ኢትዮጵያ ለመምጣት የፈለገ ቱሪስት ድረ ገጾችን ሲጐበኝ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጐንደር፣ የሰሜን ተራሮችና ሌሎችም ዕውቅ የቱሪስት መዳረሻዎችን ያገኛል፡፡ ጥምቀትና መስቀልን የመሰሉ ክብረ በዓሎችን እንዲታደም የሚያሳስቡ፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነቷን በማጉላት እንዲጐበኝ የሚጋብዙና ሌሎችም በርካታ መረጃዎች ይገኛሉ፡፡ የቱሪዝም ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ጐብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት አገሪቱን ለማስተዋወቅ በተደረገው ያላሳለሰ ጥረት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም ቱሪስቶች በግላቸው የሚያደርጉት ሙከራ ያመዝናል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ ብታስመዘግብም የመስተንግዶ ዘርፍ አለመጠናከርና ሌሎችም ችግሮች ሐብቶቹ እንዳይጐበኙ አድርገዋል፡፡
ቱሪዝሙ ማኅበረሰቡን አሳትፎ ተጠቃሚ አለማድረጉ እንደ ክፍተት ይነሳል፡፡ በእርግጥ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች ቱሪስቶችን በማስጐብኘት፣ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁስ በመሸጥ፣ ምግብና መጠጥ በማቅረብ፣ ለቱሪስቶች መጓጓዣ በማዘጋጀት በመጠኑ ይሳተፋሉ፡፡ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ እንደሚሉት ግን ተሳትፏቸው በቂ አይደለም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የኅብረተሰቡ አኗኗር የቱሪስት መስህብ በመሆኑ ነዋሪዎች በቱሪዝም ቢካተቱም በአጠቃላይ ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም ወጥነት እንደጐደለው ይገለጻል፡፡
ይህ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ማኅበረሰቡ ስለቱሪዝም ጥቅም አለመገንዘቡ እንደሆነ የሚያምኑ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከቱሪዝም የሚገኘውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማኅበረሰቡ በማመላከት ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ቱሪዝም አጠቃላይ ኅብረተሰቡን ዘንግቶ ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከሆነ ቱሪዝሙ ቀጣይነት እንደማይኖረው ያስረዳሉ፡፡
ዶ/ር ሙሉጌታ ፍሰሐ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተርና በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተመራማሪና መምህር ናቸው፡፡ ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም ላይ ያተኮሩ መጽሐፍት አሳትመዋል፡፡ ከጥናታቸው በመነሳት እንደሚናገሩት፣ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የቱሪስት መስህቦች አገር እንደመሆኗ የቱሪስቶች ቁጥር የትየለሌ መሆን ይገባዋል፡፡ ለዚህም እያንዳንዱን ሀብት በአግባቡ ማስተዋወቅና ከዚህ በተጓዳኝ ማኅበረሰቡ ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው መንገዶች መመቻቸት አለባቸው፡፡
ዶ/ር ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ መስህቦች አለመተዋወቃቸው ከዘርፉ ችግሮች ይጠቀሳል፡፡ ቅርሶች፣ ቅሪተ አካሎች፣ እንስሳት፣ እፅዋት፣ መልከዓ ምድርና ሌሎች መስህቦች የሚገኙባቸው አካባቢዎች በግልጽ መታወቅ አለባቸው፡፡ እነዚህ ቱሪስቶች በቀላሉ በሚረዱት መልኩ (በቱርጋይድ ማንዋል) ከተካተቱ በኋላ ብቁ አስጎብኝዎች መመደብ አለባቸው፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ካለው የቱሪስቶች እንቅስቃሴ አንፃር የአካባቢው ነዋሪዎች ካለመጠቀማቸው የተነሳ ቱሪስቶችን እስከመጥላት እንደደረሱ ጥናታቸው ያመለክታል፡፡
ዶክተሩ እንደሚሉት፣ ማኅበረሰቡ በቱሪዝም ከመሳተፉ አስቀድሞ ቱሪስቶች ስለ ማኅበረሰቡ እሴቶችና አኗኗር ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህም የቱሪስቶቹ እንቅስቃሴ ከነዋሪው ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲሆንና ባህሉ እንዳይበረዝ ያደርጋል፡፡
ማኅበረሰቡ በቱሪዝም ቢሳተፍም ባይሳተፍም ቱሪዝም ይኖራል፤ ሆኖም ዶክተሩ፣ ቱሪዝም ማኅበረቡን ካላሳተፈ ቀጣይነቱ አደጋ ላይ ይወድቃል ይላሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ካልተጠቀመ ቱሪስቶችን ፊት ከመንሳቱም በላይ ቅርሶችን ከመጠበቅ ቸል ማለቱ ስለማይቀር ከጊዜ በኋላ ቱሪዝም ማሽቆልቆሉ አይቀርም፡፡ ማኅበረሰቡን ማማከል የጎብኝዎችን ቁጥር እንደሚጨምርም አያይዘው ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ ቱሪስቶች ግዑዝ ቁስ ከመጎብኘት ባሻገር የማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ተካፋይ ለመሆን ይሻሉ፡፡
ዶ/ር ሙሉጌታ በቱሪዝም ስላሉ ችግሮች ተመራማሪዎች ጥናቶች ቢሠሩም በአመርቂ ሁኔታ ተተግብረው ይህ ነው የሚባል ለውጥ አምጥተዋል ለማለት አያስደፍርም በማለት፣ ቱሪስቶች ለዘመናት ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ባይካድም በዘርፉ ማኅበረሰቡን ተሳታፊ የማድረግ ፅንሰ ሐሳብ በአንፃሩ የቅርብ ጊዜ በመሆኑ ጥናቶችን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ እንዲኖር ጥሪ ያቀርባሉ፡፡
ነዋሪዎች ከዘርፉ አልተጠቀሙም ማለት ብቻም በቂ አይደለም፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በቱሪዝም ለመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንዲያውቁ የዘርፉ ባለድርሻ ተቋማት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ የባህል መበረዝ ያጋጥማል፡፡
ከ200 በላይ አባሎች ያሉት የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር በቅርቡ የዓለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው ውይይት የአገሪቱ ቱሪዝም ማኅበረሰቡን እያሳተፈ እንዳልሆነ ያመላከተ ነበር፡፡ ቱሪዝሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ ቢያስመዘግብም በተለይ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ረገድ ብዙ እንደሚቀረው ተጠቁሟል፡፡ የዶ/ር ሙሉጌታን ሐሳብ የሚጋሩት የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ አምበሉ ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡን በማማከል አልተሠራም፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተዘጋጀ ማኅበረሰብ ተኮር የቱሪዝም መርህ ለአስጎብኚ ድርጅቶች ቢሰጥም የአፈጻጸም ችግር እንዳለ ያስረዳሉ፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ችግሩ የተከሰተው ትርፍ ለማግኘት የተቋቋሙ አስጎብኚ ድርጅቶች ገቢያቸውን በሚሻማ መልኩ የማኅበረሰቡን ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነት ስለሚሰጣቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ ማኅበረሰቡን ለማሳተፍ ቅድሚያ እንደማይሰጡ ጠቁመው፣ ‹‹እውነታው ግን በዘርፉ ማኅበረሰቡ ካልተሳተፈ የቱሪዝም መዳረሻዎች አለመኖራቸው ነው፤ የቱሪዝም መዳረሻዎች ከሌሉ ደግሞ ቱሪዝም አይኖርም፤›› ይላሉ፡፡
አስጎብኚዎች የማኅበረሰቡንም ጥቅም ከግምት እንዲያስገቡ አሳስበው፣ ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትንም ያስቀመጣሉ፡፡ ቱሪዝም ከግለሰቦች አንስቶ ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና እንዳለው፣ የአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎች ከአስጎብኚዎችና ከቱሪስቶች ጋር እንደሚጋጩና መንስዔው የቱሪዝምን ጠቀሜታ ካለመረዳት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማኅበረሰቡ ሊጠቀምበት ከሚችለው መስክ አንዱ ግብርና (አግሮ ቱሪዝም) እንደሆነ ገልጸው፣ እያንዳንዱ አካባቢ ያለውን ታሪክ፣ ባህልና የተፈጥሮ አቀማመጥ ባማከለ መልኩ ሌሎች መንገዶችን መጠቀምም እንደሚቻል፣ አቶ ገዛኸኝ ያስረዳሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በፆታ፣ በዕድሜና ሥራ መስክ ከፋፍሎ እያንዳንዱ ግለሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበት አካሄድ መታቀድ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
ማኅበረሰቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ አይደለም በማለት የማይጠቀምበት አካባቢ ነው በሚል አንድ የእንግሊዝ አስጎብኚ ድርጅት ጎብኝዎችን ወደ አንዳንድ ኢትዮጵያ ቦታዎች ላለመላክ መወሰኑን አቶ ገዛኸኝ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡ መሰል አስተያየቶች ከተበራከቱ ከጊዜ በኋላ የአገሪቱ ቱሪዝም መመንመኑ አይቀርም ይላሉ፡፡
አቶ ገዛኸኝ እንደሚናገሩት፣ የአገሪቱ ሀብቶች በቅድሚያ ቢተዋወቁ የቱሪስት ፍሰቱና የሚገኘው ገቢ ያድጋል፡፡ ሀብቶችን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡን ማሳተፍም ይቻላል፡፡ አጎራባች የአፍሪካ አገሮች በጥቂት መስህቦች የቱሪስት ፍሰታቸው ከፍተኛ የሆነውም ራሳቸውን በማስተዋወቃቸውና ኅብረተሰቡን በማሳተፋቸው ነው፡፡
አቶ ሰለሞን ታደሰ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ከቀዳሚ የቱሪስቶች መዳረሻዎች አንዷ ለማድረግ አልሞ እንደሚሠራ ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቅና አዳዲስ የማግኘት ኃላፊነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰጥቶታል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የመንገድ፣ የሆቴሎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ከቱሪዝም ክፍተቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ አለማድረጉ ሌላው ነው፡፡
ቱሪስቶችን በማስጎብኘትና በአነስተኛ መደብር ቁሳቁስ በመሸጥ የሚንቀሳቀሱ ቢኖሩም ዘርፉ ከዚህ በላይ መጥቀም ይችላል፡፡ ‹‹አንድ ቱሪስት ቢያንስ ለሰባት ሰዎች የሚሆን የሥራ ዕድል መክፈት ይችላል፤›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ ምን ያህል ኅብረተሰቡ ተጠቅሞበታል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
እየተነሳሳ ያለው የኢትዮጵያ ቱሪዝም እንዲያድግ በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት በአንድነት የሚያሠራ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ገልጸው፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን ያልተገባ ፉክክር ይተቻሉ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ታዳጊዎች ቱሪስቶች ላይ ድንጋይ በመወርወር ወይም በሌላ ጥቃት ሲያደርሱ እንደሚስተዋል ተናግረው፣ እነዚህ ታዳጊዎች ለቱሪስቶች ምግብ ወይም መጠጥ እንዲሸጡ ቢደረግ ተጠቃሚ ይሆናሉ፣ ዘርፉንም ይጠብቃሉ፡፡
ድርጅቱን ከ16 ዓመታት በፊት ያቋቋሙት የተስፋ ቱር አስጐብኚ ድርጅት ባለቤት ሚስተር ማርክ፣ ከኢትዮጵያውያን እሴቶች አንዱና ዋነኛው እንግዳ ተቀባይነት በመሆኑ ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም በኢትዮጵያ በሰፊው ሊሠራበት ይችላል ይላሉ፡፡
የድርጅቱ መርህ ከቱሪስቱ አንቅስቃሴ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ በደቡብ ወሎ፣ በላሊበላ ተራሮች፣ መቄት ወረዳ፣ ላስታ፣ እንዲሁም በትግራይ በአዲግራትና ሀውዜን ወረዳዎች ይሠራሉ፡፡ በእነዚህ መዳረሻዎች እንግዳ ማረፊያዎች አዘጋጅተዋል፡፡ ማረፊያዎቹ የተሠሩት፣ የሚተዳደሩትና ከፍተኛውን ገቢ የሚያስገኙት ለአካባቢው ነዋሪዎች ነው፡፡
ማኅበረሰቡን የማካተት ሐሳብ በመነሻቸው እንደፈተናቸው ይገልጻሉ፡፡ ከዓመታት በፊት የአካባቢው ነዋሪዎች በድርጅቱ ላይ እምነትም አልነበራቸውም፡፡ ‹‹ማኅበረሰቡ በቱሪዝም ሲሳተፍ የባለቤትነት ስሜት ይሰማዋል፤ ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ ቱሪስቶችም እንቅስቃሴው ይስባቸዋል፤›› በማለት አሁን ያለውን ድባብ ይገልጹታል፡፡ ከቱሪስቶች የሚያገኙት ምላሽ አስደሳች እንደሆነና ቱሪስቶች የማኅበረሰቡን የዕለት ከዕለት ኑሮ መጋራት መቻላቸው እርካታ እንደሚሰጣቸው ይገልጻሉ፡፡
ሚስተር ማርክ እንደሚሉት፣ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ ሲደረግ የአስጐብኚ ድርጅቶች ገቢ ይቀንሳል፡፡ ቢሆንም መታሰብ ያለበት የቱሪዝሙ ቀጣይነት እንደሆነና ቱሪስቶች በሚያገኙት አቀባበል ተማርከው ተመልሰው ሲመጡ ገበያው የሚጎለብት መሆኑን ነው፡፡
‹‹ዘ ፋንዳሜንታል ኦፍ ኮሙዩኒቲ ቤዝድ ኢኮቱሪዝም ዴቨሎፕመንት ኢን ኢትዮጵያ›› የሚለው የዶ/ር ሙሉጌታ መጸሐፍ በየዘርፉ ፖሊሲ የማስተግበር፣ ማስታወቂያ የመሥራት፣ ለቱሪስቶች አመቺ ሁኔታ የመፍጠርና ኅብረተሰቡን የመጠበቅ ኃላፊነት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ በተሠራው ጥናት መሠረት ማኅበረሰቡ መሳተፍ የሚችልበት መንገድ ተለይቶ ተጠቃሚነቱ መረጋገጥም ይኖርበታል፡፡ ለማኅበረሰቡ ሥልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎች ተመድበውም የሥራው ውጤት መገምገም አለበት፡፡
ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ለቀጣይ 10 ዓመታት የሚመራበት ማስተር ፕላን ረቂቅ አዘጋጅቷል፡፡ ማስተር ፕላኑ የዘርፉን ዋና ዋና ችግሮች ከነመፍትሔዎቻቸው አስቀምጧል፡፡ የቱሪዝም ዘርፍ ማኅበረሰቡን የዘነጋ መሆኑ ተጠቅሶ፣ ችግሩ ከግንዛቤ እጥረት እንደመጣ ተገልጿል፡፡ ቱሪዝም እንደ ሥራ አማራጭና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ዜጐች በየአካባቢያቸው ያሏቸውን ሀብቶች መሠረት አድርገው መሳተፍ እንዳለባቸውም ይጠቁማል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገዛኸኝ አባተ እንደሚሉት፣ ማኅበረሰቡ ከቱሪዝሙ በአግባቡ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ ቱሪዝሙ ባሉበት ችግሮች ሳቢያ ያለበት ደረጃም ከግምት ውስጥ አይገባም፡፡ ከዘርፉ ችግሮች አንዱ የሆነውን የማኅበረሰብ ተሳትፎ ለማጎልበትም በጐንደር፣ በላሊበላና በአክሱም ኅብረተሰቡ በመስተንግዶ፣ በፀጥታ፣ ጥበቃና ፅዳት የመሳሰሉት እየተሳተፈ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡