አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በግንቦት ወር የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ውጤትን ላለመቀበል ከወዲሁ አዝማሚያ እያሳዩ መሆኑን፣ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ የካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአመዛኙ በግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫና በምርጫው ፕሮግራም እስካሁን የተጠናቀቁ ሒደቶች ዙሪያ አተኩረዋል፡፡
በዚህም መሠረት ምርጫ ቦርድ አቅዶ ከነበረው የመራጮች ቁጥር በመቶ በመቶ በላይ መራጮች ማለትም 35 ሚሊዮን ሕዝብ መመዝገቡን አድንቀዋል፡፡ በተቃዋሚዎች በኩል እየተደረገ ያለው የምርጫ ተሳትፎም ከቀድሞው የተሻለ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ 56 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጠቅላላው ከ800 በላይ ዕጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ የምርጫ ወቅት የመጀመሪያ ሒደት አንድነት ፓርቲን ለሁለት በመክፈል መንግሥትና ምርጫ ቦርድ ተንቀሳቅሰዋል መባሉን፣ እንደሁም የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች በምርጫው እንዳይሳተፉ ያልተገቡ መሥፈርቶችን በማስቀመጥ ከምርጫው እንዲወጡ ተደርጓል በሚል የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በተመለከተም ሚኒስትሩ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹ምርጫ ቦርድ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲን (አንድነት) ሊያፈርሰው ፈልጎ የነበረ ከሆነ በመጀመሪያው ቀን ሕግ አላከበረም ብሎ መቆለፍ ይችል ነበር፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በፓርቲው ውስጥ የነበረውን አለመግባባት ሕዝቡ እስከሚሰለቸው ድረስ ምርጫ ቦርድ ታግሷል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ መረጋጋትና የኢኮኖሚያዊ ዕድገት በንፅፅር በማቅረብም ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲማሩበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ዕድገት ጎረቤት አገሮችን ሁሉ እያስተሳሰረ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከውስጥ የሚመነጭ እንጂ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የማይሰማ በመሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም ለችግሮቻቸው ውጫዊ ምክንያት ከሚፈልጉ ይህንን ቢያደርጉ ይሻላል፤›› ብለዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲን በተመለከተ ተረጋግቶ ፓርቲው የውስጥ ችግሩን እንዲፈታ ነው ያደረገው ብለው፣ ይህንን በማድረጉም ቢያንስ ፓርቲውን ማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ግለሰቦች ናቸው የመሪነት ቦታውን የተለዋወጡት፤›› ብለዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ከምዝገባ መሰረዝን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በመጀመሪያም ቢሆን ሕግን አክብሮና ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል፡፡ ከሌላ ፓርቲ ይፋዊ መልቀቂያ ሳይወስዱ እንዲሁም እስከነጭራሹ ከፓርቲ ለመልቀቅ ፍላጎት እንኳን ያላሳዩ ግለሰቦችን ጭምር፣ ሰማያዊ ፓርቲ በዕጩነት መዝግቦ በመገኘቱ መሰረዛቸውን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው ተሰረዘብኝ የሚላቸውን ዕጩዎች ስምና የአባልነት ማስረጃ እንዲያመጣ ቢጠየቅም፣ እስካሁን ይህንን ማድረግ አለመቻሉን አቶ ሬድዋን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዜጎች ሳይፈቅዱና ማንም ሳይጠይቃቸው ሰማያዊ ፓርቲ መዝግቧቸው የተገኙ አሉ፡፡ ይህንን ከሕግ ውጪ የሆነ ተግባር ማስተካከል ነው ምርጫ ቦርድ ያደረገው፤›› ብለዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ባሉት 23 የምርጫ ጣቢያዎች በሁሉም ዕጩዎቹን ማቅረቡን፣ ከእነዚህ ውስጥ በአራት ቦታዎች ብቻ አለመቻሉንና ይህም በሕጉ መሠረት በአንድ የምርጫ ጣቢያ ከ12 ዕጩዎች በላይ መወዳደር ስለማይችሉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ከ12 በላይ ዕጩዎች በሚኖሩበት ጊዜ በዕጣ የመለየት ሥርዓት መኖሩን የጠቆሙት አቶ ሬድዋን፣ ይህ ከ23 የምርጫ ጣቢያዎች 18 በሚሆኑት ላይ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት በ18 ጣቢያዎች እንዲወዳደሩ የቀረቡ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ዕጣ አውጥተው ማለፋቸውን፣ ነገር ግን አጋጣሚ ሆኖ በአራት ምርጫ ጣቢያዎች በተለይም ሊቀመንበሩ በሚወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ ዕጣው ባለመሳካቱ፣ ኢዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥቱን የጣሰ መባሉ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ፓርቲዎች በዚህ የምርጫ ወቅት እያሳዩ ካሉት ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት መቆጠብ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ ላይ እምነት የለኝም እያሉ ምርጫ ለመወዳደር የሚመጡ፣ ፍርድ ቤት ገለልተኛ አይደለም እያሉ በፍርድ ቤት ክስ መመሥረት የሚፈልጉ ፓርቲዎች ውጥናቸው ሌላ መሆኑን ነው አቶ ሬድዋን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት፡፡
‹‹ምርጫውን ለሌላ ግብ መንጠሪያ እያደረጉ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የምርጫውን ውጤት የመቀበል ፍላጎት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ውጤቱን ተንተርሰው ለሚያነሱት አቧራ ከወዲሁ ደረቅ ሳር የመጎዝጎዝ ሥራ ነው እያከናወኑ ያሉት፤›› በማለት ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው ብለዋል፡፡