የእንስሳትን ባሕርይ የሚያጠኑ ሊቃውንት ዝሆኖች በጣም አስፈላጊ የሆኑ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉባቸው የረቀቁ ዘዴዎች በጣም ተደንቀዋል። ጆይስ ፑል የአፍሪካ ዝሆኖች እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩባቸውን ዘዴዎች ለ20 ዓመታት ያህል አጥንተዋል። እነዚህ በጣም ተፈላጊ በሆነው ጥርሳቸው ምክንያት በሰፊው ሊታወቁ የቻሉት ግዙፍ እንስሳት በጥቂት እንስሳት ላይ ብቻ የሚታይ ስሜት እንደሚታይባቸው ተገንዝበዋል።
“አንድ ቤተሰብ የሆኑ ወይም የሚዛመዱ ዝሆኖች በሚገናኙበት ጊዜ የሚያደርጉትን የሰላምታ ልውውጥ ወይም አዲስ የቤተሰብ አባል የሚሆን ሕፃን በሚወለድበት ጊዜ የሚከናወነውን ሥነ ሥርዓት የተመለከተ ሰው . . . ደስታ፣ ተድላ፣ ፍቅር፣ የወዳጅነት ስሜት፣ ፈንጠዝያ፣ ርህራሄና አክብሮት ሊባሉ የሚችሉ ጠንካራ ስሜቶች የሏቸውም ሊል አይችልም” ብለዋል።
ለረዥም ጊዜ ተለያይተው ቆይተው በሚገናኙበት ጊዜ ራሳቸውን ቀና አድርገውና ጆሮቻቸውን ቀልብሰው እያውለበለቡ አንዳቸው ወደ ሌላው በሚሯሯጡበት ጊዜ ከፍተኛ ትርምስ ይፈጠራል። እንዲያውም አንደኛው ዝሆን ኩንቢውን ሌላኛው አፍ ውስጥ የሚጨምርበት ጊዜ ይኖራል። የሰላምታው ልውውጥ ዝሆኖቹ “እንደገና መገናኘት መቻላችን ምንኛ የሚያስደስት ነው!” የሚሉ ያህል ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ያሳያል! ይህ ዓይነቱ ዝምድናና ትስስር ለሕልውናቸው በጣም አስፈላጊ የሆነውን እርስ በርስ የመደጋገፍ መንፈስ ያድሳል።
በተጨማሪም ዝሆኖች ቀልድ የሚያውቁ ይመስላል። ፑል ዝሆኖች የአፋቸውን የግራና ቀኝ ጠርዝ ወደኋላ ሸሸት በማድረግና ራሳቸውን በመነቅነቅ ደስ መሰኘታቸውን የሚያሳይ የሚመስል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መመልከታቸውን ገልጸዋል። አንድ ጊዜ እንስሳቱን እንዳጫወቷቸውና ለ15 ደቂቃ ያህል ሁሉም እንደቦረቁ ተናግረዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ በጨዋታው ተካፍለው ከነበሩት ዝሆኖች አንዳንዶቹ ዳግመኛ ሲመለከቷቸው፣ ጨዋታውን አስታውሰው ሳይሆን አይቀርም፣ “ፈገግ” ብለውላቸዋል። ዝሆኖች እርስ በርሳቸው በመጨዋወት ከመደሰት በተጨማሪ ድምፆችን የመኮረጅ ችሎታም አላቸው። ፑል ባከናወኑት አንድ የጥናት ፕሮጀክት ከተለመደው የዝሆኖች ጥሪ የተለየ ድምፅ ሰምተዋል። ድምፁ በሚመረመርበት ጊዜ ዝሆኖች ባጠገባቸው ያልፍ የነበረን የጭነት መኪና ድምፅ መኮረጃቸው እንደሆነ ሊታወቅ ተችሏል። ይህን ያደርጉ የነበረው ለጨዋታ ሲሉ እንደሆነ ግልጽ ነው! ዝሆኖች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለመፈንጠዝና ለመጫወት የሚፈልጉ ይመስላል።
በአንድ የቤተሰብ አባል ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ዝሆኖች እንዴት እንደሚያዝኑ ብዙ ተብሏል። አንድ ጊዜ ፑል ሞታ በተወለደች ግልገሏ አጠገብ ዞር ሳትል ለሦስት ቀናት የቆየች ዝሆን ተመልክተው ያዩትን እንዲህ በማለት ገልጸዋል። “ፊትዋ በሐዘን የተመታና በትካዜ የተዋጠን ሰው ፊት ይመስላል። ራስዋና ጆሮችዋ ወደታች ተንጠልጥለዋል። የአፏ ጠርዞች ወደታች ተዘርግተዋል።”
ዝሆኖችን ለጥርሳቸው ሲሉ የሚገድሉ ሰዎች እናታቸው ስትገደል በተመለከቱ ግልገሎች ላይ ምን ያህል ‘የሥነ ልቦና ቁስል’ እንደሚያደርሱ አያስቡም። እነዚህ ግልገሎች የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ቀናት ወላጆቻቸውን ያጡ እንስሳት በሚጠለሉባቸው ቦታዎች ተጠብቀው የደረሰባቸውን “ሐዘን” ለመርሳት ይጣጣራሉ። አንድ ጠባቂ ግልገሎቹ ማለዳ ላይ “ሲጮሁ” መስማቱን ተናግሯል። ከግድያው ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳን ሐዘኑ ሲያገረሽባቸው ታይቷል። ዝሆኖቹ ለዚህ ሁሉ ሥቃይ የሚዳርጋቸው የሰው ልጅ መሆኑን ማወቅ እንደሚችሉ ፑል ተናግረዋል።
- ጄ ደብሊው ዶት ኦርግ (እ.ኤ.አ. 2002)