የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን፣ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚከተሏቸው ርዕዮተ ዓለሞች ዙሪያ የመጀመሪያውን ክርክር የሚያደርጉበት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በመድረኩ ላይ በልማታዊ ዴሞክራሲ፣ በማኅበራዊ ዴሞክራሲና በሊበራል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለሞች ዙሪያ ክርክር ተካሂዷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚ ፋካሊቲ ቅጥር ውስጥ በሚገኘው እሸቱ ጮሌ አዳራሽ የተካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር መሪ ርዕስ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚከተሏቸው ርዕዮተ ዓለም ዙሪያ የሚያተኩር የክርክር መድረክ›› የተሰኘ ሲሆን፣ ተከራካሪዎቹም ከኢሕአዴግ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ከመድረክ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና ከኢዴፓ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ነበሩ፡፡ ሦስቱ ለክርክር የተመረጡት ርዕዮተ ዓለሞች ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲ፣ ሶሻል ዴሞክራሲና ሊበራል ዴሞክራሲ ናቸው፡፡ በክርክሩ ላይ የተገኘው ነዓምን አሸናፊ በዘገባው፣ ክርክሩ ከአማራጭ ሐሳቦች ይልቅ የርዕዮተ ዓለም ታሪክ ላይ ያተኮረ ነበር ይላል፡፡ በምሥሉ ላይ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከአቶ ዓባይ ፀሐዬ ጋር ሲጨባበጡ ይታያሉ፡፡ ዝርዝር ዘገባው በገጽ በ ፖለቲካ ላይ ተስተናግዷል፡፡