Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በቴሌቪዥን የሕወሓትን 40ኛ ዓመት የልደት በዓል አከባበር ከመቀሌ በቀጥታ ሲተላፍ እያየሁ ሳለ፣ ልብን የሚሰብር አንድ አሳዛኝ ነገር አየሁ፡፡ ሕወሓት ለትግል አነሳስቷቸው በረሃ ከወጡ በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮች አፅም ከያለበት ተሰባስቦ ወደ ቀብር ሲወሰድ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ እኔን ወደኋላ ሰላሳ ዓመታት ወሰደኝ፡፡   

በ1976 ዓ.ም. ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተመርቄ በ1977 ዓ.ም. ሥራ የጀመርኩት መቀሌ ዓፄ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ እኔ ተወልጄ ካደግኩባት አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣሁት ወደ ትግራይ ስለነበር፣ እንኳን እኔ ወላጆቼ ጭምር ደስተኛ አልነበሩም፡፡ አንዳንድ ጓደኞቼ የተሰናበቱኝ ወደ ጦር ሜዳ እንደሚሄድ ወታደር ነበር፡፡ ነገር ግን መቀሌ ስደርስ እንደፈራሁት አልነበረም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የነበረው ድርቅና ረሃብ ግን አሰቃቂ ነበር፡፡ ከሥራ ባልደረቦቼና ከማስተምራቸው ወጣቶች ጋር ወዲያው ተግባብቼ ቤተኛ ሆንኩ፡፡

በወቅቱ በተለይ በኤርትራ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ጦርነት ይካሄድ የነበረ ሲሆን፣ በትግራይ በርካታ ሥፍራዎችም ሕወሓት ከደርግ ጋር ይዋጋ ነበር፡፡ ከሥራ ባልደረቦቼም ሆነ ከተማሪዎቼ ጋር በሚደረገው የለሆሳስ ውይይት፣ ብዙዎቹ ለትግሉ ልባቸው የሸፈተ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤት ተከራይቼ የምኖርበት ግቢ ባለቤት የቀበሌ ሊቀመንበር የነበሩ ቢሆንም፣ ካደረግነው ውይይት ለመረዳት የቻልኩት ልባቸው ከበረኸኞቹ ጋር ነበር፡፡ እኔ ለአገሩ እንግዳ ለሕዝቡ ባዳ ብሆንም ገራገር መሆኔን በማወቃቸው የልባቸውን ያን ያህል አይደብቁኝም ነበር፡፡

- Advertisement -

አንዳንዴ ከከተማ ወጣ ብዬ ከጓደኞቼ ጋር ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ስንሄድ፣ ልጆቻቸው በረሃ የገቡ እናቶች የነበረባቸው ትካዜና ሰቀቀን ዓይናቸው ላይ ይታይ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የበረሃ ወሬ ሲጀመር እናቶቹ ሳይቀሩ ልባቸው በኩራት ተሞልቶ በወኔ ሲናገሩ ያስገርሙ ነበር፡፡ መቀሌ ከተማ አገኛቸው ከነበሩ የአዲስ አበባ ልጆች የሆኑ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹሞች ጋር ሳወራ ደግሞ በጦርነት መሰላቸታቸው በግልጽ ይነበብ ነበር፡፡ ይህንን እያሰብኩ የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ሲያብሰለስለኝ በሱዳን አድርገህ ጥፋ ጥፋ ይለኝ እንደነበር አሁንም አልረሳውም፡፡ የአንዲት አገር ልጆች ባለመስማማት ምክንያት ሲተላለቁ ከማየት የሚያስጠላ ምን ነገር አለ?

አንድ ቀን በ1979 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል አርዓያ ኪዳኔ የሚባል የአዲስ አበባ የሠፈሬ ልጅ መቀሌ ከተማው መሀል እንገናኛለን፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት አይቼው ስለማላውቅ እዚያ መገናኘታችን ደነቀኝ፡፡ ተቃቅፈን ከተሳሳምን በኋላ እንዴት እንደመጣ ስጠይቀው፣ ያለምንም ማመንታት በረሃ ለመውረድ መወሰኑን ነገረኝ፡፡ ከዚያ በፊት በርካታ የሥራ ባልደረቦቼ፣ ተማሪዎቼና በተለያዩ አጋጣሚዎች የተዋወቅኳቸው ወጣቶች በረሃ ገብተዋል፡፡ የአርዓያ ከአዲስ አበባ በረሃ ለመውረድ እዚያ መገኘት ደነቀኝ፡፡ ‹‹ምን ሆነሃል? ጥሩ ሥራ አለህ ለምን በረሃ ትሄዳለህ?›› በማለት መልሱን ለማወቅ ያህል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡

‹‹ወንድሜ አሰፋ ነፃነትህ ተገፎ እንደ ባሪያ ከመኖር ለመብትህ እየታገልክ መውደቅ ያስከብራል፡፡ ሕዝባችን በረሃብ፣ በበሽታ፣ በድንቁርናና በመሐይምነት የሚያየው አበሳ አልበቃ ብሎ ሰብዓዊ ክብሩ ተዋርዶ ይኖራል፡፡ ከባርነት ነፃነት ስለሚበልጥ ራሴንም አገሬንም ነፃ ለማውጣት ትግል እገባለሁ፡፡ በተለይ መጪው ትውልድ በነፃነትና በብልፅግና የሚኖርባት አገር እንድትፈጠር መስዋዕት ለመሆን ራሴን ለመስጠት ወስኛለሁ፤›› ብሎኝ ቢራችንን ጠጥተን ተሰነባበትን፡፡ ውስጡ በነፃነት ጥም የተንገበገበው አብሮ አደጌ ደጋግሞ፣ ‹‹ለዴሞክራሲያዊት አገር መፈጠር ቺርስ!›› ያለኝ አይረሳኝም፡፡ አርዓያ ኪዳኔ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በድል አድራጊነት አገሪቱን ከተቆጣጠሩት ታጋዮች ጋር አልተመለሰም፡፡ ከተሰውት 60 ሺሕ ያህል ታጋዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ እኔ ግን እስካሁን ድረስ አስታውሰዋለሁ፡፡

በሕወሓት በዓል ላይ የተሰው ታጋዮች ቤተሰቦች የልጆቻቸውን ፎቶግራፎች ይዘው በሠልፍ በቴሌቭዥኑ ካሜራ ሥር ሲያልፉ ዓይኔ በእንባ ተሞላ፡፡ የአርዓያ እናትና አባት ከበርካታ ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ሞተዋል፡፡ እሱም አንድና ብቸኛ ልጃቸው ነበር፡፡ እኔ ምናለበት የእሱን ፎቶግራፍ ይዤ በተሠለፍኩ ብዬ ተቆጨሁ፡፡ ብቆጭም ዋጋ የለውም፡፡ ሲጀመር እኔን ማን አውቆ ይጋብዘኛል? የሆነ ሆኖ አርዓያንና የትግሉን ዓላማ እያሰብኩ በነበረበት ወቅት ግን ውስጤ በንዴት ጦፈ፡፡

አርዓያ በ1979 ዓ.ም. ዲግሪውን አስቀምጦ በረሃ ሲገባ መቀሌ ከተማ ላይ እንደነገረኝ፣ ‹‹ነፃነትና ብልፅግና የሰፈነባት ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ እንድትፈጠር መስዋዕት እሆናለሁ፤›› በማለት በቃሉ መሠረት ተሰዋ፡፡ አሁን ቁጭ ብዬ ያሰብኩት አርዓያና እነዚያ ታጋዮች የታገሉለት ነፃነት የታለ? ዴሞክራሲው የት ነው? ልማት ልማት ቢባልም ገና አሥር ዓመት ያልሞላውና ጥቂቶች የሚከብሩበት ነው በስፋት የሚታየው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና የመሳሰሉት አስጠሊታ ነገሮች በየቦታው ሞልተዋል፡፡ እነዚያ ታጋዮች በወደቁበት ዓላማ ላይ የሚቀልዱ ሙሰኞችና ቢጤዎቻቸው ተንሰራፍተዋል፡፡ ሕወሓት ስኬቶቹን ሲዘክር እነዚህን የመጥፎ መጥፎ ችግሮቹን አለማየቱ አናዶኛል፡፡ እነዚያ መንፈሰ ብርቱ ታጋዮች ለክቡር ዓላማቸው በቃላቸው ፀንተው እንደወጡ ሲቀሩ፣ ጓደኞቻቸው እንደነሱ ለምን አልሆኑም? ለምን የነፃነትን ዋጋ ያሳንሳሉ? ለምንስ ምድረ ሙሰኛን ይሰበስባሉ? አሁንም በሰማዕታቱ አፅም ይዘናችኋል፡፡ ወይ ዴሞክራሲ አስፍኑ፣ ካልቻላችሁ ተውት፡፡

(አሰፋ መ.፣ ከኮልፌ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...