በወይንሸት አላምረው
እዚህ አገር የሰለቸንና የመረረን ነገር ቢኖር ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ነው፡፡ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አቋም ከማራመድ ይልቅ፣ በወጀብ እየተገፉ መንጋውን የመቀላቀልና ጅምላ ሥሪት (Mob Mentality) መሆን እየገዘፈ ነው፡፡ ለሐሳብ የበላይነት የሚሰጠው ክብደትና አክብሮት እየተተወ ከእነ እከሌና እከሊት ጋር በጭፍን መንጐድ አገሪቱን እያሳመማት ነው፡፡ ለፍቅራችንም ሆነ ለጥላቻችን መሪ መሆን የሚገባው ሥነ አመክንዮ (Logic) መሆን ሲገባው፣ በማስረጃ ያልተረጋገጠ የወሬ ሰደድ እሳት ተቆጣጥሮናል፡፡
ከላይ ያነሳሁትን ሐሳብ ገፍቼ እንዳቀርበው ያነሳሳኝ ምክንያት በማኅበረሰባችን ውስጥ በብዛት የተንሰራፋው መርህ አልባ የፖለቲካ ውግና ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ ጐራ የተሠለፉ ወገኖች የራሳቸውን ዓላማ ብፁዕ ቅዱስነት እየሰበኩ፣ የተቃራኒዎቻቸውን ዓላማ ደግሞ አገር አውዳሚና ለሕዝብ ፋይዳ የሌለው አውሬ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ በተለይ የምዕራቡን ዓለም የሊበራል ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ወገኖችን በአገር አጥፊነትና አውሬነት በመፈረጅ የማያባራ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ያደርጓቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ የያዘው ርዕዮተ ዓለም ብቻ የዚህች አገር መፍትሔ እንደሆነ ሳንወድ በግድ ሊግቱን ይሞክራሉ፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ከእነሱ በተቃራኒ የሚሰማ ሐሳብ ለማዳመጥ ፍላጐት የላቸውም፡፡
በተቃዋሚው ጎራ ያሉ በተለይ ጽንፈኝነት የተጠናወታቸው ደግሞ ከእነሱ ውጪ ያሉ ሌሎች አማራጮችን ከማበሻቀጥ አልፈው፣ የግለሰቦችን አመለካከትና ማንነታቸውን በመዳፈር ጥላሸት ይቀባሉ፡፡ በፖለቲካ ትግል ውስጥ አንዱ ዋነኛ ፀጋ ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት እንደሆነ በሚኖሩባቸው የምዕራብ አገሮች ውስጥ እያዩ፣ በሐሳብ የሚለዩዋቸውን ወገኖች በአገር ሻጭነትና ጠላትነት ይወነጅላሉ፡፡ እነሱን በሐሳብ የሚቃወም ብቻ ሳይሆን፣ ‘ጐመን በጤና’ ብሎ የሚኖረውን ወገን ‘ፈሪ፣ ከሃዲ፣ መሀል ሰፋሪ፣’ ወዘተ እያሉ ስም ያጠፋሉ፡፡ ከአንድ ጽንፍ በስተቀር ሌላ እንዲሰማ ስለማይፈልጉ፣ ለሐሳብ ነፃነት ደንቃራ ሆነዋል፡፡
በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ጽንፍ ይዘው የሚተጋተጉ ኃይሎችና አጃቢዎቻቸው ለምክንያታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሩን በመዝጋታቸው፣ ለሐሳብ ልዕልና የሚተጉ ወገኖችን በሐሜትና በአሉባልታ ሲለበለቡ ኖረዋል፡፡ በአሉባልታ ላይ የተንጠላጠሉት ፖለቲከኞቻችን በሐሳብ የሚበልጡዋቸውን ወገኖች መቆሚያ መቀመጫ ሲያሳጡ፣ በዙሪያቸው የተሰበሰበው እንደ መንጋ የሚነዳው ደግሞ ችግሩ ምንድነው? በማለት እውነታውን ለመረዳት ጥረት ሲያደርግ አይታይም፡፡ በተለይ ‹‹ተምሯል›› ተብሎ የሚታሰበው የኅብረተሰብ ክፍል ከፍርኃት ቆፈኑ ተላቆ መጠየቅ ወይም መመርመር ሲገባው፣ የወሬና የሐሜት ወፍጮውን ይሰልቃል፡፡ አደባባይ ወጥቶ በግራና በቀኝ የሚታየውን ውዥንብር ማስቆም ሲገባው፣ ይኼው የኅብረተሰብ ክፍል ዋነኛው የአሉባልታ ማራገፊያ መሆኑ ከማሳዘን በላይም ያናድዳል፡፡
ድሮ ‹‹ምሁራኑ ፈሪ ናቸው›› በሚባልበት ጊዜ አንገታቸውን አቅንተው ወደ ፖለቲካው መንደር በድፍረት ይቀላቀሉ የነበሩ ምሁራን ከኋላቸው ይከተላቸው የነበረው ሐሜት አይረሳንም፡፡ በተለይ ስድስት ኪሎ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የነበሩ ብዙዎቹ ‹‹ምሁራን ተብዬዎች›› ደፈር ብለው የወጡትን ጓደኞቻቸውን በሐሜት ቢላዋ እንዴት ይዘለዝሉዋቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በምርጫ 97 ዋዜማ በዓይን ጥቅሻ ተጠራርተው ፖለቲካ ውስጥ የገቡት እነዚህ አሉባልተኞች ድፍረት፣ ወኔና የዓላማ ፅናት ስላልነበራቸው ብዙውን ጊዜ ልባቸው እንዴት ሥልጣኑ ላይ በቶሎ እንደሚንጠላጠሉ ያብሰለስል ስለነበር፣ የፖለቲካው ጥበብ ጠፍቶባቸው ነበር፡፡ በሕዝብ ግፊት የፈጠሩትን ቅንጅት በብልኃት መምራት አቅቷቸው ትግሉን ካንኮታኮቱ በኋላ፣ ለጥፋታቸው ማሳበቢያ የተጠቀሙት አሉባልታና ሐሜትን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳቸውንም ሆነ ፖለቲካውን ቀበሩት፡፡
በወቅቱ የአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል ብለው አደባባይ ላይ በልበ ሙሉነት ያሻቸውን ሲሉ የነበሩ ወገኖችም፣ የችግሩን መንስዔ መርምረው ሀቁን ከመረዳት ይልቅ በጅምላ የተረባረቡት በተወሰኑ ወገኖች በተለይም በአንድ ግለሰብ ላይ ነበር፡፡ ያ ሁሉ የተንቦገቦገ ትግል በአንድ ግለሰብ ሴራ ተጠልፎ መውደቅ ከቻለ፣ በትግሉ ዙሪያ የነበሩ ወገኖች በሙሉ አንረባም እያሉ መሆናቸውን መዘንጋታቸው፣ ምን ያህል በአገሪቱ ሥር የሰደደ የምክንያታዊነት መንጠፍ መከሰቱን ያሳየናል፡፡ ምክንያታዊነት በሌለበት ሐሜትና አሉባልታ ነግሠው አገሪቱ ሰው አልባ እስክትመስል ድረስ የደረሰውን ድብርትና ተስፋ መቁረጥ አንዘነጋውም፡፡ በአሉባልታና በሴራ የተተበተቡት ምሁራኑ የሚደግፋቸውን ሕዝብ መርተው ለድል ለማብቃት ከመታገል ይልቅ፣ ሜዳ ላይ በትነውት እነሱም ተበታተኑ፡፡
በአገራችን ውስጥ የሚጻፉ ‹‹ታሪክ ቀመስ›› መጻሕፍትን አንድ በአንድ ለመመልከት ሞክሩ፡፡ ታፍራላችሁ፡፡ ያለምንም ማጣቀሻና ዋቢ ማስረጃዎች የአገሪቱ ታሪክ በደመነፍስ ይጻፋል፡፡ በሕይወት ያሉም ሆነ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ታዋቂ ሰዎች ያዘጋጁዋቸው የታተሙና ያልታተሙ ጽሑፎች፣ የውጭ የታሪክ ምሁራን ያሳተሟቸው መጻሕፍት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ትውፊቶችና የተለያዩ ማስረጃዎችን ግራና ቀኝ እያዩ መመዝገብ ሲገባ፣ በስማ በለው የሚጻፉት መጻሕፍት አንገት ያስደፋሉ፡፡ ገንዘብ ወይም ርካሽ ዝና ለማግኘት ሲባል የሚጻፉ መጻሕፍት አገሪቱን ችግር ውስጥ እንደሚከቱ ተዘንግቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአደዋ የድል በዓላችንን አስመልክቶ ወፍ ዘራሽ የሆኑ ትንተናዎች ከፖለቲካ ፍጆታ አንፃር ሲወጡ ማየት ያሳፍራል፡፡ ታላቁ የአደዋ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ኩራት፣ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ የነፃነት ተምሳሌት ሆኖ እያለ አንዳንድ ወገኖቻችን ድሉን ለማንኳሰስ ሲፈልጉ አይተናል፡፡ ታላቁ መሪ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክን ለመቃወም ብቻ ሲሉ ለድሉ የተለየ ገጽታ የሚሰጡ ወገኖች በሐሳብ መምከናቸውን ከመንገር ባለፈ ሌላ ቁም ነገር የላቸውም፡፡ ታሪክን ማዛባት ለህሊና የማይመች ከንቱ ተግባር መሆኑን መረዳት የተሳናቸው ወገኖች፣ አዲስ ጠማማ ታሪክ ለመጻፍ ሲዳዱ አይሆንም ሊባሉ ይገባቸዋል፡፡ አሉባልታ አገር አይገነባም፡፡
በአንድ ወቅት በአንባቢነቱና በአሰላሳይነቱ ይታወቅ የነበረ ትውልድ ለእናት አገሩ ብልፅግናና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ባደረገው ትግል መውደቁን አንዘነጋውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ላመነበት ዓላማ ደረቱን ለጦር እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ የተሰዋውን ትውልድ የዘመናችን አሉባልተኞች ‹‹ጀሌ›› ሲሉት ተደምጠዋል፡፡ እነሱ በዘመናቸው ድፍረት አጥተው ደፋሮቹን ከኋላ ሲያስመቱ እንዳልኖሩ፣ አዲሱ ትውልድ የእነሱን የተንጋደደና የአጥፍቶ ጠፊ ፖለቲካ መንበር እንዳይረከባቸው በሩን ይዘጋጉበታል፡፡ ከዚያ የመጠፋፋትና የጥላቻ አረንቋ ውስጥ ሆነው በምክንያታዊነት ለማሰብ የሚሞክረውን አናት አናቱን ይሉታል፡፡ እንኳን ትውልድ ሊቀርፁ ትውልዱን የባሰ ወደ ገደል ይገፉታል፡፡ ለሐሳብ ልዩነት ቦታ ሊሰጡ ቀርቶ ለምን የእነ እከሌ ወይም እከሊት ደጋፊ ሆንክ? ወይም ለምን መሀል ሰፋሪ ትሆናለህ? እያሉ ግራ ያጋቡታል፡፡ በጣም ይሰለቻል፡፡
በዚህ ዘመን መማር ለአገር ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ገፀ በረከት መሆን ሲገባው፣ ብዙዎቻችን በገባንና ባወቅነው መጠን ጥያቄ አናቀርብም፡፡ ቢጤዎቻችንን ወይም ታላላቆቻችንን ብቻ እየተከተልን በደመነፍስ እንነጉዳለን፡፡ በተማረውና ባልተማረው የኅብረተሰብ ክፍል መካከል ያለው ልዩነት አልታይ እያለ፣ ሁሉም በአንድ ዓይነት ወርድና ቁመት አንድ ላይ ይነጉዳል፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲን ለምን እንደምንደግፍ ስንጠየቅ፣ የዚያን የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማና ፕሮግራም በአጭሩ እንኳን የማስረዳት ብቃት የለንም፡፡ ድጋፋችን ተቃራኒውን ከመጥላት የመነጨ ስለሆነ ብቻ ስለምንደግፈው ፓርቲ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲ ትንተናዎች ሰምተን አናውቅም፡፡ ለማወቅም አንሞክርም፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት ከሆኑ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በቀር በአደባባይ የፓርቲውን ገጽታ በተብራራ ሁኔታ ለማስረዳት የሚሞክር የለም፡፡ ለነገሩ የንባብ ባህሉም ደካማ ነው፡፡
ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸውን በርዕዮተ ዓለማቸው ከማነፅ ይልቅ፣ በሚቃወሙዋቸው ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲ ላይ በጠላትነት ስለሚያዘጋጁዋቸው ለሐሳብ የበላይነት የሚደረገው ትግል ደካማ ነው፡፡ በስሚ ስሚ ካልሆነ በስተቀር ፓርቲዎቹ በተጠና ሁኔታ አባላትን በንድፈ ሐሳብ ትንተና ሲያዘጋጁ አይታዩም፡፡ ሐሳብ የመከነበት ደግሞ ለምክንያታዊ የፖለቲካ ትግል ራሱን ስለማያዘጋጅ የመጨረሻው ማረፊያው አሉባልታ ይሆናል፡፡ የገዛ የትግል ጓዶቹን ሳይቀር በሐሜት ቢላዋ ይዘለዝላቸዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት እንደ ውኃ ጥም በሚያቃጥልበት አገር ውስጥ፣ ሰዎች በነፃነት ሐሳባቸውን ሲያንፀባርቁ ጠላት ይደረጋሉ፡፡ ሐሳብ እንዲመክን እየተደረገ አሉባልታ አገሩን ይቆጣጠረዋል፡፡
አገራችንና ሕዝባችን ከአሉባልተኞችና ከሐሜተኞች ወከባና ማደናገር (Seige Mentality) ተላቀው፣ ለሐሳብ የበላይነት ትግል ውድድር ቢያደርጉ ፖለቲካው ፈቀቅ ይላል፡፡ የዴሞክራሲ ባህሉ ይለመዳል፡፡ አገር የነፃነት ፀዳል ይፈስባታል፡፡ ሐሜተኞችና አሉባልተኞች አገሪቱን በተቆጣጠሩና ጽንፈኞችና በጥላቻ የተዋጡ ወገኖች የበላይነቱን በያዙ ቁጥር፣ ለዴሞክራሲ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል ይከሽፋል፡፡ ከምንም ነገር በላይ መጠየቅ፣ መመርመርና ተጨባጭ ሁኔታውን ማወቅ ለምክንያታዊነት ከመጥቀሙም በላይ፣ የወሬ ጎተራ ከመሆን ያድናል፡፡ ምክንያታዊ አስተሳሰብ በሌለበት ለሐሳብ ነፃነት የሚደረገው ትግል ይጐዳል፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ አጥብቆ ጠያቂና መርማሪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በአሉባልታ ወጀብ እየተገፋ የሚጓዝ ትውልድ ለሐሳብ የበላይነት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል፣ ወደ ጉልበትና ጡንቻ ትግል ይቀይረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት 40 ዓመታት በላይ የተጓዘችበት ይህ የእብሪተኝነትና የጀብደኝነት ጉዞ ለሐሳብ ነፃነት ማደግ ወደሚደረግ ትግል መቀየር ይኖርበታል፡፡ በምክንያዊነት መመራት ያቃተው አጉል ፖለቲካችንም ለሐሳብ የበላይነት እጁን መስጠት አለበት፡፡ እንጠይቅ፣ እንመርምር፣ በውጤቱም ላይ ተመሥርተን ለአገራችን ዘላቂ ጥቅም የሚበጅ ውሳኔ ላይ እንድረስ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡