– ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና በብትን የሚታሸገው 30 ከመቶ እንዲሆን ታስቧል
ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና በማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን አማካይነት ለሁለት ዓመት በውጭ አማካሪ ኩባንያ ሲጠና የቆየውን ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ተግባር ላይ ሊያውል መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ስትራቴጂው ሊመልሳቸው ከሚያስባቸው የሎጂስቲክ ችግሮች መካከል በሌሎች አገሮች ውስጥ የወደብ ልማት ማካሔድ አንዱ መሆኑን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኰንን አበራ ጠቁመዋል፡፡
አቶ መኰንን ይፋ እንዳደረጉት የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየሰፋ በመምጣቱና በገቢና ወጪ ንግድ የሚስተናገዱት ዕቃዎችም እየበዙ በመምጣታቸው፣ በጂቡቲ ወደብ ላይ ተወስኖ የቆየውን የንግድ በር ወደሌሎች በሌሎች ወደቦችም እንዲስተናገድ የማድረግ ዕቅድ በአዲሱ ስትራቴጂ ውስጥ ተካተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከሶማሌላንድ በርበራ ወደብና ከሱዳን፣ ሱዳን ፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አቶ መኰንን ጠቅሰዋል፡፡
ፖርት ሱዳን በተለይ በሰሜን በኩል እስከ ባህር ዳር ላለው አካባቢ የሚዋጣ ሆኖ መገኘቱንና በቅርቡም 50 ሺሕ ቶን ማዳበሪያ በዚሁ ወደብ ተጓጉዞ መግባቱንና ለገበሬዎች እንዲሰራጭ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ምንም እንኳ ከጂቡቲ ወደብ አኳያ ሲታይ የሱዳን ወደብ ርቀት ያለው ቢሆንም፣ በመንገዱ አስፋልትነትና በሱዳን በኩል ከፍተኛ ጭነት መሸከም የሚችሉ ተሸከርካሪዎች ያሉ በመሆኑ፣ ርቀቱን እንደሚያካክሰው አስታውቀዋል፡፡ የሱዳን ከባድ ተሸከርካሪዎች ከ75 እስከ አንድ መቶ ቶን በአንድ ጊዜ ማጓጓዝ የሚችሉ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ በአንጻሩ ከጂቡቲ ወደ ወደ መሐል አገር ጭነት የሚያጓጉዙ ተሸከርካሪዎች ከፍተኛ የመጫን አቅም ቢበዛ እስከ 40 ቶን መሆኑን በመግለጽ ከሱዳን አኳያ ያለውን ልዩነት አነጻጽረዋል፡፡
ብሔራዊ ስትራቴጂውንና ሌሎችም የማሪታይም ጉዳዮችን በሚመለከት ረቡዕ፣ የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በግዮን በተካሔደ ውይይት ላይ ባለድርሻዎች በርካታ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅትን በመወከል የተሳተፉት አቶ መርሻ ፀጋዬ፣ በጸጥታ ጉዳዮች ሳቢያ የሁለቱ ወደቦች አማራጭ ሆኖ መቅረብ ከምን መነሻ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ በሱዳንም ሆነ በበርበራ ወደብ ለመጠቀም በሁለቱ አገሮች ያለው ሰላም አስተማማኝ ባለመሆኑ መንግሥት ከምን ተነስቶ ወደቦቹን ለመጠቀም እንደወሰነ ጠይቀዋል፡፡ ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት አቶ መኰንን፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለጉዳዩ ምላሽ የሰጡበት መሆኑንና ፖለቲካዊ ይዘቱን እነሱ እንደሚከታተሉት ገልጸው፣ ሁለቱን አማራጭ ወደቦች በመጠቀም በኩል ሥጋት እንደሌለና እስካሁን ጭነቶች በሰላም መጓጓዛቸውን አስታውቀዋል፡፡ የወደቦቹ አማራጭነት ከአገልግሎትም ባሻገር፣ ለጂቡቲ ተፎካካሪዎች እንዳሉ የሚያገነዝብ በመሆኑ በውድድር መንፈስ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ በር ይከፍታል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ወደፊት በሎጂስቲክስ ዘርፍ መመለስ ካለባቸው ጥያቄዎች መካከል በጎረቤት አገሮች ውስጥ የወደብ ልማቶች ላይ መሳተፍ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ መኰንን ይህም ቢባል ግን የትኞቹ አገሮች ለዚህ ተሳቢ እንደተደረጉ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ሆኖም የወደብ ልማት ላይ መሳተፍ የአገሪቱን የባሕር በር እንደልብ የማግኘት ዋስትና ሊያረጋግጡ ከሚችሉ አማራጮች ውስጥ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የሎጂስቲክስ ስትራቴጂው ወደፊት ሊመለከታቸው ይገባሉ ካሏቸው መካከልም ኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን የሞኖፖል ድርሻን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቱን የመሠረቱት የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅትና የደረቅ ወደብ አገልግሎት መሆናቸው ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ወደፊት በሚኖረው ሕልውና ላይ ከሚጠበቁ ዕርምጃዎች መካከል ወደ ግል ይዛወር አለያም የሌሎች የግል ኩባንያዎች በዘርፉ እንዲሳተፉ ይፈቀድላቸው የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን አዲሱ ስትራቴጂ ሊመለከት ይችላል፡፡
እነዚህን ጨምሮ በሎጂስቲክስ መስኩ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በሚመለከት ውይይት ከመደረጉም ባሻገር፣ በተለይ ባዶ ኮንቴይነር ወደ ጂቡቲ ወደብ ከሚሔድ ይልቅ እዚሁ በጭነት ተሞልቶ እንዲወጣ ማድረጉ ለአገሪቱ በአንድ ኮንቴይነር የሚወጣውን 121 ዶላር ሊያስቀርላት እንደሚችል አቶ መኰንን ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም እንደቡና ያሉ የወጪ ንግድ ሸቀጦችን በብትን በኮንቴይነር እዚሁ አሽጎ የመላኩ ሥራ አሁን ላይ ካለበት ሰባት ከመቶ መጠን በዚህ ዓመት መጨረሻ ወደ 30 ከመቶ ከፍ እንደሚል ይፋ አድርገዋል፡፡
ከኮንቴይነር ጋር በተያያዘ የተነሳው ሌላው ችግር የኮንቴነሩ ባለንብረት የሆኑ የመርከብ ድርጅቶች ለማስያዣ የሚያስከፍሉት ገንዘብ አላግባብ የተጋነነና፣ ለማስያዣ የተጠየቀው ገንዘብ ቀድሞ እስካልተከፈላቸው ድረስ በሚሊዮን ዶላሮች የሚተመኑ የወጪ ዕቃዎችን ጂቡቲ ወደብ ላይ በማገት እክል እየፈጠሩ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ ዝባድ ኢምፖርትና ኤክስፖርት ድርጅት በተወካዩ በኩል እንደገለጸው 1.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡና በዚህ አኳኋን ወደብ ላይ ሊጉላላበት መቻሉን ገልጿል፡፡
በአካካስ ሎጂስቲክስ የመርከብ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ግርማ ቡታ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ይህንን ሐሳብ ሲያስተጋቡ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁንም ቢሆን፣ ለአንድ ባለ40 ጫማ ኮንቴይነር የሚከፈለው የሰባት ሺሕ ዶላር ማስያዣና ለባለ20 ጫማ ኮንቴይነር የሚጠየቀውን የ3,500 ዶላር የማስያዣ ገንዘብ፣ ኮንቴይነሮችን እዚህ በሸቀጦች በመሙላትና በማሸግ ማስቀረት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም ቡናን በብትን እዚሁ አሽጎ ወደ ወደብ መላክ ቅድመ ጥንቃቄቆዎች እንደሚጠይቅ የተገለጸ ሲሆን፣ ‹‹ክራፍት ፔፐር›› የሚባለውና ቡናውን ከብክለት የሚጠብቀው ወረቀት ኮንቴይነሩ ውስጥ ማንጠፍ መቻል፣ የኮንቴይነር ተርሚናል ዝግጁ መሆን፣ የኮንቴይነር አቅርቦት አለመታጎልና የመሳሰሉት መመለስ ያለባቸው ወሳኝ ጥያቄዎች ሆነዋል፡፡