Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትደስታ እና ሐዘን የተፈራረቀበት የባሕር ዳሩ ጨዋታ

  ደስታ እና ሐዘን የተፈራረቀበት የባሕር ዳሩ ጨዋታ

  ቀን:

  ሱዳናዊው የመሀል ዳኛ የማጠናቀቂያ ፊሽካ ድምፅ አበሰሩ፡፡ በባሕር ዳር ስታዲየም የነበሩ የእግር ኳስ ተመልካቾች በደስታ ፈነጠዙ፤ ምክንያቱም ደደቢት እግር ኳስ ክለብ የሲሴልሱን ክለብ ኮትዲኦርን ከሜዳ ውጭ 3 ለ2 አሸንፎ በሜዳው ጥሩ እንቅስቃሴ ተጨምሮ በ14ኛው ደቂቃ በሥዩም ተስፋዬና በ67ኛው ደቂቃ ዳዊት ፈቃዱ ግቦች ባጠቃላይ ድምር 5 ለ2 አሸናፊ ሆነው ወደ ቀጣዩ የኮንፌዴሬሽን ማጣሪያ ጨዋታ ማለፍ ችሏልና፡፡

  46, 000 የሚጠጋው ተመልካችም ወደቤቱ በመመለስ ላይ ሳለ ከባሕር ዳር ከተማ መግቢያ ላይ የከተማውን ኅብረተሰብ ያስደመመ ድምፅ ተሰማ፡፡ ያዩትና የሰሙትን ማመን ከበዳቸው፡፡ ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሚሆኑና 60 ሰዎችን ያሳፈሩ አውቶቢሶች ከተማውን ወረሩት፡፡ በአውቶብሶቹ ብርቱካናማ መለያ የለበሱ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ ከ15 እስከ 20 ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆችና እንዲሁም ታላላቅ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በአውቶቡሱ ውስጥ በመጨፈርና በማጨብጨብ በተጨማሪም ጡሩንባቸውን በመጠቀም የከተማውን ኅብረተሰብ በሚያስገርም ዓይነት ወደ ከተማ ገቡ፡፡ አንዳንዱ ከአውቶብሱ ጣራ ላይ በመውጣትና ከፊሉ ደግሞ ግማሽ አካሉን ከአውቶብሱ ውስጥ በማውጣት ባሕር ዳርን አደመቋት፡፡

  የባሕር ዳር ከተማ ኅብረተሰብም ከመንገዱ ዳርና ዳር በመቆም በማጨብጨብ የእግር ኳስ ደጋፊዎችን በክብር ተቀበለ፡፡ አውቶቡሶቹም የጡሩንባቸውን ድምፅ እያሰሙ ከተማዋን በመዞር ለሕዝቡ ሰላምታን አቀረቡ፡፡ ምሽት ላይም እነዚህ አውቶቡሶች ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሆቴል ቤቶች ጥግ ጥግ በመያዝ ከጉዟቸው አረፍ አሉ፡፡ በዕለተ እሑድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የክለባቸውን ዓርማ በመያዝና በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች በመዞር በእጃቸው በያዙት ጥሩንባ ክለቦቻቸውን ማስተዋወቁን ቀጠሉ፡፡

  በተለይ ከአዲስ አበባ ክለባቸውን ለመደገፍ ከመጡት ደጋፊዎች ዳንኤል ከፍ ያለውና አስናቀ በላቸው እንዲሁም ዕድሜው 15 ዓመት የሚሆነው ቢኒያም አሰፋ በባሕር ዳር ጎዳናዎች ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዘፈን እየዘፈኑ ክለባቸውን ኅብረተሰቡ እንዲደግፍ ጨዋታም እስኪደርስ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

  ጨዋታው 10 ሰዓት እንደሚጀመር ቢታወቅም ደጋፊዎች ወደ አዲሱ ኢንተርናሽናል ደረጃ ያለው ስታዲየም ማቅናት የጀመሩት ገና በጠዋት ነበር፡፡ የስታዲየም በሮችም ከ10 ብር እስከ 200 ብር ተመልካቾችን ለማስተናገድ ክፍት ሆኖ ጠብቀዋል፡፡ ተመልካቾቹ የባሕር ዳርን ሙቀት በመቋቋም ለጉሮሯቸው ማርጠቢያ ውኃ በመግዛት ወደ ስታዲየም መግባት ቀጠሉ፡፡

  ከባሕር ዳር ከተወጣጡት ተመልካቾች ውስጥ አዋቂዎች፣ ወጣቶች፣ ልጆች እንዲሁም ሴቶች ወደ ሥፍራው ከሚያመሩት ውስጥ ነበሩ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የተመልካች ብዛት የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባው የባሕር ዳር ስታዲየም በተለይ ዙሪያው በደጋፊዎች ጭፈራና የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓርማን የያዙ ማድመቂያዎች በመሸጥ የተጠመዱ ወጣቶች ይታያሉ፡፡

  የባሕር ዳር የፖሊስ አባሎችም በተጠንቀቅ በመቆም የኅብረተሰቡን ሰላም ለማስፈን እያንዳንዱን እየፈተሹ በማስገባት ተጠምደዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም የከተማዋ ከላይ ወደ ታች የማዕረግ ልብሳቸው የለበሱ የማርሽ ባንዶች የሙዚቃ መሣሪያቸውን በማዘጋጀት በተጠንቀቅ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ወደ ሜዳ መውጣት ይጠባበቃሉ፡፡

  ተመልካቾችም የክለባቸውን ምልክት በገላቸውና በፊታቸው ላይ በቀለም በማስመር ከዲጄዎች (ሙዚቃ አጫዋቾች) በሚከፈተው የክለቡ ሙዚቃ ድጋፋቸውን ቀጥለዋል፡፡

  በባሕር ዳር ከተማ ከ45 ዓመት በላይ የኖሩትና ለመጀመርያ ጊዜ የክለብ የእግር ኳስ ጨዋታ ሊመለከቱ እንደመጡ የሚናገሩት አቶ አንድአርግ ወርቁ፣ ደጋፊዎች ለዚህ ጨዋታ 560 ኪሎ ሜትር አቋርጠው መምጣታቸው እንዳስገረማቸውና ወደፊት በዚሁ መንገድ ቢቀጥል ከባሕር ዳር ከተማ ጥሩ የሆኑ እግር ኳስ ተጨዋቾች ለማፍራት ይኼ አጋጣሚ እንደሚያነሳሳ ጠቆም በማድረግ የቅዱስ ጊዮርጊስን መለያ ለብሰው በአዲስ አበባው የስታዲየም አጠራር ካታንጋ በመቀመጥ ደጋፊዎችን ተቀላቀሉ፡፡

  460 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትና 90 በመቶ የተጠናቀቀው የባሕር ዳር ስታዲየም በብርቱካናማ ቀለም የለበሱ ተመልካቾች ድጋፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ በሱዳን  ዳኞች የሚመራው የቅዱስ ጊዮርጊስና የአልጄሪያው ክለብ ኤምሲ ኤልኦልማ ጨዋታ ከተጀመረ አሥር ደቂቃ ተቆጥረዋል፡፡ ስታዲየሙ በወንበር 50,000 ተመልካች ቢይዝም  ባልተጠናቀቀው የፎቁ ክፍልን ጨምሮ 100,000 የሚጠጋ ተመልካች ተገኝቷል፡፡

  የአልጄሪያው ክለብ ኤምሲ ኤልኦልማ ግብ ጠባቂ ጨዋታው ገና ከመጀመሩ ሰዓት የማቃጠል ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ተመልካቾች ቁጭ ብድግ የሚያደርግ ጨዋታ ባይታይም ደጋፊዎች የአልጄሪያ ተጨዋቾች ሰዓት ለመግደል በሚያደርጉት ተግባር ቅሬታቸውን በጩኸት ማሰማቱን ቀጥለዋል፡፡ በተለይ በኃይሉ አሰፋ ለአዳነ ግርማ በአስገራሚ ሁኔታ ያሻገራት ኳስ ወደ ጎል አለመቀየሩ ተመልካቹን አስቆጭታለች፡፡ ተመልካቹ በማንሳትና የተለያዩ የድጋፍ ዓይነቶችን በማሰማት በኃይሉ አሰፋ (ቱሳ) 40ኛው የደቂቃ ላይ ጎል በማስቆጠር የመጀመርያው ግማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገቡ፡፡ በተለምዶ ቪአይፒ ተብሎ በሚታወቀው የኃላፊዎችና የእንግዶች የክብር መቀመጫ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነዲን ባሻ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የበላይ ኃላፊ አቶ አብነት ገብረመስቀልና ሌሎችም ተገኝተው የደጋፊዎቹ ስሜት ተጋሪ ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡

  በተመልካቾች መካከል ቆመው ባንዲራ በማውለብለብና የሙዚቃ መሣሪያና በድምፅ ማጉያ በመጠቀም ድጋፋቸውን ሲሰጡ ገሚሶቹ ለሁለተኛው ግማሽ አሠልጣኞቹ ምን ዓይነት ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ሲወያዩ ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ  70ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ግርማ ጎል በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስ መምራት ቢችልም የአልጄሪያው ኤምሲኦል ማዎች ባገኙት ቅጣት ምት 72ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ተቆጠረ፡፡ ስታዲየም ሙሉ የሚገኘው ደጋፊ በፀጥታ ተዋጠ፡፡ በጭንቀት ግማሹ በመበሳጨት ሲወጣ፣ ቀሪው ለመደገፍ ጥረት ማድረጉን ቀጠለ፡፡  

  በ75ኛው ደቂቃ ላይ የአልጄሪያው ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ወጣ፡፡ በሜዳ ውስጥ የአልጄሪያዎች ሰዓት መግደል ቀጠሉ፤ እንደተጎዳ ሰው መተኛት ዳኛ ጋር በመጠጋት በሆነ ባልሆነው መጨቃጨቅም አበዙ፡፡ ያላቸውን ተቀያሪዎች እያቀያየሩ አስገቡ፡፡

  የተጨመረው አራት ደቂቃ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኞች ተቀባይነት ባይኖረውም አራተኛው ዳኛ ቦታቸው እንዲመለሱ ከማዘዝ በስተቀር ምንም ለውጥ ማምጣት አልቻሉም፡፡ የሱዳኑ ዳኛ የጨዋታ መጠናቀቂያን የምታበስር ፊሽካ ሲያሰሙ በተለይ ከአዲስ አበባ ባሕር ዳር ድረስ ለመጡ ደጋፊዎች ሊታመን አልቻለም፡፡

  ብራዚላዊውን አሠልጣኝ ናይደር ዶሳንቶስ ‹‹ይባረርልን›› የሚሉና ተጨዋቾችን የሚወቅሱ እንዲሁም በንዴት በማልቀስ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ በመጨረሻ የከተማዋ ፖሊሶች ደጋፊውን በማረጋጋት ከተጨዋቾች ላይ ለመከላከል ሲጥሩም ተስተውሏል፡፡

  የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ዶሳንቶስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹በመጀመርያ ግማሽ ከጥሩ ጨዋታ ጋር ብልጫ አሳይተን ነበር፡፡ ጎል ማስቆጠር ብንችልም አንድ ቅጣት ምት አግኝተው ጎል አስቆጥረውብናል፡፡ ስለዚህ የቻልነውን ለማድረግ ሞክረናል የአልጄሪያው ደግሞ በጣም ጠንካራ ክለብ ነው፡፡ እግር ኳስ አንዳንዴ እንደዚህ ናት፤›› ብለዋል፡፡

  ብራዚላዊውን አሠልጣኝ የተጫዋቾችን ቶሎ አለመቀየር ጥያቄ ቀርቦላቸው ‹‹ሁሉም ተጨዋቾች ጥሩ እየተጫወቱ ነበር፤›› ከማለት ባለፈ ደጋፊዎች ረዥም ኪሎ ሜትር አቋርጠው ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የማህል ተጨዋች በኃይሉ አሰፋ ትንሽ ስህተት ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግሮ የመጀመርያ ጎል ስናስቆጥር እንደምናሸንፍ ነበር የተሰማኝ ብሏል፡፡

  የአልጄሪያው ክለብ የኤል አልማ ክለብ አሠልጣኝ ጁሊስ ኤክሮስ በበኩላቸው፣ ‹‹ጎል ሲቆጠርብን የምናሸንፍ አልመሰለኝም ነበር፤ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ፈታኝ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሠልጣኝ ዶሳንቶስ ትኩረታችንን ወደ ፕሪሚየር ሊግ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

   

   

   

   

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img