Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየትራፊክ አደጋ

የትራፊክ አደጋ

ቀን:

በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ እየከፋ የመጣውና ለኅብረተሰቡ መቅሰፍት የሆነው የትራፊክ አደጋ ነው፡፡ አውቶሞቢልነቱ ቀርቶ ‹‹አውቶበላ›› ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን ንብረቶቸንም እየበላ ነው፡፡ ባለፈው ማክሰኞ (የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም.) ረፋድ ላይ ከስድስት ኪሎ ወደ አራት ኪሎ ያመራ የነበረ አንበሳ አውቶስ፣ ባጋጠመው እክል ሳቢያ ትምህርት ሚኒስቴርን በቀኝ ትቶ በድል ሐውልት በኩል በግራ ታጥፎ ፊት ለፊት ከሚገኘው ሕንፃ ጋር ለመላተም የበቃው፣ ሌላን ተሽከርካሪ በመግጨት ጭምር ነበር፡፡ የደረሰው የአደጋ መጠን ለጊዜው ባይታወቅም በሰው ሕይወት ላይ ያደረሰው ጥፋት ግን የለም፡፡ ከ41 ዓመት በፊት ከሽሮ ሜዳ በስድስት ኪሎ በኩል ወደ አራት ኪሎ ያመራ የነበረ 31 ቁጥር አንበሳ አውቶብስ በፍሬን ብልሽት ሳቢያ ከትምህርት ሚኒስቴር ሕንፃ ጋር ተላትሞ ሰዎችን ሙትና ቁስለኛ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

ምፀት

ሁላችንም ነን ወንድማማቾች፤

እንደቃየል እንደአቤል

እንደሁለቱ የአዳም ልጆች፡፡

…. 1965 ዓ.ም.

  • ዮናስ አድማሱ

[‘We are all brothers/Like Cain And Able’ ከሚለው የጆን ፖከር ግጥም የተተረጐመ]

* * *

ዕንቁው ሚዛን

በመልካም አስተሳሰብ የተሞላ አስተዋይ ሰው ከመናገሩ በፊት ያስባል፤ መቼ መናገርና መቼ ዝም ማለት እንዳለበትም ያውቃል፡፡ ሲናገር ‹‹በመጀመርያ ብዙ ከማውራት ይልቅ ብዙ ማዳመጥን እመርጣለሁ፡፡ መናገር ባስፈለገኝ ጊዜ ቃላቴ በከናፍርቴ በኩል ከመውጣታቸው በፊት ረጋ ብዬ እመዝናቸዋለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡

  • ዳንኤል ዓለሙ ‹‹ራስን የመለወጥ ምሥጢር›› (2005)

**********

ተጓዳኝ ፍለጋ

የወፎች ዝማሬ በድንገት ትኩረትህን ስቦት ያውቃል? የተለያዩ ዜማዎችን በማሰማት ችሎታቸው አልተደነቅህም? ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ዝማሬ የሚያሰሙት አንተን ለማዝናናት ብለው እንዳልሆነ ታውቃለህ? መዝሙሮቻቸው አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን የሚያስተላልፉባቸው ዘዴዎች ናቸው። ክልላቸውን ለማስከበር ሲሉ ዝማሬ የሚያሰሙበት ጊዜ ቢኖሩም አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚዘምሩት ተጓዳኝ ለመሳብ ሲሉ ነው። ኒው ቡክ ኦቭ ኖውሌጅ እንደሚለው ወንዱና ሴቷ አንዴ ከተገናኙ በኋላ “የመዝሙሩ መጠን እስከ 90 በመቶ ድረስ ይቀንሳል።”

ይሁን እንጂ ተጓዳኝ ለመማረክ ጥሩ መዝሙር ብቻ በቂ የማይሆንበት ጊዜ አለ። አንዳንድ እንስት ወፎች በተባዕቱ ከመሸነፋቸው በፊት “ጥሎሽ” እንዲጣልላቸው ይፈልጋሉ። ስለዚህ ዊቨርበርድ የተባለው ወፍ በጥያቄው ከመግፋቱ በፊት ጎጆ የመሥራት ችሎታውን ማስመስከር ይኖርበታል። ሌሎች ተባዕት የአእዋፍ ዝርያዎች ደግሞ እንስቷን ቃል በቃል በመቀለብ ለቤተሰባቸው መተዳደሪያ የማቅረብ ችሎታቸውን ማስመስከር ይኖርባቸዋል።

እንስሳት ሐሳብ ለሐሳብ የሚግባቡባቸው መንገዶች አካላዊ ፍላጎቶቻቸውን ከማሟላት አልፈው ብዙ ጠብ እንዳይፈጠር በማድረግ በዱር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋሉ። በእንስሳት የሐሳብ ልውውጥ ላይ የሚደረገው ምርምር እየቀጠለ በሄደ መጠን ስለ “ዱር አራዊት ጭውውት” የምናውቀው ብዙ ነገር ይኖረናል።

ንቁ! (2012)

* * *

‹‹ወደ አፌ በሉት››

ባልና ሚስት ምግባቸውን የሚያዘጋጁት በተለያየ ዕቃ ለየራሳቸው ነበር፡፡ አንድ ቀን ማታ ለራታቸው የሚሆን አጥሚት በተለያዩ ማሰሮ አዘጋጁ፡፡ ቀኑ እየመሸ ሲሄድ የከብቶቹ በር በአጉራ አልተዘጋም ነበርና፡፡ ‹‹አንተ ዝጋ›› በመባባል ተፋጠጡ፡፡ በመጨረሻ ሴትየዋ ወጥታ ለመዝጋት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ባልየው አጥሚቱን እንዳትሰርቅበት ማሰሮውን በጭንቅላቱ ተሸክሞ ወደ በሩ ሄደ፡፡

በአንድ እጁ አጉራውን በሌላ እጁ ማሰሮውን ደግፎ ለመዝጋት ሲታገል የሆነ ነገር አወላከፈውና ከበሩ ጋር ተላተመ፡፡ ትኩሱ አጥሚት በሰውነቱ ላይ ተደፍቶ ቢያቃጥለው ኡኡታውን ለቀቀው፡፡ በዚህ ጊዜ ጐረቤቶቹ ተሰብስበው አጥሚቱን ከሰውነቱ ላይ እየጠረጉ ወደ መሬት ሲፈነጥቁ ‹‹ኧረ እባካችሁ ወገኖቼ ሌላ እራት የለኝምና ወደ አፌ በሉት፤›› በማለት ሁሉንም አሳቃቸው፡፡

ክፍቱን ሲገኝማ

ውሻ እናት ቡችላዋን ትጠራና ትመክራታለች ‹‹ልጄ ስማችን እልም ብሎ ጠፋ እባክሽ ታሁን ወዲያ እንዳትሰርቂ ተሰው ድስት ድርሽ እንዳትይ አደራ፡፡ አለቻት እናት ውሻ ‹‹እሺ እንዳልሺኝ አደርጋለሁ፡፡ ግን ተከፍቶ ባገኝስ?›› ብላ ቡችላ ጠየቀች፡፡

ክፍቱን ሲገኝማ ምን ጥያቄ አለው አፍሽ ላይ እስኪያስቀምጡልሽ ልትጠብቂ ነው ታዲያ፡፡

ምን እየሠራሽ ነው?

ልጅ፡- በሕይወቴ እንዲህ ያለ ትልቅ መኪና አይቼ አላውቅም፡፡ ስፋቱ አዲስ አበባን ያክላል፡፡

እናት፡- አንተ ልጅ ነገር አታጋን ብዬ ሚሊዮን ጊዜ ነግሬህ አልሰማ አልክ አይደል?

ልጅ፡- እንዴ እማዬ አንቺስ ምን እየሰራሽ ነው?

– የሺጥላ ክፍሌ ከአዲስ አበባ

* * *

አገሮችና አሸባሪዎቻቸው

ኢራቅና ሶሪያ – አይኤስ

አፍጋኒስታን – አልቃይዳ

ናይጄሪያ – ቦኮሀራም

ሶማሊያ – አልሸባብ

ኢትዮጵያ – ሲኖትራክ (ሲኖጭራቅ)

  • ከድረ ገጽ

* * *

አታድርስ!

መዝጊያዋን ቆርቁሮ

ድምፅዋን ባታሰማ፤

ሽቶና ጠይቆ ቆንጆ ብታቅማማ፤

በሌሊቱ ግርማ፡፡

በጠራራ ፀሐይ ባደባባይ ወጥቶ፤

ድምፁን ከድምፅ ይልቅ ሺሕ ጊዜ አጣፍጦ፤

‹‹ቆዳዬም የገፈፍ፤

‹‹ይሁንልሽ ጫማ፤

‹‹እኔ ምን ቸግሮኝ፤

‹‹ላንቺ ከተስማማ፡፡››

ብሎ አንቆረቆረ፤

የጊዜውን ዘፈን፤

የዘመኑን ዜማ፡፡

…1965 ዓ.ም. ለዓለማየሁ እሸቴ

  • ዮናስ አድማሱ፣ ‹‹ጉራማይሌ›› (2006)

**********

 

ቲኬት ለመቁረጥ

ስኮትላንዳዊው በአሜሪካ አገር ሳለ በባቡር መጓዝ ስለፈለገ ቲኬት መሸጫ ሄዶ ወደ ስፕሪንግፊልድ የሚያደርሰውን ቲኬት ዋጋ ይጠይቃል፡፡

‹‹የትኛው ስፕሪንግፊልድ ነው የሚሄዱት ጌታው? ሚዙሪ ግዛት፣ አሃዮ ወይስ ማሳቹሴትስ?››

‹‹ከሁሉም ርካሹ የትኛው ነው?››

**********

በኑዛዜው መሠረት

አንዱ ሀብታም ሲሞት ለእንግሊዛዊ፣ አየርላንዳዊና ስኮትላንዳዊ ወዳጆቹ ለእያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ፓውንድ ሲያወርሳቸው ድንገት ሰማይ ቤት ካስፈለገው ግን እያንዳንዳቸው አንድ መቶ ፓውንድ የሬሳ ሳጥኑ ውስጥ እንዲከቱ አዘዛቸው፡፡ በታዘዙት መሠረትም እንግሊዛዊውና አየርላንዳዊው መቶ፣ መቶ ፓውንድ የሬሳ ሳጥኑ ውስጥ ከተቱ፡፡ ስኮትላንዳዊው ግን የነሱን ሁለት መቶ ፓውንድ አውጥቶ ከወሰደ በኋላ የሦስት መቶ ፓውንድ ቼክ ጽፎ ሳጥኑ ውስጥ ከተተለት፡፡

  • አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...