Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለቴሌ መዘግየት ምን ይሆን ምክንያቱ?

እነሆ ከቄራ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናው ዛሬም የራሱን ሀቅ እንደሰነቀ ነው። በዓይነት በዓይነቱ ሥጋ የተሸከመውን የመንፈሱን ሕመም እዚህ እኛ ታክሲ ውስጥ ይተነፍሰዋል። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አንዲት አዛውንት የተሳፋሪዎችን ቀልብ ይጎትታሉ። “አምጣማ ክራሬን! ክራሬን አምጣ አንተ ልጅ!” በቁጭት ወያላው ላይ ይፎክሩበታል። የፊት ድዳቸው አጥር ፈርሷል። አፋቸውን ከፍተው ለእሳቸው ብቻ በሚገባቸው የኑሮ የቁማር ጨዋታ ሲስቁ ጥቁር ዋሻ ይከፈታል። ወያላው ግራ ገብቶት “ክራር ይዘው ነበር?” ይጠይቃቸዋል። “ያውም ጣሊያን ተመልሶ ሳይመጣ! ምን ይላል ይኼ! በእኛ ደምና አጥንት ዛሬ ላይ ቆማችሁ ታሪክ እኛ ላይ ጀምሮ እኛ ላይ ጨርሷል ስትሉ እኮ እንዴት የሚያመኝ?” ይቆጣሉ። “ስማ ገና አንተ ሳትወለድ ያንተ እናት እናቷ ማኅፀን ውስጥ ሳይጎዘጎዝላት፣ ፋሽሽት ቤት ንብረቴን አውድሞ ሲያሰድደኝ እኒህ እጆቼ ምን ያበጁ ይመስልሃል? ንገረኝ!” ወያላው ደንግጦ ያያቸዋል።

በእሱ መዋከብ ዘና ወዳሉ የሥራ ባልደረቦቹ ዞሮ “ያማቸዋል እንዴ?” ይላል። አዛውንቷ ይናገራሉ “ምን ያበጀሁ ይመስልሃል? ክራር! በሰላም ከባሌ ጋር ሠርቼ በኖርኩ የጣሊያን ቂም በቀል በዘለሰኛ ገደለኝ። ልብ አድርግ! ሰው በጥይት ብቻ አይሞትም! ቀን ጠብቆ ያጠቃ ጠላት ሥጋ ብቻ አይገልም። መንፈስም ነው። ሆሆ!” ተሳፋሪው አንዴ አዳፋ ልብሳቸውን አንዴ አኳኋናቸውን እስተዋለ የወደቀ መልአክ ፊቱ ሲንፈራገጥ እንደሚያይ ሁሉ በትዕንግርት ይቃኛቸዋል። በመላው ተሳፋሪዎች ዓይን መታጀባቸውን ሲያጤኑ፣ “ሐበሻ ዓይኑ ድንጋይ ሰብሯል’ ይሉኝ ነበር እሜቴ! ነፍሳቸውን ይማርና! እኒያ ጀብደኞች አዲስ አበባን ሲያስጨፈጭፉ እሜቴም በተኙበት ቤታቸው ተቃጥሎ ሞቱ። እኔን እሜቴ! ምነው ግን እዚህ አገር ሳይገል አቁስሎ እየተወ የሚያቋስለው ይበዛል?” ሥነ ልቦናዊ ቀውሳቸው ከዕድሜያቸው መንጎድ ጋር በመጀመሩ ተሳፋሪዎች ከንፈር መምጠጥ ይዘዋል። ወያላው የቀረ ሁለት ሰው ብሎ ጋቢናውን ይከፍታል። ዛሬ እንደ ዘበት ጠብታ የምትመሸው መዓልት የነገ እኛነታችን ጠራቢ መሆኗን ጥቂቶች ልብ እንላለን። ልብ ግን ሥፍራው የት ይሆን? የዘንድሮ ሰው ግን፣ ‹‹ልብና ሲቪ ኦሪጅናል አይሰጥም፤›› እያለ ማላገጡን ሰምታችኋል?

ታክሲያችን ሞልታ መንቀሳቀስ ጀምረናል። አጭር መስላ በዘመን ክፍለ ዘመን ላይ ተፅዕኖ የምትጽፍ እዚህች ቅፅበት እንብርት ላይ ተሰብስበናል። “ስማ እንጂ!” አዛውንቷ ወያላን ይጠሩታል። “ሮም ትሄዳለህ? ሮም ውሰዱኝማ! ውዴን የበላውን አውሬ ባገኘው የት እንደጣለው ልጠይቀው እስኪ!” ንግግራቸው ሐዘን የጫረባትና ታሪካቸውን የማወቅ ጉጉት ያደረባት አጠገባቸው የተቀመጠች ቀዘባ፣ “ማንን ነው?” ስትል ጠየቀቻቸው። “ባለቤቴ! የፍካቴ ዘመን ስቅታ ነዋ። ‘ታማኝ ባልንጀራ ከእናት ልጅ እኩል ነው፤ ኧረ ተው ጓዴ ባንለያይ ምነው?’ ብዬ የተዳርኩለት። እንዳንቺ አበባ ሳለሁ። እሱም እንደ እናንተ እንደ ዛሬ ልጆች መጀመሪያ የመውደቂያዬን፣ ኮንዶሚኒየም ቤት ሳይኖረኝ፣ ሚሊየን ብር ሳልቆጥር ሳይል ባዶ እጁን አገባኝ። የደግ ቀን ባልጀራዬ ነበር። እውነት ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ሊበቀል አድዋን ወረረ? እኔን እንጃ። ማይጨው ዘምቶ ሞተ። ክፉ ቀን ሲመጣ በምርጫ የሚሞት አለ? ምርጫ የሰላም ቀን ዕጣ ነው አየሽ። ብታውቂበት ተጠቀሚበት፤” ብለው እንባ ያቀረረ ዓይናቸውን ባዳፋ ልብሳቸው አሹት። “አልቀበረዋቸውም እንዴ?” ቆንጅት ጅል ጥያቄ ጠየቀች። አዛውንቷ በሳቅ ፈረሱ። “አይ የዘንድሮ ልጆች! እንዲያው ይኼን ያህል የኑሮ ጫና ነገረ ዓለሙን ቢያጭበረብርባችሁ የአነጋገር የአጠያየቅ ወጉንም ቀማችሁ? ምነው ልማቱ ይኼን ይኼን አይመለከትም መሰል? አይ ጉድ!” በረጅሙ ተንፍሰው ሲያበቁ “ . . . አሞራ ሊቀብረው ተሰናብቶኝ ሄዶ እኔ እንዴት ልቀብረው እችላለሁ? ሞኝ። ፋሽሽት በቋሚና ሟች ለሁለት ከፍሎን አገሩ ሲገባ ‘ለበረሃው ገብርኤል አትሳልም ወይ፣ ለቁልቢው ገብርኤል አትሳልም ወይ፣ ከእኔ መለየቱን ወደኸዋል ወይ’ እያልኩ ቀረኋ! ኧረ ክራሬን ፈልጉልኝ! የፍቅር ርስቴን ባይመለስልኝ እንጉርጉሬንም ልነጠቅ?” እያሉ ጮሁ። ቆንጅት ጥያቄዋን ገታች። ሲበዛብን የዝምታን ለምድ መልበሱን አጉል የተላመድነው ይመስላል!

መሀል መቀመጫ በአዛውንቷ ቁስል የሚብተከተኩ ጎልማሳና ወይዘሮን አልፎ ካጠገቤ በስልክ ጨዋታ የያዘ ወጣት ተቀምጧል። ከሴት ጓደኛው ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደሚገኝ ያትታል። “ምን አልኳት እኔ? ዕድሜ መጠየቅ ያስኮርፋል?” ይላል። መጨረሻ ወንበር ላይ በተሰመሳሳይ የዕድሜ እርከን ውስጥ የሚገኙት አራት ተሳፋሪዎች ከአፍ ከአፉ እየነጠቁ ይተርቡታል። አንዱ፣ “ዕድሜ መደበቅ በሰው አልተጀመረ እግዜርስ መቼ ተናገረና? አቤት የዘንድሮ አፍቃሪና ፖለቲካ ፓርቲ ግን? ‘ቫላንታይንስ ዴይ’ አበባ በመግዛትና ምርጭ ሲደርስ በመቀስቀስ ይወሰን? ምነው ይኼን ያህል ጥበብ ራቀን?” ይላል። ካጠገቡ ተቀብላ፣ “ዝም ብላ 23 አትለውም? ምን አስጨነቃት? ስንትም ብትሆን የገዢው ፓርቲ ልጅ ነኝ ብላ ድርቅ ማለት ነው፤” ትላለች። አንድምታዋን ሊያስፈታ፣ “እኮ ምን ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ?” በማለት አጠር ቀጠን ያለ ተሳፋሪ ሲጠይቃት፣ “ያለልማትና ዴሞክራሲ አላውቅም ነው ሲፈታ። በአጭሩ ‘ገዴ ብልፅግና ነው’ ነው። አይ ካለ አሸባሪና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ነው ብላ ሳይቀድማት መቅደም፤” ስትለው ሳቀ። ሌሎቻችንም ፈገግ አልን። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ሆኖ ልጁ በዕድሜሽን ንገሪኝ ቀሽም ጥያቄ ላከሸፈው መግባባት ለምን እጠየቃለሁ እያለ ይደነፋል። አራተኛው ተሳፋሪ ደግሞ፣ “እውነቱን ነው እንኳን የኖሩትን መኖር አለመኖራቸውን አጣርተው የማያውቁትም አርባና ስልሳ ዓመት እንገዛለን ብለው ያስወራሉ። ምናለ ብትነግረው?” ይላል። ወደ ደራው የወጣቶቹ ጨዋታ ጆሮውን የጣደው ጎልማሳ፣ “መቼ ልጅቷ የባርነት ዘመን ተጠየቀችና ነው መግዛትና መገዛትን እዚህ መሀል የምታመጡት?” ሲል በከፊል ዞሮ ጠየቀ። ጥያቄው ሌላ ጥያቄ ወለደ። “አንተስ ማንን ለማስወንጀል ባርነትን እዚህ የምትደነጉረው?” የሚል። ጫን ያለው መጣ አለ ሰውዬው!

ጉዟችን ቀጥሏል። አጠገቤ የተሰየመው ወጣት የስልክ ጨዋታ ወላ በኔትወርክ ወላ በአንዳች መላ ሊደመደም አልቻለም። ይኼን የታዘበው ጎልማሳ “ይኼኔ እንደገና ዛፍ መብራት ቦግ እልም እያለ ስላንገላታን የኃይል መቆራረጥ እየጮህን ቢሆን ኖሮ፣ አይደለም ከኔትወርክ ቀጣና ከሲም ካርድ ባለቤትነትም በተፋቅን ነበር፤” ብሎ አዲስ ብሶት ያራግፍብን ጀመር። “የመብራትንስ ነገር ተወው፤” ካጠገቡ የተቀመጠች ወይዘሮ አገዘችው። “ምኑን ተውኩት ይኼን እንደ አቦ ሸማኔ የሚምዘገዘግ የለውጥ ጊዜ ወይ ወገቡን ወይ ጭራውን ሳልይዘው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እያስተጓጎለኝ፤” ይላታል። ጋቢና የተቀመጡት ተሳፋሪዎች በበኩላቸው፣ “ሳይናጡ ቅቤ ሳይታሹ ምጣድ ይኮናል እንዴ? ይኼው ዛሬ ጂቡቲ ካልተዋሀድኩ የምትለው እኛ በሻማ ራት በልተን ብንተኛ መስሎኝ፤” ይባባላሉ። ሾፌሩ፣ “ከይቅርታ ጋር የበላተኛው ቁጠር ትንሽ አልተጋነነም? እኛ ማለት ለመሆኑ እነማን ነን?” ብሎ ይጠይቃል። ሰዎቹ ይመልሳሉ፣ “ለዘለቄታው ከሚያጠግበን ስትራቴጂና ፖሊሲ አንፃር ዛሬ ዓይኔ ካልበራ ሙግትስ አልበዛም?”  ጥያቄውን በጥያቄ። “ጉድ እኮ ነው በዚህ የፀሐይ ንዳድ ስለጨለማ ማውራት ግፍ ነው፤” ብላ ልትገላግል ከአዛውንቷ አጠገብ ያለችው ቀዘባ ስትገባ ጎልማሳው፣ “ያደለው ስለኑክሌር ኃይል ያወራል እኛ እዚህ በፈረቃ ብርሃን እንታደላለን፤” አለና ደነፋ። “መቻል ነው ወንድሜ እዬዬም ሲደላ መሆኑን ከታሪክ መማር ይበጃል፤” ትላለች መጨረሻ ወንበር። ከጎኗ ያለው ደግሞ፣ “ምን ይደረግ? እኔም ይኼው ሳላስበው ድርግም ባለበኝ ቁጥር የዕድሜ ማራዘሚያዬን ይዤ ቁጭ እላለሁ፤” አለ። “ምንድነው ደግሞ የዕድሜ ማራዘሚያ?” ሲለው ሁሉም፣ “በርጫ ነዋ! መብራት እስኪመጣ ተብሎ ይጀመራል መጥቶ እስኪሄድ እኛ በምርቃና የራሳችንን መብራት አብርተን ዕድሜ እናራዝማለን፤” ከማለቱ “የዕብድ ቀን ቶሎ አይመሽ’ አሉ። እስኪ ሾፌር ቶሎ ቶሎ ንዳው፤” እያለ የሚያጉረመርመው በዛ። አጉረምራሚ ሁላ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወያላው ደንግጦ ዓይን ዓይናችንን ሲያይ ሒሳብ መቀበሉን የዘነጋ ይመስላል። እኛው አስታውሰን መክፈል ስንጀምር ጋቢና የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ “የእሳቸውንም አብረህ ቁረጥ፤” ብሎ አሥር ብር ሰጠው። አዛውንቷ “የማንን? ጣሊያን የሠራልኝ እግዜር ዕድሜ አርዝሞ የሚጫወትብኝ ካንተ ጋር ሒሳብ ልወራረድ መሰለህ? መልስለት እኔ ራሴ እከፍላለሁ፤” ብለው ተቆጡ። “ምን ችግር አለው እማማ ከማክበር እኮ ነው!” ሲላቸው መልሶ፣ “ነገርኩህ እኔ ካንተ ጋር ሒሳብ ልወራረድ ዘጠና እስክጠጋ አልኖርኩም። ‘ሐበሻ እንዳይደሰት እግዜር ሒሳቡን አስልቶ ጨርሶታል’ ያለውን ደራሲ ታውቀዋለህ? ረስቼው ለካ እናንተ ማንበብ አትወዱም። ምን ታደርጉ በአቋራጭ የሚበለፅገው አምታችና አጭበርባሪው ከመሬት እየተነሳ ፎቅ ሲደረድር፣ ቅንጡ አውቶሞቢል ሲያሽከረክር እያያችሁ በቅሎ የማይነዳ ደራሲ ጽሑፍ ለምን ታነባላችሁ?” እያሉ ጉንፋቸውን ፈተው አምስት ብር ለወያላው ሰጡት። ተቀበለ። “የእውነት ፍቅር እንዲህ አሳበዳቸው ብለህ ታስባለህ?” የሚለኝ ደግሞ አጠገቤ የተቀመጠው የፍቅረኛው ነገር ያስጨነቀው ወጣት ነው። ልመልስለት ስንተባተብ፣ “እያየህ እየሰማህ ምን ትጠይቃለህ? ምንስ ቢሆን ሰው ለታይታ እንዲህ በአደባባይ ያላፊ አግዳሚው መጠቋቆሚያ ሊሆን ይወጣል?” ብሎ ከኋላ ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ መለሰ። ካጠገቡ አንዷ ተቀብላ፣ “እኛስ ይኼን ፈርተን አይደል ከራስ በላይ ንፋስ በሚል ብሒል በግለኝነት ታጥረን ለእውነት ከልብ ለሆነ ነገር ዋጋ መክፈል ያቃተን? ወይ አልሞቅን ወይ አልቀዘቀዝን! እንዲሁ መሀል ላይ እሪ ብለን አናለቅስ ከት ብለን አንስቅ። ብቻ ወደነፈሰው ስንነፍስ ዕድሜ ይከንፋል፤” አለች። ወያላው “መጨረሻ” ሲለን አዛውንቷን አስቀድመን በየፊናችን ስንበታተን የሁላችንም ሞባይል ስልኮች የመልዕክት ማድረሻ ድምፆች ተንጫረሩ፡፡ ከምሽቱ 12 ሰዓት ካለፈ በኋላ ቴሌ “እንኳን ለአደዋ የድል በዓል አደረሳችሁ፤” የሚል ነው፡፡ አዛውንቷ ስልካቸውን አይተው እየሳቁ፣ “ድሮ ‘የዘገየሽበት ምን ይሆን ምክንያቱ፣ ዓይኖቼ ተራቡ ደረሰ ሰዓቱ’ ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ለቴሌ ‘የዘገየህበት ምን ይሆን ምክንያቱ፣ የአደዋ በዓል አለፈ ሰዓቱ’ እንበለው እንጂ ሌላ ምን  እንጨምርለት?” ብለውን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት