ሲኖትራክ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ቻይና ሠራሽ የጭነት ተሽከርካሪ ምክንያት የሚከሰተው አደጋ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ የአደጋውን መነሻ በመለየት ዕርምጃ ለመውሰድ መንግሥት ጥናት የሚያካሂድ ግብረ ኃይል ማቋቋሙ ተሰማ፡፡
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ሲኖትራክ የተባለው ተሽከርካሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሚያደርሰው አደጋ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሆኑን በመረዳቱ፣ ለአደጋው መንስዔ የተባሉትን ምክንያቶች የሚያጠና ቡድን አሰማርቷል፡፡ ቡድኑ ጥናቱን በአጭር ጊዜ አጠናቆ እንዲያቀርብ ተነግሮታል፡፡ ምንጮቹ ‹‹አስቸኳይ›› የተባለው ጥናት ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅና ከጥናቱ በኋላ ስለሚወሰዱ ዕርምጃዎች ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ በዋነኝነት የችግሮቹ መነሻ ከተሽከርካሪው የቴክኒክ ክፍሎች ወይስ ከአሽከርካሪዎች መሆኑን አጥንቶ ያቀርባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሲኖትራክ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ችግሩን ከተሽከርካሪው የቴክኒክ ባህሪይ ጋር ያያይዙታል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በአንድ አስመጪ ድርጅት የሚሠሩ መካኒክ ችግሩን ሲገልጹ፣ ‹‹ተሽከርካሪው የተሻለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቢኖረውም፣ የፍሬን መቆጣጠሪያው ችግር ያለበት በመሆኑ፣ የተሽከርካሪውን ፍጥነት ከክብደቱ አንፃር መቆጣጠር ስለማይቻል ብዙ ጊዜ ለአደጋ ተጋላጭ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ የተሽከርካሪው ፍሬን በቶሎ የሚታዘዝ ባለመሆኑ፣ አሽከርካሪዎች ባህሪውን ቀድመው ካመረዳት የተነሳ መቆጣጠር ይሳናቸዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ዘለዓለም ክፋይ የተባሉ የግል ተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ ግን፣ ችግሩ ከአሽከርካሪዎች የሥልጠና ማነስና ልማዳዊ የማሽከርከር ባህሪይ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መኪናዎቹ ዘመናዊና ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን አሽከርካሪዎች ቀድሞ ባላቸው የማሽከርከር ልምድ ብቻ ስለሚያሽከረክሩና ለእንዲህ ዓይነት ተሽከርካሪ ምንም ዓይነት የተለየ ሥልጠና ስለማይወስዱ ለችግሩ ይጋለጣሉ፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የትራፊክ አደጋን በተመለከተ መረጃዎችን በመስጠት የሚታወቁት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ በበኩላቸው፣ አደጋው በአብዛኛው የሚደርሰው ከተሽከርካሪው የቴክኒክ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ከአሽከርካዎች ብቃት ማነስ መሆኑን የአብዛኞቹ የትራፊክ ፖሊሶች ሪፖርት እንደሚያመለክት አስታውቀዋል፡፡
ረዳት ኢስፔክተሩ ምንም እንኳ ወቅታዊ የትራፊክ አደጋዎችን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በመስጠትና የግንዛቤ ትምህርቶችን በማሰራጨት ቢታወቁም፣ ራሳቸው በቅርቡ የሲኖትራክ አደጋ ሰለባ ሆነው እንደነበርና በአጋጣሚ መትረፋቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
በሌላ በኩል ችግሩ ከተሽከርካሪዎችና ከአሽከርካሪዎች አልፎ እንደሚታይና ከገበያው ሥርዓት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ መንግሥት ጥናቱን ሰፋ አድርጎ ማየት እንዳለበትም የሚገልጹ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በተለይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከተሽከርካሪው ዋና አከፋፋዮች አንዱ የሆነው አግታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማይ ገብረአረጋዊ፣ ‹‹ችግሩ በስፋት ሊታይ ይገባዋል፡፡ በተለይ መንግሥት ተሽከርካሪዎቹ ወደ አገር ውስጥ ስለሚገበቡበት ሁኔታ፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች አገባብና አጠቃቀም፣ እንዲሁም በገበያው ውስጥ ያለውን አጠቃላይ አሠራር በጥንቃቄ ሊያየው ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለተሽከርካሪው እዚህ አገር የሚከናወነው የመገጣጠም ሥራ ትክክል ነው ወይ ብሎ ሊያጣራም ይገባዋል ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ግርማይ፣ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ክፍተት እንዳለም ተናግረዋል፡፡
የትራፊክ አደጋ በየዕለቱ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ መምጣቱን አብዛዎቹ የሚስማሙበት ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሲኖትራክ ተሽከርካሪ የሚደርሰው አደጋ እየከፋ መምጣቱን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ችግሩ ከአዲስ አበባ አልፎም የክልል ቢሮዎችንም እያሳሰበ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እንደ ኃላፊው የካቲት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የክልሎች ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ተገኘተው ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ በየክልላቸው እያደረሰ ያለውን ጉዳት፣ ለባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ በተለይ የኦሮሚያ ክልል ተወካይ በክልላቸው በአንድ ወር ውስጥ ደረሱ ያሉዋቸውን አራት አሰቃቂ አደጋዎች በማውሳት፣ የችግሩን አሳሳቢነት ማስረዳታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት 12 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ቡራዩ አካባቢ ከሲኖትራክ ጋር ተጋጭቶ ሚኒባሱ መሉ በሙሉ በመቃጠሉ፣ የ11 ተሳፋሪዎች ሕይወት ማለፉን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ዓመት ኅዳር ወር ከአዳማ ወደ አዋሽ ይጓዝ የነበረ አይሱዙ አውቶብስ ከሲኖትራክ ጋር በመጋጨቱ ከ38 በላይ ተሳፋሪዎች መሞታቸው ለአብነት ይጠቀሳል፡፡