Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ድንበር ተሻጋሪው የኢትዮ ሱዳን ትራንስፖርት ከ40 ቀናት በኋላ ይጀመራል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰላምና ስካይ ባስ ጀማሪዎች ይሆናሉ

ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ተሻጋሪ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችላቸውን ስምምነት አደረጉ፡፡ በሁለት አገር በቀል ኩባንያዎች ሥራው እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ባለፈው ሐሙስ በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ በሁለቱም በኩል አገልግሎቱን የሚሰጡ ኩባንያዎች ሊያሟሏቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም ታሪፉ ምን ያህል ይሁን በሚለው  ነጥብ ላይ ስምምነት አድርገዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ተወካዮች በደረሱበት ስምምነት መሠረት አገልግሎቱን በ45 ቀናት ውስጥ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በስምምነቱ ውስጥ አገልግሎቱ የሚጀመረው የሁመራ ቡግዲ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል በተደረሰው ስምምነት ላይ የመነሻና መድረሻ ከተሞች የተመረጡ ሲሆን፣ 1499 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የአዲስ አበባ ካርቱም መስመር ላይ ያሉት ከተሞችም እንዲለዩ ተደርጓል፡፡

ከአዲስ አበባ መነሻውን የሚያደርገው ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ጎንደርና መተማ ከተሞችን አቋርጦ ካርቱም የሚደርስ ሲሆን፣ ከካርቱም  በጋላባት አድርጎ በጎንደር በኩል ወደ አዲስ አበባ ይዘልቃል፡፡

ከአዲስ አበባ ካርቱም ለሚደረግ ጉዞ አንድ መንገደኛ 90 የአሜሪካ ዶላር መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡ የትራንስፖርት ኩባንያዎችም መንገደኞችን አሳፍረው የሁለቱን አገሮች ድንበር ማቋረጥ ከመቻላቸውም በላይ በጉዟቸው ደብረ ማርቆስ ከተማን የምሳ ሰዓት ማረፊያ፣ ጎንደርን ደግሞ የምሽት ማረፊያ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

በዚህ ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚጠቀሙ መንገደኞች እስከ 25 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሻንጣዎችን መያዝ የሚችሉ ሲሆን፣ ክብደቱ ከዚያ በላይ ለሆነ ዕቃ በኪሎ ግራም ተጨማሪ 0.03 ዶላር ይከፍላሉ፡፡ በአጠቃላይ ለአንድ መንገደኛ የተፈቀደው የክብደት ጣሪያ 40 ኪሎ ግራም እንደሚሆን የስምምነት ሰነዱ ያሳያል፡፡

በስምምነቱ መሠረት፣ አንድ መንገደኛ ቲኬት ለመግዛት ቪዛ መያዝ የሚገባው መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በጉዞው ወቅት ፓስፖርቱን በሚጠየቅበት ቦታ ሁሉ የማሳየት ግዴታ አለበት፡፡

የሁለቱም አገሮች ትራንስፖርት አቅራቢዎች ለመንገደኛ የቲኬት ሽያጭ የሚያከናውኑበትን፣ የራሳቸውን ቢሮና ሠራተኛ በጋራ የሚገለገሉበትን አሠራር በስምምነቱ ተጠቅሷል፡፡ በአንድ ሳምንት ሁለት አውቶቡሶች ከአዲስ አበባ፣ ሁለት አውቶቡሶች ደግሞ ከካርቱም እየተነሱ አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ በዚሁ መሠረት አገልግሎቱን የሚሰጡ ኩባንያዎች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በባህር ዳር ውስጥ ተገናኝተው በአሠራር ሒደት ዙሪያ ተጨማሪ ምክክር እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡ ምክክሩ አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት የስምምነቱ አካል ሊሆኑ የሚችሉ አሠራሮችን ለመጨመር የሚያስችል ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተደረገውን አጠቃላይ ስምምነት ግን የሚቀር እንደማይሆን ተጠቁሟል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን እንደሚገባቸው በስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ውስጥ ከተካተቱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

አንድ አውቶቡስ የሚያጓጉዘው የመንገደኛ ብዛት ከ33 በታች ከሆነ፣ ጉዞውን መሠረዝ ወይም ማስተላለፍ እንደሚችል በስምምነቱ ቢገለጽም፣ ትራንስፖርተሮች ከ33 በታች መንገደኞችን ጭነው የመጓዝ መብት እንዳላቸው ታውቋል፡፡

የሁለቱን አገሮች ረዥም ርቀት የሚሸፍነውን ጉዞ ከትራፊክ አደጋ ነፃ ለማድረግ ሲባል፣ አንድ አውቶቡስ በቀን ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ አይችልም፡፡ አንድ  አውቶቡስ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሁለት ቀናት ውስጥ ካርቱም በመድረስ፣ ከአንድ ቀን ዕረፍት በኋላ ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞ ማድረግ ይችላል ተብሏል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሁለት ሾፌሮች እየተቀያየሩ መከናወን ይኖርበታል ተብሏል፡፡ ከኢሚግሬሽን ጋር በተያያዘ ላሉት አሠራሮች፣ ከኢትዮጵያ የመተማ ከተማ፣ ከሱዳን ደግሞ የጋላባት ከተማ ተመራጭ ሆነዋል፡፡

አንድ አውቶቡስ ወደ ሌላኛው አገር ድንበር ሲሻገር የኮቴ 15 ዶላር እንዲከፍል ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም የሁለቱም አገሮች አውቶቡሶች የነዳጅ አቅርቦት በደረሱበት ቦታ ላይ የማግኘት መብት እንዳላቸውም ተጠቅሷል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ከአንድ አገር ወደ ሌላኛው አገር የሚሻገር የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ የየብስ ትራንስፖርት የሌለ በመሆኑ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሰው ስምምነት ፈር ቀዳጅ ተብሏል፡፡

ሁለቱን አገሮች በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት፤ በኢትዮጵያ በኩል የትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም ሲሆኑ፣ የሱዳን ትራንስፖርት ሚኒስቴርን በመወከል የተስማሙት ኢንጂነር አህመድ ኢብራሒም ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለቱ አገሮች ስምምነት መሠረት ድንበር ዘለል የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉት ኩባንያዎች መለያታቸው ታውቋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ተሽከርካሪዎች በየተሳፋሪው መቀመጫ ትይዩ የአየር ማቀዝቀዣ ያላቸውና ዘመናዊ ሊሆኑ የሚገባ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በኩል ለዚህ አገልግሎት ሰላም ባስና ስካይ ባስ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በሱዳን በኩልም ለዚሁ አገልግሎት ብቁ የተባሉ ሦስት ኩባንያዎች በስምምነቱ ላይ እንደታደሙ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ከኢትዮጵያ ወገን አገልግሎቱን ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ሰላምና ስካይ ባስ ኩባንያዎች ስምምነቱ ሲፈረም ተገኝተዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ ግን ከሁለቱ ተቋማት በተጨማሪ መሥፈርቱን ሊያሟሉ የሚችሉ ሌሎች የትራንስፖርት ድርጅቶች ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሦስት ኩባንያዎች በመቋቋም ላይ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ሊደረግ እንደሚችል ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች