Thursday, February 29, 2024

ከአማራጭ ሐሳቦች ይልቅ የርዕዮተ ዓለም ታሪክ ላይ ያተኮረው የመጀመሪያው የፓርቲዎች ክርክር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚካሄደውን አምስተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ፣ ፓርቲዎች የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው፡፡

የተወዳዳሪ ዕጩዎች ምዝገባ ለአንድ ሳምንት መራዘሙን ምክንያት በማድረግ ለአንድ ተጨማሪ ሳምንት ተራዝሞ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳና ክርክርም፣ ከየካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ መጀመሩ በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ይፋ ሆኗል፡፡

የምረጡኝ ቅስቀሳው አንድ አካል የሆነው የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉት ክርክርም፣ የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ ተጀምሯል፡፡ ለዘንድሮ ምርጫ የመጀመሪያ የሆነው ክርክር የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚከተሉት የርዕዮተ ዓለም ዙሪያ እንዲያተኩር ተደርጎ ነበር፡፡

በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚ ፋካሊቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው እሸቱ ጮሌ አዳራሽ የተካሄደው ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚከተሏቸው ርዕዮተ ዓለም ዙሪያ የሚያተኩር የክርክር መድረክ›› የተሰኘ ሲሆን፣ ተከራካሪዎቹም ከኢሕአዴግ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ከመድረክ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና ከኢዴፓ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ነበሩ፡፡

እነዚህ ሦስት ተከራካራዎች በአገሪቱ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ሦስት ርዕዮተ ዓለሞችን ወክለው የቀረቡ ናቸው፡፡ ሦስቱ ለክርክር የተመረጡት ርዕዮተ ዓለሞች ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ (ማኅበራዊ ዴሞክራሲ) እና ሊበራል ዴሞክራሲ ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ጥናት አማካሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ልማታዊ ዴሞክራሲን ወክለው የተከራከሩ ሲሆን፣ የወቅቱ የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ደግሞ ማኅበራዊ ዴሞክራሲን በመወከል ተከራክረዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ደግሞ የሊበራል ዴሞክራሲን ወክለው የቀረቡ ተከራካሪ ነበሩ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት በዘንድሮው ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለማቸው ላይ የሚያጠነጥን የመጀመሪያውን ክርክር ማዘጋጀት ያስፈለገበትን ምክንያት በዝርዝር ያቀረቡት፣ የትምህርት ክፍሉ ዲን ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ ናቸው፡፡ ርዕዮተ ዓለም የሚቃኝበት መነጽር እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር አብዲሳ፣ የኢኮኖሚም ሆነ የማኅበራዊ ፖሊሲዎች የሚወጡት በዚህ ሁኔታ እየተቃኙ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹በትክክል ፓርቲዎቹ የሚከተሏቸውን ርዕዮተ ዓለሞች በመገንዘብ ሊያመጡ የሚችሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ የሚሰጥ ከመሆኑ የተነሳ፣ ይህን ግልጽ ለማድረግና መራጮች እንዲረዷቸው ማማቻቸት ክርክሩ የተዘጋጀበት የመጀመሪያ ምክንያት ነው፤›› በማለትም ዶ/ር አብዲሳ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ደረጃ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተሉ ብዙኃኑ ማኅበረሰብ በቂ ግንዛቤ የሌለው መሆኑን ዶ/ር አብዲሳ ጠቁመዋል፡፡ ሕዝቡ በእነዚህ አካላት ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ አኳያና በዴሞክራሲ ሒደት ውስጥ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ማድረግ እንዲችል ማገዝ ደግሞ ሁለተኛው ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ፓርቲዎችን ወይም ርዕዮተ ዓለሞችን ወክለው በመድረኩ የተገኙት ተከራካሪዎች የሚከተላቸውን ርዕዮተ ዓለሞች በዝርዝር እንዲያስቀምጡ፣ አንዱ ከሌላው እንዴት የተሻለ ተመራጭ እንደሆነ እንዲገልጹ ዕድል ለመስጠት ያለመ መድረክ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በፕሮግራሙ አዘጋጆች ግምት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በእነዚህ ሦስት ርዕዮተ ዓለሞች ዙሪያ ላይ የሚሽከረከር አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ከእነዚህ የተለየ ርዕዮተ ዓለሞች አለን ለሚሉ ሌሎች ፓርቲዎችም ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ዕድል እንደሚሰጥም እንዲሁ ከመድረኩ ተገልጿል፡፡ የተካሄደው ክርክር መደበኛው የክርክር አካሄድ የተከተለ ሳይሆን፣ ፓርቲዎች 30 ደቂቃዎች ለእያንዳንዳቸው ተሰጥቷቸው  ርዕዮተ ዓለማቸውን እንዲያብራሩ ነው የተደረገው፡፡ በመቀጠልም ከአወያዩ ለእያንዳንዳቸው ፓርቲዎች አራት ጥያቄዎች ቀርበው ተወካዮቹም ከፓርቲያቸውና ከርዕዮተ ዓለማቸው አንፃር ምላሽ፣ ማብራሪያና ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ መሠረት የመጀመሪያ ተከራካሪ ሆነው የቀረቡት ማኅበራዊ ዴሞክራሲን የወከሉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሲሆኑ፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲው እንዲህ ዓይነት ፕሮግራሞችን ማዘጋጀቱ ተገቢ ሚናውን መጫወት መጀመሩን አመላካች ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞችን ከሞላ ጎደል መቃኘታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ከዚህ ግንዛቤ የተነሳም ለአገራችን የሚበጃት ማኅበራዊ ዴሞክራሲ ነው፤›› በማለት፣ ርዕዮተ ዓለሙ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴና ቆይታ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ከዛሬ 12 ዓመት ጀምሮ በዚህ የርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ የተቃኘ የፖለቲካ አካሄድ መከተል እንደጀመሩም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የዛሬ 12 ዓመት ገደማ ይህን ርዕዮተ ዓለም መሠረት ያደረገ ፓርቲ ድሮ አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት ከምንለው ያደገ እንቅስቃሴ መሥርተን ስንንቀሳቀስ ቆይተናል፤›› በማለት ሒደቱን የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ፓርቲ ዋናው መሠረት ያደረገው ደግሞ በቡድን ሆኖ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እንደሆነ አክለው አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ በመቀጠልም ይህ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት ወደሚል ማደጉንና በ1997 ምርጫ ወቅትም በፓርላማው የተወሰኑ ወንበሮችን ማሸነፍ መቻሉንና ይህም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እንደነበር አውስተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ከጥንስሱ ጀምሮ ከመሠረቱትና ከመሩት ፓርቲዎችም አንዱ ነው በማለት፣ የማኅበራዊ ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል ገልጸዋል፡፡

የሊበራል ዴሞክራሲን የወከሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፣ ‹‹በአገራችን በርካታ ፓርቲዎች የሊበራል ዴሞክራሲ አስተሳሰብ አራማጆች ነን እንደሚሉ ይታወቃል፤›› ብለዋል፡፡ ቢሆንም ግን በአንድነት የመቆም ችግር በክፍተኛ ሁኔታ እንደሚታይ በመግለጽ፣ ፓርቲዎቹ ከስያሜ ባለፈ በተግባር ርዕዮተ ዓለማቸውን እንዲኖሩት አሳስበዋል፡፡

በዓለም ላይ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ጊዜ ለምርጫ ውድድር የሚያቀርቧቸው ሐሳቦች ሰፊ ልዩነት እንደማይታይባቸው ዶ/ር ጫኔ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በሌሎች አገሮች ዜጎች ፓርቲዎችን ለፖለቲካ ሥልጣን ለማብቃት በሚያደርጉት ጥረት የትኛው ፓርቲ ለተሻለ የኑሮ ደረጃ ያበቃኛል ብሎ ከማሰብ ባለፈ፣ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር ህልውናቸውን የሚፈትን ሥጋት ሲያድርባቸው እንደማይታይ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ጫኔ፣ ‹‹በእኛ አገር ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረታዊ በሚባሉ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ያላቸው ልዩነት በጣም የተራራቀ ከመሆኑም በላይ፣ አገሪቱን እንደ አገር ህልውናዋን አስጠብቃ ለመቀጠል ካላት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፤›› በማለትም የጉዳዩን አሳሳቢነት አጉልተዋል፡፡ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች እጅግ የተራራቀና የማይታረቅ የሚመስል ሐሳብ ማራመዳቸውና አስተሳሰባቸውን በዚሁ መቃኘታቸው፣ ለአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ እንደ አገር የመቀጠል ዕጣ ፈንታዋን አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢዴፓ ፕሬዚዳንት ገለጻ በመንግሥት አደረጃጀትና አወቃቀር፣ በብሔራዊ ደኅንነት፣ በቡድንና በግለሰብ መብት፣ በመሬት አጠቃቀም፣ በትምህርትና በጤና ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው ልዩነቶች በጣም የተራራቁ ናቸው፡፡

በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ከሚያመሳስላቸው ጉዳይ የበለጠ የሰፋ መሆኑ፣ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን ትግል እጅግ አዝጋሚ እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ያሉ ፓርቲዎች የሐሳብ ተቃርኖና በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ አለመሥራት፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ሒደት ላይ ምን ያህል ጥላውን እንዳጠላበትም ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ልማታዊ ዴሞክራሲን ወክለው የተከራከሩት አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አጠቃላይ የመከራከሪያ ነጥባቸው የነበረውም አገሪቱ ልማትንና ዴሞክራሲን በእኩልነት በአንድ ላይ በማራመድ እየተጓዘች እንደሆነና ለዚህም እንደ ሞዴልነት የምትገልጻቸው አገሮች በአብዛኛው ከወደ ምሥራቅ እንደሆነ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ልማታዊ መንግሥታት ዴሞክራሲ የላቸውም የሚለው ወቀሳ ለምሥራቅ እስያ አገሮች ሊሠራ ቢችልም፣ እነዚህ አገሮችም ኋላ ላይ የመደብለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባት መቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡ ዴሞክራሲ አለመኖሩም እነዚህን አገሮች ከማደግ እንዳላገዳቸውም በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡

በርዕዮተ ዓለሙ ላይ የሚሰነዘረውን ትችትና ወቀሳ በዚህ ሁኔታ ካቀረቡ በኋላ፣ ‹‹እኛ ያለ ዴሞክራሲ መሄድ አንችልም፡፡ ዴሞክራሲ አማራጭ አይደለም፡፡ ለእኛ ዴሞክራሲ ግዴታ ነው፤›› በማለት ፓርቲያቸው ልማትንና ዴሞክራሲን በአንድ ላይ አስተሳስሮ እንደሚጓዝ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ልማታዊ መንግሥት ውስጥ ዴሞክራሲ ባለመኖሩ እንደዚህ ሆነ እንዲያ ሆነ የሚለው ክርክር ኢሕአዴግን አይመለከተውም፤›› በማለት፣ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዴሞክራሲ ከልማትና ከዕድገት ሊነጣጠል እንደማይችል አመልክተዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ከመጀመሪያው ጀምሮ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግሥት ነው እንጂ ያለው፣ ዴሞክራሲ የሌለው ልማታዊ መንግሥት አላለም፤›› በማለት የኢሕአዴግን አካሄድና አመጣጥ ከማብራራት ባለፈ፣ ኢሕአዴግ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስካሁን ወደፊትም ይህን አስተሳሰብ እንደሚያራምድ ገልጸዋል፡፡

በርካታ ዓመታት ወደኋላ

በዕለቱ ርዕዮተ ዓለምን መሠረት አድርገው እንዲከራከሩ የተሰጣቸውን የ30 ደቂቃ ፓርቲዎቹ በአብዛኛው የርዕዮተ ዓለማቸውን ልዩነትና አንድነት፣ ያላቸውን የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጭ እንዲሁም በተመረጡ የየፓርቲዎቹ ጠንካራ ጎኖች ላይ ከማተኮር ይልቅ ሦስቱም ተከራካሪዎች ወደኋላ ተጉዘው የየርዕዮተ ዓለማቸውን ታሪካዊ ዳራ ለታዳሚዎች ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ምንም እንኳን ዘንድሮ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ይህ የመጀመሪያ የክርክር መድረክ ከመሆኑና ከታዳሚዎች ውስንነት፣ እንዲሁም ከፓርቲዎቹ የዝግጅት ጊዜ አንፃር ፓርቲዎቹ የተነሱለትን ዓላማ አልመቱም ወደ ሚል መደምደሚያ ባያደርስም፣ አቀራረባቸው ግን እምብዛም ገዢ ነበር ለማለት አስቸጋሪ ነበር፡፡ አንኳር በሆኑ የርዕዮተ ዓለምና የእነሱን ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ያለውን ትስስርና ተፅዕኖ ለማስረዳት ሙከራ አልተደረገም፡፡

ማኅበራዊ ዴሞክራሲን የወከሉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ በ30 ደቂቃ ክርክራቸው ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የሰጡት ስለማኅበራዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አመሠራረት ታሪክ ነበር፡፡

እርግጥ ነው የርዕዮተ ዓለሙን ጥቅል ታሪክ ማስረዳት ጠቃሚ ቢሆንም፣ ዘለግ ያለ ጊዜ በመውሰድ የቀረበው የኋላ ታሪክ ለአብነትም ‹‹በፈርዲናንድ ላሳሌ አማካይነት እ.ኤ.አ. በ1860 ሶሻል ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ ሲመሠረት ማርክስና ኤንግልስ ያልተደሰቱበትን የማኅበሩን ጋዜጣ መጠሪያ ስም ‹‹ሶሻል ዴሞክራሲ›› በማለት ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲተከል አድርጓል፤›› የሚል ማብራሪያ መስጠት፣ የመራጭን ይሁንታ ለማግኘት የሚኖረው ጠቀሜታ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ከዚህ ባለፈም እንዲህ ያሉ ማብራሪያዎች ፓርቲው የአስተሳሰቡን መሠረት ለጣለበት አባል ወይም ደጋፊ ቢሰጥ ከፓርቲው ጋር ያለውን ወይም የሚኖረውን ትስስር ለማጠናከር ዓይነተኛ ድርሻ ሊጫወት በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን የበርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ፊት፣ እንዲህ ዓይነት ማብራሪያዎችን ማዥጐድጐድ ጠቀሜታው ያን ያህል ነው በማለት ተሳታፊዎች ቅሬታቸውን ለሪፖርተር አካፍለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፕሮፌሰሩ በማነፃፀሪያነት ያቀረቧቸው የነበሩት አኃዞች አብዛኛዎቹ ጊዜ ያለፈባቸውና ምንም እንኳን ከአፍሪካ ቤኒን የተጠቀሰች ቢሆንም፣ ለማሳያነት የሚጠቀሱት አገሮችም እንደ ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ጀርመንና የመሳሰሉ የአውሮፓ አገሮች ነበሩ፡፡ ይህንን እውነታ ራሳቸውም ቢሆን ‹‹ይህ አኃዝ ሊጨምር ይችላል ወይም ሊቀየር ይችላል›› የሚል አስተያየት በየማብራሪያቸው መቋጫ ላይ በመጠቀም፣ በጥርጣሬ የተሞላ እንደሆነ ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡

ለዚህ እንደ አብነት ያህልም ከሁለት ዓመት በፊት በተገኘ የገቢ ደረጃ ኢትዮጵያን ከሌላዋ የማኅበራዊ ዴሞክራሲ አራማጅ አፍሪካዊት አገር ቤኒን ጋር አነፃፅረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 በተገኘ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያና የቤኒንን የትምህርት ሽፋን እንዲሁ አነፃፅረዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ለዚህ ያቀረቡት ምክንያት ደግሞ መረጃውን በቀላሉ ማግኘት አለመቻልን ነው፡፡ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን ማግኘት ያን ያህል ከባድ የሚሆን ግን አይመስልም፡፡ የልማታዊ ዴሞክራሲ ተወካይም ሆነ የሊበራል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ተወካዮችም መሠረታዊውን ነጥብ ለማስረዳት፣ እጅግ ወደኋላ ተጉዘው የርዕዮተ ዓለሞቹን ታሪክ መተንተን ላይ ተጠምደው ነበር፡፡

በዚህ ረገድ ዶ/ር ጫኔ ከበደ የሊበራል ዴሞክራሲን ትርጉም፣ ታሪካዊ ዳራ፣ የኒዮ ሊበራሊዝም አዲስ አስተሳሰብ፣ የሊበራል ዴሞክራሲ መርሆዎችና ዋና ዋና መሠረታዊ ነጥቦች፣ የነፃ ገበያ ሥርዓት በሊበራል ዴሞክራሲ አስተሳሰብ፣ ሊበራል ዴሞክራሲ በሕግ አግባብነት፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ የሊብራል ዴሞክራሲና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ልዩነቶች፣ እንዲሁም ኢዴፓና ሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች የሚሉ ርዕሶችን መሠረት ያደረገ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከዝርዝሩ ለመረዳት እንደሚቻለው አብዛኛው የተነሱት ነጥቦች የነጠረ ርዕዮተ ዓለም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ድርሻና ውስንነት ከማውሳት ይልቅ፣ የርዕዮተ ዓለሙን አመሠራረትና ታሪክ መተንተን መርጠዋል፡፡

ተከራካሪው ለማቅረብ ከዘረዘሩዋቸው ነጥቦች መካከል በቀጥታ የመራጩን ይሁንታ ለማግኘት የሚያስችል የሚመስለው፣ የሊበራል ዴሞክራሲና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ልዩነቶች የሚለውና ኢዴፓና ሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች የሚሉት ናቸው፡፡ ሌሎቹ ለጠቅላላ ዕውቀት ከመርዳት በስተቀር ይህን ያህል ልብን አሸፍቶ ይህን ፓርቲ ብመርጥ ይህን ያሳካልኛል የሚያስብል አማራጮችን ያቀረበ አልነበረም፡፡ ልማታዊ ዴሞክራሲን ወክለው የተከራከሩት አቶ ዓባይ ፀሐዬም ቢሆን ነጥባቸውን ለማስረዳት ጉዳዩን ከታሪክ አንፃር መመልከት መፍትሔ መሆኑን ጠቁመው፣ የጃፓንን ሥልጣኔና የኢንዱስትሪ ማስፋፋት ከአውሮፓውያን ጋር በንፅፅር በማቅረብና በመከራከር የእሳቸው ፓርቲም ይህንኑ የጃፓንን መንገድ እየተከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የጃፓን መንገድ ምንም ይሁን ኢሕአዴግ እየሄደበት ባለው መንገድ ለሕዝቡ የጃፓን ዓይነት ሥልጣኔ እንዴት እንደሚያመጣና እንደሚያጎናፅፍ ቢገልጹ የፓርቲዎች የክርክር መድረክ ከመሆኑ አንፃር የመራጭን ልብ ለማግኘት ሁነኛ ድርሻ ይኖረው ነበር፡፡

በክርክሩ መድረክ ላይ ፓርቲዎቹ ካቀረቧቸው መነሻ ሐሳቦችና ርዕዮተ ዓለሞች ማብራሪያ ይልቅ፣ በአወያዩ በዶ/ር አብዲሳ ዘርአይና በተሳታፊዎች የተነሱላቸውን ጥያቄዎች ተከትሎ የተሰጡት ምላሾችና ማብራሪያዎች የአብዛኛዎችን ቀልብ መግዛት የቻሉ፣ ውስብስብ ከሆነው ሰማይ ላይ ከተሰቀለው የርዕዮተ ዓለም ማብራሪያ ወደ መሬት የወረዱና የአብዛኛዎችን የልብ ትርታ የሚነኩ ነበሩ፡፡ ከታዳሚዎች ከተሰነዘሩት ጥያቄዎች መካከል ለአብነት ያህል ይህ ስለልማታዊ ዴሞክራሲ ሲነሳ፣ እያንዳንዱ ውሳኔ የሚከናወነው ከሕዝብ ጋር በመመካከርና በመወያየት እንደሆነና ሕዝቡ አይሆንም ወይም ይቅር ካለ ጠቃሚም ቢሆን እንደማይተገበር ከመድረኩ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዙሪያ የማስተር ፕላን ጉዳይ ምክክር እንዳልተካሄደበት በመጥቀስ ለአቶ ዓባይ አንድ ተሳታፊ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ‹‹በዚህ የተነሳም ተማሪዎች ተቃወሙት፡፡ በአንዳንድ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እንደሚሰማው ደግሞ የዚህን ማስተር ፕላን ጉዳይ የሚቃወም ካለ ጠንከር ያለ ዕርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል በእርስዎ በአቶ አባይ ፀሐዬ አማካይነት ተገልጿል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢሕአዴግ ይህን ጉዳይ የያዘበት አግባብ ዴሞክራሲያዊ ነው ወይ? ልዩነቱና ተግባሩ ስሙም ናቸው ወይ?›› የሚል ጥያቄ ነበር፡፡

አቶ ዓባይ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አሁንም ‹ተወደደም ተጠላም ጠንካራ ዕርምጃ ይወሰዳል› አላልኩም፡፡ ሁለቱ ከተሞች ከተስማሙ ግን ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ሕዝቡን አወያይተዋል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ከተቀበለው ሁለቱ መስተዳድሮች ከተስማሙ ማንም ጐረምሳ መጥቶ ሊያስቆመው ተገቢ አይደለም፡፡ ሕገወጥ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱ መስተዳድሮች ወይም ሕዝቡ ካልተስማማበት ተግባራዊ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ከኦሮሚያ ክልል አንድ ካሬ ሜትር መሬት ወደ አዲስ አበባ ይግባ አልተባለም፡፡ ፌዴራል መንግሥትም ደፍሮ እዚህ ውስጥ እጁን አያስገባም፡፡ ስለሚያምንበትም ስለማያገባውም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ የችግሩን መንስዔም እንቅፋት የሚፈጥሩ የአስተዳደሩ አካላትና ሌሎች ኃይሎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ በፍጥነት እንዳይወያይ ተደርጎ ዘግይቶ ስብሰባ እንደተደረገ ግን አምነዋል፡፡ ‹‹በኋላ ስብሰባ ሲደረግና ዓላማው በዝርዝር ሲገለጽለት እኛ አላወቅንም ማን የነገረን አለ?›› በማለት ሕዝቡ መግለጹም ችግሩ የመረጃ ልውውጥ ክፍተት እንደሆነ እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡

በተከራካሪዎች መካከል የነበረው መከባበርና ሐሳብን ብቻ የመሰንዘርና ሐሳብን ብቻ የመተቸት ጉዳይ ሊመሰገን የሚገባው እንደሆነ፣ በቀጣይ በሚካሄዱ የክርክር መድረኮችም ተደጋግሞ ሊታይ የሚገባው ዓብይ ጉዳይ ነው በማለት አወያዩም ሆነ ታዳሚዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የእያንዳንዱን ተከራካሪ ሰዓት በሥነ ሥርዓት በመመጠንና በማስቆም፣ እንዲሁም የታዳሚዎችን አስተያየትና ጥያቄዎችን በመግራትና ወደ ዋናው ጉዳይ እንዲገቡ ፈር በማስያዝ ክርክሩን በሰከነ መንፈስ የመሩት ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይም፣ እንዲሁ ምሥጋና እንደሚገባቸው ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

ይህ የክርክር መድረክ በቀጣይም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚካሄድ በመግለጽ፣ ለሁለት ሰዓታት ያህል አርፍዶ የተጀመረው ክርክር በቀጣይ የካቲት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በሌላ የክርክር አጀንዳ ለመገናኘት ቀጠሮ በመያዝ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -