Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ላይ የግድያ ሙከራ ታቅዶ እንደነበር...

ከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ላይ የግድያ ሙከራ ታቅዶ እንደነበር ይፋ ሆነ

ቀን:

– የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃውን በተመለከተ ዝምታን መርጧል

– የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋምን አድንቋል

እ.ኤ.እ. በ2012 የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የኮሚሽኑን ሊቀመንበርነት በተረከቡ ጥቂት ቀናት ውስጥ፣ በአዲስ አበባ የግድያ ሙከራ ታቅዶባቸው እንደነበር ያፈተለኩ የደኅንነት የመረጃ ልውውጦችን ጠቅሶ አልጄዚራ ዘገበ፡፡

- Advertisement -

አልጄዚራ ባለፈው ረቡዕ ያፈተለኩ የደኅንነት መረጃዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 2012 የአዲስ አበባ ሥራቸውን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ የግድያ መኩራ ሊደረግባቸው እንደሆነ፣ ከዚህ ጀርባም ስሟ ያልተጠቀሰ አንድ አገር መኖሯን የሚገልጽ መረጃ የደቡብ አፍሪካ የደኅንነት ተቋም እንደደረሰው ዘገባው ያስረዳል፡፡ የደኅንነት ተቋሙም መረጃውን በፍጥነት አዲስ አበባ ለሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ እንዳስተላለፈ ያስረዳል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር በፍጥነት ዶ/ር ድላሚኒ ዙማን በማግኘት፣ ለደኅንነታቸው ሲባል በጥበቃ አገልግሎቱ ላይ መጠነኛ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል እንደጠቆሟቸው የአልጄዚራ ዘገባ ጠቁሟል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኝ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሙያ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት የውጭ የደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ለአቶ ሃደራ አበራ  የታቀደውን የግድያ ሙከራ ሥጋት እንደነገሯቸው ይገልጻል፡፡

በዚህም መሠረት ሁለቱ የደኅንነት ባለሙያዎች ለሊቀመንበሯ የሚደረገውን የደኅንነት ጥበቃ አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ ለማጠናከር መስማማታቸውን፣ በዚህ መሠረትም አራት ተጨማሪ ጠባቂዎች ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ ወዳረፉበት ሆቴል እንዲሄዱ መደረጉን መረጃው ያስረዳል፡፡

የግድያ ሙከራው በሚጠበቅበት ቀን የደኅንነትና የስለላ ባለሙያዎች ያደርጉ የነበሩት በንቃት መከታተል፣ መጠበቅና ያሰማሩት የጥበቃ ኃይል የእሳቸውን ሕይወት መታደግ እንደሚችል ተስፋ ማድረግ ብቻ እንደነበር ዘገባው ያመለክታል፡፡

ውጥረቱ በአዲስ አበባ በዚህ ሁኔታ በቀጠለበት ወቅት የደቡብ አፍሪካ የደኅንነት ኃላፊ ጀነራል ቲ ናይመቤ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ሰብስበው፣ ‹‹ስሟ ያልተጠቀሰ አገር ከግድያ ሙከራው ጀርባ እንደምትገኝ›› እንዲሁም ‹‹በሌላ አካባቢም ተመሳሳይ የግድያ ሙከራ ሊኖር እንደሚችል›› ማስጠንቀቃቸውን የአልጄዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ ጥቃቱ ይደረጋል የተባለበት ቀን በሰላም በማለፉ የደቡብ አፍሪካ የደኅንነት ባለሙያዎች የኢትዮጵያ አቻዎቻቸውን እንዳገኙዋቸው መረጃው ያመለክታል፡፡ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የውጭ ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሃደራ፣ የተጠርጣሪዎችን ስም በየመግቢያ ኬላዎች ለማጣራት እንደተሞከረ እንዳብራሩላቸው ዘገባው ይገልጻል፡፡

በሱዳን ድንበር መግቢያ በኩልም የተጠርጣሪዎችን ስም በማስተያየት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንደሆነ ለማጣራት ተሞክሮ፣ ተመሳሳይ ስም አለመገኘቱን እንደገለጹ ዘገባው ያመለክታል፡፡

የደኅንነት ኃላፊው ሱዳን እንደዚህ ዓይነት ተግባር ውስጥ ልትገባ እንደማትችል፣ ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን በአዲስ አበባ በ1987 ዓ.ም ለመግደል በተደረገው ሙከራ ከፍተኛ ዋጋን መክፈሏን እንዳስረዱ መረጃው ያመለክታል፡፡

አቶ ሃደራ የደቡብ አፍሪካ የደኅንነት ሠራተኛችን በግብፁ ፕሬዚዳንት ላይ ከተደረገው መኩራ ውጪ በአዲስ አበባ እንዲህ ዓይነት ሥጋት ኖሮ እንደማያውቅ በመግለጽ፣ በድጋሚ እርግጠኛ እንደሆኑ መረጃ እንደሰጧቸው ዘገባው ያመለክታል፡፡

እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 29 ቀን 2012 ከኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋም የተላከ መረጃ የሚያመለክተው፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማቶች ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት በሚገጥማቸው ወቅት የሚያርፉበት ሁለት ደኅንነታቸው የተጠበቅና የማይደፈሩ ቦታዎች የተዘጋጁ መሆኑን የሚያመለክት መሆኑን የአልጄዚራ ዘገባ ይገልጻል፡፡

በአጠቃላይ ሁለቱም የደኅንነት ተቋማት ሥጋቱን ለማክሸፍ ዝግጁ እንዳልነበሩ የሚገልጸው መረጃው፣ በተለይ የደቡብ አፍሪካ የደኅንነት ተቋም የግድያ ሙከራውን በማክሽፍ በቁጥጥር ለማዋል አለመቻሉን እንዳመነ ዘገባው ያመለክታል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋም መረጃው በደረሰው ወቅት ሙከራውን ለማክሸፍና በቁጥጥር ሥር ለማዋል በቂ ጊዜ አልነበረውም፡፡ ቢሆንም ለደረሰው መረጃ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ተከታትሎታል፤›› ይላል አልጄዚራ የጠቀሰው ያፈተለከ የደኅንነት መረጃ ልውውጥ፡፡ ከዚህ በኋላም ቢሆን ክትትሉ እንደቀጠለ፣ ነገር ግን እስካሁን ተጠርጣሪዎቹን የተመለከተ መረጃ አለመገኘቱን ዘገባው ያስረዳል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ የተባለውን የግድያ ሙከራና በአጠቃላይ በአልጄዚራ ዘገባ ላይ የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በጉዳዩ ላይ በመንግሥት የተያዘ አቋም ስለሌለ አስተያየት መስጠት አልችልም፤›› ብለዋል፡፡

      በመንግሥት አቋም ሲያዝና መረጃ መስጠቱ ተገቢ ሲሆን ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ የደኅንነት ሥጋቱ የነበረው ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበረና በአሁኑ ወቅት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

‹‹የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በወቅቱ ላደረገውና አሁንም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርና ሌሎች ለኅብረቱ ዲፕሎማቶች የሚሰጠውን የደኅንነት አገልግሎት በእጅጉ ያደንቃል፤›› ብሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...