Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከግል ሆስፒታሎች 46 በመቶው በአገልግሎት ጥራት ቀይ ተሰጣቸው

ከግል ሆስፒታሎች 46 በመቶው በአገልግሎት ጥራት ቀይ ተሰጣቸው

ቀን:

  • የጤና ተቋማት የአገልግሎት ጥራት ደረጃ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል

የአዲስ አበባ የመድኃኒት፣ የምግብና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን በ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከሦስት ወራት በፊት ያጠናቀቀው ግምገማ እንደሚያሳየው፣ ከ34 የግል ሆስፒታሎች 46 በመቶ የሚሆኑት በዝቅተኛ የአገልግሎት ጥራት ቀይ እንደተሰጣቸው ተገለጸ፡፡

ይህ ይፋ የሆነው የካቲት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ‹‹የግል ሕክምና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በአዲስ አበባ›› በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ ነው፡፡

በጥቅሉ በአዲስ አበባ የጤና ተቋማት የአገልግሎት ጥራት ቁጥጥር የሚደረገው የተቋማቱን ቦታ (ቅጥር ግቢ)፣ የባለሙያ ስብጥር፣ አሠራር ሁኔታና ውጤት መሠረት ባደረገ አሠራር መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት የግል የጤና ተቋማቱ የአገልግሎት ጥራት በተለይም ከሕዝብ ተቋማቱ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ሊባል ቢችልም፣ በመንግሥት የተቀመጠውን የአገልግሎት ጥራት ደረጃ ከማሟላት አንፃር ተቋማቱ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በውይይት መድረኩ ላይ በቀረበ ጥናት ተመልክቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከተገመገሙት 34 ሆስፒታሎች 46 በመቶ የሚሆኑት በዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ቀይ ሲያገኙ፣ 50 በመቶ የሚሆኑት የአገልግሎት ጥራታቸውን ሊያሻሽሉ ይችላሉ በሚል ቢጫ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አራት በመቶው ብቻ ደግሞ የጥራት ደረጃውን በማሟላት አረንጓዴ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ የግሉ የሕክምና አገልግሎት ዘርፍ የከተማውን ጥሩ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን ዝቅተኛ ገቢ ያለውንም እያገለገለ መሆኑን የሚያሳየው ጥናቱ፣ 44 በመቶ የሚሆነው ዝቅተኛ ገቢ ያለው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኘው በግሉ ዘርፍ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ይህን ያህል መጠን ያለው ዝቅተኛ ገቢ ያለው ወደ ግል ተቋማት የሚሄደው መርጦ ሳይሆን አማራጭ በማጣት ተገድዶ እንደሆነ የገለጹም አሉ፡፡

በተለያየ ምክንያት የግሉ የጤና አገልግሎት ዘርፍ፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ሽፋንን በማሻሻል ረገድ አስተዋጽኦ አበርክቷል ቢባልም የአገልግሎት ጥራቱ ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት ሁኔታ እንዴት አስተዋጽኦ አበርክቷል ሊባል ይችላል? የሚል ክርክር ያነሱም አሉ፡፡

በአዲስ አበባ መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በ34 የግል ሆስፒታሎች ላይ በተደረገው ግምገማ መሠረት፣ ለሆስፒታሎቹ ከሥር ከሥር አስተያየት የተሰጣቸው ሲሆን፣ እስካሁን የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ ዕቅድ እንዲያቀርቡ በተነገራቸው መሠረት ያቀረቡ ሁለት መሆናቸውን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተጠቃሚው ላይ ጫና የሚያሳድርና ትርፍን ዒላማ ያደረገ የተጋነነ የአገልግሎት ዋጋ፣ የራሳቸው ቋሚ ሐኪም አለመኖርና ታካሚ እንዳይመለስ በሚል ጠቅላላ ሐኪሙ የፅንስና የማህፀን ሕክምና ሐኪም፣ የጤና መኮንንም እንደ ሐኪም የሚሠራበት አሠራር መኖር፣ ዘመን ያለፈባቸውን መሣሪያዎች መጠቀም፣ የግል የጤና ተቋማት አስተዳደር በቦርድ የሚተዳደር መሆን ሲኖርበት የባለቤቶች ፈላጭ ቆራጭነት የነገሠበት መሆኑ፣ በጥናቱ ላይ ግምገማዊ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጋበዙት ዶ/ር ብርሃነ ረዳኢ ያነሷቸው ነጥቦች ነበሩ፡፡

የአዲስ አበባ የመድኃኒት፣ የምግብና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ ሲስተር ገነት ያይኑ በግሉ የሕክምና ዘርፍ በተለይም ከዋጋ ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች ሲነሡ፣ በመንግሥት ተቋማት ከሚከፈለው ዋጋ ጋር ንፅፅር ማድረግ አሳሳች ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት ተቋማት የሚጠየቀው ዋጋ መንግሥት ድጐማ የሚያደርግበት በመሆኑ እንደ ትክክለኛ ዋጋ ለንፅፅር የማይሆን እንደሆነ የገለጹት ሲስተር ገነት፣ ሕክምና በራሱ ውድ መሆኑም ታሳቢ ሊደረግና ንፅፅሩም ትክክለኛ ዋጋ ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የቁጥጥር ሥርዓቱ ራሱ የአገልግሎት ጥራትን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው የሚል አስተያየታቸውን የሰነዘሩ ሲኖሩ፣ የግሉ የጤና አገልግሎት ዘርፍ በፖሊሲ መመራት ይገባዋል ያሉም አሉ፡፡ የዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ደረጃን በሚመለከት በሚሠሩ ሥራዎች የሕክምና ሙያ ማኅበራት ተሳታፊ ናቸው? የሚል ጥያቄ ያነሱት የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ምሕረት አየነው፣ ‹‹የሕክምናው ዘርፍ መመራት ያለበት በቢሮክራሲ ሳይሆን በሙያ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ከፌደራል የመድኃኒት፣ የምግብና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ፣ የመንግሥትም ሆነ የግል የጤና ተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ደረጃ በሚመለከት በሁሉም ክልሎች ግምገማ ተሠርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጥናቱ ትንታኔ እየተሠራ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው ሰነድ ላይ በመጋቢት መጀመሪያ ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ፣ ሌሎች ሚኒስትሮችና የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ተወያይተው ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ይጠበቃል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት መንግሥት ያወጣው የሕክምና ተቋማት የአገልግሎት ጥራት ደረጃ በግል ተቋማት የእፎይታ ጊዜ እየተጠየቀበት አስገዳጅ መሆን ሳይችል መቅረቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በመጋቢት መጀመሪያ ላይ የሚደረገው የባለሥልጣናቱ ውይይት ግን ለጉዳዩ እልባት እንደሚሰጥ የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ምንጮቹ እንደገለጹት በርካታ ነገሮች ተመዝነው የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት በሙሉ እንደየደረጃቸው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ የሥራ ፈቃዳቸውም በዚሁ መሠረት እንደገና የሚታይ ሲሆን፣ የተቋማቱ ደረጃ ለሕዝብ ይፋ ሆኖ ተገልጋዩ የተቋሙን ደረጃ በሚመለከት እውነታውን አውቆና መረጃ ኖሮት እንዲወስን ይደረጋል፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

በዚያን ሰሞን የሹክሹክታ ወሬ ደርቶ ነው የሰነበተው፡፡ የአገራችን ልጆች...

በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ዙሪያ

‹‹ድንጋይ ላይ ሠርተን እንዴት ነው ውጤት እንድናመጣ የሚጠበቀው?›› የኦሊምፒክ አትሌቶች በደረጀ...

በአዲስ አበባ የታቀደ ጥቃት ማክሸፉን መንግሥት አስታወቀ

በኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ የተጠረጠሩ መያዛቸው...