Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ጽንፈኝነት የአፍሪካ ቀጣዩ ፈተና

  በእስክንድር ከበደ

  በአሁኑ ወቅት በአለማችን የሽብርኝነት ሥጋት እያየለ መምጣቱ ግልጽ ነው፡፡ የሽብር መረቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡ ሲሆን፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ   ትስስራቸው ህቡዕና ረቂቅ በመሆኑ፣ የአገሮችን ህልውና እየተፈታተነ መምጣቱ  አልቀረም፡፡ በአንድ አገር የሚፈጸም የሽብር ጥቃት የዚያችን አገር ህልውና ብቻ ሳይሆን፣ የጎረቤቶቿን ብሎም የአካባቢ አገሮችን ሰላምና መረጋጋት የሚያደፈርስ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ይህንን ሰፊ ጉዳይ በአንድ መጣጥፍ መዳሰስ ቢከብድም፣ አጠቃላይ ሁኔታውን በክፍለ አኅጉር ደረጃ በመጠኑ ለመቃኘት  እንሞክራለን፡፡  

  ማሊ – አንሳር ዲን

  እ.ኤ.አ ታኅሳስ 26 ቀን 1893 የፈረንሳይ ጦር የዛሬዋ የማሊ ጥንታዊ ከተማ ቲምቡክቱ በመግባት የፈረንሣይ ግዛት መሆኗን አወጀ፡፡ በወቅቱ የበረሃማዋ ከተማ ጥንታዊ ነዋሪዎች የፈረንሣይ ጦርን ድርጊት አሜን ብለው ሳይቀበሉ፣ እ.ኤ.አ እስከ 1917 ድረስ ሲፋለሙ ቆይተው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ጥንታዊ የአገሪቱ ነዋሪዎች ቱዋሬጎች ከበርካታ ደም አፋሳሽ ፍልሚያዎች በኋላ በፈረንሣይ ጦር በመሸነፋቸው  በፈረንሣይ አገዛዝ ሥር መተዳደር ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1960  ማሊ ከፈረንሣይ ቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ የቱዋሬግ ሕዝቦች በማሊ ሥር እንዲተዳደሩ ፈረንሣይ ማድረጓን ቱዋሬጎች አልወደዱትም፡፡ የማሊ ቱዋሬጎች በሌሎች አገሮች ከሚኖሩ ቱዋሬጎች  እንደ ናይጄሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያና ሞሪታንያ ጋር ተቀላቀለው ለመኖር ባለመቻላቸው የቁርሾው መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የሰሜናዊ ማሊ ቱዋሬጎች በድኅረ ነፃነት ዘመን የባማኮን መንግሥት ከልባቸው የተቀበሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡

  የማሊ መንግሥት የቱዋሬጎ ማኅበረሰቦችን ወደ ዘመናዊነትና በተረጋጋ የግብርና ሥራ እንዲሰማሩ ያደረገው ጥረት ይበልጥ ፈታኝ ነበር፡፡ ማሊ ከአፍሪካ አገሮች የወርቅ ማዕድን በማምረት ሦስተኛዋ ትልቋ አገር ስትሆን፣ እ.ኤ.አ በ2010  52.4 ቶን ወርቅ አምርታ ነበር፡፡ ይህ ሀብቷ ግን ለሕዝቧ ከበቂ በላይ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት 5.6 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ተቀብላለች፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በአገሪቱ የሚታየው የአስተዳደር ብልሹነትና ሙስና እጅግ የከፋ ደረጃ መድረሱ ይጠቀሳል፡፡

  በማሊ እ.ኤ.አ. በ2010 ኤችአይቪ/ኤድስ፣ ወባና የሳንባ በሽታዎችን ለመከላከል  ከግሎባል ፈንድ የተገኘ አራት ሚሊዮን ዶላር መዘረፉ በአገሪቱ የሙስና ሁኔታ በጣም የከፋ ለመሆኑ ትንሹ ማሳያ ነበር፡፡ በማሊ በአማካይ የድህነት ደረጃ 64 በመቶ ሲሆን፣ ቱዋሬጎች በሚበዙበት ሰሜናዊ ከተሞች በተለይ በቲምቡክቱ ወደ 77 በመቶ ነው፡፡ እንዲሁም በጎዋ ከተማ 78.7 በመቶ፣ በኪዳል ከተማ ደግሞ 92 በመቶ መመዝገቡ በአገሪቱ ለሽብርተኛ ቡድኑ መፈጠር ድህነትን የሚጠቅሱ ብዙ ናቸው፡፡ በመላ ማሊ መጨመሩ በተለይ ቱዋሬጎች በሚበዙባቸው ሰሜናዊ የማሊ ከተሞች ድህነቱ የከፋ መሆኑ ብሶቱን እንደጨመሩት ይነገራል፡፡ በማሊ የቱዋሬግ ማኅበረሰቦች የጎጥ ጥያቄዎች መነሻ በአገሪቱ እ.ኤ.አ ከ1963 እስከ 1964፣ 1990 እስከ 1996፣ ከ2006 እስከ 2009 እና ከጥር 2012 ጀምሮ ከመንግሥት ጋር መጋጨታቸው ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ለግጭቱ ይበልጥ መባባስ ደግሞ በአካባቢው የውጭ የእስልምና አስተምህሮ ሰባኪዎች በብዛት ወደ ማሊ መግባታቸው ነው፡፡

  በርካታ ፓኪስታናውያን ሰባኪዎች (ደዋ አልቲቢክስ) እና ሳዑዲ ዓረባውያን (ዋህቢዎች) በሕዝቡ መካከል በመግባታቸው የሃይማኖት አክራሪነቱን እንዳባባሰው ይነገራል፡፡ እነዚህ የውጭ የእስልምና ሃይማኖት ሰባኪዎች እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በማሊ ውስጥ ተቀባይነት የነበራቸውን እስላማዊ ምሁራንና የሱኒ ምሁራን ሰባኪዎችን ቀስ በቀስ ተኳቸው፡፡ የአክራሪ ኃይሉ መሪ አንሳና ዲን የማሊ መንግሥት ከአልቃይዳና ከጅሃድ አራማጅ ቡድኖች ጋር በመሆን በመፈንቅለ መንግሥት እንዲወገድ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጠሩለት፡፡ በዚያች አገር አሁንም ብጥብጡና ግጭቱ አልሰከነም፡፡

  ናይጄሪያ – ቦኮ ሐራም

   ቦኮ ሐራም የተመሠረተው እ.ኤ.አ ከ1995 ቢሆንም መነሻውን ለማየት የናይጄሪያ ቅኝ አገዛዝ ዘመን መቃኘት ይጠይቃል፡፡ ናይጄሪያ እ.ኤ.አ ከ1852 እስከ ጥቅምት 1960 በብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ሥር ነበረች፡፡ በዚህ ወቅት ብሪታንያ ናይጄሪያን በሰሜን፣ በምዕራብና በምሥራቅ በመከፋፈል የተለያዩ የአስተዳደር ዘዴዎችን በማስፈን ቆይታ ነበር፡፡ በናይጄሪያ በድኅረ ነፃነት የተመሠረተው የአገሪቱ ፌዴራል መንግሥትም ይህንኑ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት የሚያጠናክር ነበር፡፡ ይህ የመንግሥት አስተዳደር ዘይቤ የጎሳ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚና የሃይማኖት ክፍፍልን ወይም ልዩነትን ማስፋቱ ይነገራል፡፡ ናይጄሪያ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች ጀምሮ የመገንጠል ችግር ወጥሮ ይዟት ቆይቷል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ቦኮ ሐራም የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የቦርኑ ኢምፓየር በሚል ይተዳደሩ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህ ግዛት ከናይጄሪያ የቅኝ ግዛት ዘመንና በብሪታኒያ ኢምፓየር ከመቀላቀሉ በፊት ሉዓላዊ ሡልጣናዊ አስተዳደር ይከተል እንደነበር ይነገራል፡፡ ከካኔም ቦርኑ ኢምፓየር መገርሰስ ተከትሎ የቦርኑ ሡልጣናዊ አገዛዝ ለ2000 ዓመታት ዘልቋል፡፡ በወታደራዊ ድል እ.ኤ.አ. በ1802 ሶኮቱ ሰለፊስት ሀውሳ/ፉላኒ ግዛት ተመሥርቶ ነበር፡፡ የቦርኑ ሡልጣናዊ አገዛዝና ሶኮቱ ሰለፊስት ሀውሳ/ፉላኒ አገዛዝ የተለያዩ ቢሆኑም፣ እ.ኤ.አ. በ1903 በብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ሥር በአንድ ላይ እንዲተዳደሩ ተደረገ፡፡ በወቅቱ በክርስትና ሚሲዮናውያን የምዕራባዊ ትምህርትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም ወንጌልን ማስፋፋት መጀመራቸው በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ እየፈጠረ መጥቶ ነበር፡፡ ይህ ድርጊት በቀሰቀሰው ቁጣ ሳቢያ በማኅበረሰቡና በሌሎች የሰሜናዊ ናይጄሪያ ሕዝቦች መካከል ጽንፈኛ ኃይሎች እንዲያቆጠቁጡ ምክንያት እንደነበር የሚጠቅሱ አሉ፡፡

  በብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ዘመን ብሪታኒያ የአገሪቱን ሰሜን፣ ምዕራብና ምሥራቅ የተለያየ አስተዳደሮች በማዋቀር ታስተዳድር ነበር፡፡ በድኅረ ነፃነት የናይጄሪያ የፌዴራል መንግሥት ይህንኑ የብሪታኒያ አስተዳደር ሥርዓት በመውረስ ተመሳሳይ አስተዳደር መከተሉን ቀጠለ፡፡ የናይጄሪያ መንግሥታት በብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ዘመን እንደነበረው የተለያየ የመንግሥት አወቃቀርና አስተዳደር ዘዬ መከተሉን በመምረጣቸው የብሔር፣ የባህል፣ የኢኮኖሚና የሃይማኖት ክፍፍሉን የበለጠ እንዲጠናከር እንዳደረጉት አንዳንድ ምሁራን ዋቢ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡

  በናይጄሪያ  የቦኮ ሐራም ጽንፈኛ ቡድን መፈጠር ከቅኝ ግዛት ጦስ ባሻገር የተባበሰ ድህነትና ብልሹ አስተዳደር እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ የናይጄሪያ ወታደራዊ አገዛዝ እ.ኤ.አ በ1999 ሲያበቃ የአገሪቱ ፖለቲከኞች በዓመት ከአራት ቢሊዮን እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደሚበዘብሩ የተለያዩ መረጃዎች መውጣት ጀመሩ፡፡  የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ናይጄሪያ ተጠቃሚ ብትሆንም፣ በአገሪቱ በሰፈነው ሙስና ሳቢያ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ዜጎች በድህነት መዘፈቃቸው በአገሪቱ እዚህም እዚያም ግጭቶችን እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡ በአገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝ እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ ሥልጣኑን በመያዙ ምክንያት የናይጄሪያ ፖለቲከኞች ከአራት ቢሊዮን እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በዓመት እንደሚመዘበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ናይጄሪያ ከነዳጅ ምርቷ 74 ቢሊዮን ዶላር በላይ በምታገኝበት ወቅት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ናይጄሪያውያን በቀን ከአንድ ዶላር በታች ያገኙ የነበረ ሲሆን፣ ከ10 ናይጄሪያውያን አራቱ ሥራ አጥ መሆናቸው የሀብት ክፍፍሉ ኢፍትሐዊ  መሆኑን ያሳያል፡፡

  ‘‘The Failure of Counter – Terrorism Initiatives in Africa’’ በሚል ጥናት ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሁሴን ሰለሞን ከናይጄሪያ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በቀን አንድ ዶላር በታች የሚያገኝ መሆኑንና ከአሥር ናይጄሪያውያን አራቱ ሥራ አጥ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህንን እውነታ የሚያባብሰው ደግሞ በሰሜናዊ ናይጄሪያ የበረታ ድህነት መኖሩ ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ጥናት 27 በመቶ የሚሆን ሕዝብ በድህነት ሲኖር፣ ይህ አኃዝ በሰሜን ናይጄሪያ ወደ 72 በመቶ ይጨምራል፡፡ ለቦኮ ሐራም ድህነቱና ብልሹ አስተዳደሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለት የሚናገሩ አሉ፡፡ ቦኮ ሐራም እ.ኤ.አ በ1995 በማላማ ላዋላ መሪነት ‹‹ሻባብ›› (የሙስሊም ወጣቶች ድርጅት) በሚል ስያሜ ይንቀሳቀስ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ላዋላ ትምህርቱን ለመቀጠል ድርጅቱን ከለቀቀ በኋላ በመሐመድ ዩሱፍ መሪነት ጊዜ ቡድኑ ከሕዝቡ ሰፊ ተቀባይነት ማግኘቱ ይነገራል፡፡ ዩሱፍ በይፋ እ.ኤ.አ በ2002 በናይጄሪያዋ ማይዱጉሪ ከተማ በመቀመጥ በቡሩና ግዛት የሸሪአ መንግሥት የማቋቋም ዓላማ ማራመድ ጀመረ፡፡ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚረዳ ግዙፍ ሕንፃ እንዲገነባ አደረገ፡፡ እ.ኤ.አ በጁላይ 2009 ቦኮ ሐራም ከመንግሥት ጋር በፈጠረው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቱና የቀድሞ መሪው መሐመድ ዩሱፍ መገደላቸው ይታወሳል፡፡

  እ.ኤ.አ በጁላይ 2010 ቦኩ ሐራም ሁለተኛው ሰው አቡበከር ሼኩ የቡድኑ መሪ መሆኑና በይፋ የሽብር ጥቃት እንደሚያካሂድ በቪዲዮ በለቀቀው መልዕክት አሳውቆ ነበር፡፡ በዚያው ዓመት በወሩ ከአልቃይዳ ጋር ትስስር እንዳለው አውጇል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ከናይጄሪያ ከ200 በላይ ሴት ተማሪዎችን አፍኖ በመውሰድ የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በቅርቡ የናይጄሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶችን አፍኖ በመውሰድ የጎረቤት አገሮችም ሥጋት እየሆነ መጥቷል፡፡

  ኬንያ – ኢስላሚክ ፓርቲ ኦፍ ኬንያና የኬንያ ሪፐብሊካን ምክር ቤት

  ኬንያ ነፃነቷን እ.ኤ.አ. በ1963 ካገኘች ጀምሮ ሙስሊሞች በሚበዙባቸው አካባቢዎች የመገንጠል የትግል እንቅስቃሴዎች ስታስተናግድ ቆይታለች። በሰሜናዊ የኬንያ የጠረፍ ግዛት የሆነው ሞምባሳ ሶማሊያውያን በብዛት የሚኖሩበት ማዕከል ነው። ከኬንያ የጠረፍ ግዛት ‘‘ሙዋንቦ’’ (‘‘ጠረፍ” በስዋህሊ) በዓረቦችና የተወሰኑ ስዋህሊ ቡድኖች የላቀ የራስ አስተዳደር ወይም ሙሉ ለሙሉ ከኬንያ መገንጠል   ይፈልጋሉ። በኬንያ ነፃነት ማግሥት ጀምሮ ኦመኒ ዓረብና የተወሰኑ የስዋህሊ ማኅበረሰቦች የኬንያ ግዛት ውስጥ ከመጠቃለል ይልቅ፣ እ.ኤ.አ. ከ1840  ጀምሮ  የጠረፍ ግዛቱን ያስተዳድር  ከነበረው የዛንዚባር ኦማንኒ ሡልጣን አስተዳደር ሥር መጠቃለል ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል። ለዚህም የሚያቀርቡት መከራከሪያ እ.ኤ.አ በ1895  በብሪታኒያና በዛንዚባር፣ ሡልጣን መካከል በተፈረመው ስምምነት የብሪታኒያ የዛንዚባር ሞግዚት አስተዳደር (እ.ኤ.አ. 1890 የታወጀው)፣ ሡልጣኑ በጠረፉ ላይ ያለውን ሉዓላዊነት የሚነካ አለመሆኑን በግልጽ አስቀምጧል የሚል ነው።

  በእርግጥ ብሪታኒያ በኬንያ ጠረፍ ግዛት አስተዳደር ውስጥ የሙስሊም አስተዳደር እንዲካተት አድርጋ ነበር። ሡልጣን የሹመት ስያሜዎች ማለትም ‘‘ሊዋሊ”(አስተዳዳሪ) ‘ሙዲር’ ‘(የወረዳ አስተዳዳሪ) ‘‘አቂዳ’’ (የአካባቢ አለቃ) እና ‘ቃዲ” (የሃይማኖት ዳኛ) በመባል ከብሪታኒያ አስተዳደር ጎን ለጎን ያስተዳድሩ ነበር። ብሪታኒያ እ.ኤ.አ.  በ1897 መቀመጫው ማዕከላዊ ሞምባሳ የሆነ ለጠቅላላ ጠረፍ አካባቢ ቃዲ ሾማ የነበረ ሲሆን፣ ቃዲው ከየአካባቢው የሚቀርቡ ይግባኝ ጉዳዮችን ላይ ብይን የሚሰጡበት አካሄድ ነበራቸው። በወቅቱ የብሪታኒያ መኮንኖች የአስፈጻሚነት ሚና ነበራቸው።

  በኬንያ የነፃነት ዋዜማ በለንደን በኬንያውያንና በእንግሊዝ መካከል በተደረገ ድርድር ላይ፣ የኬንያ የባህር ዳርቻ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው ራሱን የሙዋምቦ ኅብረት ግንባር (Mwambao United Front) ብሎ የሚጠራው ንቅናቄ ተወካዮች ተሳትፈው ነበር። በወቅቱ የንቅናቄው ተውካዮች የባህር ዳርቻ ‘የተለየ ማኅበራዊ ቡድን” መሆናቸውን በመጥቀስ የራስ ገዝ አስተዳድር ነፃነት ውይም ከኬንያ በመገንጠል ራሳቸውን እንደ ነፃ አገር ለማስተዳድር ወይም ‘‘ዳግም” ከዛንዚባር ጋር በመቀላቀል መተዳደር እንደሚፈልጉ በፅናት ሲካራከሩ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ።

  በኬንያ የጠረፍ ዳርቻ አካባቢ ሙስሊም ነዋሪዎች የመገንጠል ፍላጎት በተለያዩ ጊዜያት መከሰቱ አልቀረም። ይህም በመንግሥትና በሙስሊሙ ማኅበረሰብ አለመተማመን ፈጥሮ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኬንያ ፅንፈኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ ሳቢያ አለመተማመኑ ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጐታል። እ.ኤ.አ. በ2010 መገንጠልን የሚያቀነቅን አዲስ የሙስሊም ጽንፈኛ በድን ‘‘ሞምባሳ ሪፐብሊካን ምክር ቤት” (Mombasa Republican Council – MRC) በሚል ስያሜ ብቅ በማለቱ የአካባቢውን ፖለቲካ ማወሳሰቡ ይነገራል። የዚህ ጽንፈኛ ንቅናቄ መሪ ራዶ ሩዋ የሚሰኝ ሲሆን፣ የቡድኑ ዓላማ የጠረፍ አካባቢ ነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልና ኬንያን ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ማላቀቅ መሆኑን መሪው ይገልጻል።

  ባላል እ.ኤ.አ. በ1958 በሞባሳ የተወለደ ሲሆን፣ አባቱ የመናዊው ሳሊም አህመድ ነበር፡፡ ባላል ቁራንና ዓረቢኛን በአካባቢው ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል፡፡ ዕድሜ አሥራ ሰባት ሲሆን፣ እስልምናዊ ግዴታውን ለመወጣት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መካ (ሐጂ) ተጓዘ፡፡ እዚያው ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ከአሥር ዓመታት በላይ በመዲና ዩኒቨርስቲ ኢስላምን እያጠና ጎን ለጎን የሃይማኖት መጻሕፍትን በመሸጥ ይተዳደር ነበር፡፡ በመቀጠልም አውሮፓና እስያን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡ በብሪታንያ የቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ ከህንድ ደግሞ እስልምናን ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር የሚያነፃፅር ጥልቅ ጥናት አካሂዷል፡፡ የእስልምናና የቢዝነስ ማኔጅመንት ዕውቀትን መገብየቱ ዕውቀቱ ‘ለመሸጥ‘ ወይም የእስልምና ሃይማኖትን ለማስፋፋት እንደሚረዳው ይገልጽ ነበር፡፡ ባላል እ.ኤ.አ በ1990 ወደ ኬንያ ተመለሰ፡፡ እ.ኤ.አ በ1992 አጋማሽ ድረስ በሞምባሳ ጭንቅንቅ ገበያ መሀል የሚሰብክ አንድ ያልታወቀ ሰባኪ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ፖለቲካዊ ዲስኩሮችን በማብዛትና መንግሥትን በመተቸት የሕዝቡን ቀልብ መሳብ ጀመረ፡፡ አንደበተ ርቱዕነቱ፣ ስለእስልምና ባለው ሰፊ ዕውቀት መንግሥትን በድፍረት በመወረፉ፣ በርካታ ሰዎች በተለይ ወጣት ሙስሊሞች ተሰባስበው በተመስጦ የሚያዳምጡት ሰባኪ ለመሆን ቻለ፡፡

  ሼክ ባላል በፕሬዚዳንት ሞይ መንግሥት ላይ በድፍረት ከመናገር ባለፈ በኬንያ እስላማዊ የፖለቲካ ሥርዓት መስፈን እንዳለበት መከራከሩን ቀጠለ፡፡ ባላል እስልምናና መንግሥታዊ አስተዳደር የተነጣጠሉ አለመሆናቸውን የሚከራከር ሲሆን፣ ፖለቲካ የሃይማኖት አካል እንደሆነ በግልጽ ይናገር ነበር፡፡ የኬንያ መንግሥት ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መደራጀት እንደፈቀደው ሁሉ ‘‘የኬንያ እስላማዊ ፓርቲ’’ (Islamic Party of Kenya – IPK) ሕጋዊ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ በማድረግና ሙስሊሞች ተደራጅተው  ጥያቄያቸውን ማንሳት እንዲችሉ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ እንዲመዘገብ መፈቀድ እንዳለበት  ይሟገት ነበር፡፡ ባላል በመንግሥት  ውስጥ የሚሠሩ ሙስሊሞችን በገዢውን ፓርቲ ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ  በመንግሥት ላይ እምነት እንዲታጣበት ይቀሰቅስ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1932 አጋማሽ ባላል ’’ኢስላሚክ ፓርቲ ኦፍ ኬንያ’’ የተባለውን እስላማዊ ፓርቲ በመቀላቀል ድርጅቱ በርካታ ደጋፊዎች እንዲያገኝ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡ ባላል ፓርቲውን ወደ ጽንፍ በመምራት ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት እንዲፈጥሩ፣ ብሎም የሞይ ሥርዓት አድልኦና ሙስና የሰፈነበት በመሆኑ መወገድ አለበት በሚል በኬንያ ውጥረት አነገሠ፡፡ በዚህ ደረጃ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ በኦዲንጋ የሚመራው የፎርድ ኬንያ ፓርቲ ኢስላሚክ ፓርቲ ኦፍ ኬንያ በፖለቲካ ፓርቲነት እንዲመዘገብ ድጋፍ በመስጠቱ እንዲጠናከር ማድረጉ ይጠቀሳል፡፡

  አንዳንድ ተንታኞች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለባላል አጋርነት ያሳዩት ያለምክንያት አልነበረም፡፡ በኬንያ ቀጣዩ የፖለቲካ አጠቃላይ ምርጫና የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለተገደቡ ‘‘ኢስላሚክ ፓርቲ ኦፍ ኬንያ’’ ድምፃቸውን መስጠት የማይችሉ ሙስሊሞች እንዲመርጧቸው የቀየሱት ዘዴ ነበር፡፡ ፓርቲው በሚያዘጋጃቸው ሠልፎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተው ነበር፡፡ የባላልና የፎርድ ኬንያ ፓርቲ ግንኙነት የተቀየረው፣ የፎርድ ኬንያ ፓርቲ መሪ ኦዲንጋ ከገዢው ፓርቲ ጋር ባደረጉት ድርድር ነው፡፡ ኦዲንጋ በፕሬዚዳንት ሞይ ላይ የነበራቸው አቋም መለሳለስ እያሳየ መምጣቱን ተከትሎ መሆኑ ይነገራል፡፡

  ባላልና የኬንያ ኢስላሚክ ፓርቲ ከሱዳን፣ ከዓረብ አገሮችና ከኢራን የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ለዘብተኛ የሞምባሳ ሙስሊሞች በኢራንና በጽንፈኛ ሙስሊም ቡድኖች ተሳትፎና ድጋፍ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መካከል ውጥረትን እያነገሠ መሆኑ ሥጋታቸውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 13 ቀን 1996 ዘ ስታንዳርድ የተሰኘው የአገሪቱ ጋዜጣ “ሽብር በኬንያ ጽንፈኝነት እየነገሠ ነው” በሚል ርዕስ ዘገባ እስከ ማውጣት ደርሷል፡፡

  የኢስላሚክ ፓርቲ ኦፍ ኬንያን በየጊዜው ከመንግሥት ጋር የሚያደርገው ግጭትና የባላል የአመፅ አካሄድ ያልጣማቸው ደጋፊዎቹ ለውጥ ለማካሄድ ጥረት ቢያደርጉም፣ በተፈጠረው ልዩነት የመጀመሪያው ከፍተኛ የሽብር ጥቃት እ.ኤ.አ በኦገስት 7 ቀን 1998  በናይሮቢና በታንዛኒያ ዳሬሰላም በሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዎች በአልቃይዳ አባላት ተፈጸመ፡፡ ይህንን በመንግሥትና በሙስሊሙ ማኅበረሰብ በተፈጠረው ልዩነት አልቃይዳ ተጠቅሞ ጥቂት ጽንፈኛ ሙስሊሞችን በመመልመል፣ በኬንያ የሽብር ጥቃት አውታር በመዘርጋት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ቻለ፡፡ የኬንያ ጦር ሶማሊያ መግባቱን ተከትሎ አልሸባብ እንደዛተው በኬንያ የባህር ዳርቻ የሚገኙ  ማኅበረሰቦችን መሸሸጊያ በማድረግ፣ ባለፈው ዓመት የሽብር ጥቃቱን በቀላሉ በናይሮቢ የዌስት ጌት የገበያ ማዕከል ጥቃት አድርሶ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ፡፡

  ሶማሊያ – አልሸባብ

  የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የነበረው ዚያድ ባሬ የሰኢድ መሐመድ ሐሰንን የዘመናት ህልም ለማሳካት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አካሄዶ ለተወሰነ ጊዜ የኢትዮጵያን ግዛት መቆጣጠር ችሎ ነበር፡፡ በኋላ በጦርነቱ ተሸንፎ ከወጣ በኋላ በውስጥ ችግር ምክንያት የዚያድ ባሬ መንግሥት መንኮታኮቱ አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነትና መከፋፈል ዳረጋት፡፡

  ‹‹ሀረካት ሸባብ አል ሙጅሃዲን›› ወይም ‹‹አልሸባብ››  ተብሎ የሚጠራው የሶማሊያ አሸባሪ ቡድን እ.ኤ.አ የካቲት 29 ቀን 2008 በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በአሸባሪ ቡድንነት ተመዘገበ፡፡ ቡድኑ እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2008 በአንድ ጊዜ  በሁለት የሶማሊያ ከተሞች አምስት የአጥፍቶ ጠፊ በመኪና ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎችን በመጠቀም 26 ሰዎች እንዲገደሉና ሌሎች 29 ሰዎች እንዲጎዱ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 በኡጋንዳ ካምፓላ በአጥፍቶ ጠፊዎች 70 ሰዎችን እንዲገደሉ ከማድረጉም በላይ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሶማሊያ፣ በታንዛኒያና በኬንያ ለተካሄዱ አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶች እጁ እንዳለበት ይታወቃል፡፡

  በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ  አውሮፕላን ጥቃት የተገደለው የአልሸባብ መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔ አው መሐመድ (ጎዳኔ) እ.ኤ.አ ከ2008 ጀምሮ የቡድኑ መሪ ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡ አብዲ ጎዳኔ በሶማሌላንድ ሐርጌሳ ውስጥ ነው የተወለደው፡፡ አብዲ ጎዳኔ የዘመኑ “ማድ ሙላህ ” በመባል ይታወቃል፡፡ ልክ እንደ ሰኢድ መሐመድ ሐሰን (Mad Mullah) በግጥምና በመሳጭ ንግግሮቹ የተዋጊዎቹን ቀልብ መሳብ መቻሉ ይነገርለታል፡፡ በአጭር ጊዜ በጎሳ የተከፋፈሉትን የሶማሊያ ወጣቶች አርበኝነት መንፈስ በመቀስቀስ ተከታታይ የሽብር ጥቃቶችን በኡጋንዳና በኬንያ ማካሄዱ ይወራለታል፡፡ በአፍሪካ ጽንፈኝነት ጥናት በማድረግ የሚታወቁት ምሁር ዶ/ር ሁሴን ሰለሞን የአብዲ ጎዳኔ መገደል ስተራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ከቡድኑ መሥራቾች መካከል ተጠቃሽ የሆነውን ጎዳኔን አልሸባብ ማጣቱ ትልቅ ጉዳት እንደሚያመጣበት ይገልጻሉ፡፡

  ዶ/ር ሁሴን አልቃይዳ በጎዳኔ አመራር የምሥራቅ አፍሪካ አውታሩን መዘርጋት እንደቻለና የጥቃት አድማሱን ማስፋቱን ያስረዳሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 የኡጋንዳን መንታ የቦምብ ጥቃቶች የመራው ጎዳኔ መሆኑን የሚገልጹት ምህሩ፣ እ.ኤ.አ በ2013 በናይሮቢ ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል አሰቃቂ የሽብር ጥቃት 67 ሰዎች እንዲገደሉ ማቀነባበሩን ይጠቅሳሉ፡፡

  ጎዳኔ  ሥልጣኑን በእሱና በታማኞቹ ብቻ እንዲያዝ በማድረጉ የዕዝ ሰንሰለቱና ቁጥጥሩ እንዲሻሻል አድርጎ ነበር፡፡ እንደ አጥኚው አገላለጽ ጎዳኔ ልዩ የኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት መፍጠሩ በአልሸባብ የሽብር ጥቃት ጥናት፣ ግድያና አጥፍቶ መጥፋት አሃዶችን ማዋቀሩ፣ ውስብስብና በበለጠ ፍጥነት ጥቃትን መፈጸም መቻሉ ተጠቃሽ ስኬቶቹ ናቸው፡፡ አምስት ሺሕ ተዋጊዎቹ በየቀኑ በአካል ብቃትና በዲሲፒሊን በማሠልጠን የተዋጊዎቹን ሰርጎ ገብ እንቅስቃሴ ማሳደጉ ይነገራል፡፡ አብዲ ጎዳኔ በሶማሊያ አልሸባብ ተዋጊዎችና የአልሸባብ የውጭ ዜጎች ተዋጊዎች መካከል የነበረውን ልዩነት በማጥበብ  ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቶ እንደነበር ይነገርለታል፡፡

  አፍሪካ ወዴት እየሄደች ነው?

  በአፍሪካ ቅኝ ገዢዎች በአገሮች መካከል በዘፈቀደ ያሰመሯቸው ድንበሮች አንድ አገርን ከሌላ አገር ሲያጋጩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ተመሳሳይ ጎሳ (Ethincity) ያላቸው ማኅበረሰቦች ቅኝ ገዢዎቹ በሚከተሉት የአስተዳደር ዘይቤ በመከፋፈላቸውና እርስ በርስ እንዳይተማመኑ በመደረጋቸው፣ በብዙ የአፍሪካ አገሮች በድኅረ ነፃነትም ጦሱ አብሯቸው መዝለቁ አልቀረም፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን ቅኝ ገዢዎች በአንድ አገር የጎሳ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የሃይማኖትና አጠቃላይ የአስተዳደር ዘይቤ ልዩነት ብሎም መቃቃርን የሚያበረታቱ ስለነበር አለመተማመኑን በቀላሉ ማጥበብ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ በድኅረ ነፃነት ዘመንም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ትርጉም ያለው ዕርምት መውሰድ ባለመቻላቸው፣ ወይም ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ችግሮቹ ውስብስብ በመሆናቸው በተለያዩ ሰበቦች የእርስ በርስ ጦርነቶች ይስተዋሉ ነበር፡፡ እንግዲህ አፍሪካ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ነው ከሽብር ጋር የተፋጠጠችው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

   

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles