የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የተፅዕኖ ሥጋቶችን ለማጥናት፣ ከአራት ኩባንያዎች የቀረቡ ፕሮፖዛሎችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ እየገመገመ ነው፡፡
ቀደም ሲል ዓለም አቀፍ አጥኚዎች የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በግብፅም ሆነ በሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን ያረጋገጡ ቢሆንም፣ በሦስቱ አገሮች መካከል መተማመንን ለመፍጠር ሁለት ጥናቶች በጋራ ቢከናወኑ እንደሚጠቅም ምክረ ሐሳብ አቅርበው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚህ መሠረት በመግባባት ሦስቱ አገሮች 12 አባላት ያሉት የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመው አጥኚ ኩባንያዎችን ለመምረጥ ተስማምተዋል፡፡ እያንዳንዱ አገር ሦስት ዓለም አቀፍ አጥኚ ኩባንያዎችን በመምረጥ እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 2014 ካይሮ ውስጥ ተወያይተዋል፡፡
በመሆኑም በአጠቃላይ ሰባት ኩባንያዎች ከአምስት አገሮች የቴክኒክና የፋይናንስ ፕሮፖዛላቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቀው፣ ምላሻቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲጠበቅ እንደነበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ያለፈው ሳምንት ድረስ ክፍት የነበረው የፕሮፖዛል ማስገቢያ ጊዜ ተጠናቆ ሦስቱ አገሮች ቀደም ሲል በተስማሙት መሠረት፣ የቀረቡትን የቴክኒክ ፕሮፖዛሎች በተናጠል ለአሥር ቀናት የመገምገም ሒደት በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን በኩል መጀመሩን በኢትዮጵያ ውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተሾመ አጥናፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ፕሮፖዛል ያስገቡት ኩባንያዎች ቁጥር አራት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተሾመ፣ ስማቸውን ለመግለጽ ግን ሦስቱ አገሮች የገቡት ስምምነት እንደማይፈቅድ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሁለት የፈረንሣይ፣ አንድ የኔዘርላንድ፣ አንድ የአውስትራሊያ ኩባንያዎች ፕሮፖዛላቸውን እንዳስገቡ ጠቁመዋል፡፡ ሦስቱ አገሮች በተስማሙት መሠረት በተናጠል የመረጡትን ኩባንያ ይዘው በጋራ በድጋሚ የሚወያዩ ሲሆን፣ ለዚህም እ.ኤ.አ. ከማርች 5 ቀን እስከ 9 ቀን 2015 ድረስ ካርቱም ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከቀድሞው ዓለም አቀፍ አጥኚ ቡድን የቀረቡት ሁለት ምክረ ሐሳቦች የግድቡ ኃይድሮ ሲሙሌሽን ሞዴል ማለትም በተለያዩ የአየር ንብረት ወቅቶች የግድቡ ውኃ አሞላልና አያያዝን፣ እንዲሁም ግድቡ በሦስቱ አገሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖን ማጥናት ናቸው፡፡