለው ስምምነት፣ በሁለቱ አገሮች የትራንስፖርት ሚኒስትሮች በኩል እንደሚፈረም ለማወቅ ተችሏል፡፡

አገልግሎቱን ለማስጀመር እንዲያስችል ከሁለቱ አገሮች የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ ጉዳዩን ሊያጠናና አገልግሎቱን ለመጀመር ይረዳል የተባለ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት እስካሁን ያልነበረ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቀው ስምምነት በአካባቢው ፈር ቀዳጅ ተደርጐ ሊታይ እንደሚችልም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ድንበር ዘለል አገልግሎት እንዲያቀርቡ ለማስቻል የኢትዮጵያና የሱዳን መንግሥታት የጋራ ኮሚሽን ስምምነት ላይ ከደረሰ ዓመታት እንደተቆጠሩ ይታወቃል፡፡

የጋራ ትራንስፖርት አገልግሎቱን በተግባር ለመተርጐም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም፣ ሥራውን ለማስጀመር በሁለቱ አገሮች በኩል የተቋቋመው ኮሚቴ ጉዳዩን ካጣራና መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች ከፈተሸ በኋላ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ሊቃረብ መቻሉ ተነግሯል፡፡

ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቀው ስምምነት ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ስለድንበር ዘለል ትራንስፖርቱ የሚመለከታቸው የሁለቱም አገሮች ባለድርሻ አካላት ይመክሩበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ስምምነቱ በሁለቱም አገሮች የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን የሚመለከት በመሆኑም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲያውቁ፣ አገልግሎቱ ሲጀመርም ማከናወን ስለሚኖርባቸው ተግባራት በዝርዝር ይመክሩበታል ተብሏል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት ከሁለቱም አገሮች የተውጣጡ የትራንስፖርት ድርጅቶች ለአገልግሎቱ የሚያውሏቸው ተሽከርካሪዎች ሁኔታና የአገልግሎቱ ታሪፍ ምን ያህል ይሁን የሚለው የስምምነቱ አካል ይሆናል ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሰላም ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ኩባንያው ወደ ተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አገልግሎቱን በማስፋፋት ለመሥራት የነበረው ውጥን በመንግሥታቱ ደረጃ መፈረም የነበረበት ስምምነት በመዘግየቱ ሳይሳካለት ቆይቷል፡፡

በተለይ ወደ ሱዳን፣ ኬንያና ሶማሊያ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ጥናት አጠናቆ ከየአገሮቹ ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ በአንድ ወቅት ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

ከሌሎቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር ያለው የስምምነት ሒደት በእንጥልጥል ላይ የቆየ ቢሆንም፣ ከሱዳን ጋር ይደረጋል የተባለው ስምምነት ከተፈረመ፣ ድንበር ተሻጋሪ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመስጠት እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደረገ ስምምነት መሠረት፣ በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ስምምነት ተደርጐ ነበር፡፡ ሆኖም ድንገት በተከሰተው የደቡብ ሱዳን እርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ስምምነቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ጦርነቱ ባይከሰት ኖሮ ከኢትዮጵያ ወገን፣ በጋምቤላ ክልል ፓጋክ ተብሎ በሚጠራው ድንበር አካባቢ የሚዘልቅ የትራንስፖርት መስመር ለሕዝብ ክፍት ይደረግ እንበደነበር ሲታወቅ፣ እስከ ደቡብ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ የአስፋልት መንገድ በኢትዮጵያ በኩል መገንባቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች