Monday, July 22, 2024

አንጋፋዎቹ የኢሕአዴግ አመራሮች ስለመለስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹በክፍለ ዘመን አንዴ ከሚፈጠሩ ሰዎች የሚመደብ ነው›› አቶ በረከት ስምኦን

‹‹አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፈጠር ይችላሉ›› አቶ ስብሐት ነጋ

ሕወሓት የትጥቅ ትግሉን የጀመረበትን 40ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡ ከዋናው የበዓል ቀን ቀደም ብሎ ከተዘጋጁት መድረኮች መካከል የውይይት ፓናሎች ይገኙበታል፡፡ አብዛኞቹ የኢሕአዴግ አንጋፋ አመራሮች በመድረኮቹ ተገኝተው የጥናት ጽሑፎች በማቅረብ፣ በማወያየትና አስተያየት በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡ በአንዳንዶቹ መድረኮች ያልተገመቱ የሚመስሉ ክርክሮችም ተነስተው ነበር፡፡

በውይይት መድረኮቹ ስለ ኢሕአዴግ (ሕወሓት) ውልደት፣ ዕድገትና የዓላማ ግልጽነት እንዲሁም የአመራር ብቃትና መተካካትን በተመለከተ የቀረቡት አስተያየቶች ቀልብ የሚስቡ ነበሩ፡፡

‹‹መለስ››

አቶ መለስ ዜናዊ ሕወሓትን መርተው ለድል ካበቁት አንጋፋ የሕወሓት አመራሮች መካከል ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላም ኢትዮጵያን በበላይነት መምራት ብቻም ሳይሆን፣ አገሪቱ ባለፉት 20 ዓመታት የተገበረቻቸውን ፖሊሲዎችና አስተሳሰቦችን እንዳመነጩም ይነገርላቸዋል፡፡ ከአገር ባሻገርም የአፍሪካ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰሙ ተከራክረዋል በማለት ዕውቅና የሚሰጧቸው አካላት አሉ፡፡ በእነዚህ አካላት ‹‹የአፍሪካ ቃል አቀባይ›› የሚል ቅፅል ስም እስከማግኘትም ደርሰው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የምዕራባዊያንን የልማት አቅጣጫዎች በመሞገት አማራጭ ፖሊሲ ያሉትን በማቅረብ በዓለም አቀፍ በደረጃ ዕውቅና የተቸሩ መሪ ነበሩ፡፡

ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕልፈት በኋላ ግን በድርጅቱ አባላት ዘንድ የሚጠየቅና የሚነካ የማይመስል ‹‹የመለስ ራዕይ›› የሚል አባባል፣ እንደ ጣኦት እየተመለከ እስኪመስል ድረስ እየተሰበከ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህ የኢሕአዴግ ተቀናቃኞች ድርጅቱ ከአቶ መለስ በኋላ አዲስ አስተሳሰብ ማመንጨት የሚችል መሪ የለውም የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ያደረገ ይመስላል፡፡ ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ በሕወሓት ውስጥ የተደረገው መተካካት የሰላ ትችት የቀረበበት ሲሆን፣ በሒደቱም ‹‹የመለስ ራዕይ›› አምላኪዎችና ተቃዋሚዎች የተፋለሙበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸውና የመምራት ብቃት አላቸው ተብሎ የሚታመንባቸው ሰዎች መገለል ደርሶባቸዋል የሚል ቅሬታ መቅረቡም አይዘነጋም፡፡

በ1993 ዓ.ም. በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረው መሰንጠቅ ምክንያት አቶ መለስን የሚፈታተኑ አንጋፋ መሪዎች በአንጃነት ሲሸኙም፣ በድርጅቱም ሆነ በመንግሥት ውስጥ ተክለ ሰውነታቸው ከፍ ብሎ ስለነበር ‹‹የሚተኩ ሰዎች አይደሉም›› የሚል አስተሳሰብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የኢሕአዴግ አንጋፋ አመራሮች አቶ መለስን በመተካት ጉዳይ ላይ ልዩነት ያላቸው ይመስላል፡፡

ከአንጋፋዎቹ የኢሕአዴግ አመራሮች መካከል አቶ ስብሐት ነጋ (አቦይ) እና አቶ በረከት ስምኦን በጉዳዩ ላይ የሰጡት የተለያየ አስተያየትም የዚሁ የአስተሳሰብ ልዩነት ነፀብራቅ ነው፡፡

አቶ በረከት ስምኦን በበዓሉ ዋዜማ በሰማዕታት ሐውልት ያቀረቡት ‹‹መለስ ከትጥቅ ትግል እስከ መስዋዕትነት›› የሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው የዚሁ ክርክር መነሻ ነበር፡፡ ይህ  በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩና መቐለን ያጥለቀለቋት የበዓሉ ታዳሚዎችን ሲያነጋግር የነበረው ክርክር፣ ‹‹አቶ መለስን መተካት ይቻላል ወይስ አይቻልም?›› በሚል በብዙዎች ጭንቅላት ውስጥ ሲመላለስ የቆየውን እሳቤ ግልጽ እንዲወጣ ያደረገ አጋጣሚ ነበር፡፡

የሰማዕታት አዳራሽ እስከ ሦስት ሺሕ ሰዎች የመያዝ አቅም ያለው ነው፡፡ አቶ በረከት ይህንን ጥናታዊ ጽሐፍ ሲያቀርቡም አዳራሹ ከአፍ እስከ ገደፉ ግጥም ብሎ ሞልቷል፡፡ የአቶ በረከት ግምገማ የሚጀምረው በሁለት መንገድ ነበር፡፡ አቶ መለስ ከሰዎችና ከተፈጥሮ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ዕውቁ ፖለቲከኞችና ፈላስፋ ፍሬድሪክ ሄግል ያለውን ‹‹World Class Personality›› [ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሰብዕና] የተላበሱ ሰዎች ዝርዝርን እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርግ አቶ በረከት ተከራክረዋል፡፡ እንደ ሄግል አስተሳሰብ እነዚህ ሰዎች በአንድ ክፍለ ዘመን አንዴ የሚገኙ ናቸው፡፡

አቶ በረከትም የጀርመኑን ፈላስፋ እሳቤ ተውሰው፣ ‹‹መለስ በክፍለ ዘመን አንዴ የሚፈጠሩ ሰዎች ውስጥ የሚመደብ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ አቶ በረከት እምነት አቶ መለስ በዚሁ ትውልድ ሊተኩ የሚችሉ ዓይነት ሰው አይደሉም፡፡ ምናልባትም እንደ አቶ መለስ ዓይነት ሰው በኢትዮጵያም በአፍሪካም ብቅ የሚለው ከመቶ ዓመት በኋላ እንደሆነ ነው፡፡

‹‹መለስ ከማናችንም በላይ ምጡቅና በሳል ዓለም አቀፍ አዕምሮ የነበረው ሰው ነው፤›› ብለዋል አቶ በረከት፡፡ የአቶ በረከት ንግግር ከእነ አቶ ዓለምሰገድ፣ አቶ አዲሱ ለገሠና አቶ ታደሰ ጥንቅሹ ድጋፍ ተችሮታል፡፡ በክፍፍሉ ጊዜ አቶ መለስ ‹‹አንጃውን›› ሽባ ያደረጉበት መንገድም የዚሁ ምጡቅነት መገለጫ ተደርጎ ቀርቦ ነበር፡፡

በአቶ መለስ ሕልፈት ማግሥት ለቪኦኤ በሰጡት አስተያየት በአቶ መለስ ሞት ምክንያት በኢሕአዴግ ውስጥ አንድ ሰው ተቀንሷል ያሉት አቶ ስብሐት፣ የድርጅቱ ህልውና በግለሰቦች መሄድና መምጣት እንደማይወሰን መናገራቸው ብዙዎችን አስገርሞ ነበር፡፡

በማናቸውም ጉዳይ ላይ የኢሕአዴግ አቋም ይሁን አይሁን ምንም ሳይበግራቸው ‹‹ነፃ›› አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት አቶ ስብሐት፣ የአቶ በረከትን አስተያየት እንዳልወደዱትም በግልጽ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአቶ በረከት አስተያየት አልስማማም፤›› ብለው አቶ ስብሐት አስተያየታቸውን መሰንዘር ሲጀምሩ ብዙዎች ለመስማት የቸኮሉ ይመስሉ ነበር፡፡ አዳራሹ ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ ‹‹አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፈጠር ይችላሉ፤›› በማለትም ተቃውሟቸውን  በግልጽ ተናግረዋል፡፡ አቶ ስብሐት እንደሚሉት መሪ የሚፈጠረው ዘመናት ተቆጥረው ሳይሆን ሁኔታው ሲመቻቹ ነው፡፡ የአቶ መለስም ብቃት በተፈጥሮ ሳይሆን የትግሉ ወቅት መራራነትና ፈታኝ ሁኔታ የፈጠረው ነው፡፡

አቶ ስብሐት አቶ መለስን የሚተካ መሪ በየጊዜው ይፈጠራል በሚል አስተያየት አላበቁም፡፡ ብዙ የኢሕአዴግ ሰዎች ለመተቸት የማይደፍሩትን ‹‹የመለስ ራዕይ›› የሚለው አስተሳሰብ እንደወረደ የተቀበሉት አይመስልም፡፡ ‹‹የመለስ ራዕይ ስንል በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በመሬት በሥራ ላይ መታየት አለበት፤›› በማለትም ቀጠሉ፡፡ ብዙ ሰዎች እንደወረደ ሲሰብኩት የሚስተዋለው ይኼው ራዕይ መመዘን ያለበት በተግባር እንደሆነ አስረድተው ሌላ ተያያዥ ጥያቄም አነሱ፡፡ ‹‹ለመሆኑ ሕዝብ የሚቆጣጠረው መንግሥት ፈጥረናል ወይ?›› የሚል ከባድ ጥያቄ ለተሳታፊዎቹ ጣል አደረጉ፡፡

አቶ ስብሐት የሰጡዋቸው አስተያየቶች በዚህ ርዕስ ላይ የተገደቡ አልነበሩም፡፡ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሕወሓት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይም ለየት ያለ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ከክፍፍሉ ጊዜ ጀምሮ ኪራይ ሰብሳቢነት በአቶ መለስ የኢሕአዴግ አደጋ ተደርጎ ይቀርብ ነበር፡፡ በ1993 ዓ.ም. የሕወሓት ክፍፍል የተወገዱት አባላት ዋነኛ አጃንዳም ይኼው ነበር፡፡

አሁንም ድረስ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚለው አገላለጽ የሙስናና የብልሹ አስተዳደር ማምለጫ እስኪመስል ድረስ ደጋግመው ሲሉት ይደመጣል፡፡ ለአቶ ስብሐት ግን ይህ ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል፡፡ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት የድርጅታችን አደጋ ነው ካልንበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ግልጽ የሆነ ልዩነት ፈጥረናል ወይ?›› የአቶ ስብሐት ሌላው ከበድ ያለ ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮች መፈጠር አልነበረባቸውም፡፡ ነቅተን ስላልጠበቅን ነው የተፈጠሩት፤›› ብለዋል፡፡

የ1993 ዓ.ም. የድርጅቱን ክፍፍል በምሳሌነት በመጥቀስ ሙስናን በተመለከተ አቶ ስብሐት ከዚህ በፊት የሰጡዋቸው አስተያየቶች፣ ከአሁኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አረዳዳቸው ጋር የሚስማማ ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሙስና የድርጅቱ አደጋ ቢሆንም፣ በድርጅቱ ውስጥ ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነት የለም፡፡

አመራርን በተመለከተ አንጋፋው የሕወሓት ታጋይ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ባቀረቡት ጽሑፍ መሪ የሚፈጠረው በተግባር ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ለአመራር ቀውስ መፈጠር መንስዔ ናቸው ያሏቸውን ሦስት መሠረታዊ ነገሮችም ጠቅሰው ነበር፡፡ እነዚህም በስኬት መስከር፣ ቸለልተኝነትና ችግርን ማድበስበስ ናቸው፡፡ የድርጅቱ መሠረታዊ እሴቶች ለድሉ ምንጭ እንደሆኑ ሲያቀርቡ ከጊዜ ሒደት አንዳንድ የተንጠባጠቡ እሴቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

‹‹የሕዝቡ ግለት ሲጨምር ነው አመራሩ ጤነኛ ሊሆን የሚችለው፡፡ የሚጠይቅ ኅብረተሰብ ሲኖር ነው የአመራሩን ጤነኝነት እያረጋገጠ የሚሄደው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከአቶ ዓባይ ጋር በጋራ ጥናት ያቀረቡት አቶ ሥዩም መስፍንም፣ ‹‹ጤነኛ አመራር ማለት በአቋሙ ሳይሸማቀቅ ፀንቶ የሚቆም፣ ቅን፣ ውህደት ያለውና የሕዝብ ወገንተኝነት ያለው ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ በረከትም በዚህ ላይ የሰጡት አስተያየት ከአቶ ሥዩም ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ለሕወሓት መስዋዕትነት ክብደት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ሕወሓት ከባዱን መስዋዕትነት ከማንም በላይ ቢከፍልም ሒሳብ ሲያወራርድ ግን ሰምቼ አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በበዓሉ ላይ ባሰሙት ረዥም ንግግር ውስጥ በተደጋጋሚ ይህንን ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ ‹‹ይኼ ሕዝብ የከፈለው መስዋዕትነት ከባድ ነው፡፡ ሆኖም አንድም ቀን የከፈልኩትን ያህል መካስ አለብኝ የሚል ሒሳብ አወራርዶ አያውቅም፤›› ብለዋል፡፡

የአቶ ሥዩምና የአቶ ዓባይ ጥናት አወያይ የነበሩት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በበኩላቸው፣ መሪ ማለት ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚያመጣና ሕዝባዊነት የተላበሰ መሆኑን ገልጸው፣ የሕወሓት የድል ምንጭ ሕዝብ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡ ‹‹እስከ መጨረሻ የመራን ሕዝብ ነበር፡፡ በግለሰቦችና በቡድኖች ልዩ ብቃትና ችሎታ የመጣ ድል የለም፤›› ብለዋል፡፡

መተካካትን በተመለከተ በመድረኩ ላይ አንዳንድ ወሳኝ ጥያቄዎች አቅርቦ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ተቋም መምህር ወጣት ናሁሰናይ በላይ፣ አቶ መለስ በኢሕአዴግ ያበረከቱት የመሪነት ሚና ከፍተኛ የነበረው በተለይ ሁኔታዎችን በውል በመገንዘብና ቁርጠኛ ውሳኔ በመስጠት እንደነበር ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ ‹‹ሆኖም የኢሕአዴግ የአመራር ብቃት እዚሁ ላይ ተዘጋ ማለት ዘበት ነው፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥም ውጭም ያሉት ወጣቶች ዕድሉ ከተሰጣቸው ዘመኑ የሰጣቸውን ትምህርትና ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የበለጠ አመራር ሊሰጡ ይችላሉ፤›› ብሏል፡፡ በአስተሳሰብ ደረጃ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ትውልድ የተሻለና በመጠፋፋት ሳይሆን በክርክርና በመወያየት የሚያምን እንደሆነም አክሏል፡፡

የሕወሓት የትጥቅ ትግል 40ኛ ዓመት ክብረ በዓል የካቲት 11 በመቐለ ከተማ በድምቀት መከበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ከአንዳንድ አካባቢዎች የሰማዕታት አፅም ተሰብስቦ በሰማዕታት ሐውልት እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የትግራይ ሕዝብ በትግሉ የነበረው ተሳትፎ፣ ጥንታዊ ሥልጣኔና የተከፈለውን መስዋዕትነት መራራነት የሚያሳዩ የተለያዩ ትርዒቶች ቀርበዋል፡፡ በትግሉ ወቅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት በሕይወት ያሉ ሦስት አመራሮች (አቶ ሥዩም መስፍን፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬና አቶ ስብሐት ነጋ) ልዩ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንዲሁም ለድርጅቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር በመስጠት በመስዋዕትነት ያለፉትን ሜጀር ጄኔራል ሐየሎም አርዓያን ጨምሮ የበርካታ ታጋዮች ቤተሰቦች ልዩ ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በተለይ ከአራትና ከአምስት በላይ ታጋዮች መስዋዕት የሆኑባቸው ቤተሰቦች ልዩ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

    

        

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -