Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጀርመናዊውና ኦርኪድ በደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን መስተንግዶ እየተወዛገቡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥር ፍርድ ቤት የወሰነልኝ ሰነዶችን በፎሬንሲክ ምርመራ አረጋግጦ ነው›› የጀርመን ዜግነት ያላቸው አቶ ዮናስ ካሳሁን

‹‹የፎሬንሲክ ምርመራ ውጤት በሰነድ ላይ ሲፈረም አይቻለሁ ዓይነት ነው›› ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ

የደቡብ ሱዳን ነፃነት ቀን ሐምሌ 2 ቀን 2003 ዓ.ም. ከተከበረው የመስተንግዶ ዝግጅት በኋላ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የጀርመን ዜግነት ያላቸው አቶ ዮናስ ካሳሁንና የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አኪኮ ሥዩም፣ በሥር ፍርድ ቤት የጀመሩት ውዝግብ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሶ የመጨረሻ የቃል ክርክር ተደረገበት፡፡

ለሁለቱ ወገኖች ውዝግብ መነሻ የሆነው፣ ሐምሌ 2 ቀን 2003 ዓ.ም. የነፃነት ቀኗ የተከበረውና በአሁኑ ጊዜ በጦርነት ላይ የምትገኘው ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን የተለየችበት የነፃነት ቀንን ለማክበር የተዘጋጀ የመስተንግዶ ዝግጅት ነው፡፡

የደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀንን ለማክበር ለሚደረግ ዝግጅት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ያወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አኪኮ ሥዩም 49 በመቶ ባለድርሻ የሆኑበትና በባላቸውና በልጃቸው ስም የተሰየመው፣ ሶልዳን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ማሸነፉን፣ ራሳቸው ወ/ሮ አኪኮና ጠበቆቻቸው በፍርድ ቤት ባደረጉት ክርክር ላይ ተናግረዋል፡፡ ሰነዶችም ይኼንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ነፃነት ቀን አከባበር ከመምጣቱም በፊት የተለያዩ የሥራ ግንኙነት እንደነበራቸው የሚናገሩት ጀርመናዊው አቶ ዮናስ ካሳሁን እንደገለጹት ደግሞ፣ ወ/ሮ አኪኮ የደቡብ ሱዳን ነፃነት ቀን አከባበር ላይ መስተንግዶ ለማዘጋጀት የአገሩ መንግሥት ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱን ይነግሯቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ጨረታ በመሆኑ በኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ስም መወዳደር አይቻልም፡፡ ወ/ሮ አኪኮ 49 በመቶ ባለድርሻ በሆኑበትና መቀመጫው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሆነው ሶልዳን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ እንዲወዳደሩ እንደገፋፏቸው ለፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ አኪኮ ለውድድሩ ከመቅረባቸው በፊት አጠቃላይ ምክረ ሐሳቡን (ፕሮፖዛል) አዘጋጅተው ጨረታውን እንዲወዳደሩ እንዳደረጉት የገለጹት አቶ ዮናስ፣ ጨረታውን በአንደኝነት ማሸነፍ መቻላቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ አኪኮ ግን በአቶ ዮናስ አባባል አይስማሙም፡፡ ሁለቱም እንደሚተዋወቁ ሳይክዱ፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ያወጣውን ጨረታ ያሸነፉት አቶ ዮናስ እንደገለጹት እሳቸው በሠሩላቸው ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ሳይሆን፣ እሳቸው ደቡብ ሱዳን ውስጥ ይኖሩ ስለነበረ በሚሠሩት ሥራ ውጤታማ መሆናቸውን፣ በተለይ በወቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ሪክ ማቻር ባደረጉላቸው ዕርዳታ መሆኑን በመግለጽ የአቶ ዮናስን አስተያየት ተቃውመዋል፡፡

አቶ ዮናስ አስረግጠው የሚከራከሩት ወ/ሮ አኪኮ ስለሥራው ምንም ዓይነት ዕውቀትም ሆነ ዝግጅቱ እንዳልነበራቸውና በወቅቱ ግን ከወ/ሮ አኪኮ ጋር በነበራቸው መልካም ግንኙነት፣ ጨረታውን ካሸነፉ እሳቸው ከሚኖሩበት ጀርመን ለዝግጅቱ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ከተለያዩ የጀርመን ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር እንደሚያመጡ ነው፡፡ ጨረታው ተሳክቶ በማሸነፋቸው አቶ ዮናስ በገቡት ቃል መሠረት ለጀርመን ኩባንያዎች ከራሳቸው ቅድሚያ ክፍያ በመክፈል፣ ለዝግጅቱ የሚሆኑትን ቁሳቁሶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት ወደ ደቡብ ሱዳን መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ለድርጅቶቹ ቅድሚያ ክፍያ ከራሳቸው የከፈሉት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ላሸናፊ ተጫራቾች ቅድሚያ ክፍያ እንደሚፈጽም የተናገረ ቢሆንም፣ በወቅቱ ሊከፍል ባለመቻሉና የዝግጅት ጊዜው እያጠረ በመምጣቱ ዝግጅቱን ከጨረሱ በኋላ ከወ/ሮ አኪኮ እንደሚቀበሉ በመተማመን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን በዓል የቀድሞውና የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ሌሎች የዓለም መሪዎች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በርካቶች በተገኙበት ሲከበር፣ የነበረውን መስተንግዶ በጥሩ ሁኔታና አገርን (ኢትዮጵያን) በሚያኮራ ሁኔታ ማዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ ዮናስ፣ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ክፍያ ሲጠይቁ በወቅቱ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ክፍያ ባለመፈጸሙ ምክንያት፣ ወ/ሮ አኪኮ በምክትል ሥራ አስኪያጃቸው አቶ እንግዳ ወርቅነህ ፊርማ የ42 ሚሊዮን ብር (1.7 ሚሊዮን ዩሮ) መተማመኛ ሰነድ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ የተጻፈው የገንዘብ መጠን በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚከፈላቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ሊከፈላቸው ባለመቻሉ ጉዳዩ ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. አምርቶ ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ተሰጥቶበታል፡፡ ፍርዱን የሰጡት ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋ አቶ ዮናስ ያቀረቡትን ክስና የተከሳሽ ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕንም የመቃወሚያ መልስ መርምረዋል፡፡

ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በጠበቆቹ አቶ ኃይሉ ንጋቱ፣ አቶ ጌታቸው ካሳሁንና በአቶ ወገኔ ካሳሁን የተወከለ ሲሆን፣ የመጀመሪያ መቃወሚያ ያቀረበው አቶ ዮናስ ከኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ጋር ያደረጉት ውል ወይም የተፈራረሙት ሰነድ ስለሌለ ክርክሩ ተዘግቶ እንዲሰናበት ነው፡፡ ሶልዳን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ከኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን፣ የኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው የተባሉት አቶ እንግዳ ወርቅ ምንም የፈረሙት የመተማመኛ ሰነድ እንደሌለና ፈረሙ የተባለው ሰነድ ሐሰተኛ መሆኑንም ጠበቆቹ ተከራክረዋል፡፡

አቶ እንግዳ ወርቅ እንኳን የ42 ሚሊዮን ብር ቀርቶ የ42 ብርም ሰነድ ቢሆን ብቻቸውን እንደማይፈርሙና ሶልዳን ከሚባለው ኩባንያ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ደጋግመው ተከራክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ እህት ኩባንያ የሚባል ጽንሰ ሐሳብም እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ ከሳሹ አቶ ዮናስም ክስ ከመመሥረት ባለፈ በቂ ማስረጃ ያላቀረቡና ያላስረዱ በመሆናቸው፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን ዘግቶ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ተከራክረውና ምስክሮችንም ቆጥረው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ወገኖች ካከራከረ በኋላ አቶ እንግዳ ወርቅ ፈርመውበታል የተባለውን መተማመኛ ሰነድና የመሥሪያ ቤቱን ማኅተም ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ፎሬንሲክ) በመላክ አስመርምሯል፡፡ የምርመራ ውጤቱም ፊርማው የአቶ እንግዳ፣ ማህተሙም የድርጅቱ መሆኑን አረጋግጦ ለፍርድ ቤቱ በመላኩ፣ ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ለአቶ ዮናስ 42 ሚሊዮን ብር ከመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ከሚታሰብ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቶ መዝገቡን ዘግቶት ነበር፡፡

ሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅረ የተሰኙት የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ጠበቆች ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሲሉ፣ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ‹‹ያስቀርባል›› በማለቱ የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የቃል ክርክር አድርገዋል፡፡ የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ጠበቆች ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታን በመተቸት፣ የአቶ ዮናስ ጠበቆች አቶ አመሐ መኮንንና አቶ ሰለሞን እምሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኦርኪድ ጠበቆችም የአቶ ዮናስን ምላሽ መሠረት አድርገው የቃል ክርክራቸውን አሰምተዋል፡፡

የኦርኪድ ጠበቆች በሥር ፍርድ ቤት ሲከራከሩ እንደነበረው ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ያነሱት መከራከሪያ ነጥብ፣ ኦርኪድ የውጭ አገር ኩባንያን ወክሎ ክፍያ ለመፈጸም የተዋዋለው ውል አለመኖሩን ነው፡፡ ኦርኪድ በሶልዳን ምክንያት ሊከሰስ እንደማይገባ የገለጹት ጠበቆቹ፣ በውጭ አገር ኩባንያ የሠራውን ሥራ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የማየት ሥልጣን እንደሌለው እየተናገሩ የሥር ፍርድ ቤት እንዳለፈውና የዳኝነት ስህተት እንደፈጸመ አስረድተዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ወ/ሮ አኪኮ የሶልዳን አክሲዮን አላቸው ያለ ቢሆንም፣ እሳቸው አክሲዮን ስላላቸው ድርጅቶቹ እህትማማቾች ናቸው የሚል የሕግ ድጋፍ እንደሌለውም አክለዋል፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች በተለያዩ አገሮችና ሕግ የተቋቋሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ወ/ሮ አኪኮ የኦርኪድ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንጂ የሶልዳን አለመሆናቸውን፣ ነገር ግን የሥር ፍርድ ቤት የሶልዳን ሥራ አስኪያጅ አድርጎ መፍረዱ ፍፁም ሐሰት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ‹‹የደከመ የፍትሕ አሰጣጥ ነው›› ያሉት ጠበቆቹ፣ ኦርኪድ ባልተዋዋለበት ሁኔታ ድንበር ዘለል ኩባንያ ባደረገው ስምምነት፣ ኦርኪድ ይክፈል መባሉ አግባብ አለመሆኑንና መተማመኛ ሰነዱ የተሰጠው ከኦርኪድ ነው ቢባል እንኳን፣ በምን ሁኔታ እንደተሰጠ በደንብ አለመመርመሩ አስገራሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የመተማመኛ ሰነዱ እንዲመረመር ያደረገ ቢሆንም፣ መርማሪው ተቋም ‹‹ፈራሚው ሲፈርም አይቻለሁ›› ዓይነት መልስ በመስጠቱ፣ እንደማይስማሙበትና በሌላ ተቋም እንደገና እንዲመረመር እየጠየቁ ክርክሩ ሳይጠናቀቅ ፍርድ መስጠቱ፣ ‹‹የመጀመሪያና በምሳሌነት የሚጠቀስ ፍርድ ነው›› ብለዋል፡፡ ከሳሻቸው ከጀርመን ለኦርኪድ የገዙትን ዕቃ ለሶልዳን ማስረከባቸውን መግለጻቸው እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮናስ ከጀርመን ኩባንያዎች ዕቃዎችን ስለማምጣታቸው ሦስት ሰነዶችን ማቅረባቸውን በተመለከተ የኦርኪድ ጠበቆች በሰጡት ምላሽ፣ ሰነዶቹ አቶ ዮናስ ዕቃ መግዛታቸውን ከመግለጽ ባለፈ የሚያስረዱት ነገር ስለሌለ ማስረጃ እንደማይሆኑ ገልጸዋል፡፡ ሰነዶቹ ሳይሆኑ ሌላ ክርክር ቢነሳና የድርጅቶቹ ባለቤቶች የሚጠሩበት ሁኔታ ቢኖር፣ እንደ ምስክርነት የሚቆጠሩ ካልሆኑ በቀር በሰነድነት የሚያገለግሉ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የማስረጃ ሰነድ ጀርመን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር (ቆንስላ) ተረጋግጦ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተልኮና ተረጋግጦ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተመዝግቦ መቅረብ ቢኖርበትም፣ ሰነዶቹ ግን ይኼንን እንደማያሟሉ አክለዋል፡፡ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ፈርመዋል የተባሉት አቶ እንግዳወርቅ፣ የወ/ሮ አኪኮ ረዳትና የኦርኪድ ተቀጣሪ ከመሆናቸው ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት ሹመትም ሆነ ውክልና እንደሌላቸውና የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔም ያልሾማቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአቶ ዮናስ ጠበቆች ቀደም ብለው ከገለጹት በተጨማሪ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ክርክር፣ ሰነዶችን መርምሮ የማረጋገጥ ሥልጣን የተሰጠው የአገሪቱ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ፎሬንሲክ) ብቻ በመሆኑ፣ የኦርኪድ ጠበቆች ምን ለማለት እንደፈለጉ ስላልገባቸው ጉዳዩን ለፍርድ ቤቱ መተዋቸውን ተናግረዋል፡፡ ኦርኪድ ያቀረበው ይግባኝ ከሥርዓት ውጪ መሆኑን የገለጹት የአቶ ዮናስ ጠበቆች፣ በይግባኙ ላይ በርካታ ርዕሶችን ሰጥቶ ተደጋጋሚ ሐሳብን ከማስቀመጥ ባለፈ በጉዳዩ ላይ የማያጠነጥን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለክሱ መሠረት ያደረጉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ እንግዳወርቅ የፈረሙበት የመተማመኛ ሰነድ መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ መተማመኛ ሰነዱን የሰጣቸው በኢትዮጵያ የሚገኘውና ወ/ሮ አኪኮ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑበት የሶልዳን እህት ኩባንያ ኦርኪድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይኼ ሲሠራበት የኖረና በአገር ደረጃ ከፍተኛ እምነት የሚጣልበት ሰነድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም ዝም ብሎ ያለፈው ነገር እንደሌለም አክለዋል፡፡ መተማመኛ ሰነዱ ሐሰት ነው ሊባል እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ከጥሬ ሀቁ ርቆ ፍርድ የሰጠ ለማስመሰል ውስብስብ የሆነ ክርክር ማቅረባቸው፣ ሌላ ሀቅ እንዲይዝ ለማድረግ መሆኑንም የአቶ ዮናስ ጠበቆች ገልጸዋል፡፡ ሶልዳን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ የኦርኪድ እህት ኩባንያ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው፣ መተማመኛ ሰነዱ እንዲሠራ ወ/ሮ አኪኮ መናገራቸውን አስረድተዋል፡፡ ገንዘቡን ሲጠየቁ ‹‹እህት ኩባንያ የሚባል ነገር የለም›› ማለት ተገቢ አለመሆኑንና ማታለል መሆኑንም አክለዋል፡፡

በሕግ የክርክር ሥርዓት ማለት የተጻፈው ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት የአቶ ዮናስ ጠበቆች፣ በሰበር ችሎት ውሳኔ የተሰጠበትን መዝገብ ቁጥር 39256 ስለእህት ኩባንያዎች የተሰጠውን ውሳኔ መመልከት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮናስ ከጀርመን ያስመጧቸው ሰነዶች በኤምባሲ አልፈውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተረጋግጠው፣ በሰነዶች ማረጋገጫና መመዝገቢያ ጽሕፈት ቤት የተመዘገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ሶልዳን የኦርኪድ እህት ኩባንያ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ በሌላ ችሎት ተከሰው እየተከራከሩበት ስለሚገኘው ጉዳይ የመዝገብ ቁጥር 130567 ፍርድ ቤቱ አስቀርቦ መመልከት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮናስ ቀርበው እንዲያስረዱ ፍርድ ቤቱ ጠይቋቸው፣ ከወ/ሮ አኪኮ ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ሥራውን እንዴት እንደሠሩም ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ አኪኮም ዕድል ተሰጥቷቸው ስለግንኙነታቸው አስረድተዋል፡፡ የሶልዳን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ 49 በመቶ ባለድርሻ መሆናቸውንና የኦርኪድ ዋና ሥራ አስኪያጅ መሆናቸውን በደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን በዓል አከባበር ወቅት፣ የኦርኪድ ሠራተኞቻቸውን ይዘው በመሄድ ብቻቸውን መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሶልዳንና ኦርኪድ ግን ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተለይ አቶ ዮናስ ውሉን ከሶልዳን ጋር ተፈራርመው እንዴት ከኦርኪድ ጋር ሊሠሩ እንደቻሉ ዘርዘር ያለ ጥያቄ አቅርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መዝገቡን መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ለሚያዝያ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች