Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተሽከርካሪ አደጋ መብዛት ያሳሰበው መንግሥት ለባለድርሻዎች ጥሪ አቀረበ

የተሽከርካሪ አደጋ መብዛት ያሳሰበው መንግሥት ለባለድርሻዎች ጥሪ አቀረበ

ቀን:

  • ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ብቻ 260 ሰዎች ሞተዋል
  • ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል

ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣው በተሽከርካሪ አደጋዎች በሰውና በንብረት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እያሳሰበው የመጣው መንግሥት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር አደጋን በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ጥሪ አቀረበ፡፡

የተሽከርካሪ አደጋ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ከመቅጠፉም በተጨማሪ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም መንግሥት፣ ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ተባብረው መሥራት የግድ እንደሚላቸው የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል አሳስበዋል፡፡

የተሽከርካሪ አደጋ በአዲስ አበባ ወይም በከተሞች ብቻ ሳይሆን፣ በፌዴራል ደረጃ አሳሳቢ እየሆነና በየጊዜው መጠኑ እየጨመረ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ሁሉም ተባብሮና ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ችግሩን መቀነስ ካልቻለ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለንብረቱ፣ አሽከርካሪው፣ ኅብረተሰቡና ትራፊክ ፖሊስ ተባብረው የችግሩን መንስዔ በደንብ በማጥናትና መፍትሔ በመፈለግ፣ ችግሩን መቀነስና ማቆም እንደሚገባ ጠቁመው፣ መንግሥትም በጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት የ260 ሰዎች ሕይወት በተሽከርካሪ አደጋ ማለፉን የጠቆሙት ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ረዳት ባለሙያ፣ ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ናቸው፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ የ196 ወንዶችና የ64 ሴቶች ሕይወት እንዲያልፍ ያደረገው የተሽከርካሪ አደጋ፣ ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም እንዲወድም ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

አሽከርካሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል የሚፈልጉት ትራፊክ ፖሊስ ከሚጥልባቸው ቅጣት እንጂ፣ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመጠበቅ አለመሆኑን የገለጹት ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ፣ ከጥቂት ጨዋና ሕጉ የገባቸው ሕግ አክባሪ አሽከርካሪዎች በስተቀር፣ አብዛኛዎቹ ሕግ ለማክበር ወይም ለሕዝብ አሳቢ የሚመስሉት ትራፊክ ፖሊስ ቆሞ ሲያዩ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከትራፊክ ፖሊስ በተጨማሪ ዓለም የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ቁጥጥሩን ማዘመን አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፣ ሲሲቲቪ ካሜራና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ የትራፊክ ፖሊስ በሌለበት ቦታ ሁሉ ቁጥጥር ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በቅርብ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ የገባው የቻይና ሥሪት የሆነው ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ፣ ፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ልዩ የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም የችግሩን መንስዔ ለማጥናት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን ባለሥልጣኑ የያዘውን አቅጣጫ በመቃወም አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰጥተዋል፡፡

ተሽከርካሪው (ሲኖትራክ) በራሱ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለበት የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በኢትዮጵያ በተለይ አሁን እየተሠሩ ባሉ የመንገድ ግንባታዎች ላይ የተሰማሩ በርካታ ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች፣ በአንዳንድ ብቃት ባላቸው ኢትዮጵያውያን አሽከርካሪዎችና ቻይናውያን በአግባቡ እየተገለገሉበት ነው ብለው፣ ተሽከርካሪው ካለው ጉልበት የተነሳ ለሥራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ተሽከርካሪው በቴክኒክም ሆነ በይዘት በኩል ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው በየዕለቱ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ የተሽከርካሪ አደጋ እየደረሰ ያለው በሲኖትራክ መሆኑን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ‹‹ይኼ የሚያሳየው የተሽከርካሪውን ሳይሆን የአሽከርካሪዎችን ችግር መሆኑን ነው፤›› ሲሉ ችግሩ የአሽከርካሪዎች መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አንድ አሽከርካሪ ሁለተኛ የመንጃ ፈቃድ (ቀላል አውቶሞቢሎችን ለማሽከርከር የሚያስችል) ለማውጣት የትራፊክ ደንቦችንና ምልክቶችን ከማጥናቱም በተጨማሪ፣ የማሽከርከር ብቃቱን በደንብ የሚለካበት ሥልጠና ወስዶ፣ ሁለቴና ከዚያም በላይ በተግባር ፈተና ወድቆ፣ በደንብ ከሠለጠነ በኋላ ያገኝ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን አንድ አሽከርካሪ ራሱ ካልፈራ በስተቀር በአንድ ጊዜ አምስተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያገኝበት ዕድል እንደተፈጠረለት ጠቁመው፣ ‹‹እንኳን ሲኖትራክን ቀርቶ ቀላል የቤት አውቶሞቢልን የማሽከርከር ብቃት አይኖረውም፤›› ሲሉ፣ የችግሩ መንስዔ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተሽከርካሪውን የቴክኒክ ብቃት ለማስጠናት ኮሚቴ በማቋቋምና የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ተሽከርካሪ ለማጥናት ከማሰብ ይልቅ የአሽከርካሪዎቹን የማሽከርከር ብቃት፣ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች የማሠልጠን ብቃት፣ የትራፊክ ፖሊሶች የመቆጣጠር ብቃትና የመንገዶችን ብቃት ማጥናቱ የተሻለ እንደሚሆን መክረዋል፡፡

ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡና ረዳት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤልም አስተያየት ከሰጡት የኅብረተሰብ አካሎች ጋር ተመሳሳይነት ያለው አስተያየት በተለይ በአሽከርካሪዎች ብቃትና በትራፊክ ፖሊሶች ቁጥጥር ላይ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በአፍሪካ የተሽከርካሪዎች ብዛት ከዓለም ሁለት በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ቢሆንም፣ በአኅጉሪቱ የሚከሰተው አደጋ ግን የ20 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጥናቶች እንደሚያመለክቱ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ችግሩ የባሰ ስለሚሆን መንግሥት፣ ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ተባብረው በመሥራት ችግሩን ማጥፋት ባይችሉ እንኳን መቀነስ ተገቢ መሆኑን አክለዋል፡፡

         

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...