Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአርሶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ የገበያ ጥያቄ

የአርሶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ የገበያ ጥያቄ

ቀን:

ሰሞኑን በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ርእሰ ከተማ ሐዋሳ በተካሄደው ሰባተኛው የአርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በዓል በክልሉ እንዲሁም በኦሮምያ፣ በትግራይና በአማራ ክልሎችን ምርት ገበያ ያጠበቡ ችግሮች መኖራቸው ተገልጿል፡፡ አምራቾች ከውጤታቸው ሙሉ በሙሉ አለመጠቀማቸው ተጠቁሟል፡፡

የደቡብ ክልልን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሚዳስስ ጽሑፍ በክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ገርማሜ ገሩማ ቀርቧል፡፡ ጽሑፉ ክልሉ ከሚታወቅባቸው ምርቶች (ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ አናናስና ሌሎችም ፍራፍሬዎች) አምራቹ በስፋት  እንዳይጠቀምና በዓለም አቀፍ ገበያ እንዳይቀርቡ ያገዱትን ተግዳሮቶች አመላክቷል፡፡ አካባቢው ከባሕር ወለል በታች ያለው ከፍታና ዓመታዊ የዝናብና ሙቀት መጠኑ ለፍራፍሬ ምርት ቢመችም የሠለጠነ የሰው ኃይልና በቂ የመስኖ ውኃ አቅርቦት አለመኖሩ ምርቱን ቀንሶታል፡፡ በጽሑፉ እንደተገለጸው፣ ሌላው ችግር ተባይ ሲሆን፣ ፍራፍሬዎች ከተመረቱ በኋላ ደረጃውን የጠበቀ መሰብሰቢያ፣ ማቆያና ማጓጓዣ አለመኖሩ አምራቹን እየተፈታተነው ይገኛል፡፡

የጽሑፉ አቅራቢ የክልሉ ምርት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሊደገፍና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ሊፈጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ፍራፍሬ የበለጠ የተመቹ አካባቢዎች እየተመረጡ ክትትል ማድረግ መደረግ እንደሚገባ አክለዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከክልሉ ምርቶች ሙዝ 67 በመቶ፣ ማንጎ 31 በመቶ፣ አቮካዶ 71 በመቶና አናናስ 84 በመቶ የአገር ውስጥ ገበያ ይሸፍናል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማትና ጤና ጥበቃ ኤጀንሲ ኃላፊ ዶ/ር ሀብታሙ ተካ የክልሉን የእንስሳት እርባታ በሚያስቃኝ ጽሑፍ እንደጠቆሙት፣ ክልሉ 43 በመቶ የአገሪቱን የእንስሳት ሀብት ይሸፍናል፡፡ ዕፅዋቱ ለንብ እርባታ ምቹ ቢሆኑም በሙሉ አቅማቸው እየተመረተ አይደለም፡፡ የወትት አቅርቦት በአንፃሩ የተሻሻለ ሲሆን፣ ጽሑፉ እንደሚያትተው ቆዳና ሌጦ በተሻለ የጥራት ደረጃ ተመርቶ የውጪ ምንዛሬ እንዲጨምር የእንስሳት ጤና አጠባበቅ (መድኃኒት ክትባት አቅርቦት)ና ጤናማ እርድ ትኩረት ያሻዋል፡፡

ጽሑፍ አቅራቢው የክልሉ ግንባር ቀደም ችግር ያሉት ለአምራቹ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ አለመሰጠቱ ነው፡፡ መሻሻል አለባቸው ካሉት ዘመናዊ ቀፎ በመጠቀም የንብ ምርቱን ማሳደግ፣ በተመጣጠነ መኖ  የእንስሳት ምርቱን መጨመር ይገኙበታል፡፡ ከብቶችን በማዳቀልና በሚደልቡበት ወቅት አርቢው የሚያደርግላቸው እንክብካቤ መለወጡን መሻሻሉን አላለፉም፡፡

የአማራ ክልል ጽሑፍ ያተኮረው በሰብል ምርት ላይ ሲሆን፣ የክልሉ ግብርና ልማት ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ አጥላው እንደተናገሩት፣ ልማዳዊ አመራረት ሙሉ በሙሉ አለመቅረቱ ምርታማነቱን ቀንሷል፡፡ የግሪሳ ወፍ፣ አንበጣና ሌሎችም ወረርሸኞች ጋሬጣ የሚሆኑበት ጊዜ እንዳለ ጠቁመው፣ የምግብ ዋስትና የሌላቸው አካባቢዎች ለማብቃት የሚያስችሉ መንገዶች እንዲጠናከሩ አሳስበዋል፡፡

ምርጥ ዘር በመጠቀም ረገድ ክልሉ በ2006 ዓ.ም. ወደ 165,502 ሔክታር መሬት መድረሱን ጽሑፉ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪ ምርት መስጠት የማይችል ጥቁር አፈር እንዲያበቅልና በመኸርና በበልግ ተመሳሳይ ምርት እንዲኖር ለሚከናወኑት ሥራዎች አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በጽሑፉ ጤፍ፣ በቆሎ ስንዴና የቅባት እህሎችን ጠቅሰው በመስመር የመዝራት መንገድ ከጥቂት ስብሎች አልፎ በሌሎችም እንዲተገበር አሳስበዋል፡፡ ክልሉ የሚታወቅበት ማሽላ ካለው ስፋት አንፃር በአግባቡ ከተመረተ ክልሉን የማበልፀግ አቅም በተቃራኒው ቸል ከተባለ አሉታዊ ጎን እንዳለው አስረድተው እንዲታሰብበት ጠቁመዋል፡፡     

በትግራይ ክልል የመስኖ ልማት የሥራ ሒደት ኃላፊ አቶ ፍጹም ገብረሚካኤል በበኩላቸው፣ ክልሉ የውኃ አጠቃቀም ችግር እንዳለበትና ምርቱ ገበያ ተኮር አለመሆኑን አንስተዋል፡፡ የአካባቢው አረንጓዴዓማ አለመሆን ቢያስቸግርም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማነትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት መጠናከሩን ገልጸዋል፡፡ ከቀደመው ጊዜ በተሻለ መሬት ሲቆፈር በአጭር ርቀት ውኃ እንዲገኝ የማድረግ መንገድ አንዱ ነው፡፡ የወንዝ ውኃ በመጥለፍ፣ በመስኖ ልማት፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀምና ውኃን በትቦ በማስጓዝ በክልሉ ሰብልና ፍራፍሬ ቢበቅልም፣ በበቂ ሁኔታ አለመመረቱን ጽሑፉ ያሳያል፡፡

ሌላው ምርቶቹ በሚፈለገው መጠን ለገበያ አለመድረሳቸው ነው፡፡ በየአካባቢው ካሉ ማከፋፊያ መደብሮች ጋር በጥምረት የሚሠሩ አምራቾች ጥቂት እንደሆኑና የገበያ ተደራሽነት እንደሚቀራቸው ተናግረዋል፡፡

በጽሑፎቹ አጠቃላይ ምልከታ የሰጡት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው የየክልሉ ምርቶች ዘመናዊ መሣሪያና መንገድ ሲጠቀሙ ምርታማነት እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ በሰብል፣ በእንስሳት፣ በአትክልት ፍራፍሬና በሌሎችም ዘርፎች ከየምርቱ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አጠቃላይ የገበያ መሠረተ ልማቱ ጠንካራ ባለመሆኑን እሳቸውም ከጽሑፎቹ አቅራቢዎች ጋር ተስማምተዋል፡፡ በየዘርፉ የሚውለው መዋዕለ ንዋይ ከፍ ብሎ አምራቹ አትራፊ እንዲሆን መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡

ውይይቱን ተከትሎ የየአካባቢው ምርቶች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ምርት ለማሻሻል የሚያግዙ መሣሪያዎችን ያዘጋጁ ተቋሞችም ሥራዎቻቸውን አስጎብኝተዋል፡፡

የጌድዞ ዞን የግብርናና ገጠር ልማት ማኅበር ሥራቸውን ካሳዩ አንዱ ነው፡፡ የማኅበሩ አባል ወ/ሮ ዘቢደሩ ለገሰ  በማኅበሩ ሥር ያሉት ሴቶች ቆጮና ሌሎችም ምርቶቻቸውን ከአካቢያቸው በተጨማሪ በሌሎችም ገበያ እንዲያገኙ መሰል ማስተዋወቂያዎች እንደሚያግዟቸው ያምናሉ፡፡ በተመሳሳይ በጋሞ ጎፋ የአትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ሥራ ዩኒየን የሚሠራው አቶ ታምርአየሁ መርሻ፣ አምራቹ በገቢ ረገድ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ያሳስባል፡፡ የአካባቢውን ምርቶች ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ በምርት ወቅት የሚገጥሟቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸው ሳያሳስብ አላለፈም፡፡

አርብቶ አደሩን ምርት ይጨምራሉ ተብለው ከቀረቡት መሣሪያዎች የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ያቀረበው የማሽላና በቆሎ መፍጫ ይጠቀሳል፡፡ የድርጅቱ ተወካይ አቶ አቤል ሙላት እንደተናገሩት፣ መሣሪያው በተለያዩ አካባቢዎች እየተከፋፈለ ሲሆን፣ በባህላዊ መንገድ ሲሠራ የሚደርሰውን ብክነት ይቀንሳል፡፡ መሰል ምርቶችን ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ የሚያስረዱት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም ባለሙያ አቶ ጥሩ ሰው ገረሱ ናቸው፡፡ ድርጅታቸው በተለያየ ከፍታ መብቀል የሚችሉና በሽታን መከላከል የሚችሉ ዝርያዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ምርቶች በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እንዲመረቱ እንደሚያግዙ አስረድተዋል፡፡

‹‹እመርታዊ ለውጥ በምርታማነትና በአመራረት ዘይቤ›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በዓል መዝጊያውን ያደረገው የካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በሐዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለ920 ግለሰቦች ባበረከቱት ሽልማት ነው፡፡ ተሸላሚዎቹ አርሶ አደርነትና አርብቶ አደርነት ኋላቀር ነው የሚለውን አስተሳሰብ መቀየር እንደቻሉ ገልጸው፣ ምርቱ ግን በቂ እንዳልሆነና አሁን ካለው ትርፍ እጥፍ ማግኘት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡ ዓለም ከደረሰበት አንፃር አመርቂ ነው ተብሎ የሚቆምበት ደረጃ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡ ዘመናዊ ዘዬዎችን መጠቀምና ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ መግባት የበለጠ ትርፋማ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡

ከዘጠኙም ክልሎች የተውጣጡ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች፣ ባለሀብቶች፣ የግብርና ተመራማሪዎችና ሌሎችም በሽልማቱ ተካተዋል፡፡ ከተሸላሚዎቹ 30 በመቶ ሴቶችና 20 በመቶ ወጣቶች እንደሆኑና ባጠቃላይ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ኖሯቸው በዘርፉ ለብዙዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሽልማቱ በ1999 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ከተጀመረ ጀምሮ የዘንድሮውን ሳይጨምር 4,510 አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ተሸልመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...