Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልዓድዋ ሲታሰብ

ዓድዋ ሲታሰብ

ቀን:

. . . አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል . . . . በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ . . . ያገሬ ሰው . . . ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡ . . .

ይህ ኃይለ ቃል ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሕዝቡንና የየአካባቢውን መኳንንትና ገዢዎች በኢጣሊያ ላይ ያነሳሱበት የክተት አዋጅ ነበር፡፡ በዚህም አዋጅ መሠረትም ከ119 ዓመታት በፊት፣ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ድል ተመቶበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን እርመኛ አርበኞች በጠቅላይ አዝማቹ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አማካይነት ሕያው ታሪክ ያስመዘገቡበት ዓድዋ፡፡

ነገ፣ የካቲት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ  ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይከበራል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት መናገሻ ከተማ በአዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው ዳግማዊ ምኒልክ ሐውልትና አደባባይ እንደሁሌም በልዩ ሥነ ሥርዓት እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ታሪኩ

በ1888 ዓ.ም. ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ሕልሟን እውን ለማድረግ በተነሣች ጊዜ ሰበበ ጦርነት የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡ በአንቀጽ 17 በኢጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ጥብቅ ግዛት ነች፤ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል የሚለው የተጭበረበረ ሐረግ ነበር ፍልሚያ ውስጥ የከተታቸው፡፡

ኢትዮጵያውያንም የውስጥ ችግራቸውን ወደጎን ትተው ከየማዕዘኑ ተጠራርተው በአፄ ምኒልክ መሪነት ከፍልሚያው አውድማ ተሰለፉ፡፡ በታሪክ ጸሐፊው በአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አገላለጽ፣ የኢጣሊያንንም ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ዠመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ፡፡ ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት፡፡

የ1ኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ራአዮ ከሚባለው ስፍራ ላይ ሆኖ፣ ካራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንዲ እዚያው እጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ፡፡

ከዚህም በኋላ በመጨረሻ ያለው የኢጣሊያ ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ስፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ፡፡ ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከኢጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር የቀለጠፉ ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ ኢጣሊያኖች ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ በጉብዝና ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ወድቆ ባንዲት ጠብታ ውሃ ማነው አፌን የሚያርሰኝ እያለ እንደ ተኮነነው ነዌ ሲጮኽ ጥቂት ቆይቶ ሞተ፡፡

«ጣልያን ገጠመ ከዳኛው ሙግት

አግቦ አስመስለው በሠራው ጥይት

አሁን ማን አለ በዚህ ዓለም፣

ጣልያን አስደንጋጭ ቀን ሲጨልም

ግብሩ ሰፊ ነው ጠጁ ባሕር

የዳኛው ጌታ ያበሻ ባሕር»

ተብሎም ስለዓድዋ ድል ስንኞች ታሰሩለት፡፡

የታሪክ ጸሐፊው ቤርክሌይ ስለ ዓድዋ ዐውደ ውጊያ የጻፈውን ጳውሎስ ኞኞ «ዐጤ ምኒልክ» ብሎ ባሳተመው መጽሐፉ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

«ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮጳ ጦር በአፍሪቃ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ በኩል 25,000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ . . . አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፡፡»

የዓድዋውን ጦርነት ከመሩት የጦር አዛዦች መካከል እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ይገኙበታል፡፡

የዓድዋ ጦርነት ሲነሳ ሁሌም የሚነሳው ባሻዬ አውአሎም ሐረጎት ነው፡፡ በስለላ ሙያው ተጠቅሞ የኢጣሊያን የጦር እቅድ በማሳከር አኩሪ ተግባር አከናውኗል፡፡ የባዕዳኑ አገልጋይ የነበረው አውዓሎም በቁጭት በመነሳሳትና በብላታ ገብረእግዚአብሔር ጊላ አማካይነት ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር ይገናኛል፡፡

እንደ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ጽሑፍ ራስ መንገሻም ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ይገናኙና የጦርነቱ ጊዜ ሲቃረብ የተሳከረውን እቅድ ለዤኔራል ባራቲየሪ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡

አውዓሎምና ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ከኢጣሊያውያን ተለይተው ወደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ገብተው ጦርነቱ ሲፋፋም ከኢጣሊያ መኰንኖች አንዱ ነገሩን ተገንዝቦ «አውዓሎም አውዓሎም» እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምቶ፣ «ዝወአልካዮ አያውዕለኒ» (ከዋልክበት አያውለኝ) ብሎ አፌዘበት ይባላል፡፡

ኪነ ጥበብ

የዓድዋ ድልን አስመልክቶ በተለያዩ የጥበብ ሰዎች የተሠሩ ኪነጥበብ ተኮር ሥራዎች በፊልም፣ በተውኔት፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ግጥም፣ በቅኔ ወዘተ. የቀረቡት በርካታ ናቸው፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር ኘሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ «ዓድዋ» በሚል መጠሪያ የደረሰው ፊልም በበርካታ ታሪካዊ ፎቶግራፎች የታጀበ ነበር፡፡ በተውኔት ዘርፍ ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ነፍስ ኄር ጸጋዬ ገብረመድኅን «ዓድዋ» ከተሰኘውና በ1964 ዓ.ም. ከደረሰው ግጥም ሌላ አሜሪካ ውስጥ ለእይታ የበቃው «ምኒልክ» ተውኔት ዓድዋን ያጎላበት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩዋን በ1979 ዓ.ም. ስታከብር ታዋቂው የቴአትር ዳይሬክተር አባተ መኩሪያ በአጋጣሚው የዓድዋውን ዘመቻ ክተት የሚያሳይ ትርኢት ‹‹ክተት ወደ ዓድዋ ዘመቻ›› በሚል ርእስ አሳይቶ ነበር፡፡ ይኸው ታዋቂ አርቲስቶችን ጨምሮ 4000 ሰዎች የተሳተፉበት ትርኢት በምስል ተቀርፆ በየጊዜው በቴሌቪዥን መስኮት ከመታየት አልተቋረጠምም፡፡ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ካለፉ በኋላ የታተመው «ዓድዋ» ተውኔታቸውም ይጠቀሳል፡፡ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የ‹‹ጥቁር ሰው›› ዓድዋ ተኮር ቅንቀናውም የቅርብ ዘመን ሥራ ነው፡፡

«! . . . ያቺ ዓድዋ» የጸጋዬ ገብረመድኅን «እሳት ወይ አበባ» ከተሰኘው የሥነ ግጥም መድበሉ ውስጥ የሚገኝ ስለ ዓድዋ የዘከረበት ነው፡፡ ከፊሉ እነሆ፡፡

. . . . ዋ!

ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ

የደም ትቢያ መቀነትዋ

በሞት ከባርነት ሥርየት

በደም ለነፃነት ስለት

አበው የተሰውብሽ ለት፤ . . .

ሲያስተጋባ ከበሮዋ

ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ

ያባ መቻል ያባ ዳኘው

ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው

ያባ በለው በለው ሲለው

በለው – በለው – በለው!

       ዋ! . . . ዓድዋ . . .

ሥነ ሥዕልን በተመለከተ ድሉን የሚያሳዩ በተለያዩ ሠዓልያን የተሣሉ ባህላዊና ዘመናዊ ሥዕሎች የመኖራቸውን ያህል ኢጣሊያናውያንም የምኒልክን ታላቅነትና ድል አድራጊነት፣ የክሪስፒን ተሸናፊነትና ውድቀት የሚያሳይ የካርቱን ሥዕል አሰራጭተዋል፡፡ ሥዕሉ በ«ለ ፐቲት ጆርናል» የታተመ ሲሆን፣ ምኒልክ ክርስፒን በታላቅ ዱላ ሲጎሽሙትና ሲጥሉት ያሳያል፡፡

የዓድዋ ጦርነት ድልን በሥዕል በመግለጽ በኩል የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊዎች ዓይነተኛ ሚና እንደነበራቸው ይገለጻል፡፡ ‹‹Ethiopian Paintings on Adwa›› በሚል ርእስ ጥናት የሠሩት በሙኒክ አትኖሎጂካል ሙዚየም የኢትዮጵያ ክፍል ኃላፊ የነበሩትና በቅርቡ ላበረከቱት ሁለገብ አስተዋጽኦ ከጀርመንም ሆነ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሽልማትና ዕውቅና ያገኙት አቶ ግርማ ፍሥሐ፣ ትውፊታዊ ሠዓልያኑ የዓድዋውን ድል በሥዕላቸው የዘከሩበት መንገድ ለኢትዮጵያ ባህላዊ አሣሣል ዕድገትን አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሥዕሎች የዐፄ ምኒልክ አማካሪ በነበሩት አልፍሬድ ኢልግ ስብስብ ውስጥ በስዊዘርላንድ ሲገኙ፣ የሆልትዝ ስብስብ በበርሊንና የሆፍማን ስብስብ በዋሽንግተን ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1905 አካባቢ የተሣሉት ከነዚህ ሥዕሎች መካከል የአለቃ ኤሊያስ፣ የአለቃ ኅሩይና የፍሬ ሕይወት ይገኙበታል፡፡

በሥዕሉ ጐልተው ከሚታዩት ከጠቅላይ አዝማቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በተጨማሪ አዝማቾች፣ መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ፣  ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዝማሪዎች መካከልም አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ የሚያሳይ ሥዕልም የዘመኑ ትሩፋት ነው፡፡

አዝማሪዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት ይሰጡት የነበረው ወኔ ቀስቃሽ አዝመራ ጉልህ ነበር፡፡ ስለነዚያ አዝማሪዎች ቤርክሌይ ከጉዞው ጋር አያይዞ የጻፈው የሚጠቀስ ነው፡፡

«. . . በሠራዊቱ መሀል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ፡፡ በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ አብሮአቸው የሚጓዘው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሩዋቸዋል፡፡ አዝማሪዎቹ የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ»

‘ወንድሜ ራበህ ወይ? ወንድሜ ጠማህ ወይ

አዎን የናቴ ልጅ እርቦህ ጠምቶሃል

ታዲያ የናቴ ልጅ አዳኝ ወፍ አይደለህም ወይ?

ግፋ ብረር ወደፊትህ ሂደህ ጠላትህን አትበላም ወይ?

ግፋ ወደፊት ከበዓሉ ቦታ ፈጥነህ ድረስ

የምታርደውን ሥጋ የማቆራርጥልህ እኔ ነኝ

ግፋ የናቴ ልጅ ውሃ ጠምቶሃል

ጠጅ ብታጣ ደሜን እንድትጠጣ እሰጥሃለሁ’

ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም. ሌሊት ለእሑድ 23 አጥቢያ ወታደሩ እየሸለለ አዝማሪዎችም ማዘመር ጀመሩ፡፡

«ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ

        በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ» ይሉ ነበር፡፡

ለጦር አዝማቾችም ማንቂያም ተገጥሟል፡፡

‹‹ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ

አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ፡፡

እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው

አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው፡፡

ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ እይ

አክሱም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ፡፡

ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት

       ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት፡፡››

የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበት ዕለት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ትውፊት መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ ከቀደመው ጊዜ አንስቶ እስካሁን «ጠባቂ ቅዱስ» (ዘ ፓትረን ሴንት) ተብሎ ይታወቃል፡፡ እስከነ ዝማሬውም

«የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከምኒልክ ጋር አብሮ ሲቀድስ፤

ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ

ጣልያንን ድል አደረጉ ደም እያፈሰሱ» እየተባለ እስካሁን ይዘመራል፡፡

የዓይን ምስክር

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በዓድዋው የጦር ግንባር በመሰለፍ ያዩትን በሕይወት ታሪካቸው ጽፈው አቆይተውልናል፡፡

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ሳምንታት የአካባቢው እረኞች ሲጫወቱ ደበሎ እየሰቀሉ አዋጅ ይናገሩ እንደነበር አዋጁንም ጠቅሰው ለዘመናችን አድርሰውልናል፡፡  «እሽ ስማ ብለውሃል መስማሚያ አይንሣህ

«ያድባርን ያውጋርን ጠላት…

«ሐማሴንን ለራስ አሉላ፣ አጋሜን ተምቤንን ለራስ ስብሐት፣ እንደርታን ዋጀራትን ለደጃዝማች ሐጎስ፣ እንዳመኾኒ ሰለሞንን ለፊታውራሪ ተክሌ፣

«ዋድላን ደላንታን ለፊውታራሪ ገበየሁ፣ ሰጥቻለሁ ብለውሃል! ይበጅ ያድርግ፤

«በየካቲት ጣጣችን ክትት

«በመጋቢት እቤታችን ግብት

«በሚያዛሳ ያገግም የከሳ

«ይበጅ ያድርግ…» እያሉ ይተነባሉ፡፡

የሰው ብዛት እንደ ጎርፍ ሆነ፡፡ እግረኞችም በቅሎኞችም ተደባልቀን እንርመሰመሳለን፡፡ ፈረሰኞች በጎን እያለፉን ይቀድማሉ፡፡ ይሮጣሉ! እንደተቻለን እንሽቀዳደማለን፡፡

ጠመንጃ ሲንጣጣ ሰማን፣ መድፍ ወዲያው ያጓራ ጀመር፡፡ ተኩሱ እያደር እየባሰበት ተቃረበን፣ ዐረሮቹ ማፏጨት ጀመሩ፡፡ የቆሰሉ ሰዎች ተቀምጠው አገኘን፡፡ አያ ታደግ እጁን ተመትቶ ከመንገዱ ዳር ከዛፍ ሥር ተቀምጧል፡፡ ገና በሩቁ አይቶን ተጣራ፣ ቁስሉን በመቀነቱ አሰርንለት፡፡ ጥለነው እንዳንሄድ ለመነን፣ ፈይሣ ጠመንጃ የለውም፤ የቁስለኛውን ጠመንጃ ተሸከመና እዚያው ቀረ፡፡ እኔ ዝም ብዬ ወደ ግምባር አለፍኩ፡፡ የማውቀውን ሰው አንድም አላጋጠመኝም፡፡ ተኩስ ስለበዛ መሮጥ የማይቻል ሆነ፡፡ የሰውም ብዛት እንደልብ አያስኬድም፡፡

ደጃዝማች ማናዬ እና ልጅ አስፋው (ልጃቸው) ሁለቱም ቆስለው ድንጋይ ተንተርሰው ተጋድመው አገኘኋቸው፡፡ ልጅ አስፋው (በኋላ ፊታውራሪ አስፋው) አወቀኝና ጠቀሰኝ፡፡ ዝም ብዬው እንዳላየ ሰው ወደ ግምባር ሮጥኩ፡፡ ጦራችን ተደባልቋል፡፡ ሰውና ሰው አይተዋወቅም፡፡ ሴቶች ገምቦ ውሃ እያዘሉ፣ በበቅሎቻቸው እንደተቀመጡ፣ ለቁስለኞች ውሃ ያቀርባሉ፡፡ ሲነጋገሩ ሰማኋቸው፡፡ «ኧረ በጣይቱ ሞት» ይላሉ፡፡ እቴጌ የላኳቸው ይሆናሉ እያልኩ አሰብኩ፡፡

ነጋሪቱ ከግምባርም፣ ከጀርባም፣ ከቀኝም ከግራም ይጎሸማል፡፡ የተማረኩ ጣልያኖችን አየሁ፡፡ ወዲያው ምርኮኞቹ በዙ፣ አንዳንዶቹ ወታደሮች፣ ይበልጡን ጣልያኖችን እየነዱ መጡ፡፡ በኋላ የምርኮኞች ብዛት ለዐይን የሚያሰለች ሆነ፤ ድል ማድረጋችንን አወቅሁ፡፡ ጣልያኖች መዋጋታቸውን ትተው ማርኩን እያሉ ይለምናሉ፡፡ እንደዚህ የአድዋ ጦርነት ዕለት አንድ ጥይት እንኳ ሳልተኩስ ጦርነቱ አለቀ፡፡

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ከድል በኋላ የጣልያኖች ሰፈር በኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ሥር ሲወድቅ ዘማቹ ንብረቱን መቃራመቱ ያስታውሳሉ፡፡ ከጣሊያን ዕቃዎች ትኩረታቸውን የሳበው ሰነዶቹ ነበሩ፡፡ እንዲህም ይላሉ:-

ከወረቀቶቹ መካከል ሥዕል የተሳለባቸውን አየሁና «ትላልቆቹን እየመረጥኩ ሰበሰብኳቸው፡፡ በቀለም (በቀይ፣ በሰማያዊ፣ በሃምራዊና በቢጫ፣ በቅጠልማ፣ በአረንጓዴ) የተሣሉ ናቸው፡፡ ባንደኛው ወረቀት ላይ የጃንሆይን መልክ አወቅሁት፡፡ በሌላው ላይ የራስ መኮንን መልክ አገኘሁት፤ ደግሞ የሴት መልክ አገኘሁ፤ ሴትቱ ባለሹሩባ ነች፤ ጥልፍ ቀሚስ ለብሳለች፤ ባንገቷ ላይ ማተብ፣ በማተቡ ላይ መስቀል፣ ቀለበቶች፣ ሌላም ጌጥ አድርጋለች፡፡ ኩታ ደርባለች፤ ቆንጆ ትመስላለች፤ ጥርሶቿ ከከንፈሮቹዋ ውጪ ብቅ ብለው ይታያሉ፡፡ ጃንሆይና እቴጌ ጥርሰ ገላጣዎች ናቸው እየተባለ ሲታሙ እሰማ ነበር፡፡ ከቶም በጉርምስነታቸው በገና ጫወታ ላይ የተገጠመባቸውን ሰምቼ ነበር፡፡

«ዘመዳዬ ዘመዳዬ

በሰማይ የጠደቀ በምድር ያስታውቃል

አቤቶ ምኒልክ ዘመዳዬ

ተከንፈሩ ተርፎ ጥርሱ ጣይ ይሞቃል

ዘመዳዬ አይክፋህ አብዬ

ዘመዳዬ ጨዋታ ነው ብዬ፡፡»

እየተባለ ተገጥሞባቸዋል ይላሉ፡፡ በመላ እቴጌ ሳይሆኑ አይቀሩም አልኩና የሴትዬዋን ሥዕል አነሣሁት፡፡ የሌሎችም ሰዎች መልክ ብዙ አገኘሁ፡፡ እኔ አላውቃቸውምና ትላልቆቹን ሥዕሎች ብቻ እየመረጥኩ ሰበሰብኳቸው፡፡ በወረቀት ጠቀለልኩና በገመድ አሰርኩና ሸክሜን አሳምሬ አሰናዳሁ፡፡ እንደዚህ ሳሰናዳ አንድ ወታደር ባጠገቤ ሲያልፍ አየኝና ጠየቀኝ፡፡

«ምን ያደርግልኝ ብለህ ይህን የሰይጣን ምስል ትሰበስባለህ? ይልቅ ስንት ደህና እቃ ሞልቶልህ የለም» አለኝ፡፡

«እጫወትበታለሁ ያምራል» አልኩት፡፡

«የልጅ ነገር» እያለ እያልጎመጎመ ትቶኝ ሄደ፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ያገኟቸውን ፎቶግራፎች ለራስ መኰንን ቆይቶም ለአፄ ምኒልክ እንዳሳይዋቸው በትዝታቸው ውስጥ ተካቷል፡፡ የዓድዋውን ድል ውጤትም እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡

እንደዚህ ዓድዋ ላይ ያን ያህል ሰዎች ተላለቁና፣ ጣልያን የወሰደብንን አገር ሳናስለቅቅ ሄድን፡፡ ይህን ነገር በዚያን ጊዜ ልመለከተው አልቻልኩም ነበር፡፡ የድሉን ዋጋ ለመገመቻ የበቃ ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ በአውሮፓ መማር ከጀመርኩ በኋላ እያስታወስኩት እንደ እሳት ያቃጥለኝ ጀመር፡፡

ራስ መኰንንና ዐፄ ምኒልክ በዘመናቸው የሠሩ ሥራ ሊደነቅላቸው የተገባ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ስሕተታቸውን በኋላ እየገመትኩት መገረሜ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የዚያን ጊዜ ዕውቀትና ኃይል በማነሱ ይቅርታ ሊደረግላቸው የተገባ ነው፡፡ እነሱ በደከሙበት ሥራ ተጠቅመናል፡፡ በስሕተታቸውም አደጋ ተቀብለንበታል፡፡ እኛም ደግሞ በተራችን እንደዚሁ ማድረጋችን አይቀርም፡፡

የኢጣልያንም መንግሥት የዚያን ጊዜ ዕወቀቱና ኃይሉ ትንሽ ነበር፡፡ ስለዚህ እሱም ያደረገው ስሕተት ከኛ የበለጠ ነው፡፡ ስለዚህ ድል ተመታ፡፡ ግን በኛ ስሕተት አገር በእጁ እንደሆነ ስለቀረ፣ 50 ዓመት ያህል ቆይቶ ተሰናድቶ አጠቃን፣ መንግሥቶች ምንጊዜም ፖለቲካቸውን ማሰናዳታቸውን አይተውም ያንኑ ይተማመኑታል፡፡ ነገር ግን፣ ፖለቲካ ለጊዜው ተፈፃሚ መስሎ ቢታይም የመጨረሻውን ፍጻሜ ከፈጣሪ በቀር ማንም ሰው ሊያውቀው አይችልም፡፡ በዓድዋው ዘመቻ የሴቶች ተሳትፎ በወሳኝነት ይታወቃል፡፡ ከእቴጌ ጣይቱ አንስቶ እስከ ታች ድረስ የነበሩት አገልግሎታቸው ለድሉ ስኬት ያስጠቅሳቸዋል፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርይት በነበሩበት ዐውደ ግንባር የታዘቡትን እንዲህ ጽፈውታል፡፡

ሴት አገልጋይ የተባለችው (የቤት ውልድ ነች ወለተ አማኔል የእንኮዬ ወለተ ማርያም ልጅ ከኛው ጋር ያደገች ነች) ከዘመቻው ላይ በጣም አገለገለች፤ ከቶ እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፡፡ እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያስደንቀኛል፡፡ እቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች፡፡ ከሰፈርን በኋላ ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች፡፡ ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች፡፡ እንደዚህ የወለተ አማኔልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል፡፡

የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት፣ ደግሞ የበቅሎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል፡፡ በመጨረሻው ድምሩን ስገምተው፣ የዓድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል፡፡

ሁሉንም አያይዤ በደምሳሳነት ስመለከተው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ነፃነቱን ጠብቀው እዚህ አሁን አለንበት ኑሮ ላይ ያደረሱት፣ እነዚህ የዘመቻ ኃይሎች መሆናቸውን አልስተውም፡፡ ታዲያ ራሴ ለራሴ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባለው ተቋም ላገልጋዮቹ ውለታ መላሽ ሆኗል ወይ? የዚህን አመላለስ ለመስጠት ላስበው፣ እልቅ የሌለው መንገድ ይገጥመኛል፡፡ ሲሄዱ መኖር ይሆንብኛልና የማልዘልቀው እየሆነብኝ፣ እየተከዝኩ እተወዋለሁ፡፡ የዕለቱን፣ ያሁኑን ብቻ ለማሰብ ባጭሩ እታገዳለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ድኩምነቴን ይመሰክራል፡፡

ከዓድዋ መልስ

የዓድዋ ጦርነት ካበቃ በኋላ ድል አድራጊው ሠራዊት ወደ የመጣበት አካባቢ ሲመለስ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ሠራዊታቸውን ይዘው አዲስ አበባ የገቡት ግንቦት 15 ቀን 1888 ዓ.ም. ነበር፡፡ የመዲናው ሕዝብ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ አቀባበል ሲያደርግ፣ መድፎችም የደስታ ድምፅን አስተጋብተዋል፡፡

ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ በእማኝነት እንደጻፉትም፣ የእንጦጦ ማርያምና የራጉኤል፣ የሥላሴና የዑራኤል እንደዚሁ የጊዮርጊስ ካህናት ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው፣ በጃንሜዳ ተሰብስበው፣ «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፣ ተሐጺባ በደመ ኢጣልያ» መሬቷ በኢጣልያ ደም ታጥባ ፋሲካ (ደስታ) አደረገች የሚለውን ጠቅሰው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት አሸበሸቡ፡፡

አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ «ዐፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት» በተሰኘው መጽሐፋቸው የጐጃሙ ሊቅ መምህር ወልደ ሥላሴ እንደመልክ አድርገው ለአፄ ምኒልክ በግእዝ ደርሰው ያበረከቱት የደራሲውን ሊቅነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካውንም የጦርነቱንም ታሪክ በትክክል የተከታተሉት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ሰላም ለአፉከ ለፈጣሪ ዘየአኵቶ

ኢይትናገር ስላቀ ወኢይነብብ ከንቶ

ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ማኅቶቶ

ኃልቀ ማንጀር  ወስዕነ ፍኖቶ

ዤኔራል ባራቲዬሪ ሶበ ገብዓ ደንገፀ ኡምቤርቶ፡፡››

(ሰላም ፈጣሪን ለሚያመሰግነው አፍህ

ስላቅ ለማይናገረው፣ ከንቱ ነገር ለማያወጋው አፍህ

ሰላም ይሁን፡፡

ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ብርሃኗ

ማዦር ማለፊያ መንገድ አጥቶ አለቀ

ዤኔራል ባራቲዬሪ ወደርሱ በተመለሰ ጊዜ ኡምቤርቶ ደነገጠ፡፡)

ለዳግማዊ ምኒልክ ለእቴጌ ጣይቱ ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ የተደረሰው የአማርኛ ግጥም ብዙ ነው፡፡ የአብዛኞቹ ገጣሚዎች ስም አይታወቅም፡፡ ከነዚያ መካከል አቶ ተክለጻድቅ የሚከተለውን ይጠቅሳሉ፡፡

ዳግማዊ ምኒልክን ከትልቁ እስክንድር በክንፋማ ፈረስ ወደ ሰማይ ወጣ ከተባለው ጋር በማመሳሰል የተደረሰው ቅኔ እነሆ

«የዳኛው አሽከሮች እየተባባሉ

ብልት መቆራረጥ አንድነት ያውቃሉ

ዓድዋ ከከተማው ሥጋ ቆርጠው ጣሉ፡፡

የእስክንድር ፈረስ መቼ ተወለደ

የምኒልክ ፈረስ በክንፎቹ ሔደ»

 

ታላቁ ባለቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ዘመን ተሸጋሪ በሆነው ግጥማቸው የኢትዮጵያውያንን ኅብረ አንድነት እንዲህ አመሠጠሩት፡፡

‹‹አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣

ጎበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፣

ስመኝ አድሬያለሁ ትናንትና ዛሬ፣

ጎበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ።

ተሰበሰቡና ተማማሉ ማላ፣

አሉላ ተትግሬ ጎበና ተሸዋ፣

ጎበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ፣

አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ፣

አገሬ ተባብራ ታልረገጠች እርካብ

ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ።››

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...