በጉደታ ዘለዓለም
ኢትዮጵያ አምስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና ማለት ከያዘች ሰነባብታለች፡፡ ከ36 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለአንድ ወር ከ12 ቀናት በ45 ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ ለመምረጥ መመዝገቡን ሰምተናል፡፡ የሕዝብ የምርጫ ታዛቢዎች ከተመረጡ ሰነበተ፡፡ ፓርቲዎች ዕጩዎችን አስመዝግበዋል፡፡ ምልክታቸውንም አፅድቀው ካለፈው ሳምንት አንስቶም ፖሊሲዎቻቸውንና ስትራቴጂዎቻቸውን ከአማራጮቻቸው ጋር ማስተዋወቅ ጀማምረዋል፡፡
እስካሁን በተሄደው ርቀት የታዩ ክፍተቶች በተለይ አንዳንድ ፓርቲዎችንና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ያነታረኩ ጉዳዮች የሉም ባይባልም፣ አሻሚ የሚባሉ አይመስለኝም፡፡ አንደኛው ፓርቲዎች በውስጣቸው በተፈጠረ አለመግባባት አንድ አካል ሆኖ መሄድ ላይ ያሳዩት መጓተት ነበር፡፡ በተለይ አንድነትና መኢአድን የመሳሰሉት ፓርቲዎች አመራሮቻቸው ውዝግቦች በማንሳታቸው ብዙዎች ታዛቢዎችን ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ›› አሁን ላይ ማለት ማን ይበጃል አስብሏቸዋል፡፡ ሒደቱ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እንዲፈታ በተደረገው ጥረት የምርጫ ቦርድ ውሳኔን እንደ እንግዳ ነገርና ጫና የቆጠሩት ባይታጡም፣ ሕግና መርህን ተከትሎ ለመሥራት ግን ብቸኛው መፍትሔ ከዚህ ውጪ አልነበረም ባይ ነኝ፡፡
ከሰሞኑ አንዳንዶች እንደ ውዝግብ ምንጭ የቆጠሩት ጉዳይም በምርጫ ሕጉ መሠረት በአንድ የምርጫ ክልል የሚፎካከሩ ፓርቲዎች (ዕጩዎችን) የመወሰን ተግባር መካሄዱ ነው፡፡ ነገሩ አዲስ የመሰለው በሌላው ዓለም ተወዳዳሪዎች ሁለትና ሦስት ፓርቲዎች ወይም ዕጩ ተፎካካሪዎች ሲሆኑ፣ በእኛ አገር ግን በአሁኑ ጊዜ 57 በመሆናቸውና በመብዛታቸው ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ፓርቲዎች ደግሞ በአንድ የምርጫ ክልል በማፎካከር ሒደቱን ‹‹የጨረባ ተስካር›› ማድረግ የዴሞክራሲ ሒደቱን ሊያሳድገው ካለመቻሉም በላይ መራጩን ሕዝብም ማደናገሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ፓርቲዎች ባላቸው ብቃትና ቁመና ወይም ‹‹ሕዝብ ይደግፋቸዋል አይደግፋቸውም›› ብሎ ከመፈረጅ በመውጣት፣ በእኩል መድረክ (በዕጣ) አወዳድሮ እንዲሳተፉ ማድረግ በሕጉ ከመቀመጡም ባሻገር ፍትሐዊ እንደሆነ ጥርጥር የለውም ባይ ነኝ፡፡
አሁን የምርጫ ጉዞው ከመሰንበቻው አንድ ማርሽ ጨምሮ ወደ ፍፃሜ ጉዞው እየገሰገሰ ነው፡፡ ታዲያ የመርህ ሰብዕና መገንባት፣ ከስሜት መፅዳትና ለዘለቄታው ዴሞክራሲ መጐልበት መሥራት ግድና አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ገጽታ ማየት ስለሚበጀን እሱን ለመነካካት ልሞክር፡፡
መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ
ከሰሞኑ እንደታዘብነው የመንግሥት (የሕዝብ) መገናኛ ብዙኃን የአየር ሰዓት በተዘረጋው ድልድል መሠረት እያስተናገዱ ነው፡፡ አንዳንድ የኅትመት ውጤቶችም የተረከቡትን ጽሑፍ በማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ጽሑፍ የላኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ገጽ ጭምር ባዶ አድርገው ማስተናገዳቸውን አይተናል፡፡ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት አጠቃቀምም ቢሆን በቀመሩ መሠረት ሒደቱን የሚያግዝና በታዳጊ ዴሞክራሲ ውስጥ የሚበጅ ተግባር እንደሆነ ይታየኛል፡፡
በቀጣዩ ጊዜም ከመገናኛ ብዙኃን የምንጠብቃቸው ጉዳዮች አንደኛው የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች በተቻለ መጠን፣ የሁሉንም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች አማራጮች በፍትሐዊነት ለሕዝብ የማድረስ ሥራን መሥራት አለባቸው፡፡ በተለይ ፓርቲዎች ያላቸውን ፕሮግራምና አማራጭ ብቻ ሳይሆን፣ የዕጩዎች ጥንካሬ የፖለቲካ ሰብዕና አገራዊ ስሜት በተለይ ለሕገ መንግሥት መርሆዎችና ለብሔራዊ ጥቅም የሚያሳዩትን ፍላጐት ማቅረብና ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ መወቃቀስና መዘላለፍ የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡ በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደት ድክመትን ማጋለጥ፣ ክፍተትን ለሕዝብ ማሳየት ተገቢ ቢሆንም መጠቋቆርና መጠላላት የሚያበረታታው ጽንፈኝነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን ነው፡፡ ለትውልዱም ከሰላማዊ ውድድር ይልቅ ጽንፈኛ ፉክክርንና መበላላትን ወይም የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሒሳብን እያሳዩ ማሰገድ ከመሆን ውጪ አይሆንም፡፡ ስለዚህ መገናኛ ብዙኃን የዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አወዳዳሪነት ሚናን ማጐልበት ብቻ ይጠበቅባቸዋል፡፡
እንደ ምርጫ ቦርድና ሌሎች መንግሥታዊ የዴሞክራሲ ተቋማት መገለጫ፣ ማብራሪያና ሐሳብን የማስተናገድ ኃላፊነት የመገናኛ ብዙኃን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እዚህም ላይ ቢሆን ግን በሕግና በሥርዓት ላይ ተመሥርተው፣ በሚዛናዊና በምክንያታዊነት ላይ ተንተርሰው የቀረቡ ገለጻዎች መሆናቸውን አመሳክሮ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ገና ለጋ በሚባል የዴሞክራሲ ሜዳና ጉዞ ላይ ሁሉም ትክክል ነው ብሎ ማስተናገድ ሒደቱን አያራምደውም፡፡ በተለይ በአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ያሉ የሕዝብ ግንኙነት ሙያተኞችና ኃላፊዎች በመንግሥት ‹‹ባርኔጣ›› የፓርቲ መግለጫና ቅስቀሳን አለማደባለቃቸው ካልታየ ሚዛናዊነት ገደል ይገባል፡፡ ስለዚህ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብ የሚያምናቸውና የሚቀበላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ብርቱ መሣሪያ መሆናቸውን ሊያረጋግጡ ግድ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ጊዜ አገር ሊመሩ አይችሉም፡፡ በረጅም ጊዜ ሒደት ግን የማይደርሱበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ሒደት ነው ፖለቲካዊ ጉዞውም ሰላማዊ ነው እስከተባለ ድረስ፣ በሃያ ዓመታት ወይም በአርባ ዓመታት የሚያልቅ ትግል የለም፡፡ መቶ ዓመትም ሆነ ከዚያም በላይ በትውልድ ቅብብሎሽ ጭምር እንደሚፈጸም አስቦ መታገል ነው መፍትሔው፡፡
ይህ ማለት ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ፓርላማ አይገቡም ወይም በክልል ምክር ቤቶች አይታደሙም ማለት አይደለም፡፡ በነፃና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝብ ሊመርጣቸው ግን ግድ ነው፡፡ የሕዝብ ይሁንታ ያላገኘ ፓርቲ ወይም ተወካይ በዕጣ የፓርላማ ወንበር ሊያገኝ አይችልም፡፡ ባያገኝም ደግሞ ራሱን ከዴሞክራሲያዊ ፉክክር ሊያገል አይችልም፣ አይገባም፡፡ ይልቁንም ካለፈው ጊዜ ተምሮ፣ ጠንካራ ጎራን ለይቶ ለተጨማሪ ትግል መዘጋጀትን መፍትሔ አድርጐ ለሌላ ውጤት የሚኖረውን ጊዜ ይሠራበታል፡፡
በነገራችን ላይ በእኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፉክክር ሒደት ውስጥ ስለታሰሩ ሰዎች አትናገሩ፣ በገዥው ፓርቲ እንከኖች ላይ ሐሳብ አትስጡ፣ ወይም በመንግሥት (አሸናፊው ፓርቲ) ድክመቶች ላይ አጀንዳ አትቅረፁ የሚሉ የዋህ ወይም አታላይ ፖለቲከኞች ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ትክክልም አይደሉም ማለት እወዳለሁ፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ክፍተቶቹንና ጉድለቶቹን የሚነግረው (ሂስ የሚያደርገው አካል) ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብ ተደራጅቶና በፖለቲካ መድረክ መቀናጀት የሚችልበት አንድ መድረክ በፖለቲካ ፓርቲዎች መደራጀትና መታገል ነው፡፡
በእርግጥ ዜጐች ሊደራጁ የሚገባቸው ለመቃወምና ስህተት ለመንቀፍ ብቻ አይደለም፡፡ አማራጭ ይዞ ለመታገል ሲባል ነው፡፡ በዚያ ውስጥ ግን በነፃነትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ መተቸት የማይገሰፅ መብታቸው ነው፡፡ በየትኛውም አገር የማይተች መንግሥት የለም፡፡ በመሠረታዊ መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ ጉድለት መንገር ‹‹አገር ማፍረስ›› ሊባል አይችልም፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እኮ ተወዳድረው በአሸነፏቸው ፓርቲ መሪዎች ይተቻሉ፣ ፖሊሲያቸው ይወቀሳል፡፡ ዋናው ነገር ትችትን በውጤትና በስኬት በማስተባበል በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነትን መፍጠር እንጂ፣ ‹‹አልነካም ፍፁም ነኝ›› በሚል ፈሊጥ ራስን ኮፍሶ ዴሞክራሲን መገንባት አይቻልም፡፡
በአገራችን ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ያለው መሠረታዊ ችግር በተቋቋሙበት መርህ ላይ ግልጽ አቋም አለመያዝ ነው፡፡ ከገዥው ፓርቲ ወይም ከሌሎች ተቃዋሚዎች የሚመሳሰሉበትም ሆነ የሚለያዩበት ግልጽ አይደለም፡፡ እርስ በርሳቸው የሚዋሀዱበትና የሚተሳሰሩበት የጋራ ወሰን የላቸውም፡፡ መብዛታቸውም ያጠራጥራል፡፡ ይህ ማለት ግልጽ ፖሊሲና ማኒፌስቶ የማጣት ውጤት ነው፡፡ ይህ እውነታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ከመምጣት ይልቅ በምርጫ ሰሞን ‹‹ደፍ ደፍ›› በሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተጋረደ መምጣቱ ደግሞ አሳሳቢና ለዴሞክራሲው እንቅፋት ሆኗል፡፡
የፖለቲካ ሥራ ትልቅና የአገር ኃላፊነትን የመሸከም ወኔ የሚፈልግ ነው፡፡ መርበትበትና መሸበርን አይወድም፡፡ በሰላማዊ ትግል እስከተሠለፉ ድረስም እንደ ማንዴላ፣ ማህተማ ጋንዲና መሰል የሰላም ጀግኖች መስዋዕትን ተቀብሎ ለብርሃን መብቃትን መታገስ ግድ ይላል፡፡ ‹‹ሲሞቅ በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ ማቡካትን›› አይወድም (ሕገወጥና ሕጋዊ ተግባራትን አለመፈጸም እዚህ ውስጥ ይገባል)፡፡ በዚህ ረገድ መልካም ጅምር ያላቸው ጠንካራ የአገራችን ፖለቲከኞች የሉም ባይባሉም እየበዙ አይደሉም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና መሪዎቻችን የአገርን ጥቅም፣ ብሔራዊ ጉዳይና የሕዝብ እሴትን በድፍረት መደገፍ፣ መንከባከብና ውግናን መግለጽም የብስለት መለኪያ ነው፡፡ በአጠቃላይ ፖለቲከኞቻችን የሕዝቡን የግንዛቤ ደረጃ፣ የዓለምን የዴሞክራሲ መርሆና ዕድገት ሊያጤኑ ይገባል፡፡ ለዕለት ጥቅምና ለትዝብት ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልግም፡፡
ገዥው ፓርቲን በተመለከተ
ኢሕአዴግ ፓርቲ ቢሆንም ገዥ በመሆኑ መንግሥት ነውና ተነጥሎ መታየት አለበት፡፡ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ መወዳደርና ለማሸነፍ መሰናዳት ያለበትን ያህል፣ ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችን አለማንሻፈፍ፣ የዜጐች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አለመጉዳቱን ካላረጋገጠ ከፈተና ይወድቃል፡፡ በተሳሳተና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ‹‹ያሸነፈ›› ቢሆን እንኳን እንዳሸነፈ አይቆጠርም፡፡ ያለጥርጥር የሕዝብ ተቀባይነት አጥቶ አንድ ቀን በሌላ መንገድ ከሥልጣኑ ለመውረድ መጋለጡም አይቀርም፡፡
ማንኛውም ገዥ ፓርቲ የፈለገውን ያህል መልካምና ውጤታማ ሥራ ቢያከናውን፣ ያልተደሰቱ ወገኖችን ወይም ሕዝብ ያልረካባቸውን ዘርፎች ለይቶ መረባረብ አለበት፡፡ በውስጡ በመንቀዝና በመበላሸት ምክንያት ሕዝብ ሲያማርር ችግሩን መንቀስና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ማስወገድ ወይም ማረም ይገባዋል፡፡ በአብላጫ የሕዝብ ድምፅ ነፃና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን መመረጡን ማረጋገጥም ግድ ይለዋል፡፡
በዚህ በኩል ኢሕአዴግ የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ነገር ግን በአፈጻጸም የሚሸረሸሩ የፓርቲና መንግሥት ሚና መደበላለቅ፣ በፓርቲው ስም የግለሰቦችን ጥፋት መሸፋፈን፣ ምሁራንን በሚገባው ልክ ያለማዳመጥና ከከተማ ይልቅ ገጠር ነው መሠረቴ (80 በመቶ ገጠር መሆኑን መነሻ በማድረግ) ማለቱን መፈተሽ አለበት፡፡ በየትኛውም ዓለም የፖለቲካና ኢኮኖሚ ልሂቃኑ የከተማ ነዋሪ ሆነው ሳለ፣ ይህን ኃይል ‹‹እንደ ሌላ›› ቆጥሮ በደምሳሳው መንጐድ ይታያል፡፡ በዚህ በኩል በሊግ፣ በፎረም፣ በደጋፊ፣ በአባልና በአጋር ስም ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉ ዜጐች ቁጥራቸው ቀላል ባይሆንም የማይሳተፉና የሚቃወሙኝ እነማን ናቸው? ለምን? ምን አጥፍቼ? ወዘተ እያለ ካላጣራና የእርምት ዕርምጃ ካልወሰደ ጥረቱ ጐደሎ መሆኑ አይቀርም፡፡
ኢሕአዴግ መንግሥት በመሆኑ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ዋነኛ መሪ መሆኑንም መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህ አንፃር ከአድርባይነትና ከአስመሳይነት የወጣ፣ በትግልና ግልጽ አስተሳሰብ እየተገነባ የሚሄድ የፓርቲና የፖለቲካ ጉዞን መላበስ አለበት፡፡ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸውን አመርቂና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ሊያሰፋ የሚችለው በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ውስጡ የሚታዩት ጨለምተኛ ነገሮችም መፈተሽ አለባቸው፡፡
ከሕዝብ የሚጠበቅ
ኢትዮጵያ ብዙ ወዳጅ አገሮችና ሕዝቦች ያሏትን ያህል ጠላተ ብዙና ተቀናቃኝ የማያጣት መሆኗን ማጤን ግድ ይላል፡፡ በተለይ አሁን አሁን በልማትም ሆነ በዴሞክራሲ ለመሻሻል በሚደረግ ጥረትና በሚታይ ውጤት ውስጥ ባላንጣ እንደሚበዛ መጠራጠር ሞኝነት ነው፡፡ ይህን እውነታ በመካድ፣ እህሉን ከአረም ሳይለዩ ከጠላት ወገን አለመሠለፍን ማጤን ይገባል፡፡
በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በሰላማዊ መንገድም ሆነ ለጊዜው መስሏቸው በትጥቅ ትግል መንግሥትን የሚገዳደሩ ኢትዮጵያውያን የዚሁ ሕዝብ አካል ናቸው፡፡ እነዚህን አካላት ድክመታቸውን እንዲያርሙና ጥንካሬያቸውን እንዲያበለፅጉ ማድረግ አንድ ተግባር ነው፡፡ ጭልጥ ብለው በብሔራዊ ጥቅም፣ በሕዝብና በአገር ሉዓላዊ መብቶች ላይ ሲነሱ ዝም ማለትም ሆነ መደገፍ ግን ከዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በዚህ በኩል ከሕግና ከሥርዓት በላይ አገራዊ ክብርንና የመጪውን ብሩህ ጉዞ ከግንዛቤ ማስገባት አለባቸው፡፡
በሌላ በኩል ስሜታዊ የፖለቲካ ድጋፍና ተቃውሞን እየናቁ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ይህ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ልዕልና የሚያገኝ ባይሆንም፣ ድጋፋችንም ሆነ ተቃውሟችን ምክንያታዊ መሆን አለበት፡፡ ከገዥው ፓርቲ አባላት ጀምሮ ያለበቂ መከራከሪያና እምነት በከንቱ የሚከተሉ ጀሌዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ሊረዱ አይችሉም፡፡ እንዲያውም በሚታይ መከራከሪያና ማሳመኛ ጉድለትን የሚያመለክቱና የሚቃወሙ ወገኖች ሊበልጡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ሕዝቡ ምክንያታዊና ሚዛናዊ የመሆን ዕድሉ ይበልጥ መስፋት አለበት፡፡
በአንድ ወቅት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን፣ ‹‹አሜሪካውያን ከጥንካሬያችን ጐን በመሠለፍ የውጤቱ ዋነኛ ተዋናይ የመሆናቸውን ያህል፣ በውድቀታችንም ውስጥ ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በሒደቱ ውስጥ ተኝተውና ተዘናግተው አልፈዋል፡፡ አልያም ካለምክንያት በስሜት አጨብጭበውልናል፤›› ያሉት ንግግር ለአባባሉ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡
ሕዝብ የሚባለው ባህር በተቀደደለት ቦይ እየተፍነከነከ የሚፈስ የወንዝ ውኃ ዓይነት ቢሆንም፣ በተለይ አዲሱ ትውልድ በዕውቀትና ከስሜት በፀዳ መንገድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ሊሳተፍበት ይገባል፡፡ ከሟቹም ከገዳዩም መሆን አይጠቅምም፡፡ አገሪቱ ገና ደሃ፣ ብዙ ችግረኛ ያለባት፣ ከሌላው ዓለም አንፃር ስትታይ ከጭራዎች ተርታ ያለች መሆኗን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡ ግን ደግሞ ከድህነት የመውጣት ብሩህ ተስፋም ይታያል፡፡ ስለዚህ በኃላፊነት የሒደቱ ሁሉ ንቁ ባለቤት መሆን ግድ ይላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡