መድኃኒትና የሕክምና ግብዐቶች ለጤናው ዘርፍ ከተመደበው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 50 ከመቶውንና ከዛም በላይ የሚወስዱ ቢሆንም መድኃኒቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ የሚሰጠው በመሆኑም መድኃኒቶች ለብክነት እየተጋለጡ ነው፡፡
ዶክተር ንጉሡ መኮንን የማኔጅመንት ሳይንስ ፎረ ሔልዝ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ወደ አገሪቷ ከሚገቡት መድኃኒቶች መካከል በአማካይ ከስምንት በመቶው በላይ ይባክናሉ፡፡ አንዳንድ ጥናቶች ደግሞ የብክነት መጠኑን ከተጠቀሰው በላይ ከፍ ያደርጉታል፡፡
በአገር ደረጃ ተጠንቶ የቀረበውን የብክነት መጠን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተቀብሎት በዚህ ዓመት በሚያበቃው አራተኛው የጤናው ዘርፍ የልማት ፕላን (ሔልዝ ሴክተር ዴቪሎፕመንት ፕላን) ውስጥ በማካተት ብክነቱን ወደ ሁለት መቶ ለማውረድ እየሠራም ይገኛል፡፡
መድኃኒት በዋናነት የሚባክነው የመጠቀሚያው ጊዜ በማለፉ ሲሆን፣ ይህም የሚከሰተው ደግሞ ፍጆታን (አጠቃቀምን) በአግባቡ ካለማወቅ፤ የግዥ ሥርዓቱን በአግባቡ ካለማካሄድ፤ መድኃኒቱ ከገባ በኋላ ክምችቱን እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ካለመገንዘብ ነው፡፡
የፋርማሲ አገልግሎት በደንብ ኦዲት አለመደረግም ከብክነት ጋር እንደሚያያዝ፣ በዚህም የተነሳ በበጀት ዓመቱ በስድስትና በሰባት ወራት ውስጥ አንዳንዴም ባነሰ ጊዜ የመድኃኒት በጀት እንደሚያልቅ፣ አንዳንዴ ከጤና ተቋም የወጡ መድኃኒቶችም በግለሰብ ፋርማሲ ውስጥ ሲሸጡ እንደሚስተዋልና ይህም የቁጥጥሩ መላላቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር ንጉሱ፣ ከአንድ ጤና ተቋም መጋዘን የወጣው መድኃኒት ወደ ፋርማሲ ተወሰዶ በዚያው ለተጠቃሚው እንደሚሰራጭ ወይም ጥቅም ላይ እንደዋለ ተደርጎ ቢቆጠርም ሀቁ ግን ከዚህ የራቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ከመጋዘን የወጣ መድኃኒት በሥነ ሥርዓት ኦዲት ተደርጎ አያውቅም፡፡ በአጠቃላይ ለመድኃኒት ተብሎ በተለይ የተዘጋጀ የወጪና ገቢ መመዝገቢያ ሰነድ የለም፡፡ በዚህም የተነሳ መድኃኒቱ የት እንዳለ እንኳን የማይታወቅበት ጊዜ አለ፡፡
የተጠቀሱትን ችግሮች ፈር ለማሲያዝ የተደረገ ጥረት የለም ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶክተር ንጉሡ ሲመልሱ፣ ‹‹ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ሆስፒታል ሪፎርም ኢምፕልመንቴሽን ጋይድላይን አውጥቷል፡፡ በዚህ ጋይድ ላይን ውስጥ በዋንኛነት ማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ሔልዝ ዲዛይን ያደረገውና በመላ አገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ጤና ተቋማት/ሆስፒታሎች የመድኃኒት አያያዝን፣ አጠቃቀምንና አሰረጫጨትን አስመልክቶ ሊከተሏቸው የሚገቡ 11 ልዩ ልዩ ሥርዓቶች ተዘርግተዋል ብለዋል፡፡
ሥርዓቶቹ በ36 የመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ከነዚህ መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሰው ኦዲተብል ፋርማሲዩቲካል ትራንዛክሽን ኤንድ ሰርቪስ የሚል ሲሆን አግባብ ያለው የመድኃኒት አጠቃቀም፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና የተበላሹ መድኃኒቶችን ማስተዳደር ከሥርዓቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የተጠያቂነትንና የኃላፊነትን ባሕርይ ባሰረፀው ኦዲተብል ፋርማሲዩቲካል ትራንዛክሽን ኤንድ ሰርቪስ ሲስተም አማካይነት እያንዳንዱ መርፌ፤ ካፕሱል፣ ኪኒንና ዋና ዋና የተበከሉ መድኃኒቶች በሙሉ ዋጋቸው በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ አንድ መድኃኒት ከመጋዘን ወጥቶ ተጠቃሚው ዘንድ እስከሚደርስ ለመቆጣጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መድኃኒት ሲገባና ሲወጣ የሚያዝበት ወይም የሚመዘገብበት ሞዴልም ተዘጋጅቷል፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ለሥራ ምቹና ለተጠቃሚው የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ፋርማሲዎችን ለማቋቋም መቻሉንም ነው ዶ/ር ንጉሡ ያመለከቱት፡፡
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህንኑ ኦዲተብል ፋርማሲዩቲካል ትራንዛክሽን ኤንድ ሰርቪስ ሲስተም በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን፤ እንዲሁም 17 የፌዴራልና የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች እንዲተገብሩት ወስኗል፡፡ የኦሮሚያ፣ የትግራይና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በየክልላቸው በሕግና በአወዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን እየጣሩ ነው፡፡
ወይዘሮ አድና በሬ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጄንሲ የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንደሚሉት፣ ኤጀንሲው ደረጃቸውን የጠበቁ 17 ቅርንጫፍ መጋዘኖች፣ ለመድኃኒት ማጓጓዣ የሚውሉ 155 የጭነት ተሽከርካሪዎች አሉት፡፡ መጋዘኖቹ ማቀዝቀዣ ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን ከተሽከርካሪዎች መካከል ሃያ አንዱ ፍሪጅ የተገጠመላቸው ናቸው፡፡
ቅርንጫፍ መጋዘኖቹ የተቋቋሙት የጤና ተቋማትን ቅርበት መሰረት ባደረገ መልኩ ሲሆን የመድኃኒቶቹ ግዥ የሚከናወነውም የእያንዳንዱ ጤና ተቋም ፍላጎትና ጥያቄ ባካተተ መልኩ ነው፡፡ ፍሪጅ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች መኖር፣ የመጋዘኖቹ ዘመናዊ መሆን፣ የመድኃኒት አቅርቦቱ ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ መከናወን ብክነትን ከማስወገድ አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡