Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትምርጫውን እየታዘብን ነው

ምርጫውን እየታዘብን ነው

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

በምርጫ 2007 የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫው በዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ቀጥሏል፡፡ የተሻሻለው የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚወስነው የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ የጀመረው የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ የሚቀጥለው ደግሞ ምርጫው ሁለት ቀን እስኪቀረው ድረስ ብቻ በመሆኑ የምርጫ ውድድሩ እንቅስቃሴ የሚጠናቀቀው ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡

ያሳለፍነውን አንድ ሳምንት ጨምሮ ለምርጫው ዘመቻ የተወሰነው ጊዜ በዚህ መሠረት 88 ቀናት አሉት ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጀምራል የተባለና በዘጠኝ አጀንዳዎች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር የሚያደርጉበት የሚዲያ መድረክ መፅደቁንና መሰናዳቱን ሰምተናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ከእንግዲህ የቀረው ጊዜ የተመዘገበው ሕዝብ ሁለመናው ጆሮ ሆኖ የሚሰማበት፣ በሰማውና ባመዛዘነው ላይ ተመሥርቶ ምርጫ የሚያደርግበት ጊዜ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡

የዚህ ምክንያት ከተከናወኑትና ከተጠናቀቁት ዓበይት የምርጫ አስተዳደርና የሥራ አካሄድ ተግባራት ውስጥ፣ አሁንም እንደገና በአረም የሚመለሱባቸው በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው ነው፡፡

አንደኛው የመራጮች ምዝገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመራጮች ምዝገባ ጉዳይ ውስጥ በተለይ ዋነኛው ደግሞ በምርጫ ሕጉ የተደነገገው ‹‹ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕ የሚኖሩ ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ዜጎች›› የሚመዘገቡበትና በምርጫ የሚሳተፉበት ልዩ ሁኔታ ነው፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ በተለይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ ለሚወዳደሩ ዕጩዎች ብዛት በ12 የወሰነው የምርጫ ሕግ ይዘትና አፈጻጸም ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ ለጊዜው የምንመለከተው እነዚህን ሁለት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የመምረጥ መብትን (የመመረጥ መብትን ጭምር) የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት አድርጎ ያቋቁማል፡፡ ሕጉ፣ ሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ የአገር ሕግና የሕገ መንግሥቱ አካል አድርጋ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎች የምርጫ መርሆዎችን ይደነግጋሉ፡፡ ማንኛውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛ፣ በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃ የሚገልጽበትና ያለምንም ልዩነት በእኩል ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ ይሆናል ይላሉ፡፡ የመምረጥ መብት ከሌሎች መካከል የዕድሜ፣ የመኖሪያ ጊዜና የዜግነት ቅድመ ሁኔታዎች አሉት፡፡

በዕድሜ ረገድ ለምሳሌ ለመምረጥ አካለ መጠን መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ዕድሜው ገና 18 ዓመት ያልሞላው ሰው አካለ መጠን አልደረሰም፡፡ ለምርጫ አካለ መጠን የመድረሻ ዕድሜ በየአገሩና በኢትዮጵያም በየጊዜው የተለያየ ነበር፡፡ ለምሳሌ በ1961ዱ የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ መሠረት ድምፅ የመስጠት መብት ሃያ አንድ ዓመት የሞላው ኢትዮጵያዊ መብት ነበር፡፡ ዕጩ ለመሆን ደግሞ ሰውየው ከ25 ዓመት ያላነሰ መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ለመምረጥ ወይም ድምፅ ለመስጠት 18 ዓመት የሞላው፣ ለመመረጥ ወይም ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ደግሞ 21 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ መሆን ይበቃል፡፡ ለነገሩማ፣ ‹‹አህያ ሰባ ካልተበላ ምን ሊረባ?›› ካልተባለ በስተቀር፣ የቀድሞውን የ21 እና የ25 ዓመት የዕድሜ ገደብ ወደ 18 እና 21 ዝቅ ያደረገው ሕግ የወጣው በ1997 ዓ.ም. በደርግ ዘመን ነው፡፡

በዚህ የዕድሜ ገደብ መሻሻል ላይ ተመሥርቶ የወጣውና አሁን በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሕግ እግረ መንገዳችንን የምናነሳው አንድ የሚገርም ህፀፅ አለው፡፡ አዋጅ ቁጥር 532 በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁ መመዘኛዎችን ሊደነግግ፣ ‹‹በምዝገባው ዕለት ዕድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ›› ይላል፡፡ ለዕጩነት ስለሚያበቁ መመዘኛዎች የተደነገገውም ዕድሜን የሚያሰላው ምዝገባው ዕለት ላይ ሆኖ ነው፡፡ ‹‹በምዝገባው ዕለት ዕድሜው 21 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነው›› ይላል፡፡

የ1961ዱ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ሕግ ድምፅ ለመስጠት መብት ‹‹ምርጫው በሚደረግበት በመጀመሪያው ቀን ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ከሆነ…›› በማለት ይደነግግ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ የብሔራዊ፣ የክልላዊና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን ለማቋቋም በወጣው የጥር 1984 ዓ.ም. አዋጅ የተደነገገው የመራጭነት መመዘኛ ነጥብ፣ ‹‹በምርጫው ቀን ዕድሜው 18 ዓመት የሚሞላው ወይም ከዚያ በላይ የሆነ….›› ይላል፡፡ ከ1985 ዓ.ም. የምርጫ ሕጉ በኋላ የወጣው ሕግ እንደገና የ1984ቱ ሕግ ያስመዘገበውን ‹‹ድል›› ቀለበሰውና ‹‹ማንኛውም በምዝገባው ዕለት ዕድሜው 18 እና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ለመምረጥ የመመዝገብ መብት አለው›› በማለት ቀለበሰው፡፡ ለዕጩነት ስለሚያበቁ መመዘኛዎች የሚደነግገው የ1987 ዓ.ም. ሕግም በተመሳሳይ ሁኔታ ‹‹በምዝገባው ዕለት ዕድሜው 21 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነ›› ሰው መመዝገብ መብት አለው አለ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕግም የኢትዮጵያ የምርጫ ሕጎችና እሱ ራሱ ጭምር ያለፉበትን ብዙ ውጣ ውረዶች ዘንግቶ፣ በመራጭነትም ሆነ በዕጩነት ለመመዝገብ የሚያበቁ መመዘኛዎችን የዕድሜ ቅድመ ሁኔታ የሚያሰላው ከምርጫው ዕለት አኳያ ሳይሆን ከምዝገባው ዕለት አንፃር ነው (አንቀጽ 13 እና 45 ይመለከቷል)፡፡

ጉዳዩን ቀላል አድርገው የሚመለከቱ፣ ከጉዳዩ ቀላልነት የተነሳም የቁንጫ ሌጦ የምናወጣ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች ‹‹ታዲያ ምን ይጠበስ?›› ሊሉን ይችላሉ፡፡ ነገሩ ግን ከላይ ላይ ሲያዩት እንደሚመስለው በጭራሽ ውዳቂ ጉዳይ አይደለም፡፡

ሕገ መንግሥቱ የአንድ ዜጋ የመምረጥ መብት እንዲሁም የመመረጥ መብት የሚበስለው ዜጋው እንደየቅደም ተከተሉ አሥራ ስምንትና ሃያ አንድ ዓመት ሲሞላው ነው ይላል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለመምረጥ ወይም ድምፅ ለመስጠት 18 ዓመት ሞላው የሚባለው በሚመዘገብበት ቀን ነው? ወይስ በምርጫው ቀን ነው? የሚለውን ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ልዩ ልዩ የምርጫ ሕጎች ሥራዬ ብለው ውሳኔ ሰጥተውበታል፡፡ አቋም ይዘውበታል፡፡ በዚህ ምክንያትም የ1961ዱ ሕግ ድምፅ የመስጠት መብትን ‹‹ምርጫው በሚደረግበት በመጀመሪያው ቀን 21 ዓመት የሞላው›› አለ፡፡ (በዚያን ዘመን ምርጫው በአንድ ቀን ብቻ ስለማይፈጸምና ከሰኔ 16 እስከ ሰኔ 30 ቀን ባሉት ቀናት ውስጥ ይከናወን ስለበር ነው)

ከዚህ የበለጠው ዋናው የምርጫ ምዝገባን የሚመለከተው ጉዳይ ደግሞ የምርጫ ምዝገባ በየአምስት ዓመቱ ሁል ጊዜም እንደ አዲስ የሚሠራ መሆኑ ነው፡፡ የመምረጥ (ድምፅ የመስጠት መብት) ሕገ መንግሥቱ የሚለው እውነትና ዕውን ከሆነ፣ ‹‹በቀጥታና በነፃነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካይነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ›› መብት ነው፡፡ በየጊዜው ሲደረግ እንደምናየውም የመራጮች ምዝገባ ከምርጫ አስተዳደር ተግባሮች መካከል ግዙፉና ትልቁ ሥራ ነው፡፡ የ2007 ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያሳየውም በአንፃራዊነት ረዥም ጊዜ የተሰጠው ክንዋኔ ነው፡፡ 42 ቀናት ወይም አንድ ወር ከ12 ቀን በምርጫ ክንዋኔዎች ካሌንደር ውስጥ ረዥሙ ነጠላ ክንዋኔ ነው፡፡ ይህም ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ያጋጠመው መራጭ በተወሰኑት ቀናት ሊመዘገብ ያልቻለበትን ምክንያት አቅርቦ ውሳኔ የሚያገኝበትን፣ የመራጮች መዝገብ በየምርጫ ጣቢያው ለሕዝብ ይፋ ሆኖ የሚቆይበትንና ሌሎች የምርጫ ምዝገባን የሚመለከቱ ክርክሮች የሚስተናገዱበትን ቀናት ሳይጨምር ነው፡፡

በየጊዜውና በየአምስት ዓመቱ ምናልባትም ምክር ቤቱ በመካከል ሲበተን (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 60) ወይም ምርጫው እንዲደገም ሲወስን ደግሞ ከአምስቱ ዓመትም ባነሰ ጊዜ ውስጥ አዲስ የመራጮች ምዝገባ ማካሄድ በጣም ከፍተኛና ግዙፍ ሥራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሌም እንደ አዲስ ደግሞ እንደገና የመሥራት ግዴታን የሚያስከትል ግዳጅ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ሌላም ጣጣና ችግር አለው፡፡ አገሪቷን ትክክለኛነቱና ተዓማኒነቱን ማረጋገጥ የሚቻል ቋሚ የመራጮች መዝገብ አልባ ያደርጋታል፡፡

በመራጭነት መመዝገብና በመራጮች መዝገብ ውስጥ መግባት የመምረጥ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ድምፅ መስጠት የሚችልን ዜጋ፣ ድምፅ መስጠት ከማይቻለው ዜጋ ለይቶ አጣርቶ ማወቅና ድምፅ የመስጠት ችሎታ ያለውን አስተናግዶ ድምፅ እንዲሰጥ ማድረግ የተለያዩ፣ ራሳቸውን የቻሉ የየቅል ሥራዎች ናቸው፡፡ ድምፅ መስጠት የሚችለውን ሰው ከማይችለው የመለየት የመራጮች ምዝገባ ሥራ የምርጫ ወቅት ብቻ አይደለም፡፡ ወይም የምርጫ ወቅት ሥራ መሆን የለበትም፡፡ ከምርጫ በፊትና ሁልጊዜም የሚሠራ ሥራ ነው፡፡

እነዚያን የምርጫ ምዝገባ የሚከናወንባቸውን (ባለፈውም ወደፊትም) አርባ ሁለት ቀናት በምርጫ ካሌንደሩ ውስጥ ከሌሎች ሁሉ የበለጠ ብቸኛና ነጠላ ክንዋኔ ቀናት ናቸው ብለናል፡፡ እውነት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያን ለመሰለ ግዙፍና የተበታተነ ሕዝብ አገር 42 ቀናት ለመራጮች ምዝገባ ምንም አይደለም፡፡ የመራጮች መዝገብ በየምርጫ ጣቢያው (ለዚያውም በየምርጫው ጣቢያ ብቻ) ይፋ ሆኖ የሚቆይበት የአምስት ቀናት ጊዜ ትርጉም የለውም፡፡

በምርጫ መዝገብ ውስጥ መግባት፣ በእነዚያ 42 ቀናት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን መላ ትናጋ ሲባል እንደተሰማው ዓይነትና በተባለበት ሁኔታ ሳይሆን፣ በሌላ ከዚህ ጋር ዝምድና በሌለውና ራሱን በቻለ ፖለቲካዊ፣ የመብትና የነፃነት ምክንያት ከፍ የለ ስምና ቁምነገር ያለው ታላቅ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቋሚ የመራጮች መዝገብ መሆኑ በምርጫው ዕለት መምረጥ ፈቃደኛ የሆኑትን ዜጎች መብት በቋሚነትና በዘላቂነት ያረጋግጣል፡፡ ዜጎች ለመመዝገብ አላስፈላጊ ‹‹ኮከብ ቆጠራ›› ውስጥ አይገቡም፡፡ ለምርጫ አካለ መጠን የደረሱ ሰዎች በየጊዜውና ወዲያውኑ የሚመዘገቡበት ከዚያ ውጪ መሆን ያለባቸው (በሞት በፍርድ ወዘተ) የሚሠረዙበት ቋሚ የመራጮች መዝገብ አለመኖር ጉዳቱ፣ ግለሰባዊ የመምረጥ መብትን በማጣበብ ላይ የተወሰነ አይደለም፡፡ ለመላው የምርጫው ሥርዓትና ፍጥርጥር አደጋም አለው፡፡ ቋሚ የመራጮች መዝገብ መኖር የሁሉም የዴሞክራሲና የምርጫ ሕመማችን ብቸኛው መድንና መፍትሔ አይደለም እንጂ፣ የምዝገባ ሥርዓታችንን ቀይረን ወደ ቋሚ መዝገብ መሄድ አለብን፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተረጋገጠ ኮፒዎችን በመብትነት የሚያገኙበት፣ ድርብ ድርብርብና በየቦታው መመዝገብን የሚከላከል በአጠቃላይ ምርጫው ፅዱ እንዲሆን አስተዋጽኦ የማድረግ ያለው የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት በጣም ያስፈልገናል፡፡

ይህ የመራጮች አጠቃላይ ዝርዝር የያዘ መዝገብ ማለት አሁን አዲስ ‹‹የተገለጠ›› ነገር አይደለም፡፡ የነበረና የቆየ አማራጭ አሠራር ነው፡፡ አንዱ አማራጭ አሁን የምንከተለው በየአምስት ዓመቱ አዲስ የመመዝገብ ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን አማራጭ በመከተል ረገድ በእርግጥ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ አገር አይደለችም፡፡ በርካታ አገሮችም ከቋሚው የምዝገባ ሥርዓት ይልቅ፣ በየምርጫው ወቅት የሚመዘገብበትን የሚመርጡ አሉ፡፡ እኛን ከእነሱ የሚለየን ግን በሚቻለው መጠን ወደንና ፈቅደን፣ ዘክረንና መክረን የወሰድነው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ አለመሆኑ ነው፡፡

እንዲያውም የ25 ዓመት የምርጫ ታሪክ አላት በምትባልና አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውስጥ በምትገኝ አገር፣ ጉዳዩ እንኳንስ ለሕዝብ ‹‹ምርጫ›› እና ውይይት መቅረብ ይቅርና ከነመኖሩም ወሬው የማይታወቅበት ምክንያት የእልህ ጉዳይ ይመስላል፡፡

የዛሬውን አያድርገውና ምርጫ 97 የውጭ ታዛቢዎች ነበሩት፡፡ ከምርጫ 97 ታዛቢዎች መካከል አንዱ (እንዲሁም የምርጫ 2002 ጭምር) የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ነበር፡፡ የምርጫ 97 የአውሮፓ ኅብረት የታዛቢዎች ልዑክ መሪ ዝነኛዋና ‹‹ዝነኛዋ›› አና ጎሜዝ ነበሩ፡፡ በኋላም ‹‹ሐና ጐበዜ›› ተብለው ነበር፡፡ አና ጎሜዝ በከፊሉ ሕዝብ ከመመለካቸው በከፊሉ ደግሞ ከመወገዛቸው፣ ገና የምርጫው እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት መጀመሪያ እግራቸው አዲስ አበባ እንደረገጠ የሰጡት የመጀመሪያው የምርጫ መታዘብ አስተያየት የምርጫ ምዝገባችንን የሚመለከት ነበር፡፡ አና ጎሜዝ የሚመሩት ልዑክ የምርጫ ትዝብት ሪፖርት ገና ዘንቦ ባርቆ ከዚያ በኋላ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተው፣ እስከዚያ ድረስ ግን መቆየት የማያስፈልገው አንድ ጉዳይ የመራጮች ምዝገባ ሥራው ቋሚ መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማለትና ምርጫውን ለመታዘብ የምርጫውን ክንዋኔ መጠበቅ የለብኝም ብለው ነበር፡፡ ይህ አና ጎሜዝ የተናገሩትና ሪፖርተር ጋዜጣም አና ጎሜዝን በትኩሱ ጠቅሶ ያወጣው የዛሬ አሥር ዓመት ወሬ ነበር፡፡

የ2002 ምርጫን የታዘበው የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ምርጫውን ታዝቦ ባወጣው ሪፖርትም የገለጸውና እንዲፈጸምም የሰጠው ምክር ሐሳብ፣ የአሠራር ግልጽነትና የመታመን ክብር ያለው እንዲሁም ትክክለኛ የሆነ ቋሚ የመራጮች መዝገብ ያስፈልጋል ብሎ ነበር፡፡

ይህን የመሰለውን የመራጮች መመዝገብን ቋሚ የሚያደርገውን የፖሊሲ ውሳኔ ኢትዮጵያ የወሰደችው ግን በ1961 ዓ.ም. በወጣው የሕግ መመርያ ምክር ቤት አማካሪዎች አመራረጥ አዋጅ ቁጥር 264/1961 ነበር፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የመራጭነት መመዝገብ ቋሚ እንዲሆን፣ ማንም ሰው እንደገና ለመመዝገብ ሳይገደድ ከ1961 ዓ.ም. በኋላ ወደፊት በሚደረጉት ምርጫዎች ሁሉ ድምፅ እንዲሰጥ ለተመዝጋቢው ሰው መብት የሚሰጥ፣ ለ1961 ዓ.ም. የምርጫ ዓመት እንዲያገለግልና ከዚያም በኋላ የመራጮች ቋሚ መዝገብ ሆኖ እንዲያገለግል በመራጮች መዝገብ የተዘጋጀ የተመዘገቡ መራጮች ሁሉ የሚገኙበት ሥርዓት ዘረጋች፡፡ ከ1961 ዓ.ም. በኋላ የተደረገው የ1965 ምርጫ ነው፡፡ በ1965 ዓ.ም. የተመረጡትና በ1966 ዓ.ም. ጥቅምት 23 ሥራቸውን የጀመሩትን እንደራሴዎች ደግሞ፣ የየካቲት 66 አብዮት በተለይም ደግሞ የ1967 ዓ.ም. የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ጠራረጋቸው፡፡

ሁሉንም ነገር የምናደፋፋ ሁሉንም ነገር ከአዲስ የምንጀምር በመሆኑም የ1961 ዓ.ም. የምርጫ ሕግ ለፖሊሲ አማራጭ ግብዓት ሆኖ እንኳን እንዲያገለግለን አላደረግንም፡፡ የመራጮች ምዝገባን ጉዳይ ከሁሉም በላይ ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ሌላም ሦስተኛ ምክንያትና ሁኔታ አለ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሕግ የ1999 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢተዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ነው፡፡ በዚህ የምርጫ ሕግ የተመራው የ2002 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ብቻ ነው፡፡ በምርጫ 97 ተፈጻሚ የነበረው ይህ ሕግ አልነበረም፡፡

የምንነጋገርበትን የምዝገባ ጉዳይ የሚመለከተው፣ በቀድሞዎቹ ሕጎች ያልነበረው፣ ነገር ግን በአሁኑ አዲሱ የምርጫ ሕግ አዲስ የተካተተው ጉዳይ ‹‹በልዩ ሁኔታ የሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ›› የሚመለከተው የሕጉ አንቀጽ 24 ድንጋጌ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ቦርዱ ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕ የሚኖሩ ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች፣ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ዜጎች በምርጫው የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መራጮች በሚገኙበት ቦታ ወይም አካባቢ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ለማቋቋም ይችላል፡፡ እነዚህም በካምፕ የሚኖሩ ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ዜጐች፣ ለመራጭነት የሚመዘገቡትና ድምፅ የሚሰጡት በሚቋቋሙት ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ነው፡፡ በእነዚህ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገበ መራጭ የሚመርጠው ወደ ካምፑ ወይም ወደ ትምህርት ተቋሙ ከመምጣቱ በፊት ይኖርበት በነበረው የምርጫ ክልል ውስጥ ለውድድር ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል ነው፡፡ ወታደሮችና ተማሪዎች የሰጡትን ድምፅ ውጤት ለይቶ ቦርዱ ከሌሎች የምርጫ ክልሎች በሚደርሰው ውጤት ላይ በመደመር ውጤቱን ያሰላል፡፡ ይፋም ያደርጋል፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙም ቦርዱ በሚያወጣው መመርያ መሠረት ይወሰናል፡፡

የመራጮች መዝገብ በየደረጃው ለሚካሄድ ምርጫ መራጩ በምርጫ ጣቢያው በመራጭነት የሚመዘገብበት መዝገብ ነው፡፡ ምርጫ ጣቢያ ሲባል ደግሞ በየደረጃው በሚካሄዱ ምርጫዎች ምዝገባ የሚካሄድበት፣ መራጮች ድምፅ የሚሰጡበትና ቆጠራም ጭምር የሚካሄድበት ቦታ ነው፡፡ ይህንን የሚለው ሕጉ ነው፡፡ ሕጉ የምርጫ ጣቢያዎች ስለሚቋቋሙበት በሚደነግገው ቁጥሩ የድምፅ መስጫና የቆጠራ ጣቢያ ሆነው የሚያገለግሉ ቦርዱ በሚወስነው ሥፍራና ሁኔታ የሚቋቋሙና ለሕዝብ በይፋ የሚገለጹ ናቸው ይላል፡፡ እንዲሁም ወታደራዊ ካምፖች፣ የፖሊስ ጣቢያዎች፣ ቤተ ክርስቲያኖችና መስጊዶች፣ ሆስፒታሎች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ድርጅቶች ሕንፃዎች፣ መኖሪያ ቤቶች የምዝገባና የድምፅ መስጫ ሥፍራ በመሆን ሊያገለግሉ አይችሉም ብሎ ይከለክላል፡፡

እንዲህም ሆኖ ግን ሕጉ ራሱ ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕና በሌላ ቦታ የሚኖሩ ወታደሮችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከሚገኙበት ሩቅ ቦታ የእናት ምርጫ ክልላቸው ድምፅ ሰጪዎች ሆነው እንዲመርጡ ይፈቅዳል፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙም ቦርዱ በሚያወጣው መመርያ እንዲወሰን ያዛል፡፡ ይህ የ1999 ዓ.ም. የምርጫ ሕግ ልዩና ከዚህ ቀደም ያልነበረ አዲስ ድንጋጌ በአሠራር ወይም በተግባር የተፈተነው በ2002 ምርጫ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹መሆኑ ነው›› ያልነው ንፋስ ከሚወስደው ዜና፣ ‹‹ነጋዴ ከሚያመጣው›› ወሬ በላይ ይፋ የሆነ ዝርዝር ነገር ስለማናውቅ ነው፡፡ የ2002ቱ አገር አቀፍ ምርጫ የአውሮፓ ኅብረት ሪፖርት ምርጫ ቦርድን ዋቢ አድርጎ እንደሚናገረው ከሆነ በ111 (አንድ መቶ አሥራ አንድ) ኮሌጆችና ወተዳራዊ ካምፖች በተካሄደ የመራጮች ምዝገባ 231,269 ድምፅ ሰጪዎች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡  

ይህ ማለት ምርጫ ቦርድ ያን ያህል ከምርጫ ክልሎች ውጪ ያሉ የምርጫ ጣቢያዎችን የማቋቋም፣ ያን ያህል ሕዝብ የመመዝገብ፣ የማስመረጥ እንዲሁም ውጤቶችን መሠረት በማድረግ በመላ አገራቱ ባሉት የ2002 ዓ.ም የ43,500 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ መደመርና ይህንንም የማጠናቀቅ ከባድና ግዙፍ ሥራ አከናውኗል ማለት ነው፡፡ ሥራው እውነትም ሲበዛ ከባድና ግዙፍ በመሆኑ ምክንያት ያንኑ ያህልም የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነትም የሚያስከትል ነው፡፡

እንዲያውም በ2002 ምርጫ የአውሮፓ ኅብረት የታዛቢዎች ልዑክ ሪፖርት እንደሚለው፣ የተማሪዎቹና የወታደሮቹ ድምፅ አግባብ ባላቸው የእናት ምርጫ ክልሎች ውጤቶች ላይ የሚደመረው በምርጫ ቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በመሆኑ ይህ አሠራር ውጤቶችን የማጠናቀርና የማጠቃለልን የአሠራር ግልጽነት ይቀንሰዋል፡፡ ከዚህም በላይ እነዚህ ውጤቶች የሚታተሙት (ይፋ የሚደረጉት) የእያንዳንዱን የምርጫ ክልል አጠቃላይ ውጤት የሚለውጥ አቅም ያላቸው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በብሔራዊ የአገር ደኅንነት ምክንያት በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ያሉትን የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ሊገልጽ አለመቻሉ፣ ድምፅ የመስጠት ሥራ በነፃ ተደራሽ ባልሆኑና ታዛቢ ድርሽ በማይልባቸው ቦታዎች መከናወን አለበት ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳል ብሏል፡፡

ይህ መሠረት የሌለው ክስ፣ ተራ ጥርጣሬና አሉባልታ ሊሆን ወይም ሊባልም ይችላል፡፡ ለዚህ ግን የማያዳግም ምላሽ የመስጠቱ ዘዴ የጥርጣሬውንና የሐሜቱን ምንጭ በማድረቅ ነው፡፡

በ2007 ምርጫም ይህ ችግር በድጋሚ እንደሚነሳ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ አሁን የካቲት አጋማሽ መገባደጃ ላይ ሆነን ምርጫ ቦርድ ‹‹በልዩ ሁኔታ የሚቋቋም የምርጫ ጣቢያን በተመለከተ በመላው አገሪቱ ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርተ ተቋማት አመራሮች፣ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኃላፊና ከአገር መከላከያ ከፍተኛ መኰንኖች ጋር የምክክር መድረክ›› ማድረጉን፣ ከምክክሩ መድረክ በኋላም ለተቋማቱ ምርጫ አስፈጻሚዎች በመቀሌና በአዳማ በሦስት ተከታታይ ዙር ሥልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው ዙር ከየካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ በአዳማ እንደሚሰጥ እንሰማለን፡፡

ይህንን ዜና ለሚሰማ ሰው ቢያንስ ቢያንስ ሥልጣኑ የሚሰጣቸው የተቋማቱ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመርጠዋል ወይ? እንዴትስ ተመረጡ? የመራጮች ምዝገባ ገና አልተጠናቀቀም ማለት ነው ወይ? ለሚሉ ለበርካታ ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች ይዳርጋል፡፡

ጉዳዩን እንዲህ ያሉ ብልጭ ድርግም የሚሉ ዜናዎች ከሚያጋድዱት በላይ ሰፊ የፖሊስ ማብራሪያና መግለጫ ያስፈልገዋል፡፡ የአሠራር ግልጽነቱንም አገር ሊያውቀውና ፀሐይ ሊሞቀው ይገባል፡፡ በተለይም ‹‹በልዩ ሁኔታ የሚቋቋም የምርጫ ጣቢያን›› የሚመለከተው ጉዳይ ‹‹ዝርዝር አፈጻጸም ቦርዱ በሚያወጣው ደንብ ወይም መመርያ ይወሰናል›› መባሉ ማስረጃ አቅርቡበት የማይባል የሕግ ጉዳይ ነው፡፡

ይህን ያለው ሕግ ራሱ የሚገርም ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ውስጥ የሚገኝ መብት፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ ምን እንደሚመስል ውሳኔ የመስጠት ሥልጣንን ለቦርዱ በውክልና መስጠት ብዙ የሚያደናግር አሠራር ነው፡፡ በዚህ ሳያበቃ ይህንን በደንብ ከፈለግህ በመመርያ ብሎ መፍቀድ ቦርዱን እንዳሻህ አድርግ ከማለት የተለየ አይደለም፡፡

እንዲያም ሆኖ ቦርዱ ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕ የሚኖሩ ወታደሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ በምርጫ 2007 የሚሳተፉበትን ሁኔታ ዝርዝር አፈጻጸም የሚወስን ደንብም መመርያም እስካሁን አልወጣም፡፡ በ2002 ምርጫ የዚህን አፈጻጸም ዝርዝር ለመወሰን ጊዜያዊ መመርያ አውጥቶ ነበር፡፡ የመመርያው ጊዜያዊነት የ2002 ምርጫን ተሻግሮ ለ2007 ምርጫ ስለማስገልገሉም አይታወቅም፡፡ በአጠቃላይ የግልጽነት አለመኖርና መመርያ የማውጣት ሥልጣን ገደብ የለሽነት እየተባበሩ የሚያግዙት የዘፈቀደ አሠራር፣ የግለሰቦችን የመምረጥ መብት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የምርጫውን የመታመን ክብር ይሸረሽራሉ፡፡

አንድ ሰው አንድ ድምፅ ሲባል እንሰማለን፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ድምፅ ዋጋ እኩል ነው ማለትም የታወቀ አባባል ነው፡፡ ይህ ሁሉ ትርጉም የሚኖረው የአንድ የምርጫ ክልል  ውጤት ከአንድ የምርጫ ጣቢያ ተደምሮ በመጣ ቁጥር በዘፈቀደ ሊለውጠው እንደማይችል፣ ግልጽ የሆነ የሕግ ዋስትና ያለው አሠራር መኖሩን የሚያሳምን ሥርዓት ስንዘረጋ ነው፡፡

የምርጫ ምዝገባ ቋሚ መሆን የድምፅ መስጫና የቆጠራ ጣቢያ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ የተፈቀደላቸውን የልዩ ምርጫ ጣቢያዎች ጣጣና ችግር ባይከላከልም፣ ምዝገባን የሚመለከቱ ችግሮች ግን በዚሁ ስለመወገዳቸው አያጠራጥርም፡፡ ‹‹ሺሕ ቦታ›› መመዝገብን ከማስቀረት በላይ የዚህን የምርጫ ክልል ወይም ጣቢያ ጉዳይ በዚህኛው ወይም በእነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች ትቸዋለሁ የመሰለን ማንአለብኝነት ይቆጣጠራል፡፡

ምርጫን የምንወደውና የምርጫውን ጐዳና የምንመርጠው የምርጫው ውጤት ለአንዱ ወይም ለሌላው የፖለቲካ ቡድን ወደ ፖለቲካ ሥልጣን መወጣጫ መንገድ ይሆናል ብለን አይደለም፡፡ የዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከ25 ዓመት የምርጫ ‹‹ልምምድ›› በኋላም ቢሆን ይህንን የሚመሰክር አይደለም፡፡ ገዥው ፓርቲም ቢሆን ምርጫን ደጋግሞ እንደሚያደርገው የሕዝብ ድጋፍ ምስክር አድርጎ መቁጠሩንና ማቅረቡን ቢተወው መልካም ነው፡፡ በእኛ አገር የምርጫ ድምፅና የሕዝብ ድጋፍ ገና ገና አልተግባቡም፣ አልተገናኙም፣ አልተዋደዱም፡፡ ሌላ አመለካከት እንዳይወሰድብኝ፣ ችግር እንዳይገጥመኝ ተብሎ ወደ ምርጫ መውጣትና ያልወደዱትን መምረጥ እዚህ አዲስ አበባ ጭምር የሚፈጸም የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ መሽቆጥቆጥ፣ ኩርምት ማለት፣ አጐንብሶ ማለፍ፣ አንገት መድፋት ገና በ‹‹ማን አባቱ ያዘኛል!›› አልተተካም፡፡

ምርጫን የምንወደውና የምንመርጠው በዚህ ሒደት ውስጥ ተንጠባጥበው በሚመጡና ዞሮ ዞሮ እያደር በሚገኙ ሥርዓት መገንቢያ ድሎች ምክንያት ነው፡፡ ይህን መጻፍና ማለት ራሱ ከዚህ መንግሥት በፊት የነበሩት መንግሥታት ይታገሱት ያልነበረ መብት ነው፡፡ ይህንን መብት ‹‹በሚፈቅደው›› እና በሚታገሰው መንግሥት፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላት ዘንድም ቢሆን ሐሳብን በነፃ መግለጽ ገና አበረታች አቀባበል አላገኘም፡፡

      የጋዜጦች ወይም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አስተያየቶች አሁንም ገና በመንግሥት የሚናቁና የሚጠየፉ ልፍለፋ ናቸው፡፡ ጉድፍ መመልከቻ ከማድረግ ይልቅ የጠላት ጥቃት ተደርጐ የሚወሰድ ነው፡፡ ካስፈለገም የሚያስነክስ፣ የሚያስከስስ ነው፡፡ ምርጫውን የምንወደው በዚህ ረዥም ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ውስጥ፣ እነዚህን እንጥብጣቢ ድሎች ጭምር ለማግኘትና በዚህም አማካይነት ወደ ዘላቂው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ለመረማመድ ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...