Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የምርጫው ውጤት ተዓማኒነት የሚኖረው

  የጨዋታው ሕግ ሲከበር ብቻ ነው!

  እነሆ የዘንድሮ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጊዜ ሰሌዳው መሠረት የምረጡኝ ቅስቀሳና በአንዳንድ መድረኮች ክርክሮች ጀምረዋል፡፡ ከዚህ ወቅት ጀምሮ እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ ያሉት ጊዜያት ጤናማ የሆኑ የምርጫ ውድድሮች ይካሄድባቸው ዘንድ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉ መሠረት ሥራቸውን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የምረጡኝ ቅስቀሳውም ሆነ ክርክሩ በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ተካሂዶ፣ መራጩ ሕዝብ የተለያዩ አማራጮችን አወዳድሮ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ሰላማዊው ሒደት ቅድሚያ ሊያገኝ የግድ ይለዋል፡፡

  ምርጫው በሰላምና በዴሞክራሲያዊ አገባብ ይከናወን ዘንድ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለሕግ የበላይነት ነው፡፡ ሕግ በተከበረ ቁጥር የኃይል ተግባራትና አለመተማመን የሚፈጥሩ ሸፍጥ የተሞላባቸው ድርጊቶች ቦታ አይኖራቸውም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብም የሚፈልገው በነፃነት ተወዳድረው አዋጭ የሆኑ የፖሊሲ አማራጮችን የሚያቀርቡ ፓርቲዎችን መገምገም ነው፡፡ ለሕዝቡ ግምገማ ጠቃሚ ግብዓት ከሚያቀርቡ መድረኮች መካከል የምርጫ ቅስቀሳና ክርክር ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በሰላማዊ ትግል እናምናለን ብለው በምርጫው የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምንም ነገር በላይ የምርጫ ሕጎችን ማክበር አለባቸው የሚባለው፡፡

  ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለምርጫው በስኬት መጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና አለባቸው፡፡ ምርጫው የተወዳዳሪ ፓርቲዎችና የመራጩ ሕዝብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የመወዳደሪያ ሜዳው ለሁሉም በእኩልነት ተመቻችቷል የሚለው የዋናው አጫዋች ምርጫ ቦርድ ትልቅ ኃላፊነትም ነው፡፡ በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር ሲገጥማቸው፣ ዕጩዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ሲንገላቱ ሕግ እንዲከበር የማስደረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈራቸውን ስተው የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉን ሲጥሱ ሕግ ማስከበር ይኖርበታል፡፡

  የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ሥነ ምግባር ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 662/2002 በትክክል ተግባራዊ መደረግ ከቻለ እንደሚባለው ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ከመጠናቀቁም በላይ፣ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አመኔታና አርዓያነት ያገኛል፡፡ የአዋጁን መውጣት አስፈላጊነት በተመለከተው ክፍል ውስጥ የተብራሩት መሠረታዊ ጉዳዮችን በአፅንኦት ለሚመለከት ማንም ሰው በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ማግኘት ይችላል፡፡ የሕዝብ ፍላጎት የሚንፀባረቁባቸው በርካታ ጉዳዮችን አቅፎ ይዟል፡፡ ጠቃሚ የጨዋታ ሕግ ነው፡፡

   በአዋጁ ውስጥ ከተካተቱ ዋና ጉዳዮች መካከል በአገሪቱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ መሆናቸው ለሠለጠነ፣ ለሕጋዊና ለዴሞክራሲያዊ ትግልና ውድድር ፋይዳ እንዳለው፣ እንዲሁም የሕዝብ ሥልጣን አመንጪነት፣ ባለቤትነትና ተቆጣጣሪነት መብት አጠናክሮ ለማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ይወሳል፡፡

  ምርጫ ቦርድና የፍትሕ አካላት ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በገለልተኝነት ሕዝብን ማገልገል እንዳለባቸው፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተግባሩን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን እንዲያከናውን መደረጉን ከግንዛቤ ያስገባል፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት የግልጽነት፣ የታማኝነትና የተጠያቂነት ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው የተቀበሉና ተግባራዊነቱንም ለማክበርና ለማስከበር ቃል የገቡ መሆኑን በማመን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተፈጻሚነቱ መቆም እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡

  የፖለቲካ ፓርቲዎች በተስማሙባቸው ጉዳዮች በጋራ እየሠሩና በልዩነታቸው ላይ ደግሞ በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ ትግል በማካሄድና በሕግ መሠረት የተካሄዱ ምርጫዎች ትክክለኛ ሒደት ውጤት የሕዝብ መሆኑን በፀጋ ተቀብለው መጓዝ፣ በአገር ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚያካሂዱት ውድድር ከጥላቻና ካለመተማመን የፀዳና ጤናማ ግንኙነት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊነት ያብራራል፡፡ የሕዝብን ውሳኔ በመፃረር በመንግሥት ሥልጣን ላይ መቆየትም ሆነ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚደረጉ ማናቸውም የአገር ውስጥና የውጭ እንቅስቃሴዎች፣ ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን በአፅንኦት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ያትታል፡፡

  በተጨማሪም ማንኛውም ለምርጫ አገልግሎት ሊውል የሚችል በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ የሚገኝ ሀብት፣ ንብረትና የአካባቢ መስተዳድር አካላት አገልግሎቶች፣ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕግ መሠረት በፍትሐዊነትና ያለ አድልኦ የሚሰጥበትን አሠራር ማጠናከር አስፈላጊነት ያወሳል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመምረጥና የመመረጥ መብቱን ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ወይም እንቅፋት እንዳይደረግበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡  

  የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁ በመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓት የሚመረጥ መንግሥት ሕጋዊነት የሚመሠረትባቸውን መርሆች ሲያብራራ፣ መራጮች በምርጫ ዘመቻ አማካይነት ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎችና ዕጩዎቻቸው ባህሪ የተሟላ መረጃ አግኝተው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ መድረስ አለባቸው ይላል፡፡ መራጮች በነፃነት፣ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለ ፍርኃት፣ ያለ ተፅዕኖ፣ ያለ ጫና ወይም ከጉቦ ነፃ በሆነ ሁኔታ ድምፅ መስጠት አለባቸው ይላል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅን ልቦና እየተመሩ የምርጫ ሥነ ምግባር መርሆዎች እንዲከበሩ፣ ምርጫው የመላው ሕዝብ ነፃና ተቀባይነት ያለው ውሳኔ መገለጫ ሆኖ እንዲታወቅ፣ የመራጩ ሕዝብ ውሳኔም በሁሉም የተከበረ እንዲሆን መሥራት አለባቸው ይላል፡፡

  ከላይ የተዘረዘሩትን የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉን መሠረታዊ ጉዳዮች በአንክሮ ስንመለከት፣ ለሕዝቡ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚረዱ ዋና ዋና ጭብጦችን ይዟል፡፡ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅትም ሆነ በክርክሮቻቸው ጊዜ እነዚህን መሠረታዊና ጠቃሚ ጉዳዮች ይዘው ከተንቀሳቀሱ አላስፈላጊ ግብግቦች አይፈጠሩም፡፡ በዚህ የምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ራሳቸውን አዘጋጅተው ሲገቡ፣ የሥነ ምግባር ድንጋጌዎቹን በሚገባ በማክበር መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

  ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም እስኪጠናቀቅ ድረስ ሕግን ከማክበር በዘለለ አላስፈላጊ ተግባር ከመፈጸም መቆጠብ የዴሞክራትነት መገለጫ ነው፡፡ በምርጫ ቅስቀሳውም ሆነ በክርክሩ ተፎካካሪነትን በብቃት የሚያሳዩበት እንጂ፣ የሕገወጥ ተግባራት ማራመጃ መሆን የለበትም፡፡ የምረጡኝ ፉክክሩ የተሻሉ ሐሳቦችና አመለካከቶች ነጥረው የሚወጡበት እንጂ፣ ለይስሙላ የተገባበት እንዳይሆን ጥንቃቄ ያሻል፡፡ የምርጫው ውጤት ተዓማኒነት የሚኖረው የጨዋታው ሕግ ሲከበር ብቻ ነው!  

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...

  ኢትዮጵያ በብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፓርላማው አሳሰበ

  በብድር የተገኘ ገንዘብ በሥልጠናና ውሎ አበል መልክ እንዳይባክን ተጠየቀ የሕዝብ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...